በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ጀርመን

በ2012 አንድ ከፍተኛ የጀርመን ፍርድ ቤት በሰጠው ብያኔ መሠረት እንደ አንድ ተቋም በመንግሥት ከተመዘገበ ቤተ ክርስቲያን በይፋ የለቀቀ አንድ ሰው ከዚያ በኋላ የዚያ ሃይማኖታዊ ማኅበረሰብ አባል እንደሆነ መቀጠል አይችልም። ቀደም ሲል ከቤተ ክርስቲያናቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማቋረጣቸው ምክንያት የቤተ ክርስቲያን ግብር መክፈል ያቆሙ ሆኖም ለአምልኮ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ካቶሊኮች በቅዱስ ቁርባን ከመካፈል፣ የኑዛዜ አገልግሎት ከማግኘት፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የኃላፊነት ቦታና አልፎ ተርፎም የቀብር ቦታ ከማግኘት ሊታገዱ ይችላሉ።

ዓለም

በዓለም ሃይማኖቶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው ከሆነ “ከሃይማኖት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው” የተናገሩ ሰዎች ቁጥር በአሁኑ ጊዜ 1.1 ቢሊዮን ደርሷል፤ እነዚህ ሰዎች የግድ አምላክ የለሽ ናቸው ማለት አይደለም። የእነዚህ ሰዎች ቁጥር 2.2 ቢሊዮን ከሆኑት ክርስቲያኖችና 1.6 ቢሊዮን ከሆኑት ሙስሊሞች ቀጥሎ በሦስተኝነት ደረጃ ላይ ይገኛል። የሂንዱ እምነት ተከታዮች ደግሞ 1 ቢሊዮን በመሆን የአራተኝነትን ደረጃ ይዘዋል።

ጃፓን

የጃፓን ሳይንቲስቶች እንደገለጹት ከሆነ ምስጋና መቀበል “አድናቆትን ከማግኘት ጋር የተያያዙ መልእክቶችን የሚቀበለውን የአእምሮ ክፍል ያነቃቃል።” ይህም “የደስታ ስሜት” እንዲፈጠር ያደርጋል። ይህ ግኝት ‘አንድን ሰው ለበለጠ ሥራ ለማነሳሳት ከሚያስችሉ ግሩም መንገዶች አንዱ ግለሰቡ ላደረገው ነገር ማመስገን ነው’ የሚለውን አባባል ትክክለኝነት የሚያረጋግጥ ይመስላል።

ቦሊቪያ

በ2012 ቦሊቪያ ብሔራዊ የሕዝብ ቆጠራ አካሂዳ ነበር። በቆጠራው ላይ ምንም ዓይነት ስህተት እንዳይፈጠር ሲባል መጠይቁ በሚቀርብበት ዕለት ሕዝቡ ከቤቱ እንዳይወጣ ተደርጓል። በተጨማሪም የግል መኪኖች እንዳይንቀሳቀሱ ታግደው ነበር፤ እንዲሁም ድንበሮች የተዘጉ ከመሆኑም በላይ የአልኮል መጠጥ መጠጣት ተከልክሎ ነበር።

ጣሊያን

አንድ ጥናት እንዳሳየው ከሆነ ጣሊያኖች በቀን ውስጥ በአማካይ ከልጆቻቸው ጋር በመጫወት የሚያሳልፉት ጊዜ 15 ደቂቃ ነው። “በጨዋታ አማካኝነት ትምህርት ማስተላለፍ እንደሚቻል የሚሰማው ከ5 ወላጆች አንዱ ብቻ” እንደሆነ ላ ሪፐብሊካ የተሰኘው የጣሊያን ጋዜጣ ገልጿል። ወላጆች በጨዋታ አማካኝነት ልጆቻቸው ነገሮችን በዓይነ ሕሊናቸው የመሳል ችሎታቸው እያደገ እንዲሄድ ብሎም “ሕግ አክባሪ” እንዲሆኑ መርዳት እንደሚችሉ የሰሌዳ ጨዋታዎች ፕሮፌሽናል ንድፍ አውጪ የሆነው አንድሪያ አንጂዮሊኖ ተናግሯል።