በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዛሬው ጊዜ ሰዎች “ለቅዱሳን” ያላቸው አመለካከት

በዛሬው ጊዜ ሰዎች “ለቅዱሳን” ያላቸው አመለካከት

በዛሬው ጊዜ ሰዎች “ለቅዱሳን” ያላቸው አመለካከት

“ታላላቅ ሰዎች ስለፈጸሙት ገድል መስማት ሰልችቶን የነበረበትን ጊዜ ታስታውሳላችሁ? መስከረም 13 የተፈጸመውን የማዘር ቴሬዛ የቀብር ሥነ ሥርዓት የተከታተሉት 4.2 ሚልዮን የሚሆኑ አሜሪካውያን ግን እንዲህ ዓይነት ስሜት ያደረባቸው አይመስልም። ማዘር ቴሬዛ ከሞቱበት ከመስከረም 5 አንስቶ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ሕዝብ እኚህ ሴት በይፋ ቅድስት ተብለው እንዲጠሩ ለቫቲካን ጥያቄ አቅርቧል። ጥያቄያቸው አዎንታዊ ምላሽ እንደሚያገኝ ብዙዎቹ እርግጠኞች ነበሩ።”​—⁠ሰን ሴንቲነል፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ጥቅምት 3, 1997

ዙ ሰዎች የካቶሊክ ሚስዮናዊ የሆኑት ማዘር ቴሬዛ ሲያከናውኑት የነበረውን የበጎ አድራጎት ሥራ የእውነተኛ ቅዱስነት መለያ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። በሌሎች ሃይማኖቶች ውስጥ ብዙ ገድል የፈጸሙ ታላላቅ ሰዎችም አሉ። ይሁን እንጂ በአብዛኛው በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ተብለው የሚሰየሙትን ሰዎች ያህል ሰፊ ዕውቅና አያገኙም።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዳግማዊ ጆን ፖል በጵጵስና ዘመናቸው 300 የሚያክሉ ሰዎችን ቅዱስ ብለው የሰየሙ ሲሆን ይህ ቁጥር በ20ኛው መቶ ዘመን የተነሱት ሌሎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በአጠቃላይ ቅዱስ ብለው ከሰየሟቸው ሰዎች ቁጥር የሚበልጥ ነው። a ለመሆኑ በአብዛኞቹ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ዘንድ እምብዛም ለማይታወቁ “ቅዱሳን” ከፍተኛ አክብሮት የሚሰጠው ለምንድን ነው?

በኖትር ዳም ዩኒቨርሲቲ የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ሎረንስ ከኒንግሃም እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “በዚህ ዓለም ውስጥ ቅዱሳን አሉ የሚለው ሐሳብ ራሱ የሰዎችን ትኩረት ይስባል። ቅዱስ ተብለው ሊጠሩ የሚችሉ ሰዎች መኖራቸው በዛሬው ጊዜም እንኳን መሥዋዕትነት የሚጠይቅ ሕይወት መምራት እንደሚቻል ያሳያል።” ከዚህም በተጨማሪ “ቅዱሳን” በአምላክ ፊት የመቆም ልዩ መብት ስላላቸው በሕይወት ያሉትን ሰዎች ማማለድ ይችላሉ ተብሎ ይታመናል። የአንድ “ቅዱስ” ሰው ዕቃ ወይም ቅሪተ አካል ሲገኝ ተአምራዊ ኃይል እንዳለው ተደርጎ ስለሚታሰብ ከፍተኛ አክብሮት ይሰጠዋል።

በ16ኛው መቶ ዘመን የታተመውና የትሬንት ጉባኤ የካቶሊክን ቤተ ክርስቲያን ቀኖና ትክክለኛነት አስመልክቶ ያሳለፈውን ድንጋጌ የያዘ አንድ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “‘በጌታ ላንቀላፉ’ ቅዱሳን አክብሮት መስጠት፣ እንዲያማልዱ እነርሱን መለመን፣ እነርሱ ይገለገሉባቸው የነበሩትን ዕቃዎችና ቅሪተ አካላቸውን በአክብሮት መመልከት ለአምላክ ክብር ይጨምርለታል እንጂ ክብሩን ፈጽሞ አይቀንስበትም ብለን እንድንደመድም የሚያስችል አጥጋቢ ምክንያት አለን። ይህ ክርስቲያኑ ባለው ተስፋ ጥንካሬና ሕያውነት ላይ የተመካ ነው። ከዚህም በላይ የቅዱሳኑን አማላጅነት የሚለምነው ክርስቲያን ቅዱሳን የተከተሉትን የጽድቅ ጎዳና ለመከተል ይነሳሳል።” (ዘ ካቴቺዝም ኦቭ ዘ ካውንስል ኦቭ ትሬንት፣ 1905) እውነተኛ ክርስቲያኖች የጽድቅ አኗኗር ለመከተል፣ አምላክን በትክክለኛው መንገድ ለመቅረብና መለኮታዊ እርዳታ ለማግኘት ከልብ ይፈልጋሉ። (ያዕቆብ 4:​7, 8) በመሆኑም በአምላክ ቃል መሠረት በእርግጥ ቅዱሳን ተብለው መጠራት የሚችሉት እነማን ናቸው? የሚያበረክቱት ድርሻስ ምንድን ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንድ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አባል ከሞተ በኋላ ቅዱስ የሚል ስያሜ ማግኘቱ በመላው የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ አክብሮት ሊሰጠው እንደሚገባ ያሳያል።