የአንባብያን ጥያቄዎች
የአንባብያን ጥያቄዎች
ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 12:19 ላይ “ተወዳጆች ሆይ፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፣ ለቊጣው ፈንታ ስጡ እንጂ” በማለት የጻፈው ክርስቲያኖች መቆጣት እንደሌለባቸው ለማስገንዘብ ነበር?
በአጭር አነጋገር፣ አልነበረም። ሐዋርያው ጳውሎስ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው የአምላክን ቁጣ በማስመልከት ነው። እርግጥ ነው፣ ክርስቲያኖች ቢቆጡ ምንም ስህተት የለውም ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ቁጡዎች እንዳንሆን በግልጽ ይመክረናል። ለአብነት ያክል አንዳንድ መለኮታዊ ምክሮችን ተመልከት።
“ከቍጣ ራቅ መዓትንም ተው፤ እንዳትበድል አትቅና።” (መዝሙር 37:8) “በወንድሙ ላይ የሚቈጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል።” (ማቴዎስ 5:22) “የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፣ ርኵሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቊጣ” ነው። (ገላትያ 5:19, 20) “መራርነትና ንዴት ቊጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ።” (ኤፌሶን 4:31) “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቊጣም የዘገየ ይሁን።” (ያዕቆብ 1:19) በተጨማሪም የምሳሌ መጽሐፍ በሆነ ባልሆነው ቱግ ማለት ወይም በቁጣ መገንፈል ተገቢ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ምክር ይለግሳል።—ምሳሌ 12:16፤ 14:17, 29፤ 15:1፤ 16:32፤ 17:14፤ 19:11, 19፤ 22:24፤ 25:28፤ 29:22
በሮሜ 12:19 ዙሪያ ያሉት ሐሳቦችም ከእነዚህ ምክሮች ጋር ይስማማሉ። ጳውሎስ ፍቅራችን ግብዝነት የሌለበት እንዲሆን፣ የሚያሳድዱንን እንድንመርቅ፣ ለሌሎች መልካም እንድናስብ፣ ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን እንዳንመልስና ከሁሉም ጋር በሰላም እንድንኖር አሳስቧል። ከዚያም “ተወዳጆች ሆይ፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፣ ለቊጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፣ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ” በማለት ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጡ።—ሮሜ 12:9, 14, 16-19
አዎን፣ በቁጣ ተገፋፍተን የበቀል ድርጊት መፈጸም የለብንም። ስለ ሁኔታዎች ያለን እውቀትም ሆነ በውስጣችን ያለው የፍትሕ ስሜት ፍጽምና የጎደለው ነው። በቁጣ ተነሳስተን የበቀል እርምጃ ብንወስድ ብዙውን ጊዜ ስህተት ላይ እንወድቃለን። ይህ ደግሞ የአምላክ ባለጋራ የሆነውን የዲያብሎስን ዓላማ የምናስፈጽም ያደርገናል። በሌላ ቦታ ላይ ጳውሎስ “ተቈጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቊጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፣ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት” በማለት ጽፏል።—ኤፌሶን 4:26, 27
የተሻለውና ጥበብ የሆነው እርምጃ የበቀል እርምጃው በእነማን ላይና መቼ መወሰድ እንዳለበት ውሳኔውን ለአምላክ መተዉ ነው። እርሱ ስለ እውነታው የተሟላ እውቀት ስላለው ይህንን ማድረግ ይችላል። የበቀል እርምጃም ቢወስድ ፍጹም የሆነውን ፍትሑን የሚያንጸባርቅ ነው። ጳውሎስ “በቀልና ፍርድ የእኔ ነው” የሚሉት ቃላት የሚገኙበትን ዘዳግም 32:35, 41ን ጠቅሶ መጻፉን ካስተዋልን በሮሜ 12:19 ላይ ሊያስገነዝብ የፈለገውም ይህንኑ እንደሆነ ልንመለከት እንችላለን። (ከዕብራውያን 10:30 ጋር አወዳድር።) “አምላክ” የሚለው ቃል በግሪክኛው ጽሑፍ ላይ የማይገኝ ቢሆንም እንኳ በርካታ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ሮሜ 12:19 ላይ ይህን ቃል ጨምረዋል። አንዳንዶቹ እንደሚከተለው ይነበባሉ:- “አምላክ ይበቀል” (ዘ ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን)፣ “ለአምላክ ቁጣ ፈንታ ስጡ” (አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርሽን)፣ “ፈቃዱ ከሆነ አምላክ ይቅጣ” (ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ሞደርን ኢንግሊሽ)፣ “ለመለኮታዊ በቀል ፈንታ ስጡ።”—ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል
የእውነት ጠላቶች ጥቃት ወይም ስደት ቢያደርሱብን እንኳ ሙሴ ስለ ይሖዋ አምላክ ሲነገር በሰማው በሚከተለው መግለጫ ላይ እምነት እንዳለን ልናሳይ እንችላለን:- “እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ [“ለቁጣ የዘገየ፣” NW ] ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፣ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፣ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፣ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ [“ሳይቀጣ የማያልፍ፣” NW ]።”—ዘጸአት 34:6, 7