ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና
በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ልጆቻችሁ ተግሣጽ መስጠት የምትችሉት እንዴት ነው?
ተፈታታኙ ነገር
ልጆቻችሁ ከምሽቱ 3 ሰዓት ላይ ሞባይሎቻቸውን እንዲዘጉ መመሪያ የሰጣችኋቸው ቢሆንም ሴት ልጃችሁ በዚህ ሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ ከእኩለ ሌሊት በኋላ የጽሑፍ መልእክት ስትለዋወጥ አግኝታችኋታል። ወንድ ልጃችሁ ማታ ከተወሰነለት ሰዓት በፊት ቤት እንዲገባ ተነግሮታል፤ ሆኖም ማታ ቤት የገባው ሰዓት አሳልፎ ሲሆን ይህ ሁለተኛ ጊዜው ነው።
ልጆቻችሁ ስህተት እንደሠሩ የታወቀ ነው። ይሁንና በመጀመሪያ መመሪያችሁን የጣሱት ለምን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋችኋል። ሁኔታውን ለማወቅ ስትጥሩ በዓመፅ የተደረገ የሚመስለው ነገር፣ ሆን ተብሎ የተደረገ እንዳልሆነ ትገነዘቡ ይሆናል።
ምክንያቱ ምንድን ነው?
ግልጽ ያልሆነ ገደብ። በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ አንዳንድ ወጣቶች ደንቦችን እስከ ምን ድረስ ቢጥሱ ከቅጣት ማምለጥ እንደሚችሉ ማየት ይፈልጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወላጅ አንድ ዓይነት ጥፋት ምን መዘዝ እንደሚያስከትል ከተናገረ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ወላጃቸው የተናገረውን ይፈጽመው እንደሆነና እንዳልሆነ ለማየት ሲሉ ደንቡን ለመጣስ ይፈተኑ ይሆናል። ታዲያ እንዲህ ዓይነቶቹ ልጆች የለየላቸው ዓመፀኞች እየሆኑ ነው ማለት ነው? ላይሆን ይችላል። እውነታው እንደሚያሳየው፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ወላጆቻቸው የተናገሩትን ነገር በመፈጸም ረገድ ወጥ የሆነ አቋም ከሌላቸው ወይም ደንቦቹ ግልጽ ካልሆኑላቸው በአብዛኛው የተሰጣቸውን መመሪያ በቁም ነገር አይመለከቱትም።
ግትርነት። አንዳንድ ወላጆች ስፍር ቁጥር የሌላቸውን መመሪያዎች በማውጣት በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻቸውን ለመቆጣጠር ይሞክራሉ። ልጆቹ ሳይታዘዙ ሲቀሩ ወላጆቻቸው ይናደዱና ተጨማሪ ደንቦችን ያወጣሉ። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ እንዲህ ማድረጉ ሁኔታውን ጭራሽ ያባብሰዋል። ፓረንት/ቲን ብሬክስሩ የተሰኘው መጽሐፍ “ቁጥጥራችሁን ለማጥበቅ በሞከራችሁ መጠን በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ለመታዘዝ ይበልጥ አሻፈረኝ እያለ ይሄዳል” በማለት ይገልጻል፤ አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ቁጥጥር በማብዛት ሕግ ለማስከበር የሚደረገው ጥረት ቀዝቅዞ የደረቀ ቅቤን በለስላሳ ዳቦ ላይ ለመቀባት ከመሞከር ጋር ይመሳሰላል፤ ጉልበት ተጠቅማችሁ ለመቀባት ብትሞክሩ ዳቦው ይቆራረሳል እንጂ ቅቤው አይቀባላችሁም።”
ተገቢ የሆነ ተግሣጽ ሊጠቅም ይችላል። “ተግሣጽ” “ከቅጣት” የተለየ ነው፤ ቅጣት አንድን ሰው ማሠቃየት የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ተግሣጽ ግን መሠረታዊ ትርጉሙ ማስተማር ነው። ታዲያ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙት ልጆቻችሁ ያወጣችሁትን መመሪያ እንዲያከብሩ ማስተማር የምትችሉት እንዴት ነው?
ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
ሐሳባችሁን በግልጽ ተናገሩ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ከእነሱ የሚጠበቀው ነገር ምን እንደሆነና አለመታዘዝ የሚያስከትለውን መዘዝ በግልጽ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ገላትያ 6:7
የመፍትሔ ሐሳብ፦ የቤታችሁን መመሪያ በዝርዝር ጻፉ። ከዚያም እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘ያወጣኋቸው መመሪያዎች በጣም በዝተዋል ወይስ አንሰዋል? አንዳንዶቹ ከአሁን በኋላ የማያስፈልጉ ናቸው? በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙት ልጆቼ ኃላፊነት እንደሚሰማቸው በተግባር እያሳዩ በመሆኑ ካወጣኋቸው መመሪያዎች ጋር በተያያዘ አንዳንድ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልገኝ ይሆን?’
ወጥ አቋም ይኑራችሁ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችሁ በአንድ ወቅት ጥፋት ሠርተው በዝምታ ካለፋችኋቸው በኋላ በሌላ ጊዜ ያንኑ ጥፋት ደግመው ሲሠሩ የምትገሥጿቸው ከሆነ ግራ ሊጋቡ ይችላሉ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ማቴዎስ 5:37
የመፍትሔ ሐሳብ፦ የምትሰጡት ተግሣጽ ከተፈጸመው ጥፋት ጋር የሚጣጣም እንዲሆን ጥረት አድርጉ። ለምሳሌ ያህል፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጃችሁ ከ1 ሰዓት በፊት ቤት እንዲገባ መመሪያ ተሰጥቶት እያለ የተወሰነለትን ሰዓት ቢያሳልፍ ከ12 ወይም ከ11 ሰዓት በፊት ቤት እንዲገባ አዲስ መመሪያ በማውጣት የሠራው ጥፋት ያስከተለውን መዘዝ እንዲቀምስ ማድረጉ ይበልጥ ተስማሚ ይሆናል።
ምክንያታዊ ሁኑ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ኃላፊነት የሚሰማው መሆኑን በተግባር ካሳየ ተጨማሪ ነፃነት በመስጠት ምክንያታዊ ወላጆች እንደሆናችሁ አሳዩ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ፊልጵስዩስ 4:5
የመፍትሔ ሐሳብ፦ የምታወጧቸውን መመሪያዎች በተመለከተ ከልጃችሁ ጋር ቁጭ ብላችሁ ተወያዩ። አልፎ ተርፎም ለአንዳንድ ጥፋቶች የሚሰጠው ተግሣጽ ምን መሆን እንዳለበት የራሱን አስተያየት እንዲሰጥ ማድረግ ትችላላችሁ። ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ሆነው ላወጧቸው መመሪያዎች የመታዘዝ አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው።
የልጃችሁን ባሕርይ ቅረጹ። ግባችሁ ሊሆን የሚገባው፣ ልጃችሁ እንዲሁ ትእዛዝ የሚያከብር እንዲሆን ማድረግ ሳይሆን ጥሩ ሕሊና ማለትም በውስጡ ትክክልና ስህተት የሆነውን የመለየት ችሎታ እንዲያዳብር መርዳት ነው። (“ልጃችሁን በመልካም ባሕርያት አንጹ” የሚለውን ሣጥን ተመልከቱ።)—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ 1 ጴጥሮስ 3:16
የመፍትሔ ሐሳብ፦ ይህን ለማድረግ መጽሐፍ ቅዱስን መሣሪያ አድርጋችሁ ተጠቀሙበት። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ማስተዋል የሚያስገኝ ተግሣጽ’ የያዘ መጽሐፍ ሲሆን በውስጡ የሚገኘው ጥበብም “ብስለት ለሌላቸው አስተዋይነትን፣ በዕድሜ ለጋ ለሆኑት ዕውቀትንና ልባምነትን” ሊያጎናጽፍ ይችላል።—ምሳሌ 1:1-4