ስለ ራስህ ያለህ አመለካከት ምን ይመስላል?
ስለ ራስህ ያለህ አመለካከት ምን ይመስላል?
ሰውየው ኩራተኛ ነበር። በመንግሥቱ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን በማግኘቱ ምክንያት ከመጠን በላይ መሞገሱና መወደሱ የልብ ልብ እንዲሰማው አድርጎታል። ይሁን እንጂ ከአንድ ሌላ ባለ ሥልጣን እንዲህ የመሰለውን ክብር ሳያገኝ መቅረቱ አበሳጭቶታል። ይህ ትዕቢተኛ ባለ ሥልጣን ያበሳጨውን ሰው ለመበቀል የዚያን ሰው ወገኖች በሙሉ ከምድረ ገጽ የሚያጠፋበትን ተንኮል ጠነሰሰ። ይህ ከእኔ በላይ ሰው የለም የሚል የተሳሳተ አመለካከት ነው!
ይህ ተንኮለኛ ሰው በፋርሱ ንጉሥ በአሕሻዊሮስ ቤተ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው ሐማ ነው። የተቆጣው በማን ላይ ነበር? መርዶክዮስ በተባለ አንድ አይሁዳዊ ሰው ላይ ነበር። ሐማ የዘር ማጥፋት እርምጃ ለመውሰድ መነሳቱ የለየለት ክፋት ነው፤ ይህም ኩራት ምን ያክል አደገኛ እንደሆነና የሚያስከትለውም ውጤት ከባድ መሆኑን ጥሩ አድርጎ ያሳያል። የዚህ ሰው የዕብሪተኝነት መንፈስ በሌሎች ላይ ችግር መፍጠር ብቻ ሳይሆን እርሱን በሕዝብ ፊት ለውርደትና በመጨረሻም ለሞት ዳርጎታል።—አስቴር 3:1-9፤ 5:8-14፤ 6:4-10፤ 7:1-10
እውነተኛ አምላኪዎችም ካልተጠነቀቁ ኩራተኞች ሊሆኑ ይችላሉ
ይሖዋ ‘ከአምላካችን ጋር ልካችንን አውቀን እንድንሄድ’ ይፈልግብናል። (ሚክያስ 6:8) መጽሐፍ ቅዱስ ልካቸውን ሳያውቁ የቀሩ የተለያዩ ግለሰቦችን ታሪክ ዘግቧል። ይህም ችግርና ሐዘን አስከትሎባቸዋል። ከእነዚህ መካከል የአንዳንዶቹን ምሳሌ መመልከታችን ሚዛኑን የሳተ አመለካከት ስሕተት ላይ ሊጥልና አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል እንድንገነዘብ ይረዳናል።
የአምላክ ነቢይ የነበረው ዮናስ ክፉ በነበሩት የነነዌ ሰዎች ላይ ሊመጣ ያለውን የይሖዋን የቅጣት ፍርድ በተመለከተ እንዲያስጠነቅቅ መለኮታዊ ተልዕኮ በተሰጠው ጊዜ ሚዛናዊነት የጎደለው አመለካከት በመያዙ ለመኮብለል ሙከራ አድርጎ ነበር። (ዮናስ 1:1-3) በኋላም የነነዌ ሰዎች በእርሱ ስብከት ንሥሐ በገቡ ጊዜ ዮናስ አኮረፈ። በነቢይነት ስላገኘው ዝና በጣም ከመጨነቁ የተነሳ በነነዌ ይኖሩ የነበሩት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ቅንጣት ታክል እንኳ አላስጨነቀውም ነበር። (ዮናስ 4:1-3) ራሳችንን አለልክ ከሌሎች በላይ ከፍ አድርገን የምንመለከት ከሆነ ለሰዎችና በአካባቢያችን ለደረሱ ክስተቶች ሚዛናዊና ትክክለኛ አመለካከት እንዳይኖረን ሊጋርድብን ይችላል።
በተጨማሪም የይሁዳ ጥሩ ንጉሥ የነበረውን ዖዝያንን እንውሰድ። ሚዛናዊነት የጎደለው አስተሳሰብ ባደረበት ወቅት ካህናት ብቻ ማከናወን ያለባቸውን አንዳንድ ሥራዎች በማን አለብኝነት ለማከናወን ሙከራ አደረገ። ልኩን አለማወቁና የትዕቢት እርምጃ መውሰዱ ጤናውንና በአምላክ ፊት የነበረውን ሞገስ እንዲያጣ አድርጎታል።—2 ዜና መዋዕል 26:3, 16-21
የተሳሳተ አመለካከት መያዝ ለኢየሱስ ሐዋርያትም ሳይቀር ወጥመድ ሆኖባቸው ነበር። ስለ ግል ክብራቸውና ሥልጣናቸው ከልክ በላይ ይጨነቁ ነበር። ታላቅ ፈተና በመጣበት ወቅት ኢየሱስን ትተው ሸሹ። (ማቴዎስ 18:1፤ 20:20-28፤ 26:56፤ ማርቆስ 9:33, 34፤ ሉቃስ 22:24) ልካቸውን አለማወቃቸውና ስለ ራሳቸው የተጋነነ አመለካከት ማሳደራቸው የይሖዋን ዓላማና ከእርሱ ፈቃድ ጋር በተያያዘ የሚጫወቱትን ሚና እንዲዘነጉ አደረጋቸው።
ራስን ከልክ በላይ ከፍ አድርጎ መመልከት የሚያስከትላቸው ጎጂ ውጤቶች
ስለ ራስ የተዛባ አመለካከት መያዝ ስቃይ ሊያስከትል እንዲሁም ከሌሎች ጋር ያለንን ዝምድና ሊያበላሽብን ይችላል። ለምሳሌ ያህል በአንድ ክፍል ውስጥ ቁጭ ብለን ሳለ ሁለት ሰዎች እየተንሾካሾኩ ሲያወሩና ሲስቁ እንመለከት ይሆናል። ለራሳችን ክብር ከልክ በላይ የምንጨነቅ ከሆነ በሹክሹክታ እየተነጋገሩ የሚስቁት በእኛ ላይ እንደሆነ አድርገን በማሰብ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ልንደርስ እንችላለን። በሌላም ምክንያት ሊስቁ እንደሚችሉ ፈጽሞ ላይመጣልን ይችል ይሆናል። ደግሞስ ከእኔ ሌላ ስለ ማን ሊያወሩ ይችላሉ? በጣም ልንበሳጭና እነዚያን ሰዎች ሁለተኛ ላለማነጋገር ልንወስን እንችላለን። በዚህ መንገድ ለራሳችን ያለን ሚዛኑን የሳተ አመለካከት ወደ አለመግባባት ሊመራንና ከጓደኞቻችን፣ ከቤተሰባችን አባላትና ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ሊያበላሽብን ይችላል።
ራሳቸውን ከልክ በላይ ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች አለኝ ብለው ስለሚያስቡት ተሰጥዖ፣ ስላከናወኑት ነገር ወይም ስላገኙት ሀብት በመናገር ጉራቸውን እንደነዙ ሊኖሩ ይችላሉ። ወይም ሁልጊዜ ስለ ራሳቸው በመጥቀስ እነሱ ብቻ ተናጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ ያለው ልማድ እውነተኛ ፍቅር እንደሌላቸው የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ ሌሎችን የሚያበሳጭ ሊሆን ይችላል። ትዕቢተኛ ሰዎች በዚህ መንገድ ራሳቸውን ከሌሎች ከፍ ከፍ ሲያደርጉ ይታያሉ።—የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን በሕዝብ ፊት አገልግሎታችንን በምናከናውንበት ወቅት ሰዎች ሊያፌዙብንና ሊቃወሙን ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቱን ተቃውሞ የሚሰነዝሩት በእኛ ላይ ሳይሆን ይዘነው የሄድነው መልእክት ምንጭ በሆነው በይሖዋ ላይ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ይሁን እንጂ ስለ ራሳችን የተዛባ አመለካከት ካለን ወዳልተፈለገ ሁኔታ ሊመራን ይችላል። ከዓመታት በፊት አንድ ወንድም አንድ የቤት ባለቤት ያወረደበትን የስድብ ናዳ በቀጥታ በእርሱ ላይ እንደተሰነዘረ አድርጎ በማሰብ እርሱም መልሶ ተሳደበ። (ኤፌሶን 4:29) ከዚያን ቀን ጀምሮ ያ ወንድም ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ተካፍሎ አያውቅም። አዎን፣ ኩራት በስብከት ሥራችን ላይ እያለን ቁጣችንን መቆጣጠር እንዲሳነን ሊያደርገን ይችላል። እንዲህ ያለው ሁኔታ በእኛ ላይ እንዲደርስ ፈጽሞ አንፍቀድ። ከዚያ ይልቅ በክርስቲያን አገልግሎት የመካፈል መብታችንን በአድናቆት መመልከት እንችል ዘንድ እንዲረዳን ይሖዋን በትሕትና እንጠይቀው።—2 ቆሮንቶስ 4:1, 7፤ 10:4, 5
ራስን ከሌሎች በላይ ከፍ አድርጎ የመመልከት ዝንባሌ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ ምክርን እንዳንቀበልም ሊያደርገን ይችላል። ከጥቂት ዓመታት በፊት በመካከለኛው አሜሪካ በምትገኝ አገር የሚኖር በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ ልጅ በክርስቲያን ጉባኤ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል አቀረበ። የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ቀጥተኛ ምክር በሰጠው ጊዜ ቅር የተሰኘው ይህ ወጣት መጽሐፍ ቅዱሱን መሬት ላይ ወርውሮ ዳግም ላይመለስ ከመንግሥት አዳራሹ ወጣ። ይሁን እንጂ ከጥቂት ቀናት በኋላ ኩራቱን አስወግዶ ከትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ጋር ታረቀና ምክሩን በትሕትና ተቀበለ። ከጊዜ በኋላ ይህ ወጣት የጎለመሰ ክርስቲያን ሆነ።
ልክን አለማወቅና ከሚገባው በላይ ስለ ራስ መጨነቅ ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያበላሽብን ይችላል። ምሳሌ 16:5 “በልቡ የታበየ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነው” በማለት ያስጠነቅቃል።
ስለ ራሳችን ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
ስለ ራሳችን የተጋነነ አመለካከት ሊኖረን እንደማይገባ ግልጽ ነው። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ስንል ስለምናደርገው ወይም ስለምንናገረው ነገር በቁም ነገር ማሰብ የለብንም ማለታችን አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ የበላይ ተመልካቾችም ሆኑ የጉባኤ አገልጋዮች እንዲሁም መላው የጉባኤ አባል ቁም ነገረኞች መሆን እንዳለባቸው ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 3:4, 8, 11 NW፤ ቲቶ 2:2 NW ) ታዲያ ክርስቲያኖች ስለ ራሳቸው ልከኛና ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖራቸው እንዲሁም በጭምትነት ሊያስቡ የሚችሉት እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ራሳቸው ሚዛናዊ አመለካከት የነበራቸው የበርካታ ግለሰቦችን አበረታች ምሳሌ ይዞልናል። ከሁሉም የላቀው የኢየሱስ ክርስቶስ የትሕትና ምሳሌ ነው። የአምላክ ልጅ የአባቱን ፈቃድ ለማድረግና የሰውን ዘር ለማዳን ሲል በሰማይ የነበረውን ክብር በፈቃደኝነት በመተውና ራሱን ዝቅ በማድረግ በምድር ላይ ሰው ሆነ። ስድብ፣ ጉስቁልናና አሳፋሪ ሞት ቢደርስበትም እንኳ ራሱን ገዝቷል፤ እንዲሁም ክብሩን ጠብቋል። (ማቴዎስ 20:28፤ ፊልጵስዩስ 2:5-8፤ 1 ጴጥሮስ 2:23, 24) ኢየሱስ ይህን ሊያደርግ የቻለው እንዴት ነበር? በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ በመደገፉና መለኮታዊውን ፈቃድ ለማድረግ ቁርጥ አቋም በመውሰዱ ነው። ኢየሱስ የአምላክን ቃል በትጋት ያጠናና በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ እንዲሁም አገልግሎቱን በጋለ ስሜት ያከናውን ነበር። (ማቴዎስ 4:1-10፤ 26:36-44፤ ሉቃስ 8:1፤ ዮሐንስ 4:34፤ 8:28፤ ዕብራውያን 5:7) የኢየሱስን ምሳሌ መከተላችን ስለ ራሳችን ሚዛናዊ አመለካከት እንድናዳብርና በዚያ እንድንቀጥል ሊረዳን ይችላል።—1 ጴጥሮስ 2:21
በተጨማሪም የንጉሥ ሳኦልን ልጅ የዮናታንን ጥሩ ምሳሌ ተመልከት። ዮናታን አባቱ ታዛዥ ሳይሆን በመቅረቱ ምክንያት በሳኦል ምትክ ንጉሥ የመሆንን አጋጣሚ አጥቷል። (1 ሳሙኤል 15:10-29) ታዲያ ዮናታን ንጉሥ ሳይሆን በመቅረቱ ተናድዷልን? በእርሱ ቦታ ገዥ በሆነው በወጣቱ ሰው በዳዊት ላይ ቅናት አደረበት? ዮናታን ከዳዊት በዕድሜ የሚበልጥና ምናልባትም የላቀ ተሞክሮ የነበረው ሰው ቢሆንም እንኳ ልኩን በማወቅና በትሕትና ራሱን ለይሖዋ ዝግጅት ከማስገዛቱም በላይ በታማኝነት ዳዊትን ደግፏል። (1 ሳሙኤል 23:) የአምላክን ፈቃድ በሚገባ መገንዘቡና ለዚህም ፈቃድ ታዛዥ መሆኑ ‘ስለ ራሳችን ማሰብ ከሚገባን በላይ አልፈን በትዕቢት እንዳናስብ’ ይረዳናል።— 16-18ሮሜ 12:3
ኢየሱስ ልክን ማወቅና ትሕትና አስፈላጊ ነገሮች እንደሆኑ አስተምሯል። ይህንንም ደቀ መዛሙርቱ በሠርግ ድግስ ላይ እንዲገኙ ተጋብዘው በሚሄዱበት ጊዜ ምናልባት ከእነርሱ ይበልጥ የታወቀ ሰው መጥቶ ለእርሱ ቦታ ለቅቀው ወደ ዝቅተኛው ሥፍራ እንዲሄዱ ተደርጎ በሃፍረት እንዳይሸማቀቁ “የከበሬታ ስፍራ” መፈለግ እንደሌለባቸው የሚገልጽ ምሳሌ በመናገር አስረድቷቸዋል። ኢየሱስ ትምህርቱን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፣ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል” በማለት ጨምሮ ተናገረ። (ሉቃስ 14:7-11) እኛም ኢየሱስ የሰጠውን ምክር ብንከተልና ‘ትሕትናን እንደ ልብስ’ ብንታጠቅ ጠቢብ እንሆናለን።—ቆላስይስ 3:12፤ 1 ቆሮንቶስ 1:31
ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ የሚያስገኛቸው በረከቶች
ልክን የማወቅና የትሕትና መንፈስ መያዝ የይሖዋ አገልጋዮች በአገልግሎታቸው እውነተኛ ደስታ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ሽማግሌዎች ትሑት ሆነው ‘መንጋውን በርኅራኄ ሲጠብቁ’ በቀላሉ የሚቀረቡ ይሆናሉ። (ሥራ 20:28, 29) ይህም በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሁሉ እነርሱን ለማነጋገርና እርዳታቸውን ለመጠየቅ ነፃነት እንዲሰማቸው ያደርጋል። በዚህም የተነሳ ጉባኤው በፍቅር፣ ከልብ በመተሳሰብ ስሜትና እርስ በርስ በመተማመን መንፈስ ይበልጥ ሊቀራረብ ይችላል።
ለራሳችን ክብር ከልክ በላይ አለመጨነቃችን ጥሩ ወዳጆችን እንድናፈራ ያስችለናል። ልክን ማወቅና ትሕትና በድርጊታችን ወይም ባለን ቁሳዊ ንብረት ከሌሎች ልቀን ለመታየት በመሞከር በውስጣችን የፉክክር መንፈስ እንዳያቆጠቁጥ ይጠብቀናል። እነዚህ አምላካዊ ባሕርያት ይበልጥ ለሌሎች የምናስብ እንድንሆን ይረዱናል፤ እንዲሁም ችግር ላይ የወደቁትን ለማጽናናትና ለመደገፍ ይበልጥ ዝግጁዎች ያደርገናል። (ፊልጵስዩስ 2:3, 4) ሰዎች ፍቅርንና ደግነትን ካሳየናቸው ብዙውን ጊዜ ጥሩ ምላሽ ይሰጣሉ። ለጠንካራ ወዳጅነት መሠረት የሚሆነው እንዲህ ያለው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ዝምድና አይደለም? ለራስ ክብር ከልክ በላይ አለመጨነቅ ምንኛ በረከት ነው!—ሮሜ 12:10
ለራሳችን ሚዛናዊ አመለካከት መያዛችን አንድን ሰው በምናስቀይምበት ጊዜ ስህተታችንን በቀላሉ አምነን እንድንቀበል ያደርግልናል። (ማቴዎስ 5:23, 24) ይህም የተሻለ ዝምድና እንድንመሠርት፣ እርቅ ለማውረድና እርስ በርስ ለመከባበር ይረዳናል። የበላይ ተመልካች ሆነው የሚያገለግሉ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሽማግሌዎች ትሑትና ልካቸውን የሚያውቁ መሆናቸው ለሌሎች በርካታ ጥሩ ነገሮችን ለማድረግ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። (ምሳሌ 3:27፤ ማቴዎስ 11:29) ትሑት የሆነ ሰው በእርሱ ላይ በደል የፈጸመን ግለሰብ ይቅር ለማለት አይከብደውም። (ማቴዎስ 6:12-15) በትንሽ በትልቁ የማይጎዳ ከመሆኑም በላይ በሌላ በምንም ሊስተካከሉ የማይችሉ ነገሮችን ይሖዋ እንደሚያስተካክላቸው ሙሉ እምነት ይኖረዋል።—መዝሙር 37:5፤ ምሳሌ 3:5, 6
ልካችንን ማወቃችንና በትሕትና መመላለሳችን ከሁሉ የላቀ በረከት ማለትም በይሖዋ ፊት ሞገስና ተቀባይነት ያስገኝልናል። “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፣ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።” (1 ጴጥሮስ 5:5) ከእኔ በላይ ሰው የለም በሚል አስተሳሰብ ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅ እንጠንቀቅ። ከዚያ ይልቅ ይሖዋ ለነገሮች ባወጣው ዝግጅት ውስጥ ያለንን ቦታ በትሕትና እንቀበል። ‘ከአምላክ ጋር ልካቸውን አውቀው በመጓዝ’ ረገድ አምላክ ያወጣውን ብቃት የሚያሟሉ ሁሉ ከፊታቸው ከፍተኛ በረከት ይጠብቃቸዋል።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዮናታን በትሕትና ዳዊትን ደግፏል