በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መለኮታዊውን ትምህርት በዓለም ዙሪያ በማስፋፋቱ ሥራ ያበረከትኩት ድርሻ

መለኮታዊውን ትምህርት በዓለም ዙሪያ በማስፋፋቱ ሥራ ያበረከትኩት ድርሻ

የሕይወት ታሪክ

መለኮታዊውን ትምህርት በዓለም ዙሪያ በማስፋፋቱ ሥራ ያበረከትኩት ድርሻ

ሮበርት ኒዝቤት እንደተረከው

የስዋዚላንድ ንጉሥ የነበሩት ዳግማዊ ሶቡዛ እኔንና ወንድሜን ጆርጅን በንጉሣዊ መኖሪያቸው ተቀብለው አነጋግረውን ነበር። ይህ የሆነው በ1936 ቢሆንም ከንጉሡ ጋር ያደረግነው ውይይት አሁንም በደንብ ይታወሰኛል። ከንጉሡ ጋር ይህንን ረዘም ያለ ውይይት ለማድረግ አጋጣሚ ያገኘሁት ለረጅም ዘመን ሳከናውነው በኖርኩት መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ የተነሳ ነው። አሁን በ95 ዓመቴ በአምስት አህጉራት ውስጥ በዚህ ሥራ ያደረግሁትን ተሳትፎ መለስ ብዬ ሳስታውስ ልቤ በሐሴት ይሞላል።

ለዚህ ሁሉ ታሪክ መነሻ የሆነው ነገር የተፈጸመው በ1925 ነው። ዶብሰን የተባለ አንድ የሻይ ነጋዴ በኢደንበርግ፣ ስኮትላንድ ወደሚገኘው ቤታችን ይመጣ ነበር። በወቅቱ በአሥራዎቹ የእድሜ ክልል መገባደጃ ላይ የነበርኩ ሲሆን የፋርማሲስትነት ሙያ ሥልጠና እየወሰድኩ ነበር። ምንም እንኳን በዕድሜ ገና ልጅ ብሆንም ከ1914-1918 ድረስ የተደረገው የዓለም ጦርነት በቤተሰቦች ላይ እና ሰዎች ለሃይማኖት ባላቸው አመለካከት ላይ ያመጣው ጉልህ ለውጥ ያሳስበኝ ነበር። ሚስተር ዶብሰን አንድ ቀን ወደ ቤታችን ሲመጣ መለኮታዊው የዘመናት እቅድ የተባለ መጽሐፍ ሰጠን። መጽሐፉ ተጨባጭ “እቅድ” ስላለው ፈጣሪ የሚናገረው ሐሳብ በጣም አሳማኝ ከመሆኑም በላይ እኔም ለማምለክ የምፈልገው እንዲህ ያለ አምላክ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ እኔና እናቴ በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርን። መስከረም 1926 በግላስጎው በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ሁለታችንም ራሳችንን ለይሖዋ ወስነን ተጠመቅን። ለእያንዳንዱ የጥምቀት እጩ በዋና ልብሱ ላይ የሚደርበው ቁርጭምጭሚት ድረስ የሚደርስና ከታች ከእግር ጋር የሚታሰር እንደ ካባ ያለ ልብስ ይሰጠው ነበር። በወቅቱ ይህ እንደ ጥምቀት ላለ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሥነ ሥርዓት ተስማሚ ልብስ እንደሆነ ይታሰብ ነበር።

በእነዚያ ጊዜያት በርካታ ነገሮችን በሚመለከት የነበረን ግንዛቤ ማስተካከያ ያስፈልገው ነበር። አብዛኞቹ የጉባኤው አባላት ገናን ያከብሩ ነበር። በመስክ አገልግሎት የሚካፈሉትም በጣም ጥቂት ነበሩ። እንዲያውም አንዳንድ ሽማግሌዎች የሰንበትን ሕግ ያስጥሳል በማለት እሁድ ዕለት ጽሑፎችን ማሰራጨትን ይቃወሙ ነበር። ይሁን እንጂ በ1925 ይታተሙ የነበሩት የመጠበቂያ ግንብ ርዕሶች “አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል” እንደሚለው እንደ ማርቆስ 13:10 ባሉ ጥቅሶች ላይ ያተኮሩ ትምህርቶችን ይዘው መውጣት ጀመሩ።

ይህ ዓለም አቀፍ ሥራ እንዴት ይከናወን ይሆን? ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ለመካፈል ባደረግኩት የመጀመሪያ ሙከራ ወቅት ለቤቱ ባለቤት ግሩም ሐሳቦችን የያዙ ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን እየሸጥኩ እንደሆነ ነገርኩትና የአምላክ በገና የተባለውን አሥር ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ከአሥር የበገና ክሮች ጋር እያወዳደረ የሚያብራራውን መጽሐፍ አበረከትኩለት። ከጊዜ በኋላ የቤት ባለቤቶች እንዲያነቡት የተዘጋጀው አጭር መልእክት የያዘ የምሥክርነት መስጫ ካርድ ይሰጠን ጀመር። እንዲሁም በተንቀሳቃሽ የሸክላ ማጫወቻ አማካኝነት አራት ደቂቃ ተኩል ያህል ርዝመት ያላቸውን ንግግሮች እናሰማ ነበር። መጀመሪያ ላይ የተሠሩት የሸክላ ማጫወቻዎች ለሸክም ከባድ የነበሩ ቢሆንም በኋላ ላይ የመጡት ሞዴሎች ግን ቀላልና እንዲያውም አንዳንዶቹ ወደ ጎን ተዘቅዝቀውም መጫወት የሚችሉ ነበሩ።

ከ1925 እስከ 1930ዎቹ መጨረሻ ድረስ የስብከት ሥራችንን በወቅቱ የተሻለ ነው ብለን ባሰብነው መንገድ ስናከናውን ቆየን። ከዚያም በ1940ዎቹ መጀመሪያ ላይ በሁሉም ጉባኤዎች ውስጥ የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተቋቋመ። የመንግሥቱን መልእክት ለማዳመጥ ፈቃደኛ ለሆኑ የቤት ባለቤቶች በቀጥታ ራሳችን መልእክቱን እንዴት ማቅረብ እንደምንችል ሥልጠና ተሰጠን። እንዲሁም ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጠናት ያለውን አስፈላጊነት ተገነዘብን። በዓለም ዙሪያ እየተከናወነ ያለው መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ አሁን ባለው መልኩ መካሄድ የጀመረው ያን ጊዜ ነው ለማለት ይቻላል።

ከወንድም ራዘርፎርድ ያገኘሁት ማበረታቻ

መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ሥራ ይበልጥ ተሳትፎ ለማድረግ የነበረኝ ፍላጎት በ1931 የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድጀምር አነሳሳኝ። በለንደን በሚደረግ አንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከተካፈልኩ በኋላ የአቅኚነት አገልግሎት ለመጀመር ተዘጋጅቼ ነበር። ይሁን እንጂ በስብሰባው ላይ በምሣ እረፍት ወቅት የስብከቱን ሥራ በበላይነት ይቆጣጠር የነበረው ወንድም ራዘርፎርድ ሊያነጋግረኝ እንደሚፈልግ ነገረኝ። ወደ አፍሪካ አንድ አቅኚ ለመላክ አስቦ ነበር። “ወደዚያ ብንልክህ ለመሄድ ፈቃደኛ ነህ?” በማለት ጠየቀኝ። ምንም እንኳን ፈጽሞ ያልጠበቅሁት ነገር ቢሆንም “አዎ፣ ፈቃደኛ ነኝ” ስል በቁርጠኝነት መለስኩ።

በወቅቱ ዋነኛው ግባችን የቻልነውን ያህል በርካታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ማሰራጨት ሲሆን ይህ ደግሞ በየጊዜው ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚጠይቅ ነበር። በወቅቱ ሥራውን በበላይነት የመምራት ኃላፊነት እንደነበራቸው እንደ አብዛኞቹ ወንድሞች እኔም ነጠላ ሆኜ እንድቀጥል ማበረታቻ ተሰጠኝ። የአገልግሎት ክልሌ በደቡባዊው የአፍሪካ ጫፍ ላይ ከምትገኘው ከኬፕ ታውን አንስቶ በስተምሥራቅ ያለውን የአሕጉሩን ክፍልና በህንድ ውቅያኖስ ላይ ያሉትን የጠረፍ ደሴቶች የሚያጠቃልል ነበር። በስተምዕራብ በኩል ደግሞ በካላሃሪ በረሃ በኩል አድርጎ ቪክቶሪያ ሃይቅ ላይ እስከሚገኘው እስከ ናይል ወንዝ መነሻ ድረስ ይደርስ ነበር። ከአገልግሎት ጓደኛዬ ጋር በየዓመቱ በዚህ ሰፊ ክልል ውስጥ ከሚገኙት የአፍሪካ አገሮች በአንዱ ወይም በሁለቱ ስድስት ወር እንድናሳልፍ ታቅዶ ነበር።

ሁለት መቶ ካርቶን ሙሉ መንፈሳዊ ሃብት

ኬፕ ታውን ስደርስ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ሊላኩ የተዘጋጁ 200 ካርቶን ሙሉ ጽሑፎች አሳዩኝ። ጽሑፎቹ በአራት የአውሮፓና በአራት የእስያ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ሲሆን በአፍሪካ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ጽሑፍ ግን አልነበረም። ይህ ሁሉ ጽሑፍ እኔ ከመምጣቴ በፊት ለምን ወደዚያ እንደተላከ ስጠይቅ ጽሑፉ በቅርቡ ወደ ኬንያ ለመስበክ ለሄዱት ፍራንክና ግሬይ ስሚዝ ለተባሉት አቅኚዎች ሊላክ የታሰበ እንደነበር ነገሩኝ። ሁለቱም ኬንያ እንደደረሱ በወባ በሽታ የተያዙ ሲሆን የሚያሳዝነው ፍራንክ ሞተ።

ይህ ዜና ስላለሁበት ሁኔታ ቆም ብዬ እንዳስብ ያደረገኝ ቢሆንም ውሳኔዬን ግን አላስቀየረኝም። እኔና ዴቪድ ኖርማን የተባለው የአገልግሎት ጓደኛዬ ከኬፕ ታውን በመርከብ ተሳፍረን የመጀመሪያ የአገልግሎት ምድባችን ወደሆነችውና 5, 000 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ታንዛኒያ ጉዞ ጀመርን። በሞምባሳ፣ ኬንያ የሚገኝ አንድ የጉዞ ወኪል የጽሑፍ ክምችታችንን እየተቆጣጠረ ወደጠየቅነው ቦታ ሁሉ ካርቶኖችን ይልክልን ነበር። መጀመሪያ ላይ በእያንዳንዱ ከተማ ውስጥ በሥራ ቦታዎች ማለትም በሱቆችና በቢሮዎች እንሰብክ ነበር። ከጽሑፍ ክምችታችን ውስጥ ከፊሎቹ ካርቶኖች 9 ዓይነት መጻሕፍትንና 11 ዓይነት ቡክሌቶችን ይይዙ ስለነበር ባሏቸው የተለያዩ ቀለማት የተነሳ ባለ ሕብረ ቀለማቱ ካርቶኖች እያልን እንጠራቸው ነበር።

ከዚያም ከምሥራቃዊው ጠረፍ 30 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኘው ወደ ዛንዚባር ደሴት ለመጓዝ ወሰንን። ዛንዚባር ለብዙ መቶ ዘመናት የባሪያ ንግድ ማዕከል የነበረች ሲሆን ከተማይቱን በመዓዛው በሚያውደው የቅሩንፉድ ምርትም የታወቀች ነበረች። ከተማይቱ ያለ ፕላን የተገነባች ስለሆነች ከቦታ ወደ ቦታ እንደልብ እንዳንንቀሳቀስ በመጠኑም ቢሆን ችግር ፈጥሮብን ነበር። መንገዶቹ በጣም ጠመዝማዛና ግራ የሚያጋቡ ስለነበሩ በቀላሉ አቅጣጫችንን እንስት ነበር። ሆቴላችን አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ያሟላ ቢሆንም በሮቹ በምስማር ከላይ እስከ ታች ስለተገደገዱና ግድግዳዎቹም ወፋፍራም ስለነበሩ ከሆቴል ይልቅ እስር ቤት ይመስል ነበር። ሆኖም በአገልግሎታችን ጥሩ ውጤት ያገኘን ሲሆን አረቦች፣ ሕንዶችና ሌሎችም ጽሑፎቻችንን በፈቃደኝነት በመቀበላቸው በጣም ተደሰትን።

በባቡር፣ በጀልባና በመኪና

በዚያን ጊዜ በምሥራቅ አፍሪካ ከቦታ ወደ ቦታ መጓዝ ቀላል አልነበረም። ለምሳሌ ከሞምባሳ ወደ ኬንያ ተራራማ ቦታዎች ስንጓዝ ባቡራችን በአንበጣ መንጋ የተነሳ ለመቆም ተገድዶ ነበር። መሬቱና የባቡር ሐዲዱ በሚልዮን በሚቆጠሩ አንበጣዎች በመሸፈኑ የተነሳ የባቡሩ ጎማዎች ሐዲዱን ቆንጥጠው ለመያዝ አልቻሉም። የነበረው ብቸኛ መፍትሔ ከባቡሩ ሞተር የሚወጣውን የፈላ ውኃ በመጠቀም ከፊት ለፊት ያለውን ሐዲድ እያጠቡ መሄድ ነበር። በዚህ መንገድ በአንበጣ የተወረረውን ቦታ እስክናልፍ ድረስ ቀስ እያልን መጓዝ ቻልን። በመጨረሻም ባቡሩ ወደ ከፍታ ሥፍራ መውጣት ሲጀምርና ቀዝቀዝ ያለውን የደጋ አየር መተንፈስ ስንችል እፎይ አልን!

ወደ ጠረፍ ከተሞቹ በቀላሉ በባቡር ወይም በጀልባ መጓዝ የሚቻል ሲሆን ወደ ገጠራማ አካባቢዎች ለመጓዝ ግን የተሻለው አማራጭ መኪና ነበር። በመሆኑም ወንድሜ ጆርጅ ከእኔ ጋር አብሮኝ ለማገልገል ሲመጣ ተደሰትኩ፤ ከእርሱ ጋር ሆነን አልጋዎች፣ የማብሰያና የእቃ ማከማቻ ክፍል እንዲሁም የወባ ትንኝ የማያስገቡ መስኮቶች ሊገጠሙለት የሚችል ትልቅ መኪና ገዛን። የድምጽ ማጉያም በጣሪያው ላይ አስገጠምን። በዚህ መኪናችን በመጠቀም ቀን ቀን ከቤት ወደ ቤት እየሄድን እንሰብክ የነበረ ሲሆን ምሽት ላይ በገበያ ቦታ በምናሰማቸው ንግግሮች ላይ እንዲገኙም ሰዎችን እንጋብዝ ነበር። ብዙውን ጊዜ እናሰማው የነበረው ንግግር “ሲኦል ማቃጠያ ሥፍራ ነውን?” የሚል ነበር። “በተንቀሳቃሽ ቤታችን” ከደቡብ አፍሪካ እስከ ኬንያ ያለውን 3, 000 ኪሎ ሜትር የሚያህል ርቀት አንድ ጊዜ ያቋረጥን ሲሆን በዚህ ወቅት በበርካታ የአፍሪካ ቋንቋዎች የተዘጋጁ የተለያዩ ቡክሌቶች ስለነበሩን የአካባቢው ሰዎች እነዚህን ጽሑፎች በደስታ ይቀበሉ ነበር።

እንደዚህ ባሉ ጉዞዎች ወቅት የአፍሪካን የዱር አራዊት ማየት መቻላችን በጣም ያስደስተን ነበር። እርግጥ ከመሸ በኋላ ለደህንነታችን ስንል ከመኪናው የማንወጣ ቢሆንም የይሖዋን ልዩ ልዩ ፍጥረታት በተፈጥሯዊ መኖሪያቸው መመልከት እምነታችንን በጣም አጠናክሮልናል።

ተቃውሞ ጀመረ

የዱር እንስሳቱ እንዳይተናኮሉን መጠንቀቅ አስፈልጎን የነበረ ቢሆንም የተለያዩ የመንግሥት ባለ ሥልጣናትና አንዳንድ በንዴት የበገኑ ሃይማኖታዊ መሪዎች በመንግሥቱ የስብከት ሥራችን ላይ የሰነዘሩት ተቃውሞ ግን ከዚያ በጣም የከፋ ነበር። በወቅቱ ራሱን ምዋና ሊሳ ማለትም “የአምላክ ልጅ” እያለ ይጠራ የነበረ አንድ አክራሪ ኪታዋላ (“መጠበቂያ ግንብ” ማለት ነው) በሚል ስያሜ የሚታወቅ ቡድን አቋቁሞ የነበረ መሆኑ በስብከት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብን ነበር። እኛ ከመድረሳችን ትንሽ ቀደም ብሎ ይህ ሰው አጠምቃችኋለሁ በሚል ሰበብ በርካታ አፍሪካውያን ውኃ ውስጥ ሰጥመው እንዲሞቱ አድርጎ ነበር። ከጊዜ በኋላ ተያዘና በስቅላት ተቀጣ። ቆየት ብሎ የስቅላት ፍርዱን ያስፈጸመውን ሰው የማነጋገር አጋጣሚ በማግኘቴ ይህ ምዋና ሊሳ የተባለው ግለሰብ ከእኛ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ገለጽኩለት።

በተጨማሪም ቁሳዊ ጥቅማቸውን እንዳያጡ በመፍራት የማስተማር ሥራችንን የሚቃወሙ ብዙ አውሮፓውያን ችግር ይፈጥሩብን ነበር። አንድ የመጋዘን ኃላፊ “ነጮች በዚህች አገር እንዲቆዩ ከተፈለገ አፍሪካውያን ጉልበታቸው እየተበዘበዘ እንዳለ ማወቅ የለባቸውም” በማለት አማርሯል። የአንድ የወርቅ ማዕድን ኩባንያ ኃላፊም በዚሁ ምክንያት ከቢሮው እንድወጣ አዘዘኝና እየተቆጣ እስከ ጎዳናው ድረስ ሸኘኝ።

የሮዴዢያ (አሁን ዚምባብዌ) መንግሥት እንደነዚህ ያሉ የሃይማኖት መሪዎችና ነጋዴዎች ባደረጉበት ተጽዕኖ የተነሳ ሳይሆን አይቀርም አገሪቱን ለቅቀን እንድንወጣ አዘዘን። ይግባኝ በማለታችን ለአፍሪካውያን እስካልሰበክን ድረስ በአገሪቱ ውስጥ መቆየት እንደምንችል ተነገረን። አንድ ባለ ሥልጣን ለዚህ ውሳኔ የሰጠን ምክንያት ጽሑፎቻችሁ “ለአፍሪካውያን አእምሮ ተስማሚ አይደሉም” የሚል ነበር። ይሁን እንጂ በሌሎች አገሮች አፍሪካውያንን የማስተማር ሥራችን ያለ ምንም እንቅፋት የቀጠለ ሲሆን እንዲያውም በደስታ ይቀበሉን ነበር። ከእነዚህ አገሮች አንዷ ስዋዚላንድ ነበረች።

በስዋዚላንድ ሞቅ ያለ አቀባበል ተደረገልን

ስዋዚላንድ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የምትገኝ 17, 364 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚያህል የቆዳ ስፋት ያላት ራስ ገዝ አገር ናት። በመግቢያዬ ላይ ከጠቀስኳቸው አንደበተ ርቱዕ ከሆኑት ከንጉሥ ዳግማዊ ሶቡዛ ጋር የተገናኘነው እዚህ ነበር። በአንድ የብሪታንያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስለተማሩ እንግሊዝኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ። ቀለል ያለ የአዘቦት ልብስ ለብሰው ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልን።

ከንጉሡ ጋር ያደረግነው ውይይት አምላክ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ላላቸው ሰዎች ለመስጠት ባቀደው ምድራዊ ገነት ላይ ያተኮረ ነበር። ይህ ርዕሰ ጉዳይ ብዙም ትኩረታቸውን ባይስበውም በአእምሯቸው ሲመላለስ የቆየ ከዚህ ጋር የሚዛመድ አንድ ጉዳይ አነሱ። ንጉሡ የድሆችንና ያልተማሩ ሰዎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ይጥሩ ነበር። ሕዝቡን ከማስተማር ይልቅ የቤተ ክርስቲያን አባሎቻቸውን ቁጥር ስለመጨመር ብቻ ያስቡ የነበሩትን የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን አይወዷቸውም ነበር። ይሁን እንጂ ንጉሡ እንደ እኛ ያሉ ሌሎች በርካታ አቅኚዎች ስለሚያከናውኑት ሥራ በሚገባ የሚያውቁ ሲሆን በተለይ መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ምንም ክፍያ ወይም ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ ለማስተማር ፈቃደኞች በመሆናችን አመስግነውናል።

መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማሩ ሥራ ፈጣን እድገት አደረገ

በ1943 የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት ሚስዮናውያንን ለማሰልጠን ተቋቋመ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማሰራጨቱ ሥራ ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ተከታትሎ ለመርዳቱ ሥራም ትኩረት መሰጠት ተጀመረ። በ1950 እኔና ጆርጅ በ16ኛው የጊልያድ ክፍል እንድንሰለጥን ተጋበዝን። ጂን ሃይዲ ከተባለች ቀናተኛ አውስትራሊያዊት እህት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘነው እዚያ ነበር። ከተመረቅን በኋላ ጂን በጃፓን በሚስዮናዊነት እንድታገለግል ተመደበች። ወቅቱ በነጠላነት ማገልገል የሚመረጥበት ጊዜ ስለነበር ወዳጅነታችን ብዙም አልጠነከረም።

የጊልያድ ሥልጠናችንን ስናጠናቅቅ እኔና ጆርጅ ሕንድ ውቅያኖስ ላይ በምትገኘው የሞሪሺየስ ደሴት እንድናገለግል ተመደብን። በዚያም ከሕዝቡ ጋር ወዳጅነት መሠረትን፣ ቋንቋቸውን ተማርን እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን እናስጠናቸው ጀመር። ከጊዜ በኋላ ታናሽ ወንድሜ ዊሊያምና ሚስቱ ሙርዔል ከጊልያድ ተመረቁና በቀድሞው የአገልግሎት ክልሌ በኬንያ እንዲያገለግሉ ተመደቡ።

በዚህ ሁኔታ ሳይታወቀን ስምንት ዓመታት አለፉና በ1958 በኒው ዮርክ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ከጂን ሃይዲ ጋር በድጋሚ ተገናኘን። ዳግመኛ ወዳጅነታችን እየተጠናከረ ሄደና ለመጋባት ተስማማን። የአገልግሎት ምድቤ ከሞሪሺየስ ወደ ጃፓን ተቀየረና እዚያ በ1959 ከጂን ጋር ተጋባን። ከዚያም በወቅቱ አንድ አነስተኛ ጉባኤ ብቻ በነበረበት በሂሮሺማ አስደሳች የሆነ የሚስዮናዊነት አገልግሎት ጀመርን። በአሁኑ ወቅት በዚያች ከተማ ውስጥ 36 የሚያህሉ ጉባኤዎች አሉ።

ጃፓንን ተሰናበትን

ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ሁለታችንም በጤና እክል የተነሳ የሚስዮናዊነት አገልግሎታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ አስቸጋሪ እየሆነብን መጣ። በመጨረሻም ጃፓንን ለቅቀን በጂን የትውልድ አገር በአውስትራሊያ ለመኖር ተገደድን። ሂሮሺማን ለቅቀን የወጣንበት ቀን በጣም የሚያሳዝን ዕለት ነበር። በባቡር ጣቢያው ሰገነት ላይ ሆነን ውድ ወዳጆቻችንን በሙሉ ሳዮናራ (ደህና ሁኑ) እያልን ተሰናበትናቸው።

አሁን የምንኖረው በአውስትራሊያ ሲሆን በኒው ሳውዝ ዌልስ ግዛት ከሚገኘው የአርሚዴል ጉባኤ ጋር ሆነን አቅማችን በፈቀደው መጠን ይሖዋን እናገለግላለን። ወደ 80 ለሚጠጉ ዓመታት ውድ የሆነውን ክርስቲያናዊ እውነት ለበርካታ ሰዎች ማካፈል ምንኛ የሚያስደስት ነው! የመጽሐፍ ቅዱስ የትምህርት ፕሮግራም ያደረገውን ድንቅ እድገት አይቻለሁ፤ እንዲሁም ትልልቅ መንፈሳዊ ክንውኖችን በአካል ተገኝቼ የመመልከት መብት አግኝቻለሁ። ለዚህ ሥራ መሳካት ማንም ሰው ወይም ቡድን በግሉ ምስጋናውን ሊወስድ አይችልም። አዎን መዝሙራዊው እንዳለው “ይህች ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆነች፣ ለዓይናችንም ድንቅ ናት።”​—⁠መዝሙር 118:23

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወንድሜ ጆርጅና ተንቀሳቃሽ ቤታችን

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቪክቶሪያ ሐይቅ አጠገብ ቆሜ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1938 በስዋዚላንድ በተደረገ የሕዝብ ንግግር ላይ የተገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1959 ከጂን ጋር በተጋባንበት ዕለት እና አሁን