ክፋት ድል አድርጓልን?
ክፋት ድል አድርጓልን?
በታሪክ ዘመናት ሁሉ ጸሐፊዎችና ፈላስፎች በጥሩነትና በክፋት ኃይሎች መካከል ስለሚካሄደው ውጊያ በርካታ ግምታዊ ሐሳቦች ሰንዝረዋል። ይሁን እንጂ በአምላክ እና በዲያብሎስ መካከል ስለሚካሄደው ውጊያ ትክክለኛውን ዘገባ የያዘ አንድ መጽሐፍ አለ። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አከራካሪ የሆኑትን ጉዳዮች እንድናውቅ ከማስቻሉም በላይ አሸናፊውን ለመለየት የምንችልበትን መንገድ ይጠቁመናል።
የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ከተፈጠሩ ብዙም ሳይቆይ ሰይጣን ዲያብሎስ የተባለ አንድ መንፈሳዊ ፍጡር በአምላክ አገዛዝ ላይ ግድድር አስነሳ። እንዴት? አምላክ ፍጡሮቹ ሊያገኙት የሚገባቸውን መልካም ነገር እንዳስቀረባቸውና ሰዎች ያለ እሱ ጣልቃ ገብነት ራሳቸውን በራሳቸው ቢያስተዳድሩ የተሻለ ሕይወት መምራት እንደሚችሉ በተዘዋዋሪ መንገድ በመናገር ነው።—ዘፍጥረት 3:1-5፤ ራእይ 12:9
ቆየት ብሎም በኢዮብ ዘመን ሰይጣን ሌላ አከራካሪ ነጥብ አነሳ። ኢዮብ ለአምላክ ያለውን ታማኝነት እንዲያላላ ለማድረግ ስለፈለገ “ቁርበት ስለ ቁርበት ነው፤ ሰው ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል” የሚል ክስ አቀረበ። (ኢዮብ 2:4) ይህ እንዴት ያለ በጅምላ የተሰነዘረ ውንጀላ ነው! ሰይጣን፣ ኢዮብ ከማለት ይልቅ “ሰው” የሚለውን የወል ስም በመጠቀም የአጠቃላዩን የሰው ዘር የአቋም ጽናት ጥያቄ ላይ ጣለው። በሌላ አባባል ‘ሰው ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይልም። አጋጣሚውን ባገኝ ሰዉን ሁሉ ከአምላክ ማራቅ እችላለሁ’ እያለ ነበር።
በአምላክ እና በዲያብሎስ መካከል በሚካሄደው ውጊያ አሸናፊው የሚለየው ለሚከተሉት ሁለት ጥያቄዎች በሚሰጠው መልስ ይሆናል:- የሰው ልጅ በተሳካ መንገድ ራሱን ማስተዳደር ችሏልን? ዲያብሎስ ሁሉንም ሰው ከእውነተኛው አምላክ ማራቅ ችሏልን?
የሰው ልጅ በተሳካ መንገድ ራሱን ማስተዳደር ይችላልን?
የሰው ልጅ ላለፉት በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት የተለያዩ የአገዛዝ ዓይነቶችን ሞክሯል። በታሪክ ዘመናት ውስጥ እንደ ንጉሣዊ አገዛዝ፣ የመሳፍንት አገዛዝ፣ ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ፣ አምባገነናዊ አገዛዝ፣ ፋሺስታዊ አገዛዝና የኮሚኒስት አገዛዝ ያሉ የተለያዩ አገዛዞች ተሞክረዋል። በየጊዜው የተለያዩ የአገዛዝ ዓይነቶችን መሞከር ማስፈለጉ በራሱ እነዚህ የአስተዳደር መንገዶች ብቃት የጎደላቸው መሆናቸውን አያሳይምን?
ኤች ጂ ዌልስ ኤ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ዎርልድ በተባለው በ1922 በታተመው መጽሐፋቸው ላይ “ሮማውያን ሆን ብለውም ባይሆን የተለያዩ የአገዛዝ ዓይነቶችን ሞክረዋል” ሲሉ ጽፈዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል:- “በየጊዜው የተለያዩ የመስተዳድር ዓይነቶች ይለዋወጡ ነበር፤ በቋሚነት የዘለቀ አንድ አገዛዝ አልነበረም። በአንድ በኩል ሲታይ ሙከራው ከሽፏል ማለት ይቻላል። በሌላ በኩል ደግሞ ሙከራው ዳር ባለመድረሱ አሁንም ቢሆን አውሮፓና አሜሪካ ሮማውያን አጋጥሟቸው የነበረውን የአገዛዝ ችግር ለመፍታት በመታገል ላይ ናቸው።”
የተሻለ መስተዳድር ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት በ20ኛው መቶ ዘመንም ቀጥሎ ነበር። ያ ክፍለ ዘመን ሲያበቃ ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር። በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ሲታይ ዲሞክራሲ ሁሉንም ሰው የሚያሳትፍ አገዛዝ እንደሆነ ይነገራል። ይሁን እንጂ ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ የሰው ልጅ ያለ አምላክ ጣልቃ ገብነት በተሳካ ሁኔታ ራሱን ማስተዳደር እንደሚችል አሳይቷልን? የቀድሞው የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃዋሃርላል ኔሀሩ ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ጥሩ መሆኑን ከተናገሩ በኋላ አክለው “እንደዚህ ያልኩት ሌሎቹ የአገዛዝ ዓይነቶች የባሱ በመሆናቸው ነው” ብለዋል። የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ቫለሪ ጂስካር ዲስታንግ “ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ የሚያስከትለውን ቀውስ እየተመለከትን ነው” በማለት ተናግረዋል።
በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ እንኳን ግሪካዊው ፈላስፋ ፕላቶ ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ድክመቶች እንዳሉት ጠቁሞ ነበር። ኤ ሂስትሪ ኦቭ ፖለቲካል ቲዮሪ
የተባለው መጽሐፍ እንዳስቀመጠው ፕላቶ “የዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ድክመት እውቀቱና ብቃቱ በሌላቸው የፖለቲካ ሰዎች መመራቱ እንደሆነ” ተናግሯል። ዛሬ ያሉ አብዛኞቹ የፖለቲካ ሰዎች በአስተዳደር ሥራ ሊካፈሉ የሚችሉ ብቃት ያላቸው ግለሰቦች ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ይናገራሉ። ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ‘ከባድ ችግር ሲጋረጥባቸው ምንም ማድረግ በማይችሉ መሪዎች ሕዝቡ ተበሳጭቷል’ ብሏል። በመቀጠልም “ብዙዎች፣ አመራር የመስጠት ብቃት በጎደላቸውና ምግባረ ቢስ በሆኑ መሪዎች ተሰላችተዋል” ሲል ዘግቧል።እስቲ አሁን ደግሞ በጥንቷ እስራኤል የነበረውን የንጉሥ ሰሎሞንን አገዛዝ እንመልከት። ይሖዋ አምላክ ለሰሎሞን ወደር የሌለው ጥበብ ሰጥቶት ነበር። (1 ነገሥት 4:29-34) ሰሎሞን በገዛባቸው 40 ዓመታት የሕዝቡ ሕይወት ምን ይመስል ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ “ይሁዳና እስራኤልም እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፤ በልተውም ጠጥተውም ደስ ብሎአቸው ነበር” በማለት መልስ ይሰጠናል። ዘገባው ቀጥሎ እንዲህ ይላል:- “በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ ይሁዳና እስራኤል ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ተዘልሎ ይቀመጥ ነበር።” (1 ነገሥት 4:20, 25) በዓይን የማይታየው የአጽናፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ ይሖዋ አምላክ ጠቢብ በሆነ ምድራዊ ንጉሥ አማካኝነት ይመራቸው ስለነበር ሕዝቡ የተረጋጋ፣ ብልጽግና የሞላበትና ደስታ የሰፈነበት ሕይወት መምራት ችለው ነበር።
በሰው ልጅ አገዛዝና በአምላክ አገዛዝ መካከል ያለው ልዩነት ምንኛ ሰፊ ነው! አገዛዝን በተመለከተ በተነሳው ግድድር ሰይጣን አሸናፊ ሆኗል ብሎ በሐቀኝነት ለመናገር የሚደፍር ይኖራልን? በፍጹም፣ ነቢዩ ኤርምያስ እንደሚከተለው በማለት ሁኔታውን በትክክል አስቀምጦታል:- “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።”—ኤርምያስ 10:23
ሰይጣን ሁሉንም ሰው ከአምላክ ማራቅ ይችላልን?
ሰይጣን ሁሉንም ሰው ከአምላክ ማራቅ እንደሚችል በመናገር ያስነሳውን ግድድር በተመለከተስ ተሳክቶለት ይሆን? ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ላይ ከክርስትና በፊት የነበሩ የበርካታ ታማኝ ወንዶችና ሴቶችን ስም ዘርዝሯል። ከዚያም እንዲህ አለ:- “ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና።” (ዕብራውያን 11:32) ጳውሎስ እነዚህን ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ‘እንደ ደመና ያሉ ምሥክሮች’ በማለት ጠርቷቸዋል። (ዕብራውያን 12:1) እዚህ ላይ “ደመና” ተብሎ የተጠቀሰው የግሪክኛ ቃል በሰማይ ላይ ተበታትነው የሚታዩትን የተወሰነ መጠንና ቅርጽ ያላቸውን ደመናት ሳይሆን ሰማያትን የሸፈነውን ቅርጽ አልባ የደመናት ስብስብን የሚያመለክት ነው። ቀደም ባሉት ዓመታት የነበሩት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በርካታ ከመሆናቸው የተነሳ ከደመናት ስብስብ ጋር መመሳሰላቸው ተገቢ ነው። በእርግጥም ባለፉት መቶ ዓመታት ሁሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ብዙ ሰዎች በገዛ ፈቃዳቸው ከይሖዋ ጎን በታማኝነት ለመቆም መርጠዋል።—ኢያሱ 24:15
በጊዜያችንስ ሁኔታው ምን ይመስላል? የይሖዋ ምሥክሮች በ20ኛው መቶ ዘመን ከፍተኛ ስደትና ተቃውሞ ቢደርስባቸውም በዓለም ዙሪያ ቁጥራቸው ከስድስት ሚልዮን በላይ ሆኗል። ወደ ዘጠኝ ሚልዮን የሚጠጉ ሌሎች ሰዎችም ከእነርሱ ጋር ይተባበራሉ፤ ከእነዚህ ሰዎች ብዙዎቹ ከአምላክ ጋር የግል ዝምድና ለመመሥረት የሚያስችሏቸውን እርምጃዎች እየወሰዱ ነው።
ሰይጣን የሰው ልጆችን ከአምላክ ማራቅ እንደሚችል ላስነሳው ግድድር ከሁሉ የተሻለ መልስ ያስገኘው የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በመከራ እንጨት ላይ የደረሰበት ሥቃይ እንኳን አቋሙን እንዲያላላ አላደረገውም። ኢየሱስ ሊሞት ተቃርቦ ሳለ “አባት ሆይ፣ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” በማለት ተናገረ።—ሉቃስ 23:46
ሰይጣን መላውን የሰው ልጅ በቁጥጥሩ ሥር ለማስገባት ማታለያዎችንና ግልጽ ስደቶችን ጨምሮ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል። ሰዎችን ከይሖዋ ለማራቅ ‘የሥጋ ምኞትን፣ የዓይን አምሮትንና ስለ ገንዘብ መመካትን’ እንደ መሣሪያ አድርጎ ይጠቀማል። (1 ዮሐንስ 2:15, 16) ከዚህም በላይ ሰይጣን ‘የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው የማያምኑትን ሰዎች አሳብ አሳውሯል።’ (2 ቆሮንቶስ 4:4) ሰይጣን ዓላማውን ለማሳካት በዛቻና በሰው ፍርሃት ለመጠቀምም ይሞክራል።—ሥራ 5:40
ይሁን እንጂ በአምላክ ጎን ያሉት በዲያብሎስ አይሸነፉም። ይሖዋ አምላክን ከማወቃቸውም በላይ ‘በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹም ነፍሳቸውና በፍጹም አሳባቸው ይወድዱታል።’ (ማቴዎስ 22:37) በእርግጥም ኢየሱስ ክርስቶስና ስፍር ቁጥር የሌላቸው የሰው ልጆች ያሳዩት የማይናወጥ የታማኝነት አቋም ሰይጣን ዲያብሎስ የሽንፈት ካባ እንዲከናነብ አድርጎታል።
የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞልናል?
የሰው ልጆች የተሻለ አገዛዝ ለማግኘት የሚያደርጉት ሙከራ ማብቂያ የለውም ማለት ነው? ነቢዩ ዳንኤል እንዲህ ሲል ትንቢት ተናግሯል:- “በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።” (ዳንኤል 2:44) የሰማይ አምላክ የሚያቋቁመው መንግሥት በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራ ሰማያዊ መስተዳድር ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲጸልዩለት ያስተማራቸውም ስለዚሁ መንግሥት ነው። (ማቴዎስ 6:9, 10) ይህ መንግሥት ‘ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ ቀን በሚሆነው ጦርነት’ ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ ካጠፋ በኋላ መላውን ምድር በቁጥጥሩ ሥር ያደርጋል።—ራእይ 16:14, 16 አ.መ.ት
ሰይጣንስ ምን ይደርስበታል? መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት የሚፈጸመውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “[አንድ የይሖዋ መልአክ] የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፣ ሺህ ዓመትም አሰረው፣ ወደ ጥልቅም ጣለው አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት።” (ራእይ 20:1-3) የኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት የሚጀምረው ሰይጣን ምንም ማድረግ ወደማይችልበት ጥልቅ ውስጥ ከተጣለ በኋላ ይሆናል።
በዚያን ወቅት ምድራችን እንዴት ያለች አስደሳች ቦታ ትሆናለች! ክፋትና ክፉ አድራጊዎች በሙሉ ይጠፋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ተስፋ ይሰጣል:- “ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።” (መዝሙር 37:9-11) ሰላማቸውን የሚያደፈርሱ ሰዎችም ሆኑ እንስሳት አይኖሩም። (ኢሳይያስ 11:6-9) በታሪክ ዘመናት ሁሉ ባለማወቅም ይሁን ስለ ይሖዋ ለመማር አጋጣሚ ሳያገኙ በመቅረታቸው ምክንያት ከዲያብሎስ ጎን ቆመው የነበሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም ጭምር ትንሣኤ አግኝተው መለኮታዊ ትምህርት ይሰጣቸዋል።—ሥራ 24:15
የሺው ዓመት ግዛት ማብቂያ ላይ ምድር ወደ ገነትነት ትለወጣለች፤ የሰው ልጆችም ፍጽምና ይላበሳሉ። ከዚያም ሰይጣን “ለጥቂት ጊዜ” ይፈታል፤ ሆኖም ብዙም ሳይቆይ እሱና የአምላክን አገዛዝ የሚቃወሙ ሁሉ ለዘላለም ይጠፋሉ።—ራእይ 20:3, 7-10
ታዲያ ከማን ጎን ትቆማለህ?
ሃያኛው መቶ ዘመን ሰይጣን ምድራችንን ያመሰበት ጊዜ ነበር። በምድር ላይ እየተፈጸሙ ያሉት ሁኔታዎች ማቴዎስ 24:3-14፤ ራእይ 6:1-8) በምድር ላይ የተንሰራፋው ክፋትም ሆነ የብዙኃኑ አመለካከት አሸናፊው ማን መሆኑን ለመለየት አያስችሉንም። ወሳኝ የሆኑት ነጥቦች ከሁሉ የተሻለው የማን አገዛዝ ነው የሚለውና በፍቅር ተነሳስቶ ይሖዋን የሚያገለግል ሰው ይኖራልን የሚሉት ናቸው። በሁለቱም በኩል አሸናፊው ይሖዋ ነው።
ሰይጣን ድል እንዳደረገ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ሳይሆኑ በዚህ ክፉ ሥርዓት የመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ የምንኖር መሆናችንን የሚያመለክቱ ናቸው። (እስካሁን የተፈቀዱት ጊዜያት ሰይጣን ውሸታም መሆኑን ካረጋገጡ ይሖዋ ክፋት እንዲቀጥል የፈቀደው ለምንድን ነው? ይሖዋ ትዕግሥት ያሳየው ‘ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱና ማንም እንዳይጠፋ’ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:9) የአምላክ ፈቃድ ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) አንተም በቀረው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተህ ‘እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆነውንና እርሱ የላከውን ኢየሱስ ክርስቶስን’ ወደ ማወቅ እንደምትደርስ ተስፋ እናደርጋለን። (ዮሐንስ 17:3) የይሖዋ ምሥክሮች ይህንን እውቀት እንድታገኝና በአሸናፊዎቹ ወገን ከሚቆሙት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጎን እንድትሰለፍ ሊረዱህ ዝግጁ ናቸው።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች በአቋማቸው በመጽናት ሰይጣን የሽንፈት ካባ እንዲከናነብ አድርገውታል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ከጎኑ የቆሙ ብዙ ታማኝ አገልጋዮች አሉት