ንድፍ አውጪ አለው?
የፈረስ እግር
ፈረሶች በሰዓት 50 ኪሎ ሜትር ያህል መጋለብ ይችላሉ። ይህ ከፍተኛ ኃይል የሚጠይቅ ሥራ ቢሆንም ሲጋልቡ የሚያወጡት ኃይል በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ትንሽ ነው። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ሚስጥሩ ያለው በፈረሶቹ እግር ላይ ነው።
እስቲ አንድ ፈረስ ሲጋልብ ምን እንደሚከናወን እንመልከት። የመለጠጥ ባሕርይ ያላቸው የፈረሱ የእግር ጡንቻዎችና ጅማቶች፣ ፈረሱ እግሩን መሬት ላይ በሚያሳርፍበት ወቅት ኃይል ይሰበስባሉ፤ ከዚያም እንደ ስፕሪንግ ተስፈንጥረው ሲመለሱ የሰበሰቡትን ኃይል ስለሚለቅቁ ፈረሱ ወደ ፊት እንዲሄድ የሚገፋው ኃይል ያገኛል።
በተጨማሪም አንድ ፈረስ በሚጋልብበት ጊዜ በእግሮቹ ላይ ከፍተኛ ንዝረት ይፈጠራል፤ ይህ ደግሞ ጅማቶቹን ሊጎዳቸው ይችላል። ሆኖም በእግሮቹ ላይ ያሉት ጡንቻዎች ንዝረቱን ውጠው የማስቀረት ችሎታ አላቸው። ተመራማሪዎች የፈረስ እግር “በዓይነቱ ልዩ የሆነ ንድፍ” እንዳለው የገለጹ ሲሆን ይህ ንድፍ ፈረሱ ፍጥነትና ጥንካሬ እንዲኖረው አስችሎታል።
የምሕንድስና ባለሙያዎች የፈረስ እግርን ንድፍ በመኮረጅ ባለአራት እግር ሮቦት ለመሥራት እየሞከሩ ነው። ይሁንና በማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም ሥር የሚገኘው በተፈጥሮ ላይ የሚታየውን ንድፍ በመኮረጅ ሮቦቶችን የሚሠራው ክፍል እንደገለጸው የፈረስ እግር ንድፍ የተሠራበት መንገድ ውስብስብ በመሆኑ አሁን ባሉት ጥሬ ዕቃዎችና የምሕንድስና እውቀት ንድፉን አስመስሎ መሥራት ከባድ ነው።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? በፈረስ እግር ላይ የሚታየው ንድፍ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?