መተማመኛ አድርገህ የምትመለከተው ምንን ነው?
መተማመኛ አድርገህ የምትመለከተው ምንን ነው?
በአንዲት የምዕራብ አፍሪካ መንደር የሚኖረው ዦዝዌ ቤተሰቦቹንና ጓደኞቹን ተሰናብቶ ኑሮውን ለማሻሻል ወደ አንዲት ትልቅ ከተማ አቀና። a ይሁን እንጂ እዚያ እንደደረሰ በከተማዋ ወርቅ እንደማይታፈስ ሲገነዘብ ተስፋው ሁሉ እንደ ጉም በንኖ ጠፋ።
ዦዝዌ ከከተማ ሕይወት ጋር ራሱን ለማላመድ የሚያደርገው ትግል ተስፋ አስቆራጭ ሆነበት። የከተማ ኑሮ እሱ እንዳሰበው ሆኖ አላገኘውም። ይህ በእንዲህ እንዳለ ዦዝዌ በዚያች አነስተኛ መንደር ትቷቸው ወደመጣው ዘመዶቹና ጓደኞቹ ለመመለስ ይናፍቅ ጀመር። ሆኖም አንዳንድ የመንደሪቱ ነዋሪዎች መሳለቂያ እንዳያደርጉት ፈራ። ‘የከተማ ኑሮ ስላልተሳካልኝ ደካማ ይሉኛል’ ብሎ አሰበ።
ከሁሉም በላይ የከበደው ግን ወላጆቹ ሊሰማቸው የሚችለው የተስፋ መቁረጥ ስሜት ነው። በገንዘብ ይደጉመናል ብለው ተስፋቸውን በእርሱ ላይ ጥለው ነበር። ከደረሰበት የስሜት ጫና ጋር እየታገለ እያለ አልሞት ከነበረው በጣም ያነሰ ገንዘብ የሚያስገኝ ዝቅተኛ ሥራ ለረጅም ሰዓት መሥራት ጀመረ። ከሚገባው በላይ ስለሚሠራ በጣም ይደክመው ነበር። እንዲሁም የላቀ ቦታ ለሚሰጠው ለክርስቲያናዊ እንቅስቃሴው የሚተርፈው ጊዜ ከሳምንት ወደ ሳምንት እያሽቆለቆለ መጣ። ልባዊ ፍቅር ከሚያሳዩት ቤተሰቦቹና ከቀድሞ ጓደኞቹ በጣም ርቆ ስለሚኖር በሐዘንና በብቸኝነት ተቆራመደ። የከተማ ኑሮ በጣም ጓጉቶለት የነበረውን ከጭንቀት ነጻ የሆነ ሕይወት ሊያስገኝለት እንደማይችል ተረዳ።
የስምና የቦታ ልዩነት ካልሆነ በስተቀር የዦዝዌን የመሰለው አሳዛኝ ታሪክ በየጊዜው የሚያጋጥም ክስተት ነው። ዦዝዌ ወደ ከተማ የሄደው በራስ ወዳድነት ስሜት ተነሳስቶ ሳይሆን የሚተማመንበት አንድ ነገር ለማግኘት አስቦ ነበር። ካደገባት አነስተኛ መንደር ይልቅ በከተማ ውስጥ መኖር የተሻለ አጋጣሚ እንደሚያስገኝለት አስቦ ነበር። እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው በቁሳዊ ነገሮች አንጻር ያለበትን ደረጃ ማሻሻል ይችል ይሆናል፤ ይህ ማለት ግን እውነተኛ ደህንነት አግኝቷል ማለት አይደለም። ዦዝዌም ሆነ ሌሎች ተመሳሳይ ሙከራ የሚያደርጉ አብዛኞቹ ሰዎች እንደዚያ አይሆንላቸውም። ይህም ‘መተማመኛ ማግኘት ሲባል ምን ማለት ነው?’ ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል።
ሰኪዩሪቲ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል በተለያዩ ሰዎች የተለያየ ትርጉም ይሰጠዋል። አንድ መዝገበ ቃላት “ከአደጋ ነጻ መሆን” ወይም “ከስጋት ወይም ከጭንቀት ነፃ መሆን” በማለት ገልጾታል። ብዙ ሰዎች በዛሬው ጊዜ ሙሉ በሙሉ “ከአደጋ ነጻ መሆን” እንደማይቻል ይገነዘባሉ። በአስፈሪ ሁኔታዎች ተከብበው እያሉ እንኳን ስጋት እስካልተሰማቸው ድረስ ረክተው ይኖራሉ።
አንተስ እንዴት ነህ? መተማመኛ አድርገህ የምትመለከተው ምንን ነው? ዦዝዌ ተሰምቶት እንደነበረው ከአነስተኛ መንደር ይልቅ በከተማ ውስጥ ይገኝ ይሆን? ወይስ ከየትም ወይም እንዴትም ብለህ አግኘው በገንዘብ ይገኝ ይሆን? ከፍ ያለ የኑሮ ደረጃ ላይ ለመድረስ በመጣጣር ይገኝ ይሆን? መተማመኛ ይሆንልኛል ብለህ የምታስበው ነገር ምንም ይሁን ምን ለአንተም ሆነ ለቤተሰብህ ከለላ የሚሆንላችሁ ለምን ያህል ጊዜ ነው?
ብዙ ሰዎች መተማመኛ አድርገው የሚመለከቷቸውን ሦስት ነገሮች ይኸውም የመኖሪያ አካባቢን፣ ገንዘብንና የተደላደለ የኑሮ ደረጃን እስቲ እንመልከት። ከዚያም እውነተኛና ዘላቂ መተማመኛ ከየት ማግኘት እንደሚቻል እንመረምራለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስሙ ተቀይሯል።