የአምላክ መንፈስ በአሁኑ ጊዜ የሚሠራው እንዴት ነው?
የአምላክ መንፈስ በአሁኑ ጊዜ የሚሠራው እንዴት ነው?
ሰውዬው ሲወለድ ጀምሮ አንካሳ ነበር። መልካም ተብሎ በሚጠራው የቤተ መቅደስ በር ላይ በየቀኑ ተቀምጦ ወደ መቅደስ ከሚገቡት ሰዎች ምጽዋት ይለምን ነበር። ይሁን እንጂ በልመና ይተዳደር የነበረው ይህ የአካል ጉዳተኛ በአንድ ወቅት ከጥቂት ሳንቲሞች እጅግ የሚልቅ ዋጋ ያለው ስጦታ አገኘ። ከሕመሙ ተፈወሰ!—ሥራ 3:2-8
የሰውዬውን ‘እጅ ይዘው በማንሳት እግሩን ያጸኑለት’ ሐዋርያው ጴጥሮስና ሐዋርያው ዮሐንስ ቢሆኑም እንኳ ምስጋናውን ለራሳቸው መቀበል አልፈለጉም። ለምን? ጴጥሮስ ራሱ:- “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ በዚህ ስለ ምን ትደነቃላችሁ? ወይስ በገዛ ኃይላችን ወይስ እግዚአብሔርን በመፍራታችን ይህ ይመላለስ ዘንድ እንዳደረግነው ስለ ምን ትኵር ብላችሁ ታዩናላችሁ?” በማለት ተናግሯል። በእርግጥ ጴጥሮስና ዮሐንስ ይህን የመሰለ ነገር ሊያከናውኑ የቻሉት በራሳቸው ኃይል ሳይሆን በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር።—ሥራ 3:7-16፤ 4:29-31
በዚያ ጊዜ ይህን የመሳሰሉ “ተአምራት” ይደረጉ የነበረው አዲስ የተቋቋመው የክርስቲያን ጉባኤ የአምላክ ድጋፍ እንዳለው ለማረጋገጥ ነበር። (ዕብራውያን 2:4) ይሁን እንጂ እነዚህ ተአምራዊ ሥራዎች ዓላማቸውን ዳር ካደረሱ በኋላ ‘እንደሚሻሩ’ ሐዋርያው ጳውሎስ ተናግሮ ነበር። a (1 ቆሮንቶስ 13:8) በመሆኑም አምላክ በአሁኑ ጊዜ በእውነተኛው ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ፈውስ እንዲከናወን፣ ትንቢት እንዲነገር ወይም አጋንንትን የማውጣት ተአምር እንዲፈጸም ሲያደርግ አናይም።
ታዲያ እንዲህ ሲባል ከዚያ በኋላ የአምላክ መንፈስ በምንም ዓይነት መንገድ አይሠራም ማለት ነው? በፍጹም! የአምላክ መንፈስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የሠራባቸውንና በዘመናችን የሚሠራባቸውን ሌሎች መንገዶች እስቲ እንመርምር።
“የእውነት መንፈስ”
የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የሚያከናውነው አንዱ ተግባር አንድን ነገር ማሳወቅ፣ መንፈሳዊ የእውቀት ብርሃን መፈንጠቅና እውነትን መግለጽ ነው። ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፣ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” ብሏቸው ነበር።—ዮሐንስ 16:12, 13
“የእውነት መንፈስ” የፈሰሰው በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት 120 ደቀ መዛሙርት በኢየሩሳሌም በደርብ ላይ ባለ ክፍል ውስጥ ተሰብስበው ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ሲጠመቁ ነበር። (ሥራ 2:1-4) በዚያ ዓመታዊ በዓል ላይ ከተገኙት መካከል ሐዋርያው ጴጥሮስ አንዱ ነበር። ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ‘ቆመና’ ስለ ኢየሱስ አንዳንድ እውነቶችን በዝርዝር ወይም በግልጽ አስረድቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል “የናዝሬቱ ኢየሱስ” እንዴት “በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ” እንዳለ ተርኳል። (ሥራ 2:14, 22, 33) በተጨማሪም ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተነሳስቶ ለአይሁድ አድማጮቹ:- “ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ” ብሎ በድፍረት ተናግሯል። (ሥራ 2:36) ጴጥሮስ በመንፈስ አነሳሽነት በተናገረው መልእክት ምክንያት “ቃሉንም የተቀበሉ” ሦስት ሺህ የሚያክሉ ሰዎች ተጠመቁ። በዚህ መንገድ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ሰዎችን ወደ እውነት ለመምራት ረድቷል።—ሥራ 2:37-41
በተጨማሪም የአምላክ ቅዱስ መንፈስ አስተማሪና አስታዋሽ በመሆን አገልግሏል። ኢየሱስ “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል” ሲል ተናግሯል።—ዮሐንስ 14:26
መንፈስ ቅዱስ አስተማሪ የሆነው እንዴት ነው? የአምላክ መንፈስ ደቀ መዛሙርቱ አስቀድሞ ከኢየሱስ የሰሟቸውን ነገር ግን በሚገባ ያልተረዷቸውን ነገሮች እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን ከፍቶላቸዋል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ የይሁዳ አስተዳዳሪ ወደሆነው ሮማዊ ገዥ ጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት ለፍርድ በቀረበ ጊዜ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም” እንዳለው ሐዋርያቱ ያውቁ ዮሐንስ 18:36፤ ሥራ 1:6) ሐዋርያቱ በ33 እዘአ በጰንጤቆስጤ ዕለት የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እስከሚወርድባቸው ድረስ ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት ሙሉ በሙሉ የተረዱ አይመስልም።
ነበር። ሆኖም ከ40 ቀናት በኋላ ኢየሱስ ሊያርግ በነበረበት ጊዜ እንኳ ሳይቀር ሐዋርያቱ መንግሥቱ የሚቋቋመው በምድር ላይ ነው የሚል የተሳሳተ አመለካከት ነበራቸው። (በተጨማሪም የአምላክ መንፈስ የኢየሱስን የተለያዩ ትምህርቶች ወደ አእምሮ በማምጣት አስታዋሽ ሆኖ አገልግሏል። ለምሳሌ ያህል የኢየሱስን ሞት እና ትንሣኤ አስመልክቶ አስቀድመው የተነገሩት ትንቢቶች በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ አዲስ ትርጉም አግኝተዋል። (ማቴዎስ 16:21፤ ዮሐንስ 12:16) ሐዋርያት ኢየሱስ ያስተማራቸውን ነገር ማስታወሳቸው በነገሥታት፣ በገዢዎችና በሃይማኖት መሪዎች ፊት በቀረቡ ጊዜ ስለ አቋማቸው በድፍረት መልስ እንዲሰጡ አስችሏቸዋል።—ማርቆስ 13:9-11፤ ሥራ 4:5-20
ከዚህ በተጨማሪ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የጥንቶቹን ክርስቲያኖች ፍሬያማ ወደ ሆኑ የአገልግሎት ክልሎች መርቷቸዋል። (ሥራ 16:6-10) እንዲሁም የአምላክ መንፈስ ለመላው የሰው ዘር ጥቅም ሲባል የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ የመጻፍ ድርሻ እንዲኖራቸው አነሳስቷቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ከዚህ በግልጽ ለማየት የሚቻለው መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በተለያዩ መንገዶች ይሠራ እንደነበረ ነው። መንፈስ ቅዱስ ጥቅም ላይ የዋለው ተአምር ለማከናወን ብቻ አልነበረም።
መንፈስ ቅዱስ በዘመናችን
መንፈስ ቅዱስ በዘመናችን ለሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖችም በመሥራት ላይ ይገኛል። ይህ ሁኔታ በ19ኛው ዮሐንስ 8:32፤ 16:13
መቶ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ በዩ ኤስ ኤ ፔንሲልቫኒያ አሌጋኒ ውስጥ በነበረው አነስተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቡድን ላይ እውነት መሆኑ ተረጋግጧል። እነዚህ ቅን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች “እውነትን” የማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው።—የዚህ ቡድን አባል የነበረው ቻርልስ ቴዝ ራስል የቅዱስ ጽሑፉን እውነት ለማወቅ ያደረገውን ፍለጋ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “በልብና በአእምሮዬ ውስጥ እንቅፋት ሊሆንብኝ የሚችል መሠረተ ቢስ ጥላቻ ቢኖር ማስወገድ እንዲያስችለኝና በመንፈሱ ትክክለኛ ወደ ሆነ መረዳት እንዲመራኝ . . . ጸለይኩ።” አምላክ ለዚህ የትህትና ጸሎት መልስ ሰጥቷል።
ራስልና ተባባሪዎቹ ቅዱሳን ጽሑፎችን በትጋት ሲመረምሩ ብዙ ነገሮች ግልጽ እየሆኑላቸው መጡ። ራስል ስለ ሁኔታው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ለብዙ መቶ ዓመታት የተለያዩ ሃይማኖታዊ ኑፋቄዎችና ወገኖች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረተ ትምህርቶች ይነስም ይብዛ ከሰብዓዊ መላ ምቶችና ፈጽሞ ስህተት ከሆኑ ነገሮች ጋር አዋሕደው ለየራሳቸው ተከፋፍለዋቸው እንደነበር ተገነዘብን።” ይህ ደግሞ እንደ እርሱ አባባል “እውነትን ያለቦታው ማኖር” ነው። በእርግጥም ቅዱስ ጽሑፋዊው እውነት ሕዝበ ክርስትና ባለፉት መቶ ዓመታት አስርጋ ባስገባቻቸው የአረማዊ ትምህርቶች ጥርቅም ተቀብሮ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ራስል እውነትን ለማወቅና ለሌሎች ለማሳወቅ ቆርጦ ነበር።
ራስልና ተባባሪዎቹ የጽዮን መጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ በተባለው መጽሔት አማካኝነት ስለ አምላክ የተሳሳተ መልእክት የሚያስተላልፉ የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን በድፍረት አጋልጠዋል። ብዙ ሰዎች ካላቸው ሃይማኖታዊ አመለካከት በተቃራኒ ነፍስ ሟች እንደሆነች፣ ስንሞት ወደ መቃብር እንደምንወርድ፣ እንዲሁም ይሖዋ የሥላሴ ክፍል ሳይሆን ብቸኛው እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ተረድተው ነበር።
ይሁንና እንዲህ ያለው የሐሰት ትምህርቶችን የማጋለጥ እንቅስቃሴ የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስትን አስቆጥቷቸዋል። ይህ እንደሚሆን ደግሞ አንተም መገመት ትችላለህ። ብዙ የካቶሊክና የፕሮቴስታንት ቀሳውስት የነበራቸውን ተደማጭነት ላለማጣት ሲሉ ራስልን በማጣጣል ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ ማደራጀት ጀመሩ። ይሁን እንጂ እሱም ሆነ ተባባሪዎቹ ፈጽሞ ተስፋ አልቆረጡም። የአምላክ መንፈስ እንደሚመራቸው ትምክህት ነበራቸው። “ቤዛ፣ መካከለኛና የጉባኤው ራስ በሆነው በኢየሱስ ጥያቄና በእርሱ አማካኝነት የሚላክልን . . . የአብ ቅዱስ መንፈስ እንደሚያስተምረን ጌታችን አረጋግጦልናል” ሲል ራስል ተናግሯል። በእርግጥ መንፈስ ቅዱስ አስተምሯቸዋል! እነዚህ ቅን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ንጹህ የእውነት ውኃ እየወሰዱ በዓለም ዙሪያ ማዳረሳቸውን ገፉበት።—ራእይ 22:17
በዚህ ዘመን ያለው የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት ከመቶ ለሚበልጡ ዓመታት መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠውን አመራር በታዛዥነት ሲቀበል ቆይቷል። የይሖዋ መንፈስ ደረጃ በደረጃ መንፈሳዊ እይታቸውን እያጠራላቸው ሲመጣ ምሥክሮቹ በወቅቱ ካለው መረዳት ጋር ተስማምተው ለመመላለስ አስፈላጊውን ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኞች ሆነዋል።—ምሳሌ 4:18
“ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ”
ኢየሱስ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የሚሠራበትን ሌላ አቅጣጫ ሲያመለክት ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ . . . እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ሥራ 1:8) ደቀ መዛሙርቱ አምላክ የሰጣቸውን ሥራ ለማከናወን ይችሉ ዘንድ ኢየሱስ “በኃይል” እና “በመንፈስ ቅዱስ” ለመሙላት የገባው ቃል ዛሬም አልታጠፈም።
ትሆናላችሁ።” (በቡድን ደረጃ የይሖዋ ምሥክሮች በስብከት እንቅስቃሴያቸው በሰፊው የታወቁ ናቸው። (ሣጥኑን ተመልከት።) በእርግጥም ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች የእውነትን መልእክት ከ230 በሚበልጡ አገሮችና ደሴቶች እያዳረሱ ነው። በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ሥር ጦርነት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች እንኳ ሳይቀር በሕይወታቸው ቆርጠው የአምላክን መንግሥት በመደገፍ በድፍረት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያሰማሉ። ለክርስቲያናዊ አገልግሎት ያላቸው ቅንዓት መንፈስ ቅዱስ በዘመናችንም በመሥራት ላይ እንዳለ የሚያረጋግጥ ጉልህ ማስረጃ ነው። ይሖዋ አምላክም ጥረታቸውን እየባረከላቸው እንዳለ ግልጽ ነው።
ለምሳሌ ያህል ባለፈው ዓመት የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበክ ከአንድ ቢልዮን በላይ ሰዓት አሳልፈዋል። ውጤቱስ ምን ነበር? ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን በውኃ ጥምቀት ያሳዩ 323, 439 ሰዎች ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪ ፍላጎት ላሳዩ አዳዲስ ሰዎች 4,433,884 ሳምንታዊ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተመርቷል። በአጠቃላይ 24,607, 741 መጽሐፎች፣ 631,162, 309 መጽሔቶች እንዲሁም 63, 495, 728 ብሮሹሮችና ቡክሌቶች ተበርክተዋል። የአምላክ መንፈስ እየሠራ እንዳለ የሚያሳይ እንዴት ያለ ጉልህ ማስረጃ ነው!
የአምላክ መንፈስ እና አንተ
አንድ ሰው ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ ሲሰጥ፣ ሕይወቱን አምላክ ከሚፈልገው የአቋም ደረጃዎች ጋር ሲያስማማና በቤዛው ዝግጅት ላይ እምነት እንዳለው ሲገልጽ በአምላክ ፊት ጥሩ አቋም ለማግኘት የሚያስችለው በር ይከፈትለታል። እነዚህን ሰዎች በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ ሲናገር ‘እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን በእናንተ እንዲኖር ይሰጣል’ ብሏል።—1 ተሰሎንቄ 4:7, 8፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9-11
የአምላክን መንፈስ ማግኘት ብዙ አስደሳች በረከቶችን ያመጣል። እንዴት ያሉ በረከቶችን? በመጀመሪያ ደረጃ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ራሱ ‘የመንፈስ ፍሬ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት እና ራስን መግዛት’ እንደሆኑ ይናገራል። (ገላትያ 5:22, 23) በመሆኑ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ አንድ ሰው አምላካዊ ባሕርያትን እንዲያፈራ የሚያስችል ብርቱ ኃይል ነው።
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን የምታነብና ትምህርቱን ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነ የአምላክ መንፈስ በጥበብ፣ በእውቀት፣ በማስተዋል፣ በማመዛዘንና በማሰብ ችሎታ እንድታድግ ይረዳሃል። ንጉሥ ሰሎሞን ከሰው ይልቅ አምላክን የማስደሰት ፍላጎት ስለነበረው “እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል . . . የልብ ስፋት” ተሰጥቶታል። (1 ነገሥት 4:29) ይሖዋ ለሰሎሞን ቅዱስ መንፈሱን እንደሰጠ ሁሉ ዛሬም እርሱን ማስደሰት ለሚፈልጉ ሰዎች እንደማይነፍጋቸው የተረጋገጠ ነው።
የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ክርስቲያኖች ሰይጣንንና አጋንንትን፣ ይህን ክፉ የነገሮች ሥርዓትና የውዳቂ ሥጋቸውን የኃጢአት ዝንባሌ እንዲዋጉ ይረዳቸዋል። እንዴት? ሐዋርያው ጳውሎስ “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (ፊልጵስዩስ 4:13) መንፈስ ቅዱስ መከራ ወይም ፈተና እንዳይኖር አያደርግም፤ ይሁን እንጂ በፈተና ወቅት እንድትጸና ሊረዳህ ይችላል። በአምላክ መንፈስ ከተማመንን ማንኛውንም ዓይነት ችግር ወይም ጭንቀት ለመወጣት የሚያስችል “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” እናገኛለን።—2 ቆሮንቶስ 4:7፤ 1 ቆሮንቶስ 10:13
ማስረጃዎችን ሁሉ ስትመረምር የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በዛሬው ጊዜ እየሠራ ስለመሆኑ ቅንጣት ታክል አትጠራጠርም። የይሖዋ መንፈስ የአምላክ አገልጋዮች አስደናቂ ስለሆነው ዓላማው እንዲመሠክሩ ኃይል ይሰጣቸዋል። መንፈሳዊ ብርሃን መፈንጠቁን ይቀጥላል እንዲሁም ለፈጣሪያችን ታማኝ ሆነን እንድንቀጥል ለመርዳት እምነታችንን ያጠነክርልናል። አምላክ መንፈስ ቅዱስን ለመስጠት የገባውን ቃል በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ታማኝ አገልጋዮቹ እየፈጸመ በመሆኑ ምን ያክል አመስጋኞች ልንሆን ይገባናል!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የነሐሴ 15, 1971 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 501-5 ላይ የወጣውን “ተአምራዊ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ያቆሙት ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሌሎች ሰዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ምን ይላሉ?
“ሌሎች ቤተ ክርስቲያናት የምዕመናኖቻቸውን ቁጥር ለመጨመር አማካሪዎችን ሲቀጥሩ ወይም እንደ ግብረሰዶምና ውርጃ ባሉት የጊዜው አከራካሪ ጉዳዮች ሲወዛገቡ ምሥክሮቹ በየጊዜው ከሚለዋወጠው ዓለም ጋር ለመመሳሰል አይሞክሩም። አሁንም በተደራጀ መንገድ ምሥራቹን በምድር ዙሪያ እያዳረሱ ነው።”—ዚ ኦሬንጅ ካውንቲ ሬጂስተር ኦቭ ኦሬንጅ ካውንቲ፣ ካሊፎርኒያ፣ ዩ ኤስ ኤ
“እምነትን በማስፋፋት በኩል እንደ ይሖዋ ምሥክሮች . . . በጋለ ስሜት የሚሰብኩ የሃይማኖት ቡድኖች እምብዛም ናቸው።”—ዘ ሪፐብሊክ ኦቭ ኮሎምበስ፣ ኢንዲያና፣ ዩ ኤስ ኤ
“የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ ‘ምሥራቹን’ ከበር ወደ በር የሚያደርሱ እነርሱ ብቻ ናቸው።”—ዠቼ ሊተረትስኪይ ፖላንድ
“እስከ ዛሬ ድረስ ታይቶ በማይታወቅ መጠን በሚከናወነው ታላቅ የስብከት ዘመቻ የይሖዋ ምሥክሮች የይሖዋን መልእክት በመላው ዓለም አዳርሰዋል።”—ኒውስ ኦብዘርቨር ተማክወ፣ ፔንሲልቫኒያ፣ ዩ ኤስ ኤ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የአምላክ ቅዱስ መንፈስ፣ መንፈሳዊ ብርሃን እንዲበራልን ያደርጋል
. . . መልካም ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ያሰፍናል
. . . እንዲሁም በዓለም ዓቀፉ የስብከት ሥራ ድጋፍ ይሰጠናል