በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የአምላክ ቃል ኃይል አለው’

‘የአምላክ ቃል ኃይል አለው’

የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት

‘የአምላክ ቃል ኃይል አለው’

ጃማይካ ፀሐያማ የሆነች የካሪቢያን ደሴት ስትሆን አብዛኞቹ ነዋሪዎቿ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያውቃሉ። እንዲያውም የኪንግ ጄምስ ቨርሽን መጽሐፍ ቅዱስ በአብዛኞቹ ቤት ውስጥ ይገኛል። አንዳንዶቹም ‘የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይል ያለው’ መሆኑን ከራሳቸው ተሞክሮ አይተዋል። (ዕብራውያን 4:​12 NW ) የሚከተለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው ይህ ኃይል ሰዎችን መለወጥ ይችላል።

ክሌቭላንድ የተባለ አንድ ሰው ከሥራ ወደ ቤቱ ገና መመለሱ ነበር። ወዲያውኑ አንድ የይሖዋ ምሥክር ቤቱን አንኳኳ። ምሥክሩ ከቅዱሳን ጽሑፎች አንዳንድ ነጥቦችን ካወያየው በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለ መጽሐፍ ሰጥቶት ሄደ። ክሌቭላንድ የአምላክ ቃል በሕይወቱ ላይ ያን ያህል ከፍተኛ ለውጥ ያስከትላል ብሎ አልገመተም ነበር።

ክሌቭላንድ አምላክን ማምለክ የሚችልበትን ትክክለኛ መንገድ እንዲያሳየው በቀን ሦስት ጊዜ እየጸለየ አምላክን ይለምን ነበር። የወላጆቹ አምልኮ ትክክለኛ እንዳልሆነ ተረድቶ ነበር። ሌሎች ሃይማኖቶችን ከመረመረ በኋላ ግን ይበልጥ ግራ ተጋባ። ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የሰማ ቢሆንም የያዙት መንገድ እውነት መሆኑ ግን አጠራጠረው። ትንሽ ቢያቅማማም መጀመሪያ እቤቱ መጥቶ ካነጋገረው ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። ለምን? ምሥክሮቹ የሚከተሉት እምነት ትክክል አለመሆኑን ሊያሳያቸው ስለ ፈለገ ነበር!

ብዙም ሳይቆይ ክሌቭላንድ ከሁለት ሴቶች ጋር የነበረው ሥነ ምግባር የጎደለው ግንኙነት አምላክን እንደማያስደስት ተገነዘበ። (1 ቆሮንቶስ 6:​9, 10) ሁለት ጊዜ ካጠና በኋላ ከነዚህ ሴቶች ጋር የነበረውን ግንኙነት ለማቋረጥ ድፍረት አገኘ። በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይም መገኘት ጀመረ። ይሁን እንጂ በስብሰባ ላይ መገኘቱ ራሱ ሌላ ፈተና ሆነበት።

ክሌቭላንድ የሰፈሩ የእግር ኳስ ቡድን ተጫዋች ነበር። ቡድኑ ግጥሚያ የሚያደርግበት ሰዓት ከስብሰባው ሰዓት ጋር ይጋጭ ነበር። ምን ያደርግ ይሆን? የቡድኑ አባላት፣ አሠልጣኙና ጓደኞቹ ከፍተኛ ግፊት ቢያደርጉበትም ቡድኑን ለቅቆ ለመውጣት ወሰነ። አዎን፣ የአምላክ ቃል የሚጠቅመውን እንዲያደርግ በማነሳሳት በሕይወቱ ላይ ተጽእኖ ማሳደር ጀምሮ ነበር!

ክሌቭላንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቱን ለሌሎች ማካፈል ሲጀምር የአምላክ ቃል ኃይል እንዳለው በድጋሚ ታይቷል። (ሥራ 1:​8) ከዚህም የተነሣ ሁለት የቀድሞ የእግር ኳስ ቡድኑ አባላት የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ። ክሌቭላንድ ብቃቱን አሟልቶ የመንግሥቱ አስፋፊ ከሆነ በኋላ የአምላክን ቃል ተጠቅሞ ሌሎችን በመርዳት በአገልግሎቱ ከፍተኛ ደስታ አግኝቷል።

ክሌቭላንድ የአምላክ ቃል በሚያሳድረው ኃይል ለውጥ ማድረጉን በመቀጠል በመጨረሻ ራሱን ለይሖዋ ወስኖ ተጠመቀ። አሁን የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊና የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ በጉባኤ ውስጥ የማገልገል መብት አግኝቷል።

በጃማይካና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክ ቃል በእርግጥም “ሕያውና የሚሠራ” መሆኑን ተገንዝበዋል።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ጃማይካ

[ምንጭ]

ካርታ እና ሉል:- Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.