የወላጅነት ኃላፊነትህን በሚገባ መወጣት
የተወለደልህን ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ያቀፍክበት ጊዜ ትዝ ይልሃል?
ብዙም ሳይቆይ ልጅህ ለብዙ ዓመታት በቀጣይነት መመሪያ ማግኘት እንደሚያስፈልገው ስትገነዘብ ሁኔታው በጣም አሳስቦህ ይሆናል። ከባድ ኃላፊነት የተጣለብህ መሆኑን ለመገንዘብ ብዙ ጊዜ አልፈጀብህም።
ወላጅ መሆን የሚያስከትለው ኃላፊነት ምንጊዜም ተፈታታኝ እንደሆነ የታወቀ ቢሆንም በዛሬው ጊዜ ደግሞ ይባስ ከባድ ሆኗል። ለምን? ዓለም አንተ ልጅ ከነበርክበት ጊዜ ይልቅ አስቸጋሪ ስለሆነ ነው። ልጆች የሚደቀኑባቸው አንዳንዶቹ የሥነ ምግባር ፈተናዎች፣ ለምሳሌ ኢንተርኔትን ሲጠቀሙ የሚያጋጥሟቸው ፈታኝ ሁኔታዎች ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት የማይታወቁ ነገሮች ነበሩ።
ልጅህ በአሁኑ ጊዜ ባለው ዓለም ውስጥ ያሉትን የሥነ ምግባር አደጋዎች እንዲቋቋም ልትረዳው የምትችለው እንዴት ነው? ከዚህ ቀጥሎ ሦስት የመፍትሔ ሐሳቦች ቀርበዋል።
1 የሥነ ምግባር መሥፈርቶችህን ግልጽ አድርግ።
ልጆች እያደጉ ሲሄዱ ሥነ ምግባርን በተመለከተ የተሳሳተ መረጃ ይዥጎደጎድባቸዋል፤ አንዳንዱ መረጃ የሚመጣው ከእኩዮቻቸው ሲሆን አብዛኛው ደግሞ ከመገናኛ ብዙኃን ነው። በተለይ ልጆች ወደ አሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ሲገቡ እንዲህ ዓይነቶቹ መጥፎ ተጽዕኖዎች ይበልጥ ጫና ያሳድሩባቸዋል። ይሁን እንጂ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ብዙ ልጆች በሕይወታቸው ውስጥ ትልልቅ ውሳኔዎችን ሲያደርጉ ለእኩዮቻቸው ሳይሆን ለወላጆቻቸው አመለካከት ትልቅ ግምት ይሰጣሉ።
ምን ማድረግ ትችላለህ? በጥንቷ እስራኤል የነበሩ ወላጆች በልጆቻቸው ልብ ውስጥ ትክክለኛ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን መቅረጽ እንዲችሉ ከልጆቻቸው ጋር በየጊዜው እንዲነጋገሩ ማበረታቻ ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘዳግም 6:6, 7) አንተም ከልጅህ ጋር እንዲህ ማድረግ ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መመሪያዎች የምትመራ ከሆነ እነዚህን መመሪያዎች በጥብቅ መከተል ከሁሉ የተሻለ ሕይወት መምራት እንደሚያስችል የሚሰማህ ለምን እንደሆነ ለልጅህ ንገረው።
2 ልጅህ ድርጊቱ ምን መዘዝ እንደሚያስከትልበት እንዲገነዘብ እርዳው።
መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል” በማለት ይናገራል። (ገላትያ 6:7) የምክንያትና የውጤት መሠረታዊ ሥርዓት በሁሉም የሕይወታችን ዘርፍ ሊታይ የሚችል ነገር ነው። እስቲ ስለ ራስህ የልጅነት ዘመን መለስ ብለህ አስብ። ወላጆችህ ያደረግከው ነገር ያስከተለውን መዘዝ አንተ ራስህ እንድትወጣው በማድረጋቸው የማይረሳ ትምህርት አግኝተህ እንደነበር ጥርጥር የለውም።
ምን ማድረግ ትችላለህ? እውነተኛ የሕይወት ተሞክሮዎችን ተጠቅመህ የተሳሳተ ጎዳና የተከተሉ ሰዎች የደረሰባቸውን ጉዳት፣ ትክክለኛውን ነገር ያደረጉ ሰዎች ደግሞ ያገኙትን ጥቅም ለልጅህ አስረዳው። (ሉቃስ 17:31, 32፤ ዕብራውያን 13:7) በተጨማሪም ድርጊቱ ከሚያስከትልበት መዘዝ እንዲያመልጥ አታድርግ። ለምሳሌ ልጅህ በጥንቃቄ ጉድለት የሌላ ልጅ መጫወቻ ሰበረ እንበል። ከራሱ መጫወቻዎች ውስጥ አንዱን እንዲሰጠው ልታደርግ ትችላለህ። በዚህ ጊዜ ልጅህ የሌሎችን ዕቃ በጥንቃቄ መያዝ እንዳለበት በቀላሉ የማይረሳ ትምህርት ያገኛል።
3 ጥሩ ጠባይ እንዲያዳብር እርዳው።
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ሕፃን እንኳ ጠባዩ ንጹሕና ቅን መሆኑ፣ ከአድራጎቱ ይታወቃል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 20:11) ልጆች እያደጉ ሲሄዱ ከሌሎች ተለይተው እንዲታወቁ የሚያደርጓቸውን ባሕርያት ያዳብራሉ። የሚያሳዝነው አንዳንድ ልጆች የሚታወቁት በመጥፎ ጠባያቸው ነው። (መዝሙር 58:3) ሌሎች ደግሞ የሚያስመሰግን ጥሩ ስም ያተርፋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ወጣቱን ጢሞቴዎስን አስመልክቶ “ስለ እናንተ ጉዳይ ከልብ የሚጨነቅ እንደ እሱ ያለ በጎ አመለካከት ያለው ሌላ ማንም የለኝም” በማለት ለአንድ ጉባኤ ጽፎ ነበር።—ፊልጵስዩስ 2:20
ምን ማድረግ ትችላለህ? ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ ልጅህ ያደረገው ነገር የሚያስከትልበትን መዘዝ የመቀበልን አስፈላጊነት እንዲገነዘብ ከማድረግህ በተጨማሪ በምን ዓይነት ባሕርይ መታወቅ እንደሚፈልግ እንዲያስብበት እርዳው። ወጣቶች ተፈታታኝ ሁኔታ ሲጋረጥባቸው ራሳቸውን እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ጥሩ ውሳኔዎችን ማድረግ ሊማሩ ይችላሉ፦
-
ምን ዓይነት ሰው መሆን እፈልጋለሁ?—ቆላስይስ 3:10
-
እኔ መሆን የምፈልገው ዓይነት ሰው፣ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢገጥመው ምን ያደርጋል?—ምሳሌ 10:1
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ካደረጉት ነገር የተነሳ ጥሩ ወይም መጥፎ ሰዎች ተብለው የተገለጹ የበርካታ ወንዶችንና ሴቶችን የሕይወት ታሪክ ይዟል። (1 ቆሮንቶስ 10:11፤ ያዕቆብ 5:10, 11) እነዚህን ምሳሌዎች በመጠቀም ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆችህ ጥሩ ባሕርያትን እንዲያዳብሩ እርዳቸው።
የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጇቸው ጽሑፎች፣ በቤተሰብህ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች እንዴት በሥራ ማዋል እንደምትችልና ልጆችህም ይህንኑ አርዓያ እንዲከተሉ ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ሊረዱህ ይችላሉ።