ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት አጎልብቱ
ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት አጎልብቱ
ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 4:8) እንዲሁም መዝሙራዊው ዳዊት “እግዚአብሔር ለሚፈሩት ኃይላቸው [“ወዳጃቸው፣” የ1980 ትርጉም ] ነው” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 25:14) ይሖዋ አምላክ ከእርሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖረን እንደሚፈልግ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ አምላክን የሚያመልኩና ሕጉን የሚጠብቁ ሁሉ ከአምላክ ጋር የቀረበ ወዳጅነት እንዳላቸው ሆኖ ይሰማቸዋል ማለት አይደለም።
አንተስ? ከአምላክ ጋር የቀረበ የግል ዝምድና አለህ? ከአምላክ ጋር ይበልጥ የቀረበ ዝምድና መመሥረት እንደምትፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት የምንችለው እንዴት ነው? ይህ ለእኛ ምን ማለት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ ሦስተኛ ምዕራፍ መልሱን ይሰጠናል።
ፍቅራዊ ደግነትንና እውነትን አንጸባርቁ
የጥንቱ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ሦስተኛውን የምሳሌ መጽሐፍ የከፈተው የሚከተለውን በማለት ነበር:- “ልጄ ሆይ፣ ሕጌን አትርሳ፣ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ። ብዙ ዘመናትና ረጅም ዕድሜ ሰላምም ይጨምሩልሃልና።” (ምሳሌ 3:1, 2) ሰሎሞን መጽሐፉን የጻፈው በአምላክ መንፈስ ተገፋፍቶ እንደመሆኑ መጠን አባታዊ ምክሩ ከይሖዋ አምላክ የመጣ ሲሆን ለእኛም እንዲደርሰን ተደርጓል። የአምላክን ማሳሰቢያዎች ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙትን ሕጉን ወይም ትምህርቱንና ትእዛዛቱን እንድናከብር እዚህ ላይ ተመክረናል። እንዲህ ካደረግን “ብዙ ዘመናትና ረጅም ዕድሜ ሰላምም” ይጨምሩልናል። አዎን፣ በአሁኑ ጊዜ እንኳን ሳይቀር ሰላም የሰፈነበት ሕይወት ልንመራ እንችላለን፤ አንዲሁም ብዙውን ጊዜ በክፉዎች ላይ እንደሚደርሰው ሕይወታችንን በአጭሩ ሊቀጩ ከሚችሉ አደጋዎች ልንሰወር እንችላለን። ከዚህም በላይ ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዲኖረን ይረዳናል።—ምሳሌ 1:24-31፤ 2:21, 22
በመቀጠል ሰሎሞን እንዲህ ይላል:- “ምሕረትና [“ፍቅራዊ ደግነትና፣” NW ] እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።”—ምሳሌ 3:3, 4
“ፍቅራዊ ደግነት” የሚለው ሐረግ የተገኘበት የመጀመሪያ ቃል “ታማኝ ፍቅር” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ይህም የታመኑ መሆንን፣ አንድነትንና ታማኝነትን የሚያስተላልፍ ቃል ነው። ምንም ይምጣ ምን ከይሖዋ ጋር ተጣብቀን ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል? ከእምነት ባልደረቦቻችን ጋር ባለን የቅርብ ዝምድና ፍቅራዊ ደግነትን እናንጸባርቃለን? ከእነርሱ ጋር የመሠረትነው የተቀራረበ ዝምድና እንዳይበላሽ የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን? ዕለት ተዕለት ከእነርሱ ጋር ባለን ግንኙነት በአስቸጋሪ ወቅቶችም እንኳ ቢሆን ‘የፍቅራዊ ደግነትን ሕግ በምላሳችን ላይ እናደርጋለን?’—ምሳሌ 31:26 NW
ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነቱ የበዛ በመሆኑ ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ ነው። (መዝሙር 86:5) ካለፉት ኃጢአቶቻችን ንሥሐ ገብተን አሁን ለእግራችን ቀናውን መንገድ የምንከተል ከሆነ ከይሖዋ ዘንድ “የመጽናናት ዘመን” እንደሚመጣ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል። (ሥራ 3:19) የሌሎችን በደል ይቅር በማለት አምላካችንን መምሰል አይኖርብንም?—ማቴዎስ 6:14, 15
መዝሙር 31:5) ከክርስቲያኖች ጋር ስንሆን አንድ ዓይነት ሰው፣ እነርሱ በማያዩን ቦታ ስንሆን ደግሞ ሌላ ዓይነት ሰው በመሆን ማንነታቸውን እንደሚደብቁ “ውሸተኛ ሰዎች” ሁለት ዓይነት ኑሮ የምንኖር ከሆነ ይሖዋ ወዳጃችን ይሆናል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን? (መዝሙር 26:4) በይሖዋ “ዓይኖ[ች] ፊት ሁሉ ነገር የተራቈተና የተገለጠ” በመሆኑ እንዲህ ማድረጉ ምንኛ ሞኝነት ነው!—ዕብራውያን 4:13
ይሖዋ “የእውነት አምላክ” ነው። ከእርሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት የሚፈልጉ ሁሉ ‘እውነተኞች’ እንዲሆኑም ይፈልጋል። (ፍቅራዊ ደግነትና እውነተኝነት ‘በአምላክና በሰው ፊት ሞገስ እንድናገኝ’ የሚረዱን በመሆናቸው ዋጋው እጅግ ውድ ከሆነ ‘በአንገት ላይ ከሚታሰር’ የአንገት ጌጥ ጋር ተመሳስለዋል። እነዚህን ባሕርያት ማንጸባረቅ ብቻ ሳይሆን ቋሚ የባሕርያችን ክፍል ማድረግ እንችል ዘንድ ‘በልባችን ጽላት’ ላይ መቅረጽ ይኖርብናል።
በይሖዋ ላይ መታመንን አዳብሩ
ጠቢቡ ንጉሥ በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል።”—ምሳሌ 3:5, 6
ይሖዋ ፍጹም እምነት ልንጥልበት የሚገባው አምላክ ነው። ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ‘የኃይልና’ ‘የብርታት’ ሁሉ ምንጭ ነው። (ኢሳይያስ 40:26, 29) ዓላማዎቹን በጠቅላላ ዳር የማድረስ ችሎታ አለው። እንዲያውም ስሙ ራሱ ቃል በቃል ሲተረጎም “እንዲሆን ያደርጋል” ማለት ሲሆን ይህም ያወጣቸውን ዓላማዎቹን ለመፈጸም ባለው ችሎታ ላይ ሙሉ ትምክህታችንን እንድንጥል ያደርገናል! ‘እግዚአብሔር ሊዋሽ የማይችል መሆኑ’ የእውነት ዓይነተኛ ምሳሌ ያደርገዋል። (ዕብራውያን 6:18) ዋነኛው ባሕርይው ፍቅር ነው። (1 ዮሐንስ 4:8) “በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ ነው በሥራውም ሁሉ ቸር ነው።” (መዝሙር 145:17) በአምላክ ላይ ካልታመንን በማን ላይ ልንታመን እንችላለን? እርግጥ ነው፣ በእርሱ ላይ ያለንን እምነት ለማሳደግ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርናቸውን ነገሮች በግል ሕይወታችን ላይ ተግባራዊ በማድረግና ይህም የሚያፈራውን ፍሬ በማንጸባረቅ ‘ይሖዋ ቸር እንደሆነ መቅመስና ማየት’ ይኖርብናል።—መዝሙር 34:8
‘በመንገዳችን ሁሉ ይሖዋን ማወቅ’ የምንችለው እንዴት ነው? መዝሙራዊው በመንፈስ ተገፋፍቶ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ስላደረግኸው ነገር ሁሉ አስባለሁ፤ ስለ ታላላቅ ሥራዎችህም በማሰላሰል አስታውሳለሁ።” (መዝሙር 77:12) አምላክ በዓይን የማይታይ በመሆኑ በታላላቅ ሥራዎቹና ሕዝቦቹን ስለያዘበት መንገድ ማሰላሰሉ ከእርሱ ጋር የመሠረትነውን የጠበቀ ወዳጅነት ለማጠንከር ከፍተኛ እገዛ ያደርግልናል።
በተጨማሪም ጸሎት ይሖዋን ለማየት የሚያስችል አንዱ አስፈላጊ መንገድ ነው። ንጉሥ ዳዊት “ቀኑን ሁሉ” ያለማቋረጥ ይሖዋን ይጠራ ነበር። (መዝሙር 86:3) ዳዊት በበረሃ ስደት ላይ እያለ ሌሊቱን በሙሉ ሲጸልይ ያድር ነበር። (መዝሙር 63:6, 7) ሐዋርያው ጳውሎስ “ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ” በማለት አጥብቆ አሳስቧል። (ኤፌሶን 6:18) ምን ያህል አዘውትረን እንጸልያለን? ከአምላክ ጋር በግል ልባዊ የሐሳብ ግንኙነት መመሥረት ያስደስተናል? ችግር በሚያጋጥመን ጊዜ እንዲረዳን እንማጸነዋለን? አንድ አስፈላጊ የሆነ ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት አመራር ለማግኘት በጸሎት እንጠይቀዋለን? ለይሖዋ የምናቀርበው ከልብ የመነጨ ጸሎት በእርሱ ዘንድ ተወዳጅ ያደርገናል። እንዲሁም ለእርሱ የምናቀርበውን ጸሎት እንደሚሰማና ‘መንገዳችንን የተቃና እንደሚያደርግልን’ ማረጋገጫ አለን።
ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ መታመን ስንችል ‘በራሳችን ማስተዋል ላይ’ ወይም ታዋቂ በሆኑ ዓለማዊ ሰዎች ላይ ‘መደገፍ’ ምንኛ ሞኝነት ነው! “በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን” በማለት ሰሎሞን ተናግሯል። ከዚህ በተቃራኒ ሰሎሞን “እግዚአብሔርን ፍራ፣ ከክፋትም ራቅ፤ ይህም ለሥጋህ ፈውስ ይሆንልሃል፣ ለአጥንትህም ጠገን” በማለት ይመክራል። (ምሳሌ 3:7, 8) አምላክን ላለማሳዘን የምናሳየው ጤናማ ፍርሃት መላው ድርጊቶቻችንን፣ አስተሳሰባችንንና ስሜቶቻችንን ሊመራው ይገባል። እንዲህ ያለው አክብሮታዊ ፍርሃት መጥፎ የሆነውን ነገር እንዳንሠራ ይጠብቀናል፤ እንዲሁም መንፈሳዊ ፈውስ የሚያስገኝና የሚያነቃቃ ነው።
ለይሖዋ ምርጣችሁን ስጡ
በሌላ በምን መንገድ ወደ ይሖዋ መቅረብ እንችላለን? “እግዚአብሔርን ከሀብትህ አክብር፣ ከፍሬህም ሁሉ በኩራት” በማለት ንጉሡ መመሪያ ይሰጠናል። (ምሳሌ 3:9) ይሖዋን ማክበር ማለት ለእርሱ ከፍተኛ አክብሮት መስጠት እንዲሁም ስሙን በማወጁ ሥራ መካፈልና ለሥራውም ድጋፍ መስጠት ማለት ነው። ይሖዋን ለማክበር ከምንጠቀምባቸው ሃብታችን መካከል ጊዜያችን፣ ተሰጥኦዋችን፣ ጉልበታችንና ቁሳዊ ንብረቶቻችን ይገኙበታል። እነዚህም በኩራት ማለትም ምርጣችን መሆን አለባቸው። በግል ያፈራናቸውን ሃብታችንን የምንጠቀምበት መንገድ ‘መንግሥቱንና የአምላክን ጽድቅ ለማስቀደም’ የቆረጥን መሆናችንን የሚያንጸባርቁ መሆን አይኖርባቸውም?—ማቴዎስ 6:33
ይሖዋን በሃብታችን ማክበራችን እንዲሁ ከንቱ ሆኖ የሚቀር ነገር አይደለም። “ጐተራዎችህ በእህል የተሞሉ ይሆናሉ፤ የወይን መጥመቂያህም በአዲስ የወይን ጠጅ ሞልቶ ይትረፈረፋል” በማለት ሰሎሞን ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ምሳሌ 3:10 የ1980 ትርጉም) መንፈሳዊ ብልጥግና በራሱ ቁሳዊ ሃብት የሚያስገኝ ባይሆንም ጥሪታችንን ሳንስቆነቆን ይሖዋን ለማክበር ከተጠቀምንበት የተትረፈረፈ በረከት ያስገኝልናል። የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ለኢየሱስ ሕይወቱን ሕያው አድርጎ እንደሚያቆይ “ምግብ” ነበር። (ዮሐንስ 4:34) በተመሳሳይም ለይሖዋ ክብር በሚያመጡት በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መካፈላችን ለእኛም እንደ ምግብ ሊሆንልን ይችላል። በዚህ ሥራ ጸንተን መቀጠላችን መንፈሳዊ ጎተራችን ከአፍ እስከ ገደፉ እንዲሞላ ያደርገዋል። በአዲስ ወይን ጠጅ የተመሰለው ደስታችንም ሞልቶ የሚፈስ ይሆናል።
በተጨማሪም በየዕለቱ የሚያስፈልገንን ሰብዓዊ ምግብ ለማግኘት ፊታችንን ወደ ይሖዋ በማዞር ወደ እርሱ እንጸልይ የለምን? (ማቴዎስ 6:11) እንዲያውም ያለን ነገር ሁሉ ከአፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ያገኘነው ነው። ይሖዋ ተጨማሪ በረከቱን የሚሰጠን እኛ ሃብታችንን ለእርሱ ክብር ለማዋል በተጠቀምንበት መጠን ነው።—1 ቆሮንቶስ 4:7
ይሖዋ የሚሰጠውን ተግሣጽ በደስታ መቀበል
ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ተግሣጽ ጠቀሜታ እንዳለው ለማስገንዘብ የእስራኤሉ ንጉሥ እንዲህ በማለት ምክሩን ይለግሳል:- “ልጄ ሆይ፣ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፣ በገሠጸህም ጊዜ አትመረር። እግዚአብሔር የወደደውን ይገሥጻልና፣ አባት የሚወድደውን ልጁን እንደሚገሥጽ።”—ምሳሌ 3:11, 12
ተግሣጽን መቀበል ቀላል ላይሆን ይችላል። “ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፣ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ ጽፏል። (ዕብራውያን 12:11) ወቀሳና ተግሣጽ ወደ አምላክ እንድንቀርብ የሚረዱ አስፈላጊ የሆኑ የሥልጠና ክፍሎች ናቸው። ይሖዋ የሚሰጠው እርማት በወላጆች በኩልም ይምጣ ወይም በክርስቲያን ጉባኤ በኩል ወይም የግል ጥናት በምናደርግበት ወቅት በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ስናሰላስል የምናገኘው ይሁን እርሱ ለእኛ ያለው ፍቅር መግለጫ ነው። እርማቱን በደስታ መቀበላችን ጥበብ ነው።
ጥበብንና ማስተዋልን አጥብቆ መያዝ
ቀጥሎም ሰሎሞን ከአምላክ ጋር የቅርብ ዝምድና ለመመሥረት ጥበብና ማስተዋል የሚሰጡትን ጠቀሜታ ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል። እንዲህ አለ:- “ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን ነው፣ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ፤ በወርቅና በብር ከመነገድ ይልቅ በእርስዋ መነገድ ይሻላልና። . . . እርስዋ ለሚይዙአት የሕይወት ዛፍ ናት፣ የተመረኰዘባትም [“አጥብቆ የሚይዛትም፣” NW ] ሁሉ ምስጉን ነው።”—ምሳሌ 3:13-18
ይሖዋ በፈጠራቸው አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎች ውስጥ ጥበብና ማስተዋል የተንጸባረቁ መሆናቸውን ሲያሳስበን ንጉሡ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፣ በማስተዋልም ሰማያትን አጸና። . . . ልጄ ሆይ፣ እነዚህ ከዓይኖችህ አይራቁ፤ መልካም ጥበብንና ጥንቃቄን ጠብቅ። ለነፍስህም ሕይወት ይሆናሉ፣ ለአንገትህም ሞገስ።”—ምሳሌ 2:19-22
ጥበብና ማስተዋል አምላካዊ ባሕርያት ናቸው። እነዚህን ባሕርያት ማዳበር ብቻ ሳይሆን ቅዱሳን ጽሑፎችን በትጋት ማጥናታችንንና የተማርነውን በሥራ ላይ ማዋላችንን ፈጽሞ ችላ ባለማለት አጥብቀን ልንይዛቸው ይገባናል። “የዚያን ጊዜ መንገድህን ተማምነህ ትሄዳለህ፣ እግርህም አይሰነካከልም” በማለት ሰሎሞን ይናገራል። ጨምሮም “በተኛህ ጊዜ አትፈራም፤ ትተኛለህ፣ እንቅልፍህም የጣፈጠ ይሆንልሃል።”—ምሳሌ 3:23, 24
አዎን፣ በሰይጣን ክፉ ዓለም ላይ እንደ ሌባ ሆኖ “በድንገት” የሚመጣውን “ጥፋት” እየተጠባበቅን ተማምነን ልንሄድና የአእምሮ ሰላም ኖሮን መተኛት እንችላለን። (1 ተሰሎንቄ 5:2, 3፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ሌላው ቀርቶ በቅርቡ በሚመጣው ታላቅ መከራ ወቅት የሚከተለው ማረጋገጫ ሊኖረን ይችላል:- “ድንገት ከሚያስፈራ ነገር፣ ከሚመጣውም ከኀጥአን ጥፋት አትፈራም፤ እግዚአብሔር መታመኛህ ይሆናልና፣ እግርህም እንዳይጠመድ ይጠብቅሃልና።”—ምሳሌ 3:25, 26፤ ማቴዎስ 24:21
በጎ የሆነውን አድርጉ
“ለተቸገረው ሰው በጎ ነገርን ማድረግ አትከልክል፣ ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን” በማለት ሰሎሞን ይመክራል። (ምሳሌ 3:27) ለሌሎች በጎ ነገር ማድረግ ሃብታችንን በልግስና መጠቀምን የሚያጠቃልል ከመሆኑም በላይ ሌሎች ገፅታዎችም አሉት። ይሁን እንጂ በዚህ ‘የፍጻሜ ዘመን’ ለሰዎች ከሁሉ የተሻለ ነገር ልናደርግላቸው የምንችለው ከእውነተኛው አምላክ ጋር የቀረበ ዝምድና እንዲመሠርቱ መርዳት አይደለምን? (ዳንኤል 12:4) በመንግሥቱ የስብከት ሥራና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት የምንካፈልበት ጊዜ አሁን ነው።—ማቴዎስ 28:19, 20
በተጨማሪም ጠቢቡ ንጉሥ ልናስወግዳቸው ስለሚገቡ አንዳንድ ልማዶች እንዲህ በማለት ይናገራል:- “ወዳጅህን:- ሂድና ተመለስ ነገ እሰጥሃለሁ አትበለው፣ በጎ ነገርን ማድረግ ሲቻልህ። በወዳጅህ ላይ ክፉ አትሥራ፣ እርሱ ተማምኖ ከአንተ ጋር ተቀምጦ ሳለ። ከሰው ጋር በከንቱ አትጣላ፣ እርሱ ክፉ ካልሠራብህ። በግፈኛ ሰው አትቅና፣ መንገዱንም ሁሉ አትምረጥ።”—ምሳሌ 3:28-31
ሰሎሞን ይህን ምክር የሰጠበትን ምክንያት ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ አለ:- “ጠማማ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ርኩስ ነውና፤ ወዳጅነቱ ግን ከቅኖች ጋር ነው። የእግዚአብሔር መርገም በኀጥእ ቤት ነው፣ የጻድቃን ቤት ግን ይባረካል። በፌዘኞች እርሱ ያፌዛል፣ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል። ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፤ የሰነፎች ከፍታቸው ግን መዋረድ ነው።”—ምሳሌ 3:32-35
ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ከፈለግን ክፉና ጎጂ እቅዶችን ከማውጣት መታቀብ ይገባናል። (ምሳሌ 6:16-19) የአምላክን ሞገስና በረከት ልናገኝ የምንችለው በእርሱ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ስናደርግ ብቻ ነው። እንዲሁም የምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ከመለኮታዊው ጥበብ ጋር የሚስማሙ መሆናቸውን ሌሎች ሲመለከቱ ከፍተኛ አክብሮት ሊያስገኝልን ይችላል። ስለዚህ የዚህን ክፉና ዓመፀኛ ዓለም መጥፎ አካሄድ አንከተል። ከዚያ ይልቅ ቀና የሆነውን መንገድ እንከተል፤ እንዲሁም ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት እየጎለበተ ይሂድ!
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“እግዚአብሔርን ከሀብትህ አክብር”