ሕይወትህ የላቀ ትርጉም ሊኖረው የሚችለው እንዴት ነው?
ሕይወትህ የላቀ ትርጉም ሊኖረው የሚችለው እንዴት ነው?
አንድ ጥንታዊ ምሳሌ “ባለጠጋ ለመሆን አትድከም፤ የገዛ ራስህን ማስተዋል ተው። በእርሱ ላይ ዓይንህን ብታዘወትርበት ይጠፋል፤ ባለጠግነት ወደ ሰማይ እንደሚበርር እንደ ንስር ለራሱ ክንፍ ያበጃልና” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 23:4, 5) በሌላ አባባል፣ ሀብት እንደ ንስር ክንፍ አውጥቶ ሊበርር ስለሚችል ሀብታም ለመሆን ራስን ማድከም ጥበብ አይደለም።
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያሳየው ቁሳዊ ሀብት በቅጽበት ሊጠፋ ይችላል። በተፈጥሮ አደጋ፣ በኢኮኖሚ ግሽበት ወይም በሌሎች ያልተጠበቁ ክስተቶች በአንድ ሌሊት ሊወድም ይችላል። ከዚህም በላይ ቁሳዊ ሀብት በማካበት የተሳካላቸው ሰዎች እንኳ በአብዛኛው የጠበቁትን ነገር ሳያገኙ ይቀራሉ። የፖለቲካ ሰዎችን፣ የታወቁ ስፖርተኞችንና ንጉሣውያን ቤተሰብን ከማዝናናት ጋር የተያያዘ ሥራ ያለውን የጆንን ሁኔታ ተመልከት።
ጆን እንዲህ ይላል:- “ለሥራዬ ያደርኩ ሰው ነበርኩ። በገንዘብ በለጸግሁ፣ የማርፈው በትልልቅ ሆቴሎች ውስጥ ነበር፤ አንዳንድ ጊዜ ወደ ሥራ የምሄደው በግል አውሮፕላን ነበር። መጀመሪያ ላይ በጣም ደስ አለኝ፤ የኋላ ኋላ ግን አሰልቺ ሆነብኝ። እንዲደሰቱ ለማድረግ የምደክምላቸው ሰዎች ቀልለው ታዩኝ። ሕይወቴ ትርጉም አጣ።”
ጆን እንደተገነዘበው ሁሉ መንፈሳዊ ቁም ነገሮች የሌሉት ሕይወት አርኪ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ በዝነኛ የተራራ ስብከቱ ላይ ዘላቂ ደስታ ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ አመልክቷል። “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው፣ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ነውና” ብሏል። (ማቴዎስ 5:3 NW ) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው በሕይወት ውስጥ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠቱ ጥበብ ነው። ይሁን እንጂ ሕይወት የላቀ ትርጉም እንዲኖረው ሊረዱ የሚችሉ ሌሎች ነገሮችም አሉ።
ቤተሰብህና ጓደኞችህ ድርሻ አላቸው
ከቤተሰብህ ጋር የማትገናኝ ብትሆንና የቅርብ ጓደኞች ባይኖሩህ ኖሮ ሕይወት አስደሳች ይሆንልህ ነበር? እንደማይሆን የታወቀ ነው። ፈጣሪያችን የመውደድና የመወደድ ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ፈጥሮናል። ኢየሱስ ‘ባልንጀራችንን እንደ ነፍሳችን የመውደድን’ አስፈላጊነት ያጎላበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። (ማቴዎስ 22:39) ቤተሰብ ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር ለማሳየት የተመቻቸ ሁኔታ የሚፈጥር መለኮታዊ ስጦታ ነው።—ኤፌሶን 3:14, 15
ቤተሰባችን ሕይወታችን የላቀ ትርጉም እንዲኖረው የሚያደርገው እንዴት ነው? አንድነት ያለው ቤተሰብ የየዕለቱ ሕይወት ከሚያስከትለው ውጥረት እረፍት ከሚሰጥ ውብ መናፈሻ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። በተመሳሳይም በቤተሰብ ውስጥ የብቸኝነትን ስሜት ሊያስወግድ የሚችል መንፈስን የሚያድስ ወዳጅነትና ሞቅ ያለ ስሜት ልናገኝ እንችላለን። እርግጥ ነው፣ ቤተሰብ እንዲህ ያለውን ሁኔታ ወዲያው ሊፈጥር አይችልም። ይሁን እንጂ የቤተሰብ ግንኙነታችንን ባጠናከርን መጠን እርስ በርስ ያለን ግንኙነት እየጠበቀ የሚሄድ ሲሆን ሕይወታችንም አርኪ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል ለትዳር ጓደኛችን ፍቅርና አክብሮት ለማሳየት የምናውለው ጊዜና የምንሰጠው ትኩረት የኋላ ኋላ ትርፍ ከሚያስገኝ በየዕለቱ ከሚወጣ መዋዕለ ንዋይ ጋር ሊመሳሰል ይችላል።—ልጆች ካሉን እነሱን የምናሳድግበት ተስማሚ ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። አብረናቸው ጊዜ ለማሳለፍ፣ የሐሳብ ግንኙነት መስመሩን ክፍት ለማድረግና ለእነሱ መንፈሳዊ መመሪያ ለመስጠት ጥረት ይጠይቅብን ይሆናል። ሆኖም ለእነዚህ ሁሉ የምናውለው ጊዜና ጥረት ታላቅ እርካታ ሊያስገኝልን ይችላል። ስኬታማ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን እንደ በረከትና ከአምላክ የተገኙ ውርሻ አድርገው ስለሚመለከቷቸው ጥሩ አድርገው ይንከባከቧቸዋል።—መዝሙር 127:3
ጥሩ ጓደኞችም አርኪና ትርጉም ያለው ሕይወት እንዲኖረን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። (ምሳሌ 27:9) የሌላውን ችግር እንደ ራሳችን አድርገን በመመልከት ብዙ ጓደኞች ማፍራት እንችላለን። (1 ጴጥሮስ 3:8) እውነተኛ ወዳጆች፣ ተደናቅፈን ብንወድቅ እንድንነሳ ይረዱናል። (መክብብ 4:9, 10) እንዲሁም ‘እውነተኛ ወዳጅ ለመከራ ጊዜ የተወለደ ወንድም ነው።’—ምሳሌ 17:17
እውነተኛ ወዳጅነት ከፍተኛ እርካታ ሊያስገኝ ይችላል! ከወዳጅ ጋር የፀሐይ መጥለቅ ይበልጥ ይማርካል፣ ምግብ ይበልጥ ጣዕም ይኖረዋል እንዲሁም ሙዚቃ ይበልጥ አስደሳች ይሆናል። እርግጥ ነው፣ የተቀራረበ ቤተሰብና እምነት የሚጣልባቸው ወዳጆች ትርጉም ያለው ሕይወት ሁለት ገጽታዎች ናቸው። አምላክ ሕይወታችን የላቀ ትርጉም እንዲኖረው ለማድረግ ሌሎች ምን ዝግጅቶች አድርጎልናል?
መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማርካት
ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ደስታን ለመንፈሳዊ ፍላጎታችን ንቁ ከመሆን ጋር አዛምዶታል። መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ችሎታ ይዘን ተፈጥረናል። ከዚህ የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ “መንፈሳዊ ሰው” እንዲሁም “የተሰወረ የልብ ሰው” ይናገራል።—1 ቆሮንቶስ 2:15፤ 1 ጴጥሮስ 3:3, 4
በደብልዩ ኢ ቫይን የተዘጋጀው አን ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ወርድስ እንደሚለው ከሆነ ምሳሌያዊው ልብ “ምክንያታዊውንም ሆነ ስሜታዊውን ክፍል ጨምሮ የሰውየውን የአእምሮና የሥነ ምግባር እንቅስቃሴ ባጠቃላይ” ለማመልከት ያገለግላል። ቫይን ጉዳዩን ሲያብራሩ “በሌላ አባባል ልብ የተሰወረውን ውስጣዊ ሰው ለማመልከት በምሳሌያዊ መንገድ ተሠርቶበታል” በማለት አክለዋል። በተጨማሪም ይኸው መጽሐፍ “ከውስጥ ተቀምጦ ያለው ልብ ‘የተሰወረውን ሰው’ . . . እውነተኛውን ሰው ይዟል” ሲል ተናግሯል።
‘የመንፈሳዊውን ሰው’ ወይም “የተሰወረውን ሰው” ማለትም ‘የተሰወረውን የልብ ሰው’ ፍላጎቶች ማርካት የምንችለው እንዴት ነው? መዝሙራዊው በመንፈስ አነሳሽነት “እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ እወቁ፤ እርሱ ሠራን እኛም አይደለንም፤ እኛስ ሕዝቡ የማሰማርያውም በጎች ነን” ብሎ የጠቀሰውን ነጥብ አምነን ስንቀበል ይህን ለማድረግና መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ለማርካት አንድ አስፈላጊ እርምጃ እንወስዳለን። (መዝሙር 100:3) ይህን መቀበላችን በአምላክ ፊት ተጠያቂዎች ነን ወደሚለው ምክንያታዊ መደምደሚያ ያደርሰናል። ‘ከሕዝቡና ከማሰማርያው’ በጎች ጋር መቆጠር ከፈለግን ከቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ተስማምተን መኖር አለብን።
በአምላክ ፊት ተጠያቂ መሆን ጉዳት አለውን? የለውም፤ አምላክ ለአኗኗራችን ትኩረት እንደሚሰጥ ማወቃችን ለሕይወታችን ተጨማሪ ትርጉም ይሰጠዋል። የተሻልን ሰዎች እንድንሆን ያበረታታናል። ይህ ደግሞ ፈጽሞ የማያስቆጭ ግብ ነው። መዝሙር 112:1 “እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ትእዛዙንም እጅግ የሚወድድ ሰው ምስጉን ነው” ይላል። ለአምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳየትና መመሪያዎቹን ከልብ መታዘዝ ሕይወታችን የላቀ ትርጉም እንዲኖረው ሊያደርግ ይችላል።
አምላክን መታዘዛችን እርካታ የሚያስገኝልን ለምንድን ነው? ይህ የሆነበት ምክንያት አምላክ ለሰው ልጆች ሁሉ የሰጠው ሕሊና ስላለን ነው። ሕሊና ያደረግነው ወይም ልናደርግ ያሰብነው ነገር ትክክል መሆን አለመሆኑን የሚጠቁም የሥነ ምግባር መመዘኛ ነው። ሁላችንም የተረበሸ ሕሊና የሚያስከትለውን የስሜት ስቃይ ቀምሰነዋል። (ሮሜ 2:15) ሆኖም ሕሊናችን ሊክሰንም ይችላል። ለአምላክ እና ለሰዎች ከራስ ወዳድነት የራቀ ተግባር ስንፈጽም ደስታና እርካታ እናገኛለን። ‘ከመቀበል ይልቅ መስጠት ይበልጥ ደስታ እንደሚያስገኝ’ እንገነዘባለን። (ሥራ 20:35) ይህ ሊሆን የቻለበት አንድ ዐቢይ ምክንያት አለ።
ፈጣሪያችን የሠራን የሌሎች ሰዎች ምኞትና ፍላጎት እንዲነካን በሚያደርግ መንገድ ነው። ሌሎችን ስንረዳ ልባችን ውስጥ የደስታ ስሜት ይፈጥርልናል። በተጨማሪም የተቸገረ ሰው በምንረዳበት ጊዜ አምላክ ለራሱ እንደተደረገ አድርጎ እንደሚቆጥረው መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል።—ምሳሌ 19:17
ለመንፈሳዊ ፍላጎታችን ትኩረት መስጠት ውስጣዊ እርካታ ከማስገኘት በተጨማሪ ተግባራዊ በሆነ መንገድ ሊረዳን ይችላልን? በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖር ራይሞንድ የሚባል አንድ ነጋዴ ተግባራዊ ጥቅም ሊያስገኝ እንደሚችል ያምናል። እንዲህ ይላል:- “ዋነኛው ግቤ ገንዘብ ማካበት ነበር። ሆኖም የአምላክን ህልውና እና እሱ ምን እንደሚፈልግ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ማመን ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ ለውጥ አደረግሁ። አሁን መተዳደሪያ ለማግኘት የማደርገው ጥረት በሕይወቴ ውስጥ ሁለተኛ ቦታ ይዟል። አምላክን ለማስደሰት በመጣር አፍራሽ ከሆነው የጥላቻ ስሜት መላቀቅ ችያለሁ። አባቴ የሞተው ከሰዎች ጋር በተፈጠረ ጠብ ሳቢያ ቢሆንም ገዳዮቹን የመበቀል ፍላጎት የለኝም።”
ራይሞንድ እንደተገነዘበው ሁሉ ‘የመንፈሳዊውን ሰው’ ፍላጎት በሚገባ ማሟላት ሥር የሰደዱ የስሜት ቁስሎችን ሊያሽር ይችላል። ይሁን እንጂ በየዕለቱ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ካልተቋቋምን በስተቀር ሕይወት ሙሉ በሙሉ አርኪ አይሆንልንም።
“የእግዚአብሔር ሰላም” ሊኖረን ይችላል
በዚህ ሁከት በነገሠበት ዓለም ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ከችግር አናመልጥም። አደጋ ያጋጥመናል፣ ያወጣናቸው እቅዶች መና ይቀራሉ፣ ሰዎችም ቅር ያሰኙናል። እነዚህ መሰናክሎች ደስታችንን ሊሰርቁብን ይችላሉ። ይሖዋ አምላክን የሚያገለግሉ ሰዎች ግን “የእግዚአብሔር ሰላም” የሆነውን ውስጣዊ እርካታ እንደሚያገኙ መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይሰጣል። ይህን ሰላም እንዴት ማግኘት እንችላለን?
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ችግሮቻችንን ለብቻችን ለመሸከም ከመሞከር ይልቅ ከልብ የመነጨ ጸሎት በማቅረብ በየዕለቱ የሚያጋጥመንን ሸክም በአምላክ ላይ መጣል ይኖርብናል። (መዝሙር 55:22) መንፈሳዊነታችንና አምላክ እንዴት እየረዳን እንዳለ ያለን ማስተዋል እያደገ ሲሄድ አምላክ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ለእንዲህ ዓይነቱ ልመና መልስ እንደሚሰጥ ያለን እምነት እየጨመረ ይሄዳል።—ዮሐንስ 14:6, 14፤ 2 ተሰሎንቄ 1:3
‘ጸሎት ሰሚ’ በሆነው በይሖዋ አምላክ ላይ ትምክህት ካሳደርን ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ በሽታ፣ እርጅና ወይም የዘመድ ሞት የመሳሰሉ ፈተናዎችን ለመቋቋም የተሻለ ብቃት ይኖረናል። (መዝሙር 65:2) ሆኖም እውነተኛ ትርጉም ያለው ሕይወት ለማግኘት የወደፊቱን ጊዜም ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን።
ከፊታችን ባለው ተስፋ ተደሰቱ
መጽሐፍ ቅዱስ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ማለትም ታዛዥ በሆኑ የሰው ልጆች ቤተሰብ ላይ የሚገዛ ጻድቅና አሳቢ የሆነ ሰማያዊ መንግሥት እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል። (2 ጴጥሮስ 3:13) አምላክ ተስፋ በሰጠው በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ በጦርነትና በፍትሕ መጓደል ፋንታ ሰላምና ፍትሕ ይሰፍናል። ይህ እንዲሁ ብልጭ ብሎ የሚጠፋ ተስፋ ሳይሆን በየቀኑ ይበልጥ እየተጠናከረ ሊሄድ የሚችል ጽኑ እምነት ነው። በእርግጥም ምሥራች ነው፤ ደግሞም ለደስታ ምክንያት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።—ሮሜ 12:12፤ ቲቶ 1:2
መግቢያው ላይ የተጠቀሰው ጆን በአሁኑ ጊዜ ሕይወቱ የላቀ ትርጉም እንዳለው ሆኖ ይሰማዋል። እንዲህ ይላል:- “ሃይማኖተኛ የነበርኩ ባልሆንም እንኳ በአምላክ ላይ እምነት ነበረኝ። ሆኖም ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው እስካነጋገሩኝ ጊዜ ድረስ ያለኝን እምነት በተመለከተ ያደረግሁት ጥረት አልነበረም። ‘እዚህ ምድር ላይ የምንኖርበት ዓላማ ምንድን ነው? የወደፊቱስ ጊዜ ምን ይዞልናል?’ በሚሉ ጥያቄዎች አጣደፍኳቸው። አርኪ የሆነው ቅዱስ ጽሑፋዊ መልሳቸው በሕይወቴ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ዓይነት ዓላማ እንዲኖረኝ አደረገ። ይህ መነሻው ብቻ ነበር። ለእውነት ያደረብኝ ጥማት ለነገሮች የነበረኝን አመለካከት ሙሉ በሙሉ እንድቀይር አደረገኝ። ምንም እንኳ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ እንደበፊቱ ሀብታም ባልሆንም በመንፈሳዊ ግን እጅግ ባለጸጋ እንደሆንኩ ይሰማኛል።”
ምናልባት እንደ ጆን አንተም መንፈሳዊ ፍላጎትህ ለብዙ ዓመታት ተዳፍኖ እንዲኖር አድርገህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ‘ጥበበኛ ልብ’ በማዳበር እንዲያንሰራራ ልታደርገው ትችላለህ። (መዝሙር 90:12 NW ) ቁርጥ ውሳኔና ጥረት በማድረግ እውነተኛ ደስታ፣ ሰላምና ተስፋ ማግኘት ትችላለህ። (ሮሜ 15:13) አዎን፣ ሕይወትህም የላቀ ትርጉም ሊኖረው ይችላል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጸሎት ‘የአምላክን ሰላም ’ እንድናገኝ ሊያደርግ ይችላል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቤተሰብን ሕይወት ይበልጥ አርኪ የሚያደርገው ምን እንደሆነ ታውቃለህ ?