ንድፍ አውጪ አለው?
እጅብ ብለው የሚዋኙ ዓሦች
በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች በመኪና አደጋ የሚሞቱ ሲሆን ወደ 50 ሚሊዮን ገደማ በሚሆኑም ላይ የአካል ጉዳት ይደርሳል። በሌላ በኩል ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዓሦች እጅብ ብለው የሚዋኙ ቢሆኑም አንዳቸው ከሌላው ጋር አይጋጩም። ዓሦች ይህን ማድረግ የቻሉት እንዴት ነው? የሰው ልጆችስ የመኪና አደጋዎችን ለመቀነስ ከእነሱ ምን ልንማር እንችላለን?
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ አንድ ላይ እጅብ ብለው የሚዋኙ ዓሦች በአካባቢያቸው ስላለው ነገር የሚያውቁት በዓይናቸው እንዲሁም ላተራል ላይን በሚባል ልዩ የሆነ የስሜት ሕዋስ አማካኝነት ነው። በዙሪያቸው ያሉት ዓሦች የሚገኙበትን ቦታ ለማወቅ በእነዚህ የስሜት ሕዋሳት የሚጠቀሙ ሲሆን ከዚያም ከታች ያሉትን እርምጃዎች ይወስዳሉ፦
-
ጎን ለጎን መዋኘት፦ ከጎናቸው ካለው ዓሣ ጋር ርቀታቸውን ጠብቀው ተመሳሳይ በሆነ ፍጥነት ይዋኛሉ።
-
መጠጋት፦ ከእነሱ ርቆ ወደሚዋኘው ዓሣ ይጠጋሉ።
-
ግጭት ማስቀረት፦ ሲዋኙ ከሌሎች ዓሦች ጋር እንዳይነካኩ አቅጣጫቸውን ያስተካክላሉ።
አንድ የጃፓን መኪና አምራች ኩባንያ፣ እጅብ ብለው የሚጓዙ ዓሦች ላይ የሚታዩትን እነዚህን ሦስት ባሕርያት መሠረት በማድረግ በርከት ያሉ የሮቦት መኪኖችን ሠርቷል፤ እነዚህ ትናንሽ መኪኖች አንድ ላይ እጅብ ብለው ቢጓዙም አይጋጩም። ሮቦቶቹ በዓይን ፋንታ በመገናኛ ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም በላተራል ላይን ፋንታ በጨረር በሚጠቀም የርቀት መለኪያ ይገለገላሉ። ኩባንያው፣ ይህ ቴክኖሎጂ “የማይጋጩ” መኪኖችን ለመሥራት እንደሚያስችለው እንዲሁም “የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስና የትራፊክ መጨናነቅን ለማስወገድ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ መኪኖች የማምረት” ግቡን ለማሳካት እንደሚረዳው ያምናል።
የሮቦት መኪኖቹ ፕሮጀክት ዋና መሃንዲስ የሆኑት ቶሺዩኪ አንዶ እንዲህ ብለዋል፦ “የተራቀቁ የኤሌክትሮኒክ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀማችን እጅብ ብለው የሚዋኙ ዓሦችን ባሕርይ መኮረጅ ችለናል።” በተጨማሪም “ተሽከርካሪዎችን በማምረት መስክ የተሰማራን ሁሉ፣ እጅብ ብለው ከሚዋኙ ዓሦች ብዙ የምንማረው ነገር አለ” በማለት ተናግረዋል።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? ዓሦች እጅብ ብለው የመዋኘት ችሎታ ያገኙት እንዲሁ በአጋጣሚ ነው? ወይስ ይህን ችሎታ ያገኙት ማሰብ ከሚችል ንድፍ አውጪ ነው?