ከዓለም አካባቢ
ዓለም
ረሃብን ለማጥፋት መፍትሔው በቂ እህል ማምረት ብቻ አይደለም። በአሁኑ ጊዜ ገበሬዎች ለ12 ቢሊዮን ሕዝብ ማለትም አሁን ምድራችን ላይ ካሉት ሰዎች በተጨማሪ ለ5 ቢሊዮን ሕዝብ የሚበቃ ምግብ እያመረቱ እንዳሉ ይገመታል። በመሆኑም ችግሩ በዋነኝነት ከገንዘብ አቅም፣ ከስርጭትና ከብክነት ጋር የተያያዘ ነው።
ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ
ቃለ መጠየቅ ከተደረገላቸው የፋይናንስ ዘርፍ ባለሙያዎች መካከል አንድ አራተኛ (24 በመቶ) የሚሆኑት “ስኬታማ ለመሆን ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ወይም ሕጋዊ ያልሆነ ድርጊት መፈጸም ሊኖርባቸው እንደሚችል” ያምናሉ። አሥራ ስድስት በመቶ የሚሆኑት “ማምለጥ የሚችሉበት መንገድ ካለ” ወንጀል ከመሥራት እንደማይመለሱ አምነዋል።
አርጀንቲና
በአርጀንቲና ከ5 መምህራን መካከል 3ቱ በውጥረትና በሥራ ገበታቸው ላይ በሚደርስባቸው የዓመፅ ድርጊት የተነሳ ፈቃድ ጠይቀው ከሥራ ይቀራሉ።
ደቡብ ኮሪያ
በደቡብ ኮሪያ ቤተሰብ ካላቸው ይልቅ ለብቻቸው የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጣም እየጨመረ እንደሚሄድ ይታሰባል።
ቻይና
ከቻይና ከተሞች መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት በ2016 ተፈጻሚ የሚሆነውን መንግሥት ያወጣውን አዲስ የከተሞች የአየር ጥራት ደረጃ ማሟላት እንደማይችሉ ይታሰባል። በተጨማሪም ከአብዛኞቹ ጉድጓዶች የሚወጣው የከርሰ ምድር ውኃ “መጥፎ ወይም ከልክ በላይ መጥፎ” የሚል የጥራት ደረጃ ተሰጥቶታል።