የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሕይወትህን መቆጣጠር ትችላለህ?
ተፈታታኙ ነገር፦ ተደራራቢ ኃላፊነት
ልጆችሽ አሁኑኑ ያንቺን ትኩረት ማግኘት ፈልገዋል። አለቃሽም ቢሆን በሥራ ገበታሽ ላይ እንድትገኚ ይጠብቃል። የትዳር ጓደኛሽ ደግሞ ስልክ እየደወለልሽ ነው። በዚህ ላይ ታማሚ ወላጅሽን መንከባከብ ይጠበቅብሻል። መምራት የምትፈልጊው እንዲህ ያለ ሕይወት አልነበረም፤ ሆኖም ሁሌ እንዲህ እንደባከንሽ ነው። “ምን ይሻለኛል? ሁሉም የእኔን እርዳታ ይፈልጋሉ” ብለሽ ታስቢያለሽ። ያንቺንም ሆነ የእነሱን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ማሟላት እንደማትችዪ የታወቀ ነው። ታዲያ ለዚህ ሁሉ ጊዜ ማግኘት የምትችዪው እንዴት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ፦ ሙሴ
ሙሴ በጥንት ዘመን በእስራኤል ብቻውን ዳኛ ሆኖ ሲያገለግል የሚጠበቅበትን ነገር እየተወጣ እንደሆነ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አማቱ ‘እያደረግክ ያለኸው ነገር መልካም አይደለም። መድከምህ አይቀርም’ አለው። ከዚያም ሙሴ ፍርድ የመስጠቱን ሥራ ብቃት ላላቸው ሌሎች ሰዎች እንዲሰጥና ሰዎቹ የከበዳቸውን ጉዳይ ብቻ ወደ ሙሴ እንዲያመጡ ሐሳብ አቀረበ። እንዲህ ማድረጉ ምን ውጤት ያስገኛል? የሙሴ አማት ሙሴን እንዲህ ብሎታል፦ “ውጥረቱ ይቀንስልሃል፤ እያንዳንዱም ሰው ተደስቶ ወደ ቤቱ ይሄዳል።”—ዘፀአት 18:17-23
ዴሊና ያደረገችው ነገር
በመግቢያው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ዴሊና ዲስቶኒያ ኒውሮመስኩላር ዲስኦርደር በሚባል በሽታ ትሠቃያለች። በዚህ ላይ ደግሞ የአካል ጉዳተኛ የሆኑ ሦስት ወንድሞቿን ትንከባከባለች። “ስለ ነገ አለመጨነቅና አንድን ነገር ለመሥራት ዛሬ ነገ አለማለት ውጥረት እንደሚቀንሱ ተገንዝቤያለሁ” ብላለች። “ስላለሁበት ሁኔታ ለሌሎች በግልጽ መናገሬ ከባለቤቴም ሆነ ከሌሎች እርዳታ እንዳገኝ በር ከፍቶልኛል። በተጨማሪም በየዕለቱ ጠዋት ጠዋት አትክልቶችን ለመንከባከብ ትንሽ ጊዜ እመድባለሁ፤ ይህም ከፍተኛ እርካታ አምጥቶልኛል።”
“ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው።”—መክብብ 3:1
ምን ማድረግ ትችያለሽ?
ካሉብሽ ተደራራቢ ኃላፊነቶች የተነሳ ሕይወትሽን የምትመሪበት መንገድ ከቁጥጥርሽ ውጭ እንደሆነ ከተሰማሽ የሚከተለውን ለማድረግ ሞክሪ፦
-
ሌሎች እንዲረዱሽ ጠይቂ። ለምሳሌ ያህል፣ ቤት ውስጥ ሊረዱሽ የሚችሉ ልጆች አሉ? አንዳንድ ነገሮችን ሊያግዙሽ የሚችሉ ዘመዶች ወይም ጓደኞች በአቅራቢያሽ አሉ?
-
የምትፈልጊውን ነገር ተናገሪ። ለምሳሌ ያህል፣ አሠሪሽ የሚጠብቅብሽ ነገር ከአቅምሽ በላይ እንደሆነ ከተሰማሽ አነጋግሪው። ይህ ማለት ግን ሥራዬን እለቃለሁ ብለሽ ታስፈራሪዋለሽ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ያሉብሽን ችግሮች በግልጽ ንገሪው። ያለብሽን የሥራ ጫና ሊያቀልልሽ ይችል ይሆናል።
-
በአንድ ሳምንት ውስጥ ሊያጋጥሙሽ የሚችሉ ያንቺን ትኩረት የሚሹ ነገሮችን መዝግቢ። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹን ለሌሎች መስጠት ትችዪ ይሆን?
-
በተጠራሽባቸው ግብዣዎች ሁሉ ላይ መገኘት እንዳለብሽ አይሰማሽ። በግብዣው ላይ መገኘት ጊዜሽን የሚሻማብሽ ወይም ኃይልሽን የሚያሟጥጥብሽ ከሆነ መገኘት እንደማትችዪ ለጋበዘሽ ሰው በአክብሮት ንገሪው።
ዋናው ነጥብ፦ ሁሉን ነገር ራስሽ ለማድረግ የምትሞክሪ ከሆነ አተርፍ ባይ አጉዳይ ልትሆኚ ትችያለሽ።