ግብ አውጣ
መማርህ የት እንደሚያደርስህ የምታውቅ ከሆነ ትምህርት ጠቃሚ ብቻ ሳይሆን አስደሳችም ይሆንልሃል።
ግብ ሳይኖርህ እንዲሁ መማር የመጨረሻ መስመር በሌለው የሩጫ መወዳደሪያ ቦታ ላይ ከመሮጥ ጋር ይመሳሰላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ እናገኛለን፦ “እኔ መድረሻውን እንደማያውቅ ሰው አልሮጥም፤ ቡጢዬን የምሰነዝረውም አየር ለመምታት አይደለም።” (1 ቆሮንቶስ 9:26) ግብ ካለህ በግብህ ላይ የምታተኩር ከመሆኑም ሌላ ወደ ሥራው ዓለም የምታደርገው ሽግግር ቀላል ይሆንልሃል። ታዲያ ግብ ማውጣት የምትችለው እንዴት ነው?
‘ራሴን ችዬ ለመኖር እቅድ ማውጣት የምችለው እንዴት ነው?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። እንዲህ ያለ እቅድ ለማውጣት ዛሬ ነገ አትበል። ከዚህ ይልቅ ቀደም ብለህ እቅድ አውጣ። ይህን ማድረግህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? እስቲ ሁኔታውን ከዚህ አንጻር ለመመልከት ሞክር፦ ጉዞ ለማድረግ ብትፈልግ በመጀመሪያ የምትሄድበትን ቦታ መወሰን ያስፈልግሃል። ከዚያ በኋላ ካርታ በመመልከት ወደዚያ መሄድ የምትችልበትን ከሁሉ የተሻለ መንገድ ትመርጣለህ። ከትምህርትህ ጋር በተያያዘም የምታደርገው ነገር ተመሳሳይ ነው። ወደፊት በምን ዓይነት የሙያ መስክ መሰማራት እንደምትፈልግ አስብና ወደ ግብህ ለመድረስ የሚረዱህን ትምህርቶች ምረጥ።
መጠንቀቅ ያለብህ ነገር፦ ብዙ ወጣቶች በጣም የሚወዱትን ነገር ብቻ ለመሥራት ያስባሉ፤ ለምሳሌ ያህል በሙዚቀኝነት ሙያ ለመሠማራት ካሰቡ ከዚያ ውጪ ሌላ ምንም ዓይነት ሥራ መሥራት ጨርሶ አይታያቸውም። ታዲያ የሚሻለው ምን ማድረግ ነው?
ያሉህን ችሎታዎች ከግምት አስገባ፦ ለምሳሌ ያህል፣ ለሌሎች አገልግሎት ከመስጠት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን መሥራት ያስደስትሃል? በሒሳብ፣ በገንዘብ አያያዝ ወይም ዕቃዎችን በመጠገን ረገድ አሊያም በመካኒክነት ጥሩ ችሎታ አለህ?
ያሉህን አማራጮች ከግምት አስገባ፦ አንተ ካሉህ ችሎታዎች ጋር የሚሄዱት የትኞቹ ሙያዎች ናቸው? ትኩረትህን አንተ “በምታልመው” ሥራ ላይ ብቻ ከማድረግ ይልቅ ብዙ አማራጮችን አስብ። ደግሞም ተግባራዊ ሊሆን የሚችለውን ነገር ለማሰብ ሞክር። ለምሳሌ ያህል፣ ድንገት ወደ ሌላ ቦታ መዛወር ቢያስፈልግህ ልትሠማራበት የምትፈልገው የሥራ መስክ በሌሎችም ቦታዎች ሊገኝ የሚችል ነው? ለሙያው የሚያስፈልግህ ሥልጠና ከባድ ዕዳ ውስጥ የሚያስገባህ ነው?
ያሉህን አጋጣሚዎች ከግምት አስገባ፦ ልትሠማራበት የምትፈልገውን ሙያ ከወሰንክ በኋላ በአካባቢህ በዚህ ሙያ ምን ያህል የሥራ ዕድል እንዳለ ለማጥናት ሞክር። ወደፊት በዚህ ሙያ ሊቀጥሩህ የሚችሉ ሰዎች ታውቃለህ? ከሆነ ከእነሱ ጋር በመሥራት የሙያ ሥልጠና እንድታገኝ ይፈቅዱልሃል? በአካባቢህ የሙያ ሥልጠና የሚሰጥባቸው ኮርሶች ይኖራሉ?
ጠቃሚ ምክር፦ ወላጆችህን፣ አስተማሪዎችህንና ወዳጆችህ የሆኑ ሌሎች ትላልቅ ሰዎችን አማክር። በአካባቢህ በሚታተሙ ጋዜጦችና በኢንተርኔት አማካኝነት መረጃ ለማግኘት ጥረት አድርግ።
ዋናው ነጥብ፦ ግብ ካለህ ትምህርትህ አንድ አቅጣጫ የተከተለና ዓላማ ያለው ይሆናል።
አሁኑኑ ለምን አትጀምርም? ከላይ የቀረቡትን ሦስት ነጥቦች አሁን፣ ገና በትምህርት ላይ ሳለህ አስብባቸው። ግቦችህን በጽሑፍ አስፍር፤ እንዲሁም ከወላጆችህ ጋር ተወያይባቸው።