ጥንትም ሆነ ዛሬ ጠቃሚ የሆነው “ሴፕቱጀንት”
ጥንትም ሆነ ዛሬ ጠቃሚ የሆነው “ሴፕቱጀንት”
ከኢትዮጵያ የመጣ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ከኢየሩሳሌም ወደ አገሩ እየተጓዘ ነበር። በሰረገላ ተቀምጦ ምድረ በዳውን አቋርጦ በሚጓዝበት ወቅት አንድ ሃይማኖታዊ ጽሑፍ ጮክ ብሎ ያነብብ ነበር። ያነብበው ለነበረው ሐሳብ የቀረበለት ማብራሪያ ልቡን ስለነካው ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሕይወቱ ተለወጠ። (ሥራ 8:26-38) ሰውዬው ያነብ የነበረው የመጀመሪያ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ከሆነው ከግሪክኛው ሴፕቱጀንት ላይ ኢሳይያስ 53:7, 8ን ነበር። ይህ ትርጉም ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለማዳረስ ከፍተኛ ድርሻ ያበረከተ ከመሆኑ የተነሳ ዓለምን የለወጠ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለመባል በቅቷል።
የሴፕቱጀንት ትርጉም የተዘጋጀው መቼና በምን ዓይነት ሁኔታዎች ሥር ነበር? እንዲህ ዓይነት ትርጉም ማዘጋጀት ያስፈለገው ለምን ነበር? ባለፉት መቶ ዘመናት ምን ጥቅም አበርክቷል? የሴፕቱጀንት ትርጉም ዛሬስ ምን ጥቅም ይሰጠናል?
ግሪክኛ ተናጋሪ ለሆኑ አይሁዳውያን የተዘጋጀ
በ332 ከዘአበ ታላቁ እስክንድር የከነዓን ከተማ የሆነችውን ጢሮስን ከደመሰሰ በኋላ ወደ ግብፅ ሲገባ እንደ ነፃ አውጪ ተቆጥሮ አቀባበል ተደረገለት። ግብፅ ውስጥ የጥንቱ ዓለም የትምህርት ማዕከል የሆነችውን እስክንድርያ የምትባል ከተማ ቆረቆረ። እስክንድር ድል አድርጎ በያዛቸው አገሮች ውስጥ የግሪክን ባሕል ለማስፋፋት ከነበረው ፍላጎት የተነሳ ሰፊ በሆነው ግዛቱ ውስጥ ተራ ግሪክኛ (ኮይኔ) የመግባቢያ ቋንቋ እንዲሆን አደረገ።
በሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ እስክንድርያ የበርካታ አይሁዳውያን መኖሪያ ሆና ነበር። ከባቢሎን ግዞት በኋላ ከጳለስጢና ውጪ በተለያዩ አገሮች ተበታትነው ይኖሩ የነበሩ ብዙ አይሁዳውያን ወደ እስክንድርያ መፍለስ ጀመሩ። እነዚህ አይሁዳውያን ዕብራይስጥን ምን ያህል ያውቁ ነበር? ማክሊንቶክ እና ስትሮንግስ ሳይክሎፔዲያ እንዲህ ይላል:- “አይሁዳውያን ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሱ በኋላ ቀድሞ ቋንቋቸው የነበረውን ጥንታዊውን ዕብራይስጥ በአብዛኛው እንደረሱት የታወቀ ነው። በመሆኑም ጳለስጢና ውስጥ በሚገኙ ምኩራቦች የሙሴ መጽሐፍ ከተነበበ በኋላ በከለዳውያን ቋንቋ ይተረጎምላቸው ነበር . . . በእስክንድርያ የሚኖሩ አይሁዳውያን ደግሞ የዕብራይስጥ ቋንቋ ችሎታቸው በጣም ዝቅተኛ ሳይሆን ስለማይቀር መግባቢያ ቋንቋቸው የእስክንድርያ ግሪክኛ ነበር።” ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው እስክንድርያ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ወደ ግሪክኛ ለመተርጎም የሚያስችል አመቺ ሁኔታ ነበራት።
በዕብራይስጥ ቋንቋ የሚገኘውን የሕጉን ቅጂ ወደ ግሪክኛ የመተርጎሙ ሥራ በቶሌሚ ፊላደልፈስ (285-246 ከዘአበ) የግዛት ዘመን እንደተጠናቀቀ በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የኖረ አሪስቶቡለስ የተባለ አንድ አይሁዳዊ ጽፏል። አሪስቶቡለስ “ሕጉ” ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ አወዛጋቢ ሆኖ ቆይቷል። አንዳንዶች ሕጉ ሲል ኦሪትን ብቻ ማመልከቱ እንደሆነ ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን በሙሉ ማለቱ ሊሆን ይችላል ይላሉ።
ያም ሆነ ይህ ቅዱሳን ጽሑፎችን ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክኛ ለመጀመሪያ ጊዜ በጽሑፍ በተተረጎመው በዚህ ሥራ ላይ ወደ 72 ገደማ የአይሁድ ምሁራን ተሳትፈው እንደነበር ሲነገር ቆይቷል። ከጊዜ በኋላ 70 ብሎ መጥራቱ አመቺ ሆኖ ተገኘ። በመሆኑም ይህ ትርጉም “70” የሚል ፍቺ ባለው ሴፕቱጀንት በሚል ስያሜ መጠራት የጀመረ ሲሆን 70ን የሚያመለክተው የሮማውያን ቁጥር ማለትም LXX የትርጉሙ መለያ ሆነ። በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ማብቂያ ላይ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በሙሉ ወደ ግሪክኛ ተተርጉመው ነበር። ይህም በመሆኑ ሴፕቱጀንት የሚለው ስያሜ ወደ ግሪክኛ የተተረጎሙትን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በአጠቃላይ ያመለክት ጀመር።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል
ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያቱ በኖሩበትም ሆነ ከዚያ በፊት በነበረው ዘመን ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ አይሁዳውያን በሴፕቱጀንት ትርጉም በሰፊው ይጠቀሙ ነበር። በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም ተሰብስበው የነበሩ አብዛኞቹ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ግሪክኛ ተናጋሪ ከነበሩ ግዛቶች ማለትም ከእስያ፣ ከግብፅ፣ ከሊቢያ፣ ከሮምና ከቀርጤስ የመጡ ነበሩ። እነዚህ ሰዎች የሴፕቱጀንትን ትርጉም የማንበብ ልማድ እንደነበራቸው ምንም ጥርጥር የለውም። (ሥራ 2:9-11) በመሆኑም ይህ ትርጉም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ምሥራቹን በማዳረስ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አበርክቷል።
ለምሳሌ ያህል ደቀ መዝሙሩ እስጢፋኖስ ከቀሬና፣ ከእስክንድርያ፣ ከኪልቅያና ከእስያ ከመጡ ሰዎች ጋር በተነጋገረበት ወቅት “ዮሴፍም አባቱን ያዕቆብንና ሰባ አምስት ነፍስ የነበረውን ቤተ ዘመድ ሁሉ ልኮ [ከከነዓን] አስጠራ” ሲል ተናግሯል። (ሥራ 6:8-10፤ 7:12-14) ዘፍጥረት ምዕራፍ 46 ላይ በዕብራይስጥ የተጻፈው ጥቅስ የዮሴፍ ዘመዶች ብዛት ሰባ እንደሆኑ ይናገራል። ሆኖም ሴፕቱጀንት ቁጥራቸው ሰባ አምስት እንደሆነ ይገልጻል። በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው እስጢፋኖስ ጠቅሶ የተናገረው ከሴፕቱጀንት ላይ ነበር።—ዘፍጥረት 46:20, 26, 27
ሐዋርያው ጳውሎስ በሁለተኛውና በሦስተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት በመላዋ ትንሿ እስያና ግሪክ ሲመላለስ አምላክን ለሚፈሩ በርካታ አሕዛብና እሱን ‘ለሚያመልኩ ለግሪክ ሰዎች’ ምሥራቹን ሰብኮ ነበር። (ሥራ 13:16, 26፤ 17:4) እነዚህ ሰዎች አምላክን ወደ መፍራት ወይም ወደ ማምለክ ደረጃ የደረሱት ከሴፕቱጀንት ላይ ስለእሱ የተማሯቸው አንዳንድ ነገሮች ስለነበሩ ነው። ጳውሎስ ለእነዚህ ግሪክኛ ተናጋሪዎች በሚሰብክበት ጊዜ በአብዛኛው ከዚህ ትርጉም ላይ አንዳንድ ክፍሎችን በቀጥታ ይጠቅስ አሊያም በራሱ አባባል ይገልጽ ነበር።—ዘፍጥረት 22:18፤ ገላትያ 3:8
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ በቀጥታ የተወሰዱ 320 ጥቅሶችን የያዙ ሲሆን በድምሩ 890 የሚያህሉ በቀጥታ የተጠቀሱ ጥቅሶችና የጥቅስ ሐሳቦች ይዘዋል። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የተወሰዱት ከሴፕቱጀንት ትርጉም ነው። ከዚህም የተነሳ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል ለመሆን የበቁት በዕብራይስጥ ቋንቋ ከተዘጋጁት ቅጂዎች ላይ ሳይሆን ከሴፕቱጀንት ትርጉም ላይ የተወሰዱት ጥቅሶች ናቸው። ይህ ምንኛ ከፍተኛ ትርጉም ያዘለ ጉዳይ ነው! ኢየሱስ የመንግሥቱ ምሥራች በዓለም ሁሉ እንደሚሰበክ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) ይህን ዳር ለማድረስ ይሖዋ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ቃሉን በመላው ዓለም የሚኖሩ ሰዎች ማንበብ እንዲችሉ ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች እንዲተረጎም ያስችላል ማለት ነው።
ዛሬም ጠቃሚ ነው
የሴፕቱጀንት ትርጉም ዛሬም ቢሆን ጠቃሚ ሲሆን ከጊዜ በኋላ በተዘጋጁ የዕብራይስጥ ጽሑፍ ቅጂዎች ላይ ገልባጮች የፈጸሟቸውን ስህተቶች ለማግኘት ይረዳል። ለምሳሌ ያህል ዘፍጥረት 4:8 ላይ ያለው ዘገባ “ቃየንም ወንድሙን አቤልን:- ና ወደ ሜዳ እንሂድ አለው። በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፣ ገደለውም” ይላል።
“ና ወደ ሜዳ እንሂድ” የሚለው ሐረግ ከአሥረኛው መቶ ዘመን እዘአ ወዲህ በዕብራይስጥ ቋንቋ በተዘጋጁ የቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎች ላይ አይገኝም። ይሁን እንጂ ረጅም ዕድሜ ባስቆጠሩ በእጅ የተገለበጡ የሴፕቱጀንት ትርጉም ቅጂዎችና ቀደምት በሆኑ ሌሎች ጥቂት የትርጉም ሥራዎች ላይ ሠፍሮ ይገኛል። በዕብራይስጥ ቋንቋ የተዘጋጁት ቅጂዎች ቃየን አንድ የሆነ ነገር መናገሩን የሚጠቁም ቃል የያዙ ቢሆንም የተናገራቸው ቃላት ግን አልተጻፉም። ይህ ሊሆን የቻለው በምን ምክንያት ነው? ዘፍጥረት 4:8 “ወደ ሜዳ” የሚል ትርጉም ባለው የዕብራይስጥ ቃል የሚደመደሙ በተከታታይ የተቀመጡ ሁለት ሐረጎችን ይዟል። ማክሊንቶክ እና ስትሮንግስ ሳይክሎፔዲያ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- “ይህንን የዕብራይስጥ ቃል የያዙ ሁለት ተከታታይ ሐረጎች ስለሚገኙ ገልባጩ በስህተት የመጀመሪያውን ዘልሎ ሁለተኛውን በመጻፉ የተፈጠረ ግድፈት ሊሆን ይችላል።” ገልባጩ “ወደ ሜዳ” በሚሉት ቃላት የሚደመደመውን የመጀመሪያውን ሐረግ ሳያስገባ የቀረው በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ሴፕቱጀንትም ሆነ እስካሁን ድረስ ያሉ በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎች ከጊዜ በኋላ በተዘጋጁት የዕብራይስጥ ጽሑፍ ቅጂዎች ላይ የተሠሩ ግድፈቶችን ለማግኘት ይረዳሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ የሴፕቱጀንት ቅጂዎችም ግድፈት የማያጣቸው ሲሆን ግሪክኛውን ጽሑፍ ለማረም የዕብራይስጡ ጽሑፍ ማመሳከሪያ ሆኖ የሚያገለግልበት ጊዜ አለ። በመሆኑም በዕብራይስጥ ቋንቋ የተዘጋጁ ቅጂዎችን ከግሪክኛውና በሌሎች ቋንቋዎች ከተዘጋጁ ትርጉሞች ጋር በማነጻጸር የትርጉም ግድፈቶችንም ሆነ ገልባጮች የፈጸሟቸውን ስሕተቶች ለማግኘት ከመቻሉም በላይ የአምላክን ቃል በትክክል ለመተርጎም የሚያስችል መሠረት አስገኝተዋል።
በዛሬው ጊዜ ያሉት የተሟሉ የሴፕቱጀንት ትርጉም ቅጂዎች የተዘጋጁት ከአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ ወዲህ ነው። እንደዚህ ያሉት በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ ጽሑፎችም ሆኑ ከጊዜ በኋላ የተዘጋጁ ቅጂዎች ይሖዋ የተባለውን መለኮታዊ ስም የሚወክሉትን አራት የዕብራይስጥ ፊደላት (የሐወሐ) አልያዙም። እነዚህ ቅጂዎች በዕብራይስጥ ቋንቋ በተዘጋጁ ጽሑፎች ላይ የይሖዋን ስም የሚወክሉ አራቱ ፊደላት የሚገኙባቸውን ቦታዎች በሙሉ “አምላክ” እና “ጌታ” የሚል ትርጉም ባላቸው የግሪክኛ ቃላት ተክተዋቸዋል። ይሁን እንጂ ከ50 ዓመት ገደማ በፊት በጳለስጢና የተገኙት ጽሑፎች በዚህ ጉዳይ ላይ ብርሃን ፈንጥቀዋል። በሙት ባሕር በስተ ምዕራብ በኩል ባለው ዳርቻ በሚገኙ ዋሻዎች ላይ ጥናት ያደረገ አንድ ቡድን በግሪክኛ የተጻፉ የአሥራ ሁለቱን ነቢያት (ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ) ጥንታዊ የብራና ጥቅልል ቁርጥራጮች አገኘ። እነዚህ ጽሑፎች የተዘጋጁት ከ50 ከዘአበ እስከ 50 እዘአ ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር። በእነዚህ ጥንታዊ ቁርጥራጮች ላይ የይሖዋን ስም የሚወክሉት አራቱ የዕብራይስጥ ፊደላት “አምላክ” እና “ጌታ” የሚል ትርጉም ባላቸው የግሪክኛ ቃላት አልተተኩም። በመሆኑም መለኮታዊው ስም ጥንት በተዘጋጁት የሴፕቱጀንት ትርጉም የቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎች ላይ ይገኝ እንደነበር ማረጋገጥ ተችሏል።
በ1971 የአንድ ጥንታዊ የፓፒረስ ጥቅልል (ፉአድ 266 ፓፒረስ) ቁርጥራጮች ታትመው ወጡ። በሁለተኛው ወይም በአንደኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተዘጋጁት እነዚህ የሴፕቱጀንት ክፍሎች ምን ቁም ነገር ይዘዋል?
መለኮታዊው ስም በእነዚህ ጽሑፎችም ውስጥ ይገኝ ነበር። እነዚህ ቀደምት የሴፕቱጀንት ትርጉም ቁርጥራጮች ኢየሱስና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ደቀ መዛሙርቱ የአምላክን ስም ያውቁና በስሙ ይጠሩት እንደነበር ጠንካራ ማስረጃ ይሰጡናል።በዛሬው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ በታሪክ ዘመናት ሁሉ በከፍተኛ መጠን የተተረጎመ መጽሐፍ ነው። ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ የሰው ልጆች ቢያንስ የመጽሐፉን የተወሰነ ክፍል በራሳቸው ቋንቋ ማንበብ ይችላሉ። በዘመናዊ የእንግሊዝኛ ቋንቋ በትክክል የተተረጎመውን የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም በማግኘታችን እጅግ አመስጋኞች ነን። ይህ ትርጉም በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ወይም የተወሰነውን ክፍል ከ40 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል። ባለማጣቀሻው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ከሴፕቱጀንትም ሆነ ከሌሎች ጥንታዊ ጽሑፎች ላይ የተወሰዱ በመቶዎች የሚቆጠሩ የግርጌ ማስታወሻዎች አሉት። በእርግጥም ሴፕቱጀንት በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ዘንድ ትኩረት የሚስብና ዋጋማ ሆኖ ቀጥሏል።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ደቀ መዝሙሩ ፊልጶስ ከ“ሴፕቱጀንት” ላይ የተወሰደን ጥቅስ አብራርቷል
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሐዋርያው ጳውሎስ ከ“ሴፕቱጀንት” ላይ በተደጋጋሚ ጠቅሷል