በሐዘን የተደቆሱ ልጆችን ማጽናናት
በሐዘን የተደቆሱ ልጆችን ማጽናናት
መርዶ መናገር በራሱ ከባድ ነገር እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። የሚወዱት ሰው መሞቱን ለልጆች መናገር ደግሞ ይበልጥ ፈታኝ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም።
ብዙ ልጆች የቤተሰባቸውን አባል በሞት ሲያጡ ግራ ሊጋቡ አልፎ ተርፎም በፍርሃት ሊዋጡ ይችላሉ። እንዲህ ባለው ወቅት አንድን ልጅ ማረጋጋት በተለይም ሐዘን ለደረሰባቸው ወላጆች ተፈታታኝ ሊሆንባቸው ይችላል። ምክንያቱም እነሱ ራሳቸው በዚህ ወቅት ስሜታዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።
አንዳንድ ወላጆች፣ ልጃቸው ሁኔታውን መቀበል ቀላል እንዲሆንለት ለማድረግ ሲሉ ሟቹ ትቷቸው እንደሄደ ይናገሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው አገላለጽ አሳሳች ከመሆኑም ሌላ ውሸት ነው። ታዲያ ለአንድ ልጅ ስለ ሞት መንገር የምትችሉት እንዴት ነው?
ሬናቱና ኢዛቤል እንዲህ ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። ኒኮል የተባለችው ልጃቸው በሦስት ዓመት ተኩል ዕድሜዋ በሞተች ጊዜ የአምስት ዓመት ልጅ የነበረው ወንድሟ ፊሊፒ እንዲጽናና መርዳት ነበረባቸው።
ንቁ!፦ የኒኮልን መሞት ለፊሊፒ ምን ብላችሁ ነገራችሁት?
ኢዛቤል፦ ነገሩን በሐቀኝነትና በግልጽ ለማስረዳት ጥረት አደረግን። ጥያቄ ካለው እንዲጠይቅ እናበረታታው የነበረ ሲሆን እኛም ምንጊዜም ጥያቄዎቹን ስንመልስ ዕድሜውን ግምት ውስጥ እናስገባ ነበር። ኒኮል የሞተችው በባክቴሪያ በሚመጣ ኢንፌክሽን ምክንያት ነበር፤ ስለዚህ አንዲት ትንሽ ነፍሳት ወደ ኒኮል ሰውነት እንደገባችና ሐኪሞች ሊገድሏት ስላልቻሉ ኒኮል እንደሞተች ለፊሊፒ ነገርነው።
ንቁ!፦ ለፊሊፒ ከሞት ጋር በተያያዘ ያላችሁን እምነት ነገራችሁት?
ሬናቱ፦ እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ነን፤ ስለዚህ ሞትን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን እምነታችንን ለፊሊፒ ብንነግረው እንደሚያጽናናው እናውቃለን። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ በጣም ግልጽ ሲሆን ሙታን ምንም እንደማያውቁ ያስተምራል። (መክብብ 9:5) ይህን ለፊሊፒ ብናስረዳው ሊኖረው የሚችለውን ማንኛውንም ዓይነት ፍርሃት ሊያጠፋለት እንደሚችል አሰብን። ለምሳሌ ያህል፣ ይህን ማወቁ ማታ ላይ ብቻውን መሆን እንዳይፈራ ያደርገዋል።
ኢዛቤል፦ መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ትንሣኤ እንደሚያገኙም ያስተምራል። እኛ ይህን የምናምን ሲሆን ይህ ትምህርት ፊሊፒንም እንደሚያጽናናው ተሰማን። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ማርቆስ 5:22-24, 35-42፤ ዮሐንስ 5:28, 29
ነገር ነገርነው። ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ የነበረችውን የኢያኢሮስ ልጅ እንዳስነሳት የሚገልጸውን ታሪክ ተረክንለት። ከዚያም ኒኮልም እንደምትነሳ ለፊሊፒ አስረዳነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ ያስተምራል።—ንቁ!፦ ፊሊፒ የነገራችሁት ነገር በሙሉ የገባው ይመስላችኋል?
ሬናቱ፦ አዎ፣ እንደገባው ይሰማናል። ልጆች ትክክለኛ፣ ቀላልና ግልጽ እንዲሁም ሐቀኝነት የሚንጸባረቅበት ማብራሪያ ካገኙ ሁኔታውን መረዳትና መጽናናት አይከብዳቸውም። ነገሩን መሸፋፈን አያስፈልግም። ሞት ያለ ነገር ነው። የሚያሳዝነው ደግሞ ሁላችንም በሕይወታችን ያጋጥመናል። ስለዚህ ወላጆች ሞት የሚያስከትለውን ሐዘን እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ ለልጆቻቸው ማስተማር ያስፈልጋቸዋል፤ እኛም ከጊዜ በኋላ ለትንሹ ልጃችን ለቪኒስየስ ስለዚህ ጉዳይ አስተምረነዋል። *
ንቁ!፦ ፊሊፒን ወደ ቀብር ሥነ ሥርዓቱ ወስዳችሁት ነበር?
ሬናቱ፦ ጥቅምና ጉዳቱን ካመዛዘንን በኋላ ይዘነው ላለመሄድ ወሰንን። በእሱ ዕድሜ ያሉ ልጆች ያዩት ነገር አእምሯቸው ውስጥ ተቀርጾ ይቀራል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ወላጆች ልጃቸውን ወደ ቀብር ሥነ ሥርዓቱ ይዘው ለመሄድ ሊወስኑ ይችላሉ፤ ደግሞም የእያንዳንዱ ልጅ አቅም ለየቅል ነው። አንድ ልጅ ወደ ቀብር ሥነ ሥርዓቱ የሚወሰድ ከሆነ በዚያ ስለሚከናወነው ነገር አስቀድሞ በግልጽ መንገሩ ጥሩ ነው።
ንቁ!፦ የኒኮል ሞት ለእናንተ እጅግ አሳዛኝ እንደሆነ ግልጽ ነው። ልጃችሁ ስታለቅሱ እንዳያያችሁ ትጨነቁ ነበር?
ኢዛቤል፦ ስሜታችንን ከፊሊፒ ለመደበቅ ፈጽሞ አልሞከርንም። ኢየሱስ እንኳ የሚወደው ሰው ሲሞት ‘እንባውን አፍስሶ’ የለ? (ዮሐንስ 11:35, 36) ታዲያ ፊሊፒ ስናለቅስ ቢያየን ምናለበት? ፊሊፒ እንዳዘንን ማየቱ ማልቀስ ስህተት እንዳልሆነ እንዲገነዘብ አድርጎታል። ማልቀስ ስሜታችንን የምንገልጽበት ተፈጥሯዊ መንገድ ነው። ፊሊፒም ሐዘኑን አፍኖ ከመያዝ ይልቅ በማልቀስ ስሜቱን መግለጽ እንደሚችል እንዲያውቅ ፈልገን ነበር።
ሬናቱ፦ በቤተሰብ ውስጥ አሳዛኝ መከራ ሲደርስ ልጆች ፍርሃት ያድርባቸዋል። እኛ ወላጆች ስለሚሰማን ነገር ግልጽና
ሐቀኞች ከሆንን ልጆቻችንም ስሜታቸውን በግልጽ ይነግሩናል። ልጆች ስለሚያስጨንቃቸው ነገር ሲነግሩን በጥሞና ካዳመጥን ልናጽናናቸውና ፍርሃታቸውን ለማስወገድ ልንረዳቸው እንችላለን።ንቁ!፦ ከሌሎች ያገኛችሁት እርዳታ አለ?
ሬናቱ፦ አዎ፣ የጉባኤያችን አባላት ከፍተኛ ድጋፍ አድርገውልናል። የእምነት ባልንጀሮቻችን እየመጡ ሲያጽናኑን፣ ስልክ ሲደውሉልንና ካርድ ሲልኩልን ፊሊፒ ማየቱ ምን ያህል እንደሚወዱንና እንደሚያስቡልን እንዲገነዘብ አስችሎታል።
ኢዛቤል፦ የቤተሰባችን አባላትም በጣም ረድተውናል። ኒኮል ከሞተች በኋላ አባቴ በየቀኑ ጠዋት እየመጣ አብሮን ቁርስ ለመብላት ወሰነ። ይህን ያደረገው ፍቅሩንና አሳቢነቱን ለማሳየት ነበረ። ደግሞም አያቱ ከጎኑ መሆኑ ፊሊፒን ጠቅሞታል።
ሬናቱ፦ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ያገኘነው መንፈሳዊ ማጽናኛም እጅግ ጠቅሞናል። አንዳንድ ጊዜ እንባችንን መቆጣጠር ቢያስቸግረንም እንኳ ከስብሰባ ላለመቅረት ጥረት እናደርጋለን። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ከኒኮል ጋር በተያያዘ ብዙ ትዝታዎች ይቀሰቅስብናል። ያም ቢሆን በተለይ ለፊሊፒ ስንል ጠንካሮች መሆን እንዳለብን እናውቅ ነበር።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.12 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በሚዘጋጀው መጠበቂያ ግንብ መጽሔት የሐምሌ 1, 2008 እትም ገጽ 18-20 ላይ የወጣውን “ልጃችሁ የደረሰበትን ሐዘን እንዲቋቋም እርዱት” የሚለውን ርዕስ እንዲሁም የምትወዱት ሰው ሲሞት የተባለውን ብሮሹር ተመልከት።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ከታች የተዘረዘሩት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ መጻሕፍት የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ሰዎችን ሊያጽናኗቸው ይችላሉ።
ለአዋቂዎች
ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
ምዕራፍ 6፦ ሙታን የት ናቸው?
ምዕራፍ 7፦ በሞት የተለዩህ የምትወዳቸው ሰዎች ያላቸው እውነተኛ ተስፋ
ለትናንሽ ልጆች
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ
ታሪክ 92፦ ኢየሱስ የሞቱ ሰዎችን አስነሳ
ለታዳጊዎች
ከታላቁ አስተማሪ ተማር
ምዕራፍ 34፦ ስንሞት ምን እንሆናለን?
ምዕራፍ 35፦ ከሞት ልንነሳ እንችላለን!
ምዕራፍ 36፦ ከሞት የሚነሱት እነማን ናቸው? የሚኖሩትስ የት ነው?
ለወጣቶች
Questions young people ask—answers that work VOLUME 1 *
ምዕራፍ 16፦ ይህን ያህል ማዘን የጤና ነውን?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.39 የአማርኛውን የወጣቶች ጥያቄ፣ ጥራዝ 1 ተመልከት።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
መርዳት የሚቻልበት መንገድ
● ልጃችሁ ጥያቄ እንዲጠይቅ አበረታቱት። ልጃችሁ በፈለገው ጊዜ ስለ ሞት ሊያዋራችሁ እንደሚችል እንዲሰማው አድርጉ።
● ስለ ሟቹ ስትናገሩ “ሩቅ አገር ሄዷል” ወይም “ትቶን ሄዷል” እንደሚሉ ያሉ ግልጽ ያልሆኑ ወይም ለመረዳት አዳጋች የሆኑ አገላለጾችን አትጠቀሙ።
● ሞትን ቀላል በሆነና በማያሻማ መንገድ አስረዱት። አንዳንዶች የሟቹ ሰውነት “መሥራቱን እንዳቆመ” እና “ሊጠገን እንዳልቻለ” ለልጃቸው ይነግሩታል።
● ለልጁ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ምን እንደሚከናወን ንገሩት፤ ሟቹ እየተከናወነ ያለውን ነገር ማየትም ሆነ መስማት እንደማይችል ግለጹለት።
● ስሜታችሁን አትደብቁ። እንዲህ ማድረጋችሁ ልጃችሁ ሐዘንን መግለጽ ተፈጥሯዊ ነገር መሆኑን እንዲረዳ ያስችለዋል።
● ሐዘንን መግለጽ የሚቻልበት “ትክክለኛ” የሚባል መንገድ እንደሌለ አስታውሱ። ሁኔታው ከልጅ ልጅ ይለያያል።
[የሥዕሉ ንንጭ]
ምንጭ፦ www.kidshealth.org
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከግራ ወደ ቀኝ፦ ፊሊፒ፣ ሬናቱ፣ ኢዛቤል እና ቪኒስየስ