በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዘመናዊ መካነ አራዊትን መጎብኘት

ዘመናዊ መካነ አራዊትን መጎብኘት

ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት ይኖር የነበረ አንድ የቻይና ንጉሥ የእንስሳት ፓርክ ካቋቋመ በኋላ ፓርኩን ‘የእውቀት ገነት’ በማለት ሰየመው። ሰዎች፣ ፓርኩ ውስጥ የሚገኙትን በርካታ እንስሳት መጎብኘት ይችሉ የነበረ ሲሆን ፓርኩ 607 ሄክታር ስፋት ነበረው። በዚያ ዘመን እንዲህ ያለ ፓርክ የተለመደ አልነበረም።

ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ መካነ አራዊት በመሄድ በቀላሉ የዱር አራዊትን መጎብኘት ይችላሉ። ዙስ ኢን ዘ ትዌንቲ ፈርስት ሴንቸሪ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “በዓለም ላይ የተፈጥሮ አካባቢዎች እየተመናመኑ በመምጣታቸውና በከተሞች የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ በመሄዱ ብዙ ሰዎች የዱር አራዊትን ማየት የሚችሉበት ከሁሉ የቀለለው መንገድ መካነ አራዊትን መጎብኘት ሆኗል።”

ዘመናዊ መካነ አራዊት የሚሰጠው አገልግሎት

ሰዎች መካነ አራዊትን ሲጎበኙ በተቻለ መጠን ተፈጥሯዊ አካባቢያቸውን በሚመስል ቦታ እንዲኖሩ የተደረጉትን የምድራችንን ውብና አስደናቂ እንስሳት መመልከት ይችላሉ። ወደ መካነ አራዊት ብትሄዱ ደማቅ ቀለም ያላቸው ቢራቢሮዎች ሞቃታማ አካባቢዎችን እንዲመስል ተደርጎ በተሠራ መናፈሻ ውስጥ ብር ብር ሲሉ ወይም ፔንግዊኖች በበረዶ የተሸፈነውን የአንታርክቲክ አካባቢን እንዲመስል ተደርጎ በተከለለ ቦታ ላይ ብን ብን የሚል የበረዶ ቅንጣት ሲወርድባቸው ማየት ትችሉ ይሆናል።

በምድር ወገብ አካባቢ የሚገኙትን ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች እንዲመስል ሆኖ በተሠራ አካባቢ በእግር በመንሸራሸር እንዲህ ባሉ ቦታዎች ከሚኖሩት እንስሳትና አእዋፍ መካከል አንዳንዶቹን ማየት ትችላላችሁ። ወይም ደግሞ ጨለማ ወደሆነ ክፍል በመግባት ማታ ማታ ብቻ የሚንቀሳቀሱ እንስሳትን ማየት ይቻላል። ሌላው ቀርቶ በአንዳንድ ቦታዎች በሚገኝ መካነ አራዊት ውስጥ አዳኝ አእዋፍ ሲበርሩ ወይም ዶልፊኖች አየር ላይ የአክሮባት ትርዒት ሲያሳዩ መመልከት ትችላላችሁ። አደገኛ የሆኑ እንስሳት ከዚህ በፊት ይቀመጡ የነበረው በብረት በታጠሩ አነስተኛ ክፍሎች ነበር፤ አሁን ግን እንደ ልብ መንቀሳቀስ በሚያስችላቸው ሰፊ የተከለለ ቦታ የሚኖሩ ሲሆን እንስሳቱ በሰዎች ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ የሚያግድ ጉድጓድ ዙሪያውን ይማሳል።

ሁለት ተቃራኒ አመለካከቶች

አንዳንድ የእንስሳት መብት ተሟጋቾች እንስሳትን ከትክክለኛ መኖሪያቸው ወስዶ ተፈጥሯዊ ባልሆነ አካባቢ ማኖር ተገቢ እንዳልሆነ ይከራከራሉ። ተሟጋቾቹ የሚያቀርቡት የመከራከሪያ ሐሳብ የዱር አራዊት የሚታዩባቸው እነዚህ ቦታዎች የእንስሳቱን እንቅስቃሴ የሚገድቡ ከመሆኑም በላይ የተፈጥሮ ባሕርያቸውን ያቃውሳሉ የሚል ነው።

በመካነ አራዊት ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያዎች ደግሞ ለዚህ ክርክር መልስ ሲሰጡ መካነ አራዊት የዱር እንስሳቱን ከጥፋት በመታደግና ትምህርት በመስጠት ረገድ የጎላ ሚና እንዳለው ይገልጻሉ። በማድሪድ፣ ስፔን የሚገኘው የፋውኒያ ፓርክ ባልደረባ የሆኑት ሃይሜ ሩል እንዲህ ብለዋል፦ “ዓላማችን ሰዎች ለእንስሳቱ አክብሮት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። የእኛ ፍላጎት ጎብኚዎቻችን የእንስሳቱን መኖሪያ ስፍራ የመጠበቅ ተነሳሽነት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፤ አለበለዚያ የእነዚህ እንስሳት ሕልውና አደጋ ላይ ይወድቃል።” አንዳንድ ጥናቶች እንዳመለከቱት ከሆነ በጥሩ መንገድ የተያዘ መካነ አራዊት ሰዎች፣ ለመጥፋት የተቃረቡ እንስሳትን መጠበቅ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ያስችላል።

አንዳንድ ብርቅዬ እንስሳት በሰዎች ልብ ውስጥ ልዩ ፍቅር ያገኙ ይመስላል። ጃይንት ፓንዳ የተባለውን የድብ ዝርያ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ማድሪድስ ዙ አኳሪየም በተባለ መካነ አራዊት ውስጥ የሚሠሩት ኖኤልያ ቢኔቶ እንዲህ ብለዋል፦ “ሁሉም ጎብኚዎች ሁለቱን ፓንዳዎቻችንን ማየት ይፈልጋሉ። ይህ ታዋቂ እንስሳ ሊጠፉ የተቃረቡ እንስሳትን ለማዳን ላደረግነው ትግል እንደ አርማ ሆኖልናል። ፓንዳዎች ተጓዳኝ ሲፈልጉ በጣም መራጮች ቢሆኑም ዘራቸውን እንደሚተኩ ተስፋ እናደርጋለን።”

ከፓንዳዎች በተለየ ብዙ እንስሳት፣ የሚኖሩበት ሁኔታ በመሻሻሉና ጥሩ የሕክምና ክትትል የሚደረግላቸው በመሆኑ በመካነ አራዊት ውስጥ በቀላሉ መራባት ችለዋል። እንስሳትን የማራባት ፕሮግራሞች ውጤታማ መሆናቸው መካነ አራዊት፣ ሊጠፉ የተቃረቡ የእንስሳት ዝርያዎችን በመጠበቁ ሥራ ውስጥ መግባት የለበትም ለሚሉ ተቺዎች ምላሽ አስገኝተዋል። የዱር እንስሳት የሚታዩባቸው በርካታ ቦታዎች አውደ ርዕይ ከመሆን ባለፈ ለመጥፋት የተቃረቡ እንስሳትን ለማራባት ጥረት ያደርጋሉ፤ ይህን የሚያደርጉት እንዲህ ያሉ እንስሳትን ውሎ አድሮ ወደ ዱራቸው ለመልቀቅ ነው።

አንዳንድ የእንስሳት ዝርያዎች ከምድር ገጽ ከሚጠፉባቸው ምክንያቶች ዋነኛው የእንስሳቱ የመኖሪያ አካባቢ እየጠፋ መምጣቱ ነው። ስለሆነም መካናተ አራዊት፣ በምድር ወገብ አካባቢዎች በሚገኙ አገሮች ውስጥ ካሉ ጥብቅ ፓርኮች ጋር እጅና ጓንት ሆነው በመሥራት የዱር እንስሳት ጥበቃ ፕሮግራሞችን በገንዘብ ይደግፋሉ። *

ተፈጥሮን መመልከት

አብዛኞቹ ልጆች በተፈጥሯቸው ስለ እንስሳት ማወቅ ስለሚያስደስታቸው ቅዳሜና እሁድ ወይም ትምህርት ቤት ሲዘጋ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ መካነ አራዊትን መጎብኘት ይቻላል፤ እንዲህ ማድረግ ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ አምላክ ፍጥረት ማስተማር የሚችሉበት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። አንድ ላይ ሆነው ተፈጥሮን መመልከት ይችላሉ።

የሰው ልጅ ታሪክ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሰዎች ስለ እንስሳት የማወቅ ጉጉት አላቸው። የፍጥረት ሥራዎች የፈጣሪን ባሕርያት ጠልቀን እንድናስተውል ስለሚረዱን ልጆቻችን ስለ ተፈጥሮ የማወቅ ፍላጎት እንዲኖራቸው ማድረጋችን የሚክስ ነው። በተጨማሪም መካነ አራዊትን መጎብኘት በቋፍ ላይ ባለችው ምድራችን ላይ ለሚኖሩት አስደናቂ ፍጥረታት ያለን አክብሮትና ግንዛቤ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል።

^ አን.12 መካናተ አራዊት በእስያ የሚገኙ ታይገሮችን፣ በማዳጋስካር የሚገኙ ሊመሮችን እንዲሁም በአፍሪካ የሚገኙ የዝንጀሮ ዝርያዎችን ከጥፋት ለመታደግ ያደረጉት ጥረት የተሳካላቸው ይመስላል።