ሰይጣን አፈ ታሪክ ነው ወይስ በእውን ያለ ክፉ ፍጡር?
ሰይጣን አፈ ታሪክ ነው ወይስ በእውን ያለ ክፉ ፍጡር?
የሰው ልጅ ቀደም ካሉት ዘመናት ጀምሮ የክፋት ምንጭ ማን እንደሆነ ለማወቅ ሲሞክር ቆይቷል። በጄምስ ሄስቲንግስ የተዘጋጀው ኤ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል እንዲህ ይላል:- “የሰው ልጅ በአካባቢው ያሉትን ነገሮች መረዳት ሲጀምር ሊቆጣጠራቸው የማይችል ጎጂ ወይም አጥፊ ኃይሎች እንዳሉ ተገነዘበ።” ይኸው የማመሳከሪያ ጽሑፍ አክሎ እንዲህ ይላል:- “ቀደም ባሉት ዓመታት ይኖሩ የነበሩት ሰዎች የተለያዩ ነገሮችን መንስኤ ለማወቅ ይጥሩ የነበረ ሲሆን የተፈጥሮ ኃይሎችና ክስተቶች ሌሎች አካላት የሚፈጽሟቸው ነገሮች እንደሆኑ አድርገው ያስቡ ነበር።”
ታሪክ ጸሐፊዎች እንደሚናገሩት ከሆነ በአጋንንታዊ አማልክትና በክፉ መናፍስት ማመን የተጀመረው በጥንቷ ሜሶጶጣሚያ ነው። የጥንቶቹ ባቢሎናውያን ኔርጋል ተብሎ የሚጠራ ቁጡ አምላክ የሙታንን ዓለም ወይም “መመለሻ የሌለውን አገር” እንደሚቆጣጠር ያምኑ የነበረ ሲሆን ይኸው አምላክ “የሚያቃጥል” ተብሎም ይጠራ ነበር። ባቢሎናውያኑ አጋንንትንም ይፈሩ ስለነበር አስማታዊ ድርጊቶችን በመፈጸም ሊያስደስቷቸው ይሞክሩ ነበር። በግብጻውያን አፈ ታሪክ ሴት የሚባል “ቀጭን ቆልማማ አፍንጫ፣ ቀጥ ያሉና አራት ማዕዘን ቅርጽ ያላቸው ጆሮዎች እንዲሁም ደረቅ የሆነ መንታ ጅራት ባለው ግራ የሚያጋባ እንስሳ የተመሰለ” የክፋት አምላክ እንዳለ ይታመን ነበር።—ላሩስ ኢንሳይክሎፔዲያ ኦቭ ሚቶሎጂ
ግሪካውያንና ሮማውያን በጎና መጥፎ አማልክት ቢኖሯቸውም አንድ ከሁሉ ጎላ ብሎ የሚታይ ክፉ አምላክ ግን አልነበራቸውም። ፈላስፎቻቸው ሁለት ተጻራሪ ኃይሎች እንዳሉ ያስተምሩ ነበር። ኤምፔዶክሊዝ እነዚህን ተጻራሪ ኃይሎች ፍቅርና ብጥብጥ ብሏቸዋል። ፕላቶ ደግሞ ዓለም ሁለት “ነፍሶች” እንዳሉትና አንደኛው ለመልካም ነገር ሌላው ደግሞ ለክፋት መንስኤ እንደሆኑ ያምን ነበር። ዦርዥ ሚንዋ ለ ዲያብል (ዲያብሎስ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት “ጥንታዊው [የግሪካውያንና የሮማውያን] አረማዊ ሃይማኖት የዲያብሎስን ሕልውና አያምንም።”
ኢራን ውስጥ የዞራስተር ሃይማኖት አሁራ ማዝዳ ወይም ኦርመዝድ የተባለው የሁሉ የበላይ የሆነው መለኮታዊ ኃይል አንግረ ማይንዩን ወይም አሪመንን እንደፈጠረና አንግረ ማይንዩ ክፋትን በመምረጡ ምክንያት አጥፊ መንፈሳዊ አካል እንደሆነ ያስተምራል።
የአይሁድ ሃይማኖት ሰይጣን የአምላክ ተጻራሪ እንደሆነና ኃጢአትን እንዳመጣ ቀለል ባለ መንገድ አስቀምጦታል። ይሁን እንጂ ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ይህ ትምህርት በአረማዊ ሐሳቦች ተበከለ። ኢንሳይክሎፔዲያ ጁዳይካ እንዲህ ይላል:- “ከዘአበ በነበሩት ምዕተ ዓመታት መገባደጃ ላይ . . . ከፍተኛ ለውጥ ተከናውኗል። በዚህ ጊዜ ውስጥ [የአይሁድ] ሃይማኖት . . . ሁለት ተጻራሪ ኃይሎች አሉ የሚለውን እምነት የሚያንጸባርቁ ብዙ ጽንሰ ሐሳቦችን ተቀብሏል፤ በዚህ እምነት መሠረት አምላክንና የጥሩነትና የእውነት ኃይሎችን የሚቃወሙ የክፋትና የተንኮል ኃይሎች በሰማይና በምድር አሉ። ይህ የፋርሳውያን ሃይማኖት ያስከተለው ተጽዕኖ ሳይሆን አይቀርም።” ዘ ኮንሳይስ
ጁዊሽ ኢንሳይክሎፔዲያ “አሥርቱን ትእዛዛት በመጠበቅና ክታብ በማድረግ ከ[አጋንንት] ጥበቃ ማግኘት ይቻላል” ብሏል።የከሃዲ ክርስቲያኖች ትምህርት
የአይሁድ እምነት ሰይጣንንና አጋንንቱን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ሐሳቦችን እንደተቀበለ ሁሉ ከሃዲ የሆኑ ክርስቲያኖችም ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ሐሳቦችን አዳብረዋል። ዚ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ እንዲህ ይላል:- “መጽሐፍ ቅዱስን በእጅጉ ከሚቃረኑት ጥንታዊ መንፈሳዊ ትምህርቶች መካከል አምላክ ለሰይጣን ቤዛ በመክፈል ሕዝቡን ዋጅቷል የሚለው ትምህርት ይገኝበታል።” ይህንን ሐሳብ ያቀረበው አይሪኒየስ (በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ) ነበር። “ዲያብሎስ በሰዎች ላይ ሕጋዊ መብት እንዳለውና የክርስቶስ ሞት . . . ለዲያብሎስ የተከፈለ ቤዛ እንደሆነ” የገለጸው ኦሪጀን (በሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ) ይህንን ሐሳብ የበለጠ አዳበረው።—ሂስትሪ ኦቭ ዶግማ፣ በአዶልፍ ሃርናክ የተዘጋጀ
ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔዲያ እንዳለው “[ቤዛው የተከፈለው ለዲያብሎስ ነው የሚለው ሐሳብ] ወደ አንድ ሺህ ለሚጠጉ ዓመታት ያህል በክርስትና ታሪክ ውስጥ የጎላ ቦታ የነበረው” ሲሆን ቤተ ክርስቲያኒቷ ከምታምንባቸው ትምህርቶች አንዱ ሆኖ ቆይቷል። አውግስቲንን (ከአራተኛው እስከ አምስተኛው መቶ ዘመን እዘአ) ጨምሮ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አባቶችም ቤዛው የተከፈለው ለዲያብሎስ ነው የሚለውን ሐሳብ ተቀብለውት ነበር። በመጨረሻም በ12ኛው መቶ ዘመን እዘአ የካቶሊክ ሃይማኖት ምሁራን የሆኑት አንሴልም እና አቢላር የክርስቶስ መሥዋዕት የቀረበው ለሰይጣን ሳይሆን ለአምላክ ነው ወደሚለው መደምደሚያ ደረሱ።
የመካከለኛው ዘመን አጉል እምነቶች
አብዛኞቹ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጉባኤዎች ሰይጣንን በተመለከተ አስተያየት ከመስጠት ቢቆጠቡም በ1215 እዘአ የተካሄደው አራተኛው የላተራን ጉባኤ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔዲያ “ከባድ የእምነት መግለጫ” ብሎ የጠራውን ሐሳብ አቀረበ። ቀኖና 1 “ዲያብሎስና ሌሎች አጋንንት አምላክ ሲፈጥራቸው ጥሩ የነበሩ ቢሆንም በሥራቸው ክፉ ሆነዋል” ይላል። ጨምሮም የሰው ልጆችን ለማሳሳት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጿል። ይህ አባባል በመካከለኛው ዘመን ይኖሩ የነበሩ ብዙ ሰዎችን አስጨነቃቸው። ምክንያቱ ያልታወቀ ሕመም፣ ድንገተኛ ሞት ወይም የሰብል መበላሸትና ይህንን የመሰለ ማንኛውም ያልተለመደ ክስተት የሰይጣን እጅ እንዳለበት ይታሰብ ነበር። በ1233 እዘአ የሮማ ሊቀ ጳጳሳት የነበሩት ግሪጎሪ 9ኛ መናፍቃንን የሚያወግዙ በርካታ ድንጋጌዎች ያወጡ ሲሆን ከድንጋጌዎቹ አንደኛው ሉሲፈሪያን በሚባሉት ዲያብሎስን እንደሚያመልኩ በሚነገርላቸው ሰዎች ላይ የወጣ ድንጋጌ ነበር።
ሰዎች የዲያብሎስ ወይም የአጋንንቱ መንፈስ ሊያድርባቸው ይችላል የሚለው እምነት ብዙዎች አስማታዊ ድርጊቶችንና ጥንቆላን በጣም እንዲፈሩ አደረጋቸው። ከ13ኛው እስከ 17ኛው መቶ ዘመን ባለው ጊዜ ውስጥ ሰዉ ለጠንቋዮች ያደረበት ፍራቻ በመላው አውሮፓ ከመዳረሱም በላይ በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች አማካኝነት በሰሜን አሜሪካ አገሮችም ተዛመተ። የፕሮቴስታንት የለውጥ አራማጆች የነበሩት ማርቲን ሉተርና ጆን ካልቪን እንኳን ሳይቀሩ ጠንቋዮች እየታደኑ እንዲያዙ መደረጉን ደግፈዋል። አውሮፓ ውስጥ የጥንቆላ ድርጊት ይፈጽማሉ የሚባሉ ሰዎች ተራ በሆነ አሉባልታ ወይም በተንኮል ተወንጅለው በካቶሊክና በመንግሥት ፍርድ ቤቶች ችሎት ፊት ይቀርቡ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ንጹሐን ሰዎችን “ጥፋተኛ ነኝ” ብለው እንዲያምኑ ለማድረግ ያሰቃዩአቸው ነበር።
ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ሰዎች በእሳት ተቃጥለው እንዲሞቱ ይደረግ የነበረ ሲሆን በእንግሊዝና በስኮትላንድ ደግሞ ተሰቅለው እንዲሞቱ ይፈረድባቸው ነበር። ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔዲያ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “አንዳንድ ታሪክ ጸሐፊዎች እንደሚናገሩት ከሆነ ከ1484 እስከ 1782 ባለው ጊዜ ውስጥ
ቤተ ክርስቲያን ጠንቋዮች ናቸው ያለቻቸውን 300, 000 ሴቶች ገድላለች።” በመካከለኛው ዘመን ለተፈጸመው ለዚህ አሳዛኝ ድርጊት ተጠያቂው ሰይጣን ከሆነ መሣሪያዎቹ ሆነው ያገለገሉት ሟቾቹ ናቸው ወይስ አክራሪ የነበሩት ሃይማኖታዊ አሳዳጆች?ዛሬ ያለው አመለካከት
በ18ኛው መቶ ዘመን ማንኛውም አስተሳሰብና እምነት ተጨባጭ በሆነ ምክንያት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት የሚል ፍልስፍና ብቅ አለ። ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “በ18ኛው መቶ ዘመን የነበረው ፍልስፍናና ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ዲያብሎስ አለ የሚለው እምነት በመካከለኛው ዘመን የተፈጠረ አፈ ታሪክ እንደሆነ በማስተማር ከክርስቲያኖች አእምሮ ሊያወጣው ሞክሯል።” በምላሹም የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሰይጣን ዲያብሎስ መኖር እንደምታምን በመጀመሪያው የቫቲካን ጉባኤ (1869-70) ላይ በድጋሚ ግልጽ ያደረገች ሲሆን ይህንኑ እምነትዋን በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ (1962-65) ላይም ፈራ ተባ እያለች ጠቅሳዋለች።
ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔዲያ እንደገለጸው “ቤተ ክርስቲያኗ በመላእክትና በአጋንንት መኖር ታምናለች።” ሆኖም ቴኦ የተባለው በፈረንሳይኛ የተዘጋጀ የካቶሊክ መዝገበ ቃላት “ዛሬ ያሉ ብዙ ክርስቲያኖች በዓለም ላይ ለሚፈጸመው ክፋት ተጠያቂው ዲያብሎስ ነው ብለው ማመን አይፈልጉም” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የካቶሊክ የሃይማኖት ምሁራን ኦፊሴላዊውን የካቶሊክ መሠረተ ትምህርትና ዘመናዊውን አስተሳሰብ ጎን ለጎን አጣጥመው ለማስኬድ እየሞከሩ ነው። ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “ልል የሆነ አቋም የሚንጸባረቅባቸው የክርስትና ንድፈ ሐሳቦች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰይጣን የሚሰጠው ሐሳብ ቃል በቃል መወሰድ የለበትም የሚል አዝማሚያ የያዙ ይመስላል። ከዚህ ይልቅ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የሚገኘውን ክፋት ለማመልከት የተሰራበት ‘ሥዕላዊ መግለጫ’ እንደሆነ ያምናሉ።” ፕሮቴስታንቶችን በተመለከተ ይኸው የማመሳከሪያ ጽሑፍ ሲናገር “ዘመናዊው የፕሮቴስታንት እምነት ዲያብሎስ ራሱን የቻለ አካል እንደሆነ አድርጎ ማመን አስፈላጊ አይደለም የሚል አቋም እየያዘ መጥቷል” ብሏል። ይሁን እንጂ እውነተኛ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰይጣን የሚሰጠውን ሐሳብ እንደ “ሥዕላዊ መግለጫ” ብቻ ሊመለከቱት ይገባልን?
ቅዱሳን ጽሑፎች ምን ያስተምራሉ?
ሰብዓዊ ፍልስፍናና ሃይማኖታዊ ጽንሰ ሐሳቦች የክፋትን ምንጭ በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጸው የተሻለ ማብራሪያ መስጠት አልቻሉም። ቅዱሳን ጽሑፎች ሰይጣንን በተመለከተ የሚሰጡት ሐሳብ የክፋት ምንጭ ማን እንደሆነ፣ የሰው ልጆች ለምን ሥቃይና መከራ እንደሚደርስባቸውና ከዓመት ወደ ዓመት ክፋት እየጨመረ የሚሄድበትን ምክንያት ለማወቅ ያስችለናል።
አንዳንዶች ‘አምላክ ጥሩና አፍቃሪ ከሆነ እንደ ሰይጣን ያለ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር ለምን ፈጠረ?’ ብለው ይጠይቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ሥራዎች በሙሉ ፍጹም እንደሆኑና የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡሮቹ በሙሉ ነፃ ምርጫ እንደተሰጣቸው ይናገራል። (ዘዳግም 30:19፤ 32:4፤ ኢያሱ 24:15፤ 1 ነገሥት 18:21) በኋላ ሰይጣን የሆነው መንፈሳዊ አካል ፍጹም ሆኖ የተፈጠረ ቢሆንም በገዛ ፈቃዱ ከእውነትና ከጽድቅ መንገድ ዞር ብሎአል ማለት ነው።—ዮሐንስ 8:44፤ ያዕቆብ 1:14, 15
ሰይጣን የተከተለው የዓመፅ ጎዳና “ውበትህም የተፈጸመ መደምደሚያ” እና “ከተፈጠርህበት ቀን ጀምረህ በደል እስኪገኝብህ ድረስ በመንገድህ ፍጹም ነበርህ” ተብሎ ውብ በሆኑ ቃላት ከተገለጸው ‘የጢሮስ ንጉሥ’ ጋር በብዙ መንገዶች ይመሳሰላል። (ሕዝቅኤል 28:11-19) ሰይጣን የተገዳደረው የይሖዋን የበላይነት ወይም ፈጣሪነት አልነበረም። ደግሞስ እሱ ራሱ የአምላክ ፍጥረት ሆኖ እያለ እንዴት ይህንን ማድረግ ይችላል? ሆኖም ሰይጣን ይሖዋ ሉዓላዊነቱን የሚጠቀምበት መንገድ ትክክል አይደለም የሚል ክርክር አስነስቷል። ሰይጣን በኤደን የአትክልት ሥፍራ ውስጥ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ፍጡራን መብታቸው የሆነውንና ሕልውናቸው የተመካበትን ነገር እንደከለከላቸው በተዘዋዋሪ መንገድ ተናገረ። (ዘፍጥረት 3:1-5) አዳምና ሔዋን ትክክለኛ በሆነው የይሖዋ ሉዓላዊ አገዛዝ ላይ እንዲያምፁ በማድረግ በእነሱና በልጆቻቸው ላይ ኃጢአትንና ሞትን አመጣ። (ዘፍጥረት 3:6-19፤ ሮሜ 5:12) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ ሥቃይ ዋነኛ መንሥኤ ሰይጣን እንደሆነ ያሳያል።
ከጥፋት ውኃው ቀደም ብሎ ሌሎች መላእክትም ከሰይጣን ጋር ተባብረው ዓመፁ። ከሰው ሴቶች ልጆች ጋር የጾታ ፍላጎታቸውን ለማርካት ሲሉ ሰብዓዊ አካል ለብሰው ወደ ምድር መጡ። (ዘፍጥረት 6:1-4) በጥፋት ውኃው ወቅት እነዚህ ከዳተኛ መላእክት ወደ መንፈሳዊው ዓለም ቢመለሱም በሰማይ ከአምላክ ጋር ወደ ነበራቸው ወደ ቀድሞ “መኖሪያቸው” አልተመለሱም። (ይሁዳ 6) በመንፈሳዊ ሁኔታ ወደ ድቅድቅ ጨለማ ተጥለዋል። (1 ጴጥሮስ 3:19, 20፤ 2 ጴጥሮስ 2:4) ለይሖዋ ሉዓላዊነት ከመገዛት ይልቅ የሰይጣን ተገዢዎች በመሆን አጋንንት ሆኑ። እነዚህ አጋንንት እንደገና ሰብዓዊ አካል መልበስ ባይችሉም አሁንም ቢሆን በሰው ልጆች አእምሮና ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላሉ፤ ዛሬ ለምንመለከተው ለአብዛኛው ክፋት ተጠያቂዎቹ እነሱ እንደሆኑም ምንም ጥርጥር የለውም።—ማቴዎስ 12:43-45፤ ሉቃስ 8:27-33
የሰይጣን አገዛዝ መጨረሻው ቀርቧል
ዛሬ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ክፉ ኃይሎች ተጽዕኖ እያደረሱ እንዳሉ ግልጽ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ ‘ዓለምም በሞላው በክፉው ተይዟል’ ሲል ጽፏል።—1 ዮሐንስ 5:19
ይሁን እንጂ ፍጻሜያቸውን ያገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እንደሚያሳዩት ዲያብሎስ ከመታሰሩ በፊት ችግርና ሁከት ለመፍጠር የቀረው ‘ጊዜ ጥቂት’ መሆኑን ስላወቀ በምድር ላይ የሚያደርሰውን ወዮታ እያባባሰው ነው። (ራእይ 12:7-12፤ 20:1-3) የሰይጣን አገዛዝ ሲያከትም እንባ፣ ሞት እና ሥቃይ ‘የማይኖርበት’ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ይመጣል። በዚያን ጊዜ የአምላክ ፈቃድ ‘በሰማይ እንደሆነ እንዲሁ በምድር ይሆናል።’—ራእይ 21:1-4፤ ማቴዎስ 6:10
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባቢሎናውያን ኔርጋል (በስተ ግራ ጥግ ላይ ) ተብሎ በሚጠራ ቁጡ አምላክ ያምኑ ነበር፣ ፕላቶ (በስተ ግራ ) ሁለት ተጻራሪ “ነፍሳት” እንዳሉ ያምን ነበር
[ምንጭ]
ሲሊንደር:- Musée du Louvre, Paris; ፕላቶ:- National Archaeological Museum, Athens, Greece
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አይሪኒየስ፣ ኦሪጀንና አውጉስቲን ቤዛው የተከፈለው ለዲያብሎስ እንደሆነ አስተምረዋል
[ምንጭ]
ኦሪጀን:- Culver Pictures; አውጉስቲን:- ግሬት ሜን ኤንድ ፌመስ ዊመን ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጠንቋዮችን መፍራት በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች መገደል ምክንያት ሆኗል
[ምንጭ]
ቢልዴርዛል ዶይቸር ግሽሽቴ ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ