ልክን ማወቅ—ሰላምን ለማስፈን የሚረዳ ባሕርይ
ልክን ማወቅ—ሰላምን ለማስፈን የሚረዳ ባሕርይ
ሁሉም ሰው ልኩን የሚያውቅ ቢሆን ኖሮ ዓለማችን ምንኛ ማራኪ ትሆን ነበር! የሰዎች ፍላጎት ገደብ ያለው ይሆን ነበር፣ በቤተሰብ መካከል የሚፈጠረው ጭቅጭቅ፣ በነጋዴዎች መካከል የሚኖረው ፉክክር እንዲሁም በብሔራት መካከል የሚፈጠረው ጠብ ይቀንስ ነበር። እንዲህ በመሰለ አካባቢ መኖር አትፈልግም?
እውነተኛ የይሖዋ አምላክ አገልጋዮች ልክን ማወቅ እንደ ድክመት ሳይሆን እንደ ጥንካሬና እንደ መልካም ምግባር በሚታይበት አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ራሳቸውን እያዘጋጁ ናቸው። (2 ጴጥሮስ 3:13) እንዲያውም ከአሁኑ ልክን የማወቅ ባሕርይ እያዳበሩ ናቸው። ለምን? በተለይ ይህ የሆነበት ምክንያት ይሖዋ ይህን ባሕርይ እንዲያሳዩ ስለሚጠብቅባቸው ነው። ነቢዩ ሚክያስ “ሰው ሆይ፣ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ ከአምላክህም ጋር በትሕትና [“ልክህን አውቀህ፣” NW ] ትሄድ ዘንድ አይደለምን?” በማለት ጽፏል።—ሚክያስ 6:8
ልክን ማወቅ ከእብሪት ወይም ከትዕቢት መራቅ እንዲሁም አንድ ሰው ስላለው ችሎታ፣ ስላገኘው ስኬትና ብልጥግና ጉራ ከመንዛት መቆጠብ እንደሚሉት ያሉ በርካታ ትርጉሞች ሊኖሩት ይችላሉ።
በተጨማሪም አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ልክን ማወቅ “ከገደብ አለማለፍ” በማለት ፈቶታል። ልኩን የሚያውቅ ሰው ከመልካም ባሕርያት ውጭ የሆነ ነገር አያደርግም። በተጨማሪም እንዲያደርግ በሚጠበቅበትና ሊያደርግ በሚችለው ነገር መካከል ገደብ እንዳለ ይገነዘባል። እርሱን የማይመለከተው ነገር እንዳለ ያውቃል። ሁላችንም ልካቸውን ከሚያውቁ ሰዎች ጋር መሆን ያስደስተናል። እንግሊዛዊው ባለ ቅኔ ጆሴፍ ኤዲሰን “ልኩን እንደሚያውቅ ሰው ተወዳጅ የለም” በማለት ጽፏል።ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ልክን የማወቅ ባሕርይ ይዘው አይወለዱም። ይህንን ባሕርይ ለማዳበር ጥረት ማድረግ ይገባል። የአምላክ ቃል ልክን የማወቅ ባሕርይ በተለያየ መንገድ የተንጸባረቀባቸውን አበረታች ታሪኮችን ይዞልናል።
ልካቸውን ያውቁ የነበሩ ሁለት ነገሥታት
በከፍተኛ ደረጃ ይሖዋን በታማኝነት ካገለገሉት ሰዎች መካከል አንዱ ዳዊት ሲሆን የእስራኤል የወደፊት ንጉሥ እንዲሆን የተሾመው ገና ብላቴና ሳለ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዙፋን ላይ የነበረው ንጉሥ ሳዖል እርሱን ለመግደል በመሞከርና የስደት ኑሮ እንዲያሳልፍ በማድረግ በዳዊት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳደረበት።—1 ሳሙኤል 16:1, 11-13፤ 19:9, 10፤ 26:2, 3
በዚህ ወቅትም ቢሆን ዳዊት ሕይወቱን ለመጠበቅ በሚያደርገው ነገር ገደቡን ማለፍ እንደሌለበት ያውቅ ነበር። በአንድ ወቅት ንጉሥ ሳዖል በምድረ በዳ እንቅልፍ ተኝቶ ሳለ አቢሳ ጉዳት ሊያደርስበት ሲል ዳዊት “በእኔ በኩል ይሖዋ በቀባው ላይ እጄን ማንሳት በይሖዋ ዓይን ሲታይ የማይታሰብ ነገር ነው” በማለት ከልክሎታል። (1 ሳሙኤል 26:8-11 NW ) ዳዊት ሳዖልን ከንግሥናው ማስወገድ የእርሱ ቦታ እንዳልሆነ አውቋል። በዚህም ዳዊት ከመልካም ባሕርይ ውጭ የሆነ ነገር ባለማድረግ ልኩን የሚያውቅ ሰው መሆኑን አሳይቷል። በተመሳሳይም በዘመናችን የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮች የአንድ ሰው ሕይወት አደጋ ላይ ቢወድቅ እንኳ “በይሖዋ ዓይን ሲታይ” ሊያደርጓቸው የማይችሏቸው ነገሮች እንዳሉ ያውቃሉ።—ሥራ 15:28, 29፤ 21:25
ምንም እንኳ ትንሽ ለየት ባለ መንገድ ቢሆንም የንጉሥ ዳዊት ልጅ የነበረው ሰሎሞንም ወጣት በነበረበት ጊዜ ልክን የማወቅ ባሕርይ አሳይቷል። ሰሎሞን ዙፋን ላይ በተቀመጠ ጊዜ ንጉሥ መሆን የሚያስከትለውን ከባድ ኃላፊነት ለመሸከም እንደማይበቃ ሆኖ ተሰምቶታል። እንዲህ ሲል ጸለየ:- “አምላኬ ሆይ፣ እኔን ባሪያህን በአባቴ በዳዊት ፋንታ አንግሠኸኛል፤ እኔም መውጫንና መግቢያን የማላውቅ ታናሽ ብላቴና ነኝ።” በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሰሎሞን ችሎታና ተሞክሮ የሚያንሰው መሆኑን በሚገባ አውቋል። ይህም እብሪተኛ ወይም ትዕቢተኛ ሳይሆን ልኩን የሚያውቅ ሰው መሆኑን የሚያሳይ ነው። ሰሎሞን ማስተዋል እንዲሰጠው ይሖዋን ጠየቀ፤ በልመናውም መሠረት ማስተዋል አገኘ።—1 ነገሥት 3:4-12
መሲሑና የእርሱ መንገድ ጠራጊ
ከሰሎሞን ዘመን 1, 000 ዓመታት ካለፉ በኋላ አጥማቂው ዮሐንስ ለመሲሑ መንገድ ጠራጊ ሆኖ ሠርቷል። ዮሐንስ የመሲሑ መንገድ ጠራጊ በመሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እየፈጸመ ነበር። ስላገኘው መብት በጉራ መናገር ይችል ነበር። በተጨማሪም የመሲሑ የሥጋ ዘመድ ስለነበር ኩራት ሊሰማው ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ዮሐንስ ሌላው ቀርቶ የኢየሱስን ጫማ ለመፍታት የሚበቃ ሰው አለመሆኑን ተናግሯል። እንዲሁም ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ለመጠመቅ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ዮሐንስ “እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን?” በማለት ተናግሯል። ይህም ዮሐንስ ጉረኛ እንዳልነበር የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ዮሐንስ ልኩን የሚያውቅ ሰው ነበር።—ማቴዎስ 3:14፤ ሚልክያስ 4:5, 6፤ ሉቃስ 1:13-17፤ ዮሐንስ 1:26, 27
ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመረ። ኢየሱስ ፍጹም ሰው የነበረ ቢሆንም እንኳን “እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ . . . የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና” በማለት ተናግሯል። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ከሰዎች ክብር ለማግኘት አልፈለገም። ላከናወናቸው ነገሮች ሁሉ ክብር የሰጠው ለይሖዋ ነው። (ዮሐንስ 5:30, 41-44) እንዴት ያለ ልክን የማወቅ ባሕርይ ነው!
እንደ ዳዊት፣ ሰሎሞን፣ አጥማቂው ዮሐንስና ሌላው ቀርቶ ፍጹም ሰው እንደነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ ያሉት ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ልክን የማወቅ ባሕርይ አሳይተዋል። ጉረኞች፣ እብሪተኞች ወይም ትዕቢተኞች አልነበሩም፤ እንዲሁም ከገደባቸው አላለፉም። የእነርሱ ምሳሌነት በዘመናችን የሚገኙት የይሖዋ አገልጋዮች ልክን የማወቅን ባሕርይ እንዲያዳብሩና እንዲያንጸባርቁ በቂ ምክንያት ይሰጧቸዋል። ሆኖም ይህን ባሕርይ እንድናሳይ የሚያደርጉ ሌሎች ምክንያቶችም አሉ።
በዚህ ሁከት በነገሠበት የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ልክን ማወቅ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። አንድ ሰው ከይሖዋ አምላክ፣ ከሰዎችና ከራሱም ጋር ሳይቀር ሰላም እንዲኖረው ያስችለዋል።
ከይሖዋ አምላክ ጋር ሰላም መፍጠር
ከይሖዋ ጋር ሰላም መፍጠር የምንችለው ለእውነተኛ አምልኮ ከወሰነው ክልል እስካልወጣን ድረስ ብቻ ነው። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን አምላክ ካስቀመጠላቸው ገደብ አልፈው በመሄዳቸው ልካቸውን ሳያውቁ የቀሩ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ሆነዋል። በይሖዋ ፊት የነበራቸውን ጥሩ አቋምም ሆነ መኖሪያቸውን፣ የወደፊት ተስፋቸውንና ሕይወታቸውን አጡ። (ዘፍጥረት 3:1-5, 16-19) ምንኛ አሳዛኝ ውጤት ነው!
እውነተኛ አምልኮ በምናደርገው ነገር ረገድ ገደብ ስለሚያበጅ ከአዳምና ከሔዋን ውድቀት ትምህርት እናግኝ። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ “ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) ይሖዋ እነዚህን ገደቦች ያስቀመጠው ለእኛው ጥቅም ሲል ነው። እኛም ካስቀመጠልን ገደብ ባለማለፍ ጥበበኞች መሆናችንን እናሳያለን። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ምሳሌ 11:2 “በትሑታን [“ልካቸውን በሚያውቁ፣” NW ] ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች” በማለት ይነግረናል።
አንድ የሃይማኖት ድርጅት እነዚህን ገደቦች አልፈን መሄድ እንደምንችልና ይህም ከአምላክ ጋር ያለንን ሰላም እንደማያደፈርስብን ቢነግረንስ? ይህ ድርጅት እኛን ለማሳት እየሞከረ ነው። በሌላው በኩል ግን ልክን ማወቅ ከይሖዋ አምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንድናዳብር ይረዳናል።
ከሰዎች ጋር በሰላም መኖር
ልክን ማወቅ ከሰዎች ጋር ሰላማዊ ዝምድና እንዲኖረንም ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል ወላጆች ባሏቸው መሠረታዊ ነገሮች በመርካትና መንፈሳዊ ነገሮችን በማስቀደም ረገድ ምሳሌ ከሆኑ ልጆቻቸውም እንዲህ ያለውን ዝንባሌ መኮረጃቸው የማይቀር ነው። በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኙት ልጆች ሁልጊዜ የጠየቁትን ሁሉ ማግኘት የማይችሉ ቢሆንም እንኳ ባሏቸው ነገሮች ረክቶ መኖር አይከብዳቸውም። ይህም ልካቸውን አውቀው እንዲኖሩ ከመርዳቱም በላይ የቤተሰቡ ሕይወት ይበልጥ ሰላም የሰፈነበት እንዲሆን ያደርጋል።
የበላይ ተመልካች ሆነው የሚያገለግሉ ሁሉ ሥልጣናቸውን ያለአግባብ እንዳይጠቀሙበት ልክን የማወቅ ባሕርይ ለማዳበር ለየት ያለ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል። ለምሳሌ ያህል ክርስቲያኖች “ከተጻፈው አትለፍ” የሚል ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 4:6) የጉባኤ ሽማግሌዎች የራሳቸውን የግል ምርጫ ሌሎች እንዲቀበሉ ለማስገደድ መሞከር እንደሌለባቸው ይገነዘባሉ። ከዚያ ይልቅ ጠባይን፣ አለባበስን፣ አበጣጠርን ወይም መዝናኛን በመሰሉ ጉዳዮች ትክክለኛውን አቅጣጫ ለማስያዝ የአምላክን ቃል እንደ መሠረት አድርገው ይጠቀማሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:14-17) ሽማግሌዎች ቅዱሳን ጽሑፎች ካስቀመጡት ገደብ የማያልፉ መሆናቸውን የጉባኤው አባላት ሲመለከቱ አክብሮት ያተርፍላቸዋል እንዲሁም በጉባኤው ውስጥ ሞቅ ያለ፣ ፍቅራዊና ሰላማዊ መንፈስ እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ያበረክታል።
ውስጣዊ ሰላም ማግኘት
ልካቸውን አውቀው የሚኖሩ ሁሉ ውስጣዊ ሰላም በማግኘት ይካሳሉ። ልኩን የሚያውቅ ሰው አለ አቅሙ አይንጠራራም። ይህ ማለት ግን ለራሱ ግቦችን አያወጣም ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል ተጨማሪ የአገልግሎት መብት ለማግኘት ይመኝ ይሆናል፤ ሆኖም አምላክን ይጠብቃል እንዲሁም ለሚያገኛቸው ክርስቲያናዊ መብቶች ሁሉ ይሖዋን ያመሰግናል። በግሉ ጥሮ ግሮ ያገኛቸው እንደሆኑ አድርጎ አይመለከትም። ይህም ልኩን የሚያውቀው ግለሰብ ‘የሰላም አምላክ’ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ይበልጥ እየቀረበ እንዲሄድ ያደርገዋል።—ፊልጵስዩስ 4:9
ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ችላ ብለው እንዳለፉን ሆኖ ይሰማን ይሆናል። ልካችንን የማናውቅ ሆነን ሰዎች ትኩረታቸውን በእኛ ላይ እንዲያደርጉ ከማድረግ ይልቅ ልካችንን የምናውቅ በመሆናችን ምክንያት ቸል ብንባል አይሻልም? ልካቸውን የሚያውቁ ሰዎች አጉል አለ አቅማቸው አይንጠራሩም። በዚህም የተነሳ ለስሜትና ለአካላዊ ጤንነት ጠቃሚ የሆነው ውስጣዊ ሰላም ይኖራቸዋል።
ልክን የማወቅ ባሕርይ ማዳበርና መጠበቅ
አዳምና ሔዋን ልካቸውን ሳያውቁ ቀርተዋል። በዚህም የተነሳ ይህን ባሕርይ ለልጆቻቸው አስተላልፈዋል። እኛም የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የፈጸሙት ዓይነት ስህተት ደግመን እንዳንሠራ ምን ሊረዳን ይችላል? ግሩም የሆነውን ልክን የማወቅ ባሕርይስ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?
በመጀመሪያ የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ለእኛ ያስቀመጠልንን ቦታ በትክክል ማወቁ ይረዳናል። አምላክ ከሠራቸው ጋር ሊወዳደር የሚችል በግላችን የሠራነው ምን ነገር ልንጠቅስ እንችላለን? ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዩ ለኢዮብ “ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ ወዴት ነበርህ? ታስተውል እንደ ሆንህ ተናገር” በማለት ጥያቄ አቅርቦለታል። (ኢዮብ 38:4) ኢዮብ ዝም ከማለት ሌላ ምንም መልስ አልነበረውም። እኛስ ብንሆን ያለን እውቀት፣ ችሎታና ተሞክሮ እንዲሁ ውስን አይደለም? ያሉብንን የአቅም ገደቦች አምኖ መቀበሉ የተሻለ አይሆንም?
ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ “ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት፣ ዓለምም በእርስዋ የሚኖሩ ሁሉ” በማለት ይነግረናል። ይህም “የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ በሺህ ተራራዎች ያሉ እንስሶችም” ሁሉ የእርሱ ናቸው ማለት ነው። ይሖዋ “ብሩ የእኔ ነው፣ ወርቁም የእኔ ነው” ብሎ ሊናገር ይችላል። (መዝሙር 24:1፤ 50:10፤ ሐጌ 2:8) ይሖዋ ካለው ነገር ጋር ሊወዳደር የሚችል የትኛውን ሀብታችንን ልንጠቅስ እንችላለን? ሌላው ቀርቶ በጣም ሀብታም ናቸው የሚባልላቸው ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ ባካበቱት ሀብት ለመኩራራት የሚያበቃ ምንም ምክንያት ሊኖራቸው አይችልም! ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች በመንፈስ አነሳሽነት የላከውን ምክር መከተሉ ጥበብ ይሆናል። “ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ።”—ሮሜ 12:3
የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ልክን የማወቅ ባሕርይ ማዳበር ስለምንፈልግ የመንፈስ ፍሬ የሆኑትን ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ ትዕግሥትን፣ ቸርነትን፣ በጎነትን፣ እምነትን፣ የውሃነትን፣ ራስ መግዛትን ለማፍራት መጸለይ ይኖርብናል። (ሉቃስ 11:13፤ ገላትያ 5:22, 23) ለምን? ምክንያቱም እነዚህ ባሕርያት ልካችንን በማወቅ ረገድ ቀላል እንዲሆንልን ይረዱናል። ለምሳሌ ያህል ለሰዎች ያለን ፍቅር የጉረኝነትን ወይም የትዕቢተኝነትን ዝንባሌ እንድንዋጋ ይረዳናል። እንዲሁም ራስን መግዛት ልካችንን ሳናውቅ ቀርተን አንድ ዓይነት እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት ቆም ብለን እንድናስብ ይረዳናል።
ስለዚህ ጠንቃቆች እንሁን! ልክን ያለማወቅ ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅ ሁልጊዜ ጠንቃቆች መሆን ያስፈልገናል። ቀደም ሲል ከተጠቀሱት ነገሥታት መካከል ሁለቱ ልካቸውን ሳያውቁ የቀሩባቸው ወቅቶች ነበሩ። ንጉሥ ዳዊት በችኩልነት በእስራኤል የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ አድርጓል። ይህ ደግሞ ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚጋጭ ነበር። ከጊዜ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን ልኩን የማያውቅ መሆኑ በሐሰት አምልኮ እስከ መካፈል አድርሶታል።—2 ሳሙኤል 24:1-10፤ 1 ነገሥት 11:1-13
ይህ አምላክ የለሽ ዓለም እስካለ ድረስ ልክን የማወቅ ባሕርይ ማዳበር ሁልጊዜ ትጉህ መሆንን ይጠይቃል። ጥረታችንም ከንቱ ሆኖ አይቀርም። በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖረው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ልካቸውን በሚያውቁ ሰዎች የተገነባ ይሆናል። እነርሱም ልክን ማወቅን የጥንካሬ እንጂ የደካማነት ምልክት አድርገው አይመለከቱትም። እያንዳንዱ ግለሰብና ቤተሰብ ልኩን ማወቁ የሚያስገኘውን ሰላም አግኝተው ሲኖሩ እንዴት ያለ አስደናቂ ጊዜ ይሆናል!
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ልኩን የሚያውቅ ሰው ስለ ነበር በሚያደርገው ነገር ሁሉ ለይሖዋ ክብር ይሰጥ ነበር