ለአንድ የመንግሥት አዳራሽ የተሰጠ የሜዳልያ ሽልማት
የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ለአንድ የመንግሥት አዳራሽ የተሰጠ የሜዳልያ ሽልማት
የፊንላንድ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የ2000 ‘ዓመት መርህ ገጸ ምድርን ማስዋብ’ እንዲሆን ወስኖ ነበር። ፕሮግራሙን ካዘጋጁት ሰዎች አንዷ እንደተናገሩት “ገጸ ምድርን ማስዋብ የዓመቱ መርህ እንዲሆን የተደረገው አካባቢያችን ለምለም መሆኑ በዕለት ተዕለት ሕይወታችንና በደህንነታችን ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ሁላችንም እንድናስተውል ለማድረግ ነው።”
ጥር 12, 2001 በፊንላንድ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ከፊንላንድ የገጸ ምድር እንክብካቤ ማህበር የተላከ ደብዳቤ ይደርሰዋል። ደብዳቤው ግሩም በሆነው የሕንፃው ንድፍና በሚገባ በተያዘው የአትክልት ቦታው ምክንያት በቲኩሪላ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በዓመቱ ከተዘጋጁት ሜዳልያዎች አንዱን እንደተሸለመ ይገልጻል። ደብዳቤው አክሎም እንዲህ ይላል:- “የመንግሥት አዳራሹ ግቢ በክረምትም ሆነ በበጋ ደስ የሚል፣ በጣም ውብና ደረጃውን የጠበቀ ነው።”
የሽልማት ፕሮግራሙ የተከናወነው በታምፐሬ፣ ፊንላንድ በሮዘንዳል ሆቴል 400 ባለሙያዎችና ነጋዴዎች በተገኙበት ነበር። የፊንላንድ የገጸ ምድር እንክብካቤ ማህበር ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዲህ ብሏል:- “በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙት ሁሉም የመንግሥት አዳራሾች ማለት ይቻላል የሚያምር ንድፍ አላቸው። የመንግሥት አዳራሾቹ ግቢ በሚገባ የተያዘ በመሆኑ በዚያ የሚያልፍን ማንኛውንም ሰው የሚማርክ ነው። በቲኩሪላ የሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ድንቅ ከሚባሉት የአትክልት ቦታዎች አንዱ ነው። ሕንፃውና ግቢው ለተመልካች ውብና መንፈስን የሚያድስ ነው።”
በፊንላንድ 233 የመንግሥት አዳራሾች የሚገኙ ሲሆን አብዛኞቹ ውብ የሆኑ የአትክልት ቦታዎች አሏቸው። እነዚህን ቦታዎች የበለጠ ውበት የሚሰጣቸው ግን የእውነተኛው አምልኮ ማዕከልና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚሰጥባቸው ቦታዎች መሆናቸው ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙት ከስድስት ሚልዮን የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሻቸው ትልቅም ሆነ ትንሽ ለእነሱ ተወዳጅ ቦታ በመሆኑ ጥሩ አድርገው ይንከባከቡታል። የመንግሥት አዳራሾቹ ለማንኛውም ሰው ክፍት ናቸው።