ንድፍ አውጪ አለው?
ቶርኒ ዴቭል የተባለው እንሽላሊት ውኃ የሚስብ ቆዳ
የአውስትራሊያው ቶርኒ ዴቭል እንሽላሊት (ሞሎክ ሆሪደስ) ከጭጋግ፣ እርጥበት ካዘለ አየርና ከእርጥብ አሸዋ ውኃ ይስባል። ከዚያም ይህ ውኃ ወደ አፉ ይሄድና ይጠጣዋል። እንዴት? የዚህ ጥያቄ መልስ እንሽላሊቱ ካለው አስገራሚ ቆዳ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የቶርኒ ዴቭል ቆዳ በተነባበሩ ቅርፊቶች የተሸፈነ ነው። አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት እንደሚያስቡት በቅርፊቶቹ ላይ የተጠራቀመው እርጥበት ወይም ጤዛ ሸካራ በሆነው የላይኛው የቆዳ ክፍል አልፎ በቅርፊቶቹ መካከል ወደሚገኙት በከፊል ክፍት ወደሆኑት ቱቦዎች ይገባል። እርስ በርስ በተገናኙት በእነዚህ ቱቦዎች አማካኝነት የሚመጣው ውኃ ወደ ቶርኒ ዴቭል አፍ ይሄዳል።
ይሁን እንጂ ይህ እንሽላሊት የስበትን ኃይል ተቋቁሞ ውኃው በእግሮቹ በኩል ሽቅብ ወደ ሰውነቱ እንዲወጣ ከዚያም ወደ አፉ እንዲሄድ የሚያደርገው እንዴት ነው? ደግሞስ ቶርኒ ዴቭል እርጥበት ካለው ነገር ጋር ሆዱን በማነካካት ውኃውን የሚስበው እንዴት ነው?
ተመራማሪዎች የቶርኒ ዴቭልን ሚስጥር የደረሱበት ይመስላል። በእንሽላሊቱ ቆዳ የላይኛው ክፍል ላይ ያሉት ቱቦዎች በቆዳው ሥር ካሉት እርስ በርስ የተያያዙ ሌሎች ቱቦዎች ጋር ይገናኛሉ። የእነዚህ ቱቦዎች አሠራር ቀጫጭን የደም ቧንቧዎች (ካፒላሪስ) ከሚያከናውኑት ሥራ ጋር ይመሳሰላል፤ ይህም የስበት ኃይል እያለ እንኳ ውኃው በቀጫጭን ቱቦዎች ውስጥ ሽቅብ እንዲወጣ ያስችለዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ የእንሽላሊቱ ቆዳ ልክ እንደ ስፖንጅ ሆኖ ያገለግላል።
ጀኒን ቢንየስ የተባሉ የባዮሚሚክሪ ተቋም ፕሬዚዳንት እንዳሉት ከሆነ መሐንዲሶች ይህ እንሽላሊት ያለውን ውኃ የመሳብ ችሎታ በመኮረጅ ከእርጥበት አዘል አየር ውስጥ ውኃውን ለይተው በማውጣት ሕንፃዎችን ለማቀዝቀዝ አልፎ ተርፎም የመጠጥ ውኃ ለማግኘት የሚያስችል ዘዴ እንዲያገኙ ሊረዳቸው ይችላል።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? ውኃ የመሳብ ችሎታ ያለው የቶርኒ ዴቭል ቆዳ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?