ወጪህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?
ማስታወቂያዎች ከሚያሳድሩብን ተጽዕኖ በተጨማሪ ስሜታችንና ልማዳችን አላግባብ ገንዘብ እንድናወጣ ሊያደርጉን ይችላሉ። ወጪህን ለመቆጣጠር የሚረዱህ ስድስት የመፍትሔ ሐሳቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል።
ያማረህን ሁሉ ከመግዛት ተቆጠብ። ገበያ መውጣት ወይም በቅናሽ ዋጋ የሚገኙ ዕቃዎችን መግዛት ያስደስትሃል? ከሆነ ያየኸውን ሁሉ ለመግዛት ልትፈተን ትችላለህ። አንድ ነገር ከመግዛትህ በፊት ቆም ብለህ ማሰብህ ይህንን ስሜት ለመቋቋም ይረዳሃል፤ ለመግዛት የምታወጣውን ገንዘብ እንዲሁም የዕቃው ባለንብረት መሆን ብሎም ለዕቃው ጥገናና እንክብካቤ ማድረግ ምን እንደሚጠይቅብህ አርቀህ አስብ። ከዚህ በፊት ያማረህን በመግዛትህ የተቆጨህባቸውን ጊዜያት አስብ። የመጨረሻ ውሳኔ ከማድረግህ በፊት የማሰቢያ ጊዜ ይኑርህ።
ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ ስትል ብቻ አትግዛ። ገበያ መውጣት የተሰማህን መጥፎ ስሜት ለጊዜው ሊያስታግሥልህ ይችላል። መጥፎ ስሜቱ ተመልሶ ሲመጣ ግን ዕቃ በመግዛት ከመጥፎ ስሜትህ ለመገላገል ያለህ ፍላጎት ይጨምራል። ዕቃዎችን በመግዛት ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ ሊያበረታቱህ የሚችሉ ወዳጆችን ፈልግ፤ ወይም በእግር እንደመጓዝ ያሉ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን አድርግ።
ለመዝናናት ብለህ አትሸምት። በሚስብ ሁኔታ የተዘጋጁ የገበያ አዳራሾች መሸመትን አዝናኝ እንዲሆን አድርገዋል። ወደ ገበያ አዳራሾች የምትሄደው ወይም ኢንተርኔት የምትቃኘው ለመዝናናት ያህል ብቻ ይሆናል። ይሁንና አብዛኞቹ የምታያቸው ነገሮች የመግዛት ፍላጎትህን ለመቀስቀስ ተብለው የተዘጋጁ መሆናቸውን ማወቅ ይኖርብሃል። ያሰብከውን ነገር ብቻ ለመግዛት ጥረት አድርግ፤ በዚህ ውሳኔህ ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።
አብረህ የምትውላቸውን ሰዎች ምረጥ። የጓደኞችህ አኗኗር ወይም የሚያወሩት ነገር በፍላጎትህ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። ከጓደኞችህ እኩል ለመሆን ስትል ከአቅምህ በላይ ገንዘብ የምታወጣ ከሆነ ለገንዘብና ለቁሳዊ ነገሮች ብዙ ግምት የማይሰጡ ጓደኞችን መምረጥ ይሻልሃል።
በዱቤ ስትገዛ ጥንቃቄ አድርግ። ክሬዲት ካርድ ወይም ዱቤ ዕቃ መግዛትን ቀላል ቢያደርግልህም በኋላ ላይ የሚመጣውን ጣጣ እንዳታገናዝብ እንቅፋት ሊሆንብህ ይችላል። የወሩን ዕዳህን በዚያው ወር ውስጥ ከፍለህ ለመጨረስ ሞክር። የክሬዲት ካርድህ ኩባንያ ምን ያህል ወለድና የአገልግሎት ክፍያ እንደሚጠይቅ እወቅ፤ ከዚያም አነስተኛ ክፍያ የሚጠይቁ ድርጅቶችን አፈላልግ። ከፍተኛ ክፍያ የሚጠይቁና ለአንተ ምንም ፋይዳ የሌላቸውን ጥቅማ ጥቅሞች የሚሰጡ ውድ ካርዶችን ከመጠቀም ተጠንቀቅ። ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ዕቃዎችን በዱቤ ከመግዛት ይልቅ ገንዘቡን አጠራቅመህ እጅ በእጅ ከፍለህ ግዛ።
የገንዘብ አቅምህን እወቅ። የገንዘብ አቅምህ ምን ያህል እንደሆነ በእርግጠኝነት ካላወቅክ ከአቅምህ በላይ ልታወጣ ትችላለህ። ገቢና ወጪህን በየጊዜው መዝግበህ በመያዝ የገንዘብ አቅምህን እወቅ። ገቢህንና ባለፉት ወራት የነበሩህን ወጪዎች መሠረት በማድረግ ወርኃዊ ባጀት አውጣ። ወጪዎችህን ተከታትለህ በመመዝገብ ከባጀትህ ጋር አስተያይ። ከገንዘብ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ለመረዳት የቸገረህ ጉዳይ ካለ የምታምነው ወዳጅህ እንዲረዳህ ጠይቀው።