ንድፍ አውጪ አለው?
የኢሰስ ሊፍሆፐር እግር ላይ ያሉ ጥርሶች
አውቶማቲክ የማሽን ጥርስ የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤት ብቻ እንደሆነ ተደርጎ ለረጅም ጊዜ ሲታሰብ ቆይቷል። ይህ አመለካከት ግን ስህተት መሆኑ ተረጋግጧል! እርስ በርስ በመቆላለፍ የሚሠሩ ጥርሶች ያሏቸው ሕያዋን ፍጥረታት እንዳሉ ማወቅ ተችሏል፤ ይህም የፌንጣ ዝርያ የሆነውና እድገቱን ያልጨረሰው የኢሰስ ሊፍሆፐር ሲሆን በመላው አውሮፓ በአትክልት ስፍራዎች ይገኛል። *
እድገቱን ያልጨረሰ ሊፍሆፐር የሴኮንድ አንድ ሁለት ሺኛ በሚሆን ጊዜ ውስጥ በሴኮንድ 3.9 ሜትር በሚያህል ፍጥነት መስፈንጠር ይችላል፤ ይህን ሲያደርግ የመሬት ስበት ሰውነቱ ላይ የሚያሳድረውን ኃይል 400 ጊዜ ገደማ የሚበልጥ ኃይል ይጠቀማል! ይህ ፌንጣ በቅጽበት ከዓይን ሊሰወር ይችላል። በዚህ መንገድ ለመዝለል ሁለቱ የኋላ እግሮቹ ተመሳሳይ በሆነ ኃይል እንዲሁም ዝንፍ ሳይሉ ተመሳሳይ በሆነ ጊዜ መስፈንጠር አለባቸው። ይህ ፌንጣ ያለ አንዳች መዛነፍ እንዲስፈነጠር የሚያስችለው ምንድን ነው?
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የሳይንስ ሊቃውንት የሊፍሆፐር ሁለት የኋላ እግሮች የሚገጣጠሙበት ቦታ ላይ፣ እርስ በርስ በመቆላለፍ የሚሠሩ ሁለት ጥርሶች መኖራቸውን ደርሰውበታል። ፌንጣው በሚዘልበት ጊዜ እነዚህ ጥርሶች፣ ሁለቱ እግሮቹ ሙሉ በሙሉ እኩል እንዲንቀሳቀሱ ያስችላሉ። ይህ ባይሆን ኖሮ ፌንጣው ከመዝለል ይልቅ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ይሽከረከር ነበር!
ትላልቅ ፍጥረታት በሚዘሉበት ጊዜ እግራቸው እንዲቀናጅ የሚያደርገው የነርቭ አውታራቸው ነው። እድገቱን ያልጨረሰ ሊፍሆፐር ግን የነርቭ ሥርዓቱ ፍጥነቱን እጅግ ያጓትትበታል። በመሆኑም ለዚህ የሚረዱት ተቀናጅተው የሚሠሩት ሁለቱ ጥርሶች ናቸው። ጸሐፊና ተመራማሪ የሆኑት ግሪገሪ ሰተን “አብዛኛውን ጊዜ ማሽን ላይ የተገጠመ ጥርስ፣ ሰዎች የፈለሰፉት ነገር እንደሆነ እናስባለን” ብለዋል። አክለውም የዚህን ምክንያት ሲገልጹ “[በሌላ ቦታ] ለማግኘት ከልብ ጥረት ባለማድረጋችን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? የኢሰስ ሊፍሆፐር እግር ያለው ጥርስ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?
^ አን.3 ይህ የፌንጣ ዝርያ ወደ መጨረሻ የእድገት ደረጃው ሲሸጋገር የበፊት አካሉን ገፍፎ ስለሚያወልቅ በእግሩ ላይ ያሉት እንደ ጥርስ የሚቆላለፉ የሰውነት ክፍሎች ይወድቃሉ።