በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን በትክክል በማወቅ የሚገኝ መጽናኛ

አምላክን በትክክል በማወቅ የሚገኝ መጽናኛ

አምላክን በትክክል በማወቅ የሚገኝ መጽናኛ

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ አፍቃሪና መሐሪ እንደሆነ የሚናገረው ሐሳብ በአንዳንዶች አእምሮ ውስጥ ግራ የሚያጋቡ ጥያቄዎችን ይፈጥራል። አምላክ ክፋትን የማስወገድ ፍላጎት፣ እውቀቱና ኃይሉ ካለው ክፋት እንደዚህ የተስፋፋው ለምንድን ነው? ብለው ይጠይቃሉ። ቀጥሎ የቀረቡትን ሦስት የተለያዩ ሐሳቦች ለማስማማት ይቸገራሉ። (1) አምላክ ኃያል ነው፤ (2) አምላክ አፍቃሪና ደግ ነው፤ (3) ችግሮች አሁንም ይከሰታሉ። የመጨረሻው ሐሳብ ማንም ሊያስተባብለው የማይችለው ሐቅ ስለሆነ መጀመሪያ ከተጠቀሱት ሁለት ሐሳቦች ውስጥ ቢያንስ አንዱ እውነት ሊሆን አይችልም ብለው ያስባሉ። እንደ እነርሱ አስተሳሰብ ከሆነ ወይ አምላክ ክፋትን ማስቆም ተስኖታል፤ አሊያም ለሚደርሰው መከራ ግድ የለውም።

የዓለም የንግድ ማዕከል ከወደመ ከጥቂት ቀናት በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ አንድ እውቅ የሃይማኖት መሪ እንዲህ ብለው ነበር:- “አምላክ ሐዘንና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ሰዎች በተደጋጋሚ ጠይቀውኛል። ለዚህ ጥያቄ የራሴን አእምሮ እንኳን የሚያሳርፍ መልስ እንደሌለኝ ልገልጽላችሁ እወዳለሁ።”

አንድ የሃይማኖታዊ ትምህርት ፕሮፌሰር ይህን አባባል አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ይህ ሃይማኖታዊ መሪ የሚሰብከው “ሃይማኖታዊ ትምህርት” ልባቸውን ይነካው እንደነበር ጽፈዋል። እንዲሁም “የአምላክን ማንነት ሙሉ በሙሉ መረዳት እንደማንችል ሁሉ ክፋት እንዲኖር የፈቀደበትንም ምክንያት ማወቅ አንችልም” ብለው የጻፉትን የአንድ ምሁር አመለካከት ደግፈው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያት ፈጽሞ ማወቅ አይቻልም?

የክፋት መንስኤ

መጽሐፍ ቅዱስ ሃይማኖታዊ መሪዎች ከሚያስተምሩት በተቃራኒ አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያት ለመረዳት አስቸጋሪ እንደሆነ አይናገርም። በክፋት መንስኤ ዙሪያ ለተነሳው ጥያቄ መልስ ለማግኘት የሚረዳን አንዱ ቁልፍ ነጥብ ይሖዋ በክፋት የተሞላ ዓለም እንዳልፈጠረ መገንዘብ ነው። የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት የፈጠራቸው ፍጹምና ከኃጢአት ነጻ አድርጎ ነው። ይሖዋ የፍጥረት ሥራውን ሲመለከት “እጅግ መልካም” ሆኖ አግኝቶታል። (ዘፍጥረት 1:26, 31) አዳምና ሔዋን ኤደንን አስፋፍተው መላውን ምድር ገነት እንዲያደርጉና በአፍቃሪ ሉዓላዊነቱ ሥር በሚተዳደሩ ደስተኛ ሕዝቦች እንዲሞሏት ዓላማው ነበር።​—⁠ኢሳይያስ 45:18

መጀመሪያ ላይ ለአምላክ ታማኝ የነበረ አንድ መንፈሳዊ ፍጡር የመመለክ ምኞት በውስጡ እንዲዳብር በፈቀደ ጊዜ ክፋት ጀመረ። (ያዕቆብ 1:14, 15) ከዚያም ይህ መንፈሳዊ ፍጡር የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ከእርሱ ጋር ወግነው በአምላክ ላይ እንዲያምፁ ሲያደርግ ዓመፁ በምድርም ላይ ታየ። አዳምና ሔዋን መልካምና ክፉውን የሚያስታውቀውን ዛፍ ፍሬ እንዳይበሉ ወይም እንዳይነኩ አምላክ የሰጣቸውን ግልጽ መመሪያ በመታዘዝ ፋንታ ከፍሬው ወስደው በሉ። (ዘፍጥረት 3:1-6) በዚህ ድርጊታቸው የአምላክን ትእዛዝ ከመጣሳቸውም በላይ ከእርሱ ርቀው በራሳቸው ፈቃድ የመመራት ፍላጎት እንዳላቸውም አሳይተዋል።

በመግዛት መብት ላይ የተነሳ ግድድር

በኤደን ገነት የተፈጸመው ይህ ዓመፅ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውን በመግዛት መብት ላይ ያተኮረ ግድድር አስነስቷል። የሰው ልጆች የፈጸሙት ዓመፅ ይሖዋ ፍጡራኑን የሚገዛው ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ስለ መሆኑ ጥያቄ አስነስቷል። ፈጣሪ የሰው ዘር ሙሉ በሙሉ ለእርሱ እንዲታዘዝ የመጠበቅ መብት አለው? ሰዎች ከአምላክ ርቀው ራሳቸውን በራሳቸው ቢያስተዳድሩ የተሻለ ይሆናል?

ይሖዋ በሉዓላዊነቱ ላይ ለተነሳው ለዚህ ግድድር እልባት ያስገኘው ፍቅሩን፣ ፍትሑን፣ ጥበቡንና ኃይሉን ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ እንደሚጠቀምባቸው በሚያሳይ መንገድ ነው። ኃይሉን ተጠቅሞ ዓመፀኞቹን ወዲያውኑ ማጥፋት ይችል ነበር። እንዲህ የማድረግ መብት ስለነበረው ወዲያውኑ ቢያጠፋቸው ኖሮ ፍትሕን ተጻርሯል አያሰኘውም ነበር። ይሁን እንጂ ይህ በመግዛት መብቱ ላይ ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት አያስችልም። በሌላ በኩል ደግሞ አምላክ ኃጢአታቸውን በይቅርታ ሊያልፈው ይችል ነበር። በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች ይህ አፍቃሪነቱን የሚያሳይ አማራጭ እንደሆነ አድርገው ያስቡ ይሆናል። ቢሆንም የሰው ልጆች ራሳቸውን በራሳቸው ቢያስተዳድሩ የተሻለ ሕይወት መኖር ይችላሉ ለሚለው ለሰይጣን ክስ መልስ ለመስጠት አያስችልም። ከዚያም አልፎ እንዲህ ማድረጉ ሌሎች ሰዎችም ከይሖዋ መንገድ እንዲያፈነግጡ መንገድ የሚከፍት አይሆንም? ውጤቱም ማብቂያ የሌለው መከራ ይሆን ነበር።

ይሖዋ በጥበቡ ተጠቅሞ የሰው ልጆች ለተወሰነ ጊዜ በራሳቸው መንገድ እንዲሄዱ ፈቀደላቸው። ይህ ክፋት ለጊዜው እንዲቀጥል መፍቀድ ማለት ቢሆንም የሰው ልጆች ትክክል የሆነውንና ስህተት የሆነውን በራሳቸው መሥፈርት እየለዩ ያለ አምላክ ጣልቃ ገብነት ራሳቸውን በአግባቡ ማስተዳደር ይችሉ እንደሆነና እንዳልሆነ እንዲያሳዩ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ጦርነት፣ የፍትሕ መጓደል፣ ጭቆናና መከራ ያልታየበት ጊዜ አልነበረም። የሰው ልጆች ከይሖዋ ተለይተው ለመኖር ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱ በኤደን ለተነሱት ጥያቄዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ያስገኛል።

እስከዚያው ድረስ ግን ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰብዓዊ ሕይወቱን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ እንዲሰጥ በማድረግ አምላክ ፍቅሩን አሳይቷል። ይህ ዝግጅት ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች የአዳም አለመታዘዝ ካስከተለው የኃጢአት ኩነኔና ሞት ነጻ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ቤዛው በኢየሱስ ለሚያምኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ መንገድ ከፍቷል።​—⁠ዮሐንስ 3:16

የሰው ልጅ መከራ ለረጅም ጊዜ እንደማይቆይ ይሖዋ የሚያጽናና ማረጋገጫ ሰጥቶናል። መዝሙራዊው “ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል” በማለት ጽፏል።​—⁠መዝሙር 37:10, 11

ወደፊት ሰላምና ደስታ የሰፈነበት ጊዜ ይመጣል

ፍጻሜያቸውን ያገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አምላክ ሕመም፣ ሐዘንና ሞት እንዲያቆሙ የሚያደርግበት ጊዜ መቅረቡን ያሳያሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ ከተመለከታቸው ወደፊት የሚፈጸሙ ድንቅ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን ተመልከት:- “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፣ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፣ ባሕርም ወደ ፊት የለም። . . . እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ [ከሰው ልጆች] ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።” እነዚህ ተስፋዎች እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸውን ለማረጋገጥ ዮሐንስ “እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ” ተብሎ ተነግሮት ነበር።​—⁠ራእይ 21:1-5

በኤደን ከተፈጸመው ዓመፅ ጀምሮ የሞቱት በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችስ ተስፋቸው ምንድን ነው? ይሖዋ አሁን በሞት አንቀላፍተው የሚገኙትን ሰዎች እንደሚያስነሳቸው ቃል ገብቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ” በማለት ተናግሯል። (ሥራ 24:15) እነዚህ ሰዎች ‘ጽድቅ በሚኖርበት’ አዲስ ዓለም ውስጥ የመኖር ተስፋ ይኖራቸዋል።​—⁠2 ጴጥሮስ 3:13

አንድ አፍቃሪ አባት ለልጁ ዘላቂ ፈውስ የሚያስገኝ ከሆነ ጊዜያዊ ህመም የሚያስከትልበት ቢሆንም እንኳ ቀዶ ሕክምና እንዲደረግለት እንደሚፈቅድ ሁሉ ይሖዋም በምድር ላይ ክፋት ለጊዜው እንዲኖርና በሰው ልጆችም ላይ ችግር እንዲደርስ ፈቅዷል። ቢሆንም የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ለሚጥሩ ሁሉ ዘላለማዊ የሆነ በረከት ከፊታቸው ተዘርግቶላቸዋል። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፣ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው።”​—⁠ሮሜ 8:20, 21

እውነትም ይህ በቴሌቪዥን እንደምናየው ወይም በጋዜጣ ላይ እንደምናነበው ዓይነት ዜና ሳይሆን የምሥራች ነው። ለእኛ ከልብ ከሚያስብልን ‘ከመጽናናት ሁሉ አምላክ’ የተገኘ ከሁሉ የተሻለ ዜና ነው።​—⁠2 ቆሮንቶስ 1:3

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰው ልጆች ከአምላክ ርቀው ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንደማይችሉ በጊዜ ሂደት ተረጋግጧል

[ምንጭ]

የሶማሊያ ቤተሰብ:- UN PHOTO 159849/M. GRANT; የአውቶሚክ ፍንዳታ:- USAF photo; ማጎሪያ ካምፕ:- U.S. National Archives photo