የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ
ደስተኛ ለመሆን የሚያስፈልጉ ነገሮች
“ደስተኛ የምሆነው ሳገባና ልጅ ስወልድ ነው።”
“ደስተኛ የምሆነው የራሴ ቤት ሲኖረኝ ነው።”
“ደስተኛ የምሆነው የምፈልገውን ሥራ ካገኘሁ ነው።”
“ደስተኛ የምሆነው . . .”
አንተስ እንደዚህ ተሰምቶህ ያውቃል? ግብህ ላይ ከደረስክ ወይም የተመኘኸውን ነገር ካገኘህ በኋላስ ደስታህ ዘላቂ ሆኗል? ወይስ ቀስ በቀስ መክሰም ጀምሯል? ግባችን ላይ ስንደርስ ወይም የተመኘነውን ነገር ስናገኝ ደስተኛ እንደምንሆን የተረጋገጠ ቢሆንም እንዲህ ዓይነቱ ደስታ ቀስ በቀስ እየከሰመ ሊሄድ ይችላል። ዘላቂ ደስታ የሚኖረን ስኬት ወይም አንድ ዓይነት ንብረት ስላገኘን አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንድ ሰው ጤናማ መሆኑ በተለያዩ ነገሮች ላይ የተመካ እንደሆነ ሁሉ እውነተኛ ደስታም የተለያዩ ነገሮች ድምር ውጤት ነው።
ሁላችንም የተለያየን ሰዎች ነን። አንተን የሚያስደስትህ ነገር ሌላውን ሰው ላያስደስተው ይችላል። በተጨማሪም ዕድሜያችን እየጨመረ ሲሄድ ፍላጎታችንም ይለወጣል። ሆኖም ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት አብዛኛውን ጊዜ እውነተኛ ደስታ ከማግኘት ጋር ተያይዘው የሚጠቀሱ አንዳንድ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል ባለን ረክተን መኖር፣ ምቀኝነትን ማስወገድ፣ ለሌሎች ፍቅር ማሳየት እንዲሁም ችግሮችን ተቋቁሞ የማለፍ ችሎታ ማዳበር ለእውነተኛ ደስታ ቁልፍ የሆኑ ነገሮች ናቸው። እንዲህ የምንለው ለምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
1. ባለን ረክተን መኖር
የሰውን ተፈጥሮ በሚገባ ያጠና አንድ ጠቢብ ሰው “ገንዘብ ጥላ ከለላ [ነው]” በማለት ተናግሯል። ይሁን እንጂ “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ ብልጽግናም የሚወድ፣ በትርፉ አይረካም፤ ይህም ከንቱ ነው” ሲልም ጽፏል። (መክብብ 5:10፤ 7:12) ይህ ጠቢብ ሰው ለማስተላለፍ የፈለገው ቁም ነገር ምንድን ነው? ለመኖር ገንዘብ እንደሚያስፈልገን ግልጽ ቢሆንም ስግብግብነት እንዳይጠናወተን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፤ ምክንያቱም ስግብግብ ሰው በምንም ነገር አይረካም! ይህን ሐሳብ የጻፈውና የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰለሞን ብልጽግናና የቅንጦት ኑሮ እውነተኛ ደስታ ያስገኝ እንደሆነ ለማወቅ ሙከራ አድርጎ ነበር። ሰለሞን “ዐይኔ የፈለገውን ሁሉ አልከለከልሁትም፤ ለልቤም ምድራዊ ደስታን አልነፈግሁትም” ብሎ ነበር።—መክብብ 1:13፤ 2:10
ሰለሞን ብዙ ንብረት ያካበተ ሲሆን ትላልቅ ቤቶችን ገንብቷል፤ ውብ መናፈሻዎችንና የውኃ ማጠራቀሚያዎችን ሠርቷል፤ እንዲሁም ብዙ አገልጋዮች ነበሩት። የተመኘውን ነገር ሁሉ አግኝቷል። ታዲያ ከዚህ ምን ትምህርት አገኘ? እንዲህ ዓይነት ሕይወት መምራቱ ለተወሰነ ጊዜ ደስተኛ ቢያደርገውም ደስታው ዘላቂ አልነበረም። “ሁሉም ከንቱ” እንደሆነ ገልጿል፤ እንዲሁም “ምንም ትርፍ አልነበረም” በማለት ጽፏል። ሌላው ቀርቶ ሕይወትን እስከ መጥላት ደርሶ ነበር! (መክብብ 2:11, 17, 18) አዎን፣ ሰለሞን የቅንጦት ሕይወት መምራት የኋላ ኋላ የባዶነትና እርካታ የማጣት ስሜት ሊያስከትል እንደሚችል ተገንዝቧል። *
በዘመናችን የተደረጉ ጥናቶች ጥንት የነበረው ጠቢብ ሰው ከደረሰበት መደምደሚያ ጋር ይስማማሉ? ጆርናል ኦቭ ሀፒነስ ስተዲስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ “አንድ ሰው መሠረታዊ ነገሮችን ለማግኘት የሚበቃ ገቢ እስካለው ድረስ የገቢው መጠን መጨመሩ ለደስታው ያን ያህል አስተዋጽኦ አይኖረውም” በማለት ገልጿል። በእርግጥም ሀብትና ንብረት ለማግኘት የሚሯሯጡ ሰዎች በተለይም ይህን የሚያደርጉት የሥነ ምግባር ደንቦችና እና መንፈሳዊ ነገሮችን ችላ ብለው ከሆነ ደስታ እየራቃቸው እንደሚሄድ ጥናቶች ያሳያሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ አሁን ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ።”—ዕብራውያን 13:5
2. ምቀኝነትን ማስወገድ
ምቀኝነት ሲባል ሌሎች ጥሩ ነገር በማግኘታቸው ቅር መሰኘት ማለት ሲሆን ምቀኛ የሆነ ሰው ያንኑ ነገር ለማግኘት ይቋምጣል። እየተሰራጨ እንደሚሄድ የካንሰር በሽታ ሁሉ ምቀኝነትም የአንድን ሰው ሕይወት ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠረውና የግለሰቡን ደስታ ሊያጠፋበት ይችላል። ታዲያ ምቀኝነት ሥር የሚሰደው እንዴት ነው? ይህ ባሕርይ በውስጣችን እንዳለ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ደግሞስ ይህን ባሕርይ ማስወገድ የምችለው እንዴት ነው?
ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሶሻል ሳይኮሎጂ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ሰዎች በአብዛኛው የሚቀኑት በዕድሜ፣ በልምድ ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ባላቸው ቦታ ከእነሱ ጋር ተቀራራቢ በሆኑ ሰዎች ላይ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ነጋዴ በአንድ ዝነኛ የፊልም ተዋናይ ላይቀና ይችላል። ነገር ግን እንደ እሱ ያለ ነጋዴ ከእሱ ይበልጥ ከተሳካለት ይመቀኘው ይሆናል።
ለምሳሌ ያህል፣ በጥንቷ ፋርስ የነበሩ አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተመቀኙት ንጉሡን ሳይሆን ከእነሱ ይልቅ ብልህ የነበረውን ዳንኤል የተባለ የሥራ ባልደረባቸውን ነው። እነዚህ ሰዎች ምን ያህል ቅናት እንዳንገበገባቸው የሚያሳየው ዳንኤልን ለመግደል እስከ ማሴር መድረሳቸው ነው! ይሁን እንጂ ሴራቸው ከሽፏል። (ዳንኤል 6:1-24) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል፦ “ምቀኝነት ሌሎችን ወደ መጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል። በታሪክ ውስጥ ብዙ ግፍ የተፈጸመው በምቀኝነት የተነሳ መሆኑ ይህንን ያሳያል።” *
ምቀኝነት አንድን ሰው ባሉት ጥሩ ነገሮች እንዳይደሰት ሊያደርገው ይችላል
የምቀኝነት ባሕርይ በውስጥህ እንዳለ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ከእኔ ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ያለ አንድ ሰው ሲሳካለት እደሰታለሁ ወይስ ቅር እሰኛለሁ? ወንድሜ፣ እህቴ፣ አብሮኝ የሚማር ወይም የሚሠራ ሰው በሆነ መንገድ ሳይሳካላቸው ቢቀር አዝናለሁ ወይስ እደሰታለሁ?’ ለዚህ የምትሰጠው መልስ በውስጥህ ምቀኝነት እያቆጠቆጠ መሆን አለመሆኑን ሊጠቁምህ ይችላል። (ዘፍጥረት 26:12-14) ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሶሻል ሳይኮሎጂ እንዲህ ይላል፦ “ምቀኝነት አንድን ሰው ባሉት ጥሩ ነገሮች እንዳይደሰት እንዲሁም በሕይወቱ ላገኛቸው ብዙ መልካም ነገሮች አመስጋኝ እንዳይሆን ሊያደርገው ይችላል። . . . እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ ያለው ሰው ደስታ ሊኖረው አይችልም።”
ትሑት መሆናችን ምቀኝነትን ለማስወገድ ይረዳናል፤ ምክንያቱም ትሕትና ሌሎች ያሏቸውን ችሎታዎችና ጥሩ ባሕርያት እንድናደንቅ ያደርገናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ አድርጋችሁ በትሕትና አስቡ እንጂ በምቀኝነት ወይም በትምክህተኝነት ምንም ነገር አታድርጉ” ይላል።—ፊልጵስዩስ 2:3
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በመካከላችን የፉክክር መንፈስ በማነሳሳትና አንዳችን ሌላውን በመመቅኘት በከንቱ አንመካ።”—ገላትያ 5:26
3. ሰዎችን መውደድ
ሶሻል ሳይኮሎጂ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ሰዎች ከሥራቸው፣ ከገቢያቸው፣ ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ ሌላው ቀርቶ ከጤንነታቸው የበለጠ ለደስታቸው አስተዋጽኦ የሚያደርገው ከሌሎች ጋር የመሠረቱት ወዳጅነት ነው።” በአጭሩ ለመናገር፣ ሰዎችን መውደድና በምላሹም የእነሱን ፍቅር ማግኘት እውነተኛ ደስታ ያስገኛል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “ፍቅር . . . ከሌለኝ ከንቱ ነኝ” በማለት ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 13:2
አንድ ሰው ቀደም ሲል የነበረበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ለሰዎች ፍቅር ማሳየት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ቫኔሳ አባቷ የመጠጥ ሱሰኛ የነበረ ሲሆን ብዙ ጊዜ ጥቃት ያደርስባት ነበር። ቫኔሳ 14 ዓመት ሲሆናት ከቤት ወጥታ የተለያዩ ሰዎች ቤት ተጠግታ መኖር ጀመረች፤ ከዚያም ቤት ለሌላቸው ሰዎች በተዘጋጀ አመቺ ያልሆነ አንድ መጠለያ መኖር የጀመረች ሲሆን በዚያ ሳለች አምላክ እንዲረዳት እንደጸለየች ትዝ ይላታል። ምናልባትም የጸሎቷ መልስ ሳይሆን አይቀርም ከጊዜ በኋላ ከአንድ ቤተሰብ ጋር የመኖር አጋጣሚ አገኘች፤ ይህ ቤተሰብ “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ የሚከተል ነበር። (1 ቆሮንቶስ 13:4) ይህ ቤተሰብ ያደረገላት እርዳታ መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ከተማረችው ነገር ጋር ተዳምሮ ቫኔሳ ከደረሰባት የስሜት ጉዳት ማገገም ቻለች። ቫኔሳ የትምህርት ውጤቷም ቢሆን በጣም እንደተሻሻለ ተናግራለች።
የቫኔሳ የስሜት ጠባሳ አሁንም ቢሆን ሙሉ በሙሉ አልሻረም። ይሁን እንጂ አሁን አስደሳች ትዳር አላት፤ እንዲሁም የሁለት ሴት ልጆች እናት ናት።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ፍቅርን ልበሱ፤ ምክንያቱም ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነው።”—ቆላስይስ 3:14
4. ችግሮችን ተቋቁሞ ማለፍ
በሕይወቱ ችግር የማይገጥመው ማን አለ? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “ለማልቀስ” እንዲሁም “ለሐዘን ጊዜ አለው።” (መክብብ 3:4) እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ችግሩን ለመቋቋም ጥረት ማድረጋችን እንዲሁም ችግሩ ቢኖርም እንኳ አዎንታዊ አመለካከት መያዛችን ጠቃሚ ነው። እስቲ የካሮልን እና የሚልድሬድን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት።
ካሮል እያደር እየተባባሰ በሚሄድ የአከርካሪ በሽታ፣ በስኳር በሽታ፣ በእንቅልፍ ጊዜ በሚከሰት የትንፋሽ መቋረጥ እና የግራ ዓይኗ እንዲታወር ባደረገ አንድ የዓይን በሽታ ትሠቃያለች። ሆኖም እንዲህ ብላለች፦ “ተስፋ ቆርጬ ለረጅም ጊዜ እንዳልቆይ ጥረት አደርጋለሁ። ባለሁበት ሁኔታ የማዝንበት ጊዜ አለ። ከዚያ በኋላ ግን ስለ ራሴ ብቻ ማሰቤን አቆምና ማድረግ ስለምችላቸው ነገሮች አምላክን አመሰግነዋለሁ፤ በተለይም ለሌሎች ሰዎች ጥሩ ነገር ማድረግ መቻሌ አመስጋኝ እንድሆን ያደርገኛል።”
ሚልድሬድም የአርትራይተስ በሽታን፣ የጡት ካንሰርን እና የስኳር በሽታን ጨምሮ በርካታ በሽታዎች አሉባት። ይሁን እንጂ እሷም እንደ ካሮል በችግሮቿ ላይ ላለማተኮር ትጥራለች። እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ለሰዎች ፍቅር ማሳየትን እንዲሁም በሚታመሙበት ጊዜ እነሱን ማጽናናትን ተምሬያለሁ፤ ይህ ደግሞ እኔንም ይጠቅመኛል። እንዲያውም ሌሎችን በማጽናናበት ወቅት የራሴን ሕመም እንደምረሳው ተገንዝቤያለሁ።”
እርግጥ ነው ሁለቱም ሴቶች ለሕመማቸው ጥሩ ሕክምና ማግኘት የሚፈልጉ ቢሆንም ከሕክምናው የበለጠ አስፈላጊ እንደሆነ የሚሰማቸው አመለካከታቸውና ጊዜያቸውን የሚጠቀሙበት መንገድ ነው። በዚህም የተነሳ ማንም ሊነጥቃቸው የማይችል ውስጣዊ ደስታ አግኝተዋል። በተጨማሪም የብዙዎችን ፍቅር አትርፈዋል፤ እንዲሁም የተለያዩ መከራዎች የሚደርስባቸው ሰዎች እነሱን በማየት ይጽናናሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ፈተናን በጽናት ተቋቁሞ የሚኖር ሰው ደስተኛ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ሰው ተቀባይነት በሚያገኝበት ጊዜ . . . የሕይወት አክሊል ይቀበላል።”—ያዕቆብ 1:12
መጽሐፍ ቅዱስ፣ በውስጡ ያለውን ጥበብ የሚከተሉ ሰዎችን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፦ “ጥበብን የሚያገኙ ሰዎች ደስ ይበላቸው፤ ምክንያቱም ጥበብ እውነተኛ ሕይወትን ትሰጣቸዋለች።” (ምሳሌ 3:13-18 የ1980 ትርጉም) ታዲያ አንተው ራስህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘውን ጥበብ በሥራ ላይ በማዋል የዚህን ሐሳብ እውነተኝነት ለምን አትመለከትም? ደግሞም የዚህ ቅዱስ መጽሐፍ ባለቤት ‘ደስተኛ የሆነው አምላክ’ ተብሎ ተጠርቷል፤ አንተም ደስተኛ እንድትሆን ይፈልጋል።—1 ጢሞቴዎስ 1:11
^ አን.11 ሰሎሞን ያካሄደው ሙከራ በመክብብ 2:1-11 ላይ ይገኛል። ።
^ አን.17 ለዚህ በዋነኝነት እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችለው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተፈጸመው ግፍ ነው። “የካህናት አለቆች” ኢየሱስን እንዲገደል “አሳልፈው የሰጡት በቅናት ተነሳስተው እንደሆነ” ማርቆስ 15:10 ይናገራል።