የእንጀራ ልጆችን ማሳደግ—የሚያጋጥሙ ለየት ያሉ ፈተናዎች
የእንጀራ ልጆችን ማሳደግ—የሚያጋጥሙ ለየት ያሉ ፈተናዎች
● የእንጀራ ልጆችን የሚያሳድጉ ቤተሰቦች አማካሪ የሆኑት ዶክተር ፐትሪሻ ፔፐርናው እንዳሉት እንደነዚህ ያሉ ቤተሰቦች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት የተለመደውን ቤተሰብ እንደ ምሳሌ መውሰድ፣ በአንድ ከተማ ውስጥ የሚገኝን አካባቢ ለማግኘት የሌላ ከተማ ካርታ እንደመጠቀም ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የእንጀራ ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች የሚገጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የሚመሠረቱ ቤተሰቦች ከሚገጥሟቸው ፈተናዎች ለየት ያሉ ከመሆናቸውም ሌላ ይበልጥ ውስብስብ ናቸው። እንዲያውም የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ዊልያም መርከል፣ የእንጀራ ልጆች ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ የሚኖረው ሕይወት “የሰው ልጆች ካሏቸው ግንኙነቶች ሁሉ እጅግ ውስብስብ፣ ለመልመድ የሚከብድ ብሎም አስቸጋሪ” እንደሆነ ተናግረዋል።
ሁኔታው ይህን ያህል አስቸጋሪ ከሆነ ታዲያ የእንጀራ ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች ስኬታማ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? በእንደዚህ ዓይነት ቤተሰብ ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚኖራቸው ግንኙነት የተለያዩ ጨርቆችን በመገጣጠም ከተሠራ አልጋ ልብስ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ጨርቆቹ የተጋጠሙበት ቦታ መጀመሪያ ላይ ያን ያህል ጠንካራ ባይሆንም በደንብ ከተሰፋ ግን አልጋ ልብሱ ተሠርቶ ሲያልቅ በአንድ ወጥ ጨርቅ የተሠራ ያህል ጥንካሬ ሊኖረው ይችላል።
የእንጀራ ወላጆችና ልጆች የሚገኙባቸው ቤተሰቦች የሚያጋጥሟቸውን አንዳንድ የተለመዱ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እስቲ እንመልከት፤ እንዲሁም እንደዚህ ያሉ በርካታ ቤተሰቦች ተስማምተው አንድ ላይ ለመኖር የረዷቸውን ነገሮች እንመረምራለን። ከዚያም የእንጀራ ልጆች ያሏቸው አራት ቤተሰቦች ሊሳካላቸው የቻለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ታሪካቸውን እናያለን።
ተፈታታኝ ሁኔታ 1፦ የጠበቁት ሳይሆን ሲቀር
“የባለቤቴን ልጆች ፍቅር ባሳያቸውና ትኩረት ብሰጣቸው እንደሚቀበሉኝ ተስፋ አድርጌ ነበር፤ ነገር ግን ስምንት ዓመታት ቢያልፉም እስካሁን ድረስ አልተሳካልኝም።”—ግሎሪያ *
ልጆች እያሏቸው የሚያገቡ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ትዳራቸውን የሚጀምሩት ብዙ ተስፋ ሰንቀው ነው። ተጋቢዎቹ በቀድሞ ትዳራቸው የፈጸሟቸውን ስህተቶች ላለመድገም አለዚያም ለማስተካከል ይፈልጋሉ፤ እንዲሁም ቀደም ሲል ያጡትን ፍቅርና የተረጋጋ ሕይወት እንደሚያገኙ ተስፋ ያደርጋሉ። አንዳንዶቹ ተስፋዎች እውን ሊሆኑ የማይችሉ ነገሮች ቢሆኑም አለመፈጸማቸው በቤተሰቡ ውስጥ ውጥረት እንዲነግሥ ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ለነገ የሚባል ተስፋ ልብን ያሳምማል።” (ምሳሌ 13:12) እናንተም የጠበቃችሁት ነገር ሳይሆን መቅረቱ ልባችሁን እያሳመመው ከሆነ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ?
ማድረግ የምትችሉት ነገር
የተሰማችሁ ቅሬታ ውሎ አድሮ መጥፋቱ እንደማይቀር በማሰብ ስሜታችሁን ችላ አትበሉት። ከዚህ ይልቅ እንደጠበቃችሁት ሳይሆን በመቅረቱ የሚያበሳጫችሁን ነገር ለይታችሁ ለማወቅ ሞክሩ። ከዚያም የጠበቃችሁት ነገር እንዲፈጸም አጥብቃችሁ የምትፈልጉት ለምን እንደሆነ ለመረዳት ጣሩ። በመጨረሻም የምትጠብቁት ነገር አሁን ባላችሁበት ሁኔታ ሊፈጸም የሚችልና እውነታውን ያገናዘበ እንዲሆን ለማድረግ ሞክሩ። ቀጥሎ አንዳንድ ምሳሌዎች ቀርበዋል፦
1. ገና ከመጀመሪያው፣ የእንጀራ ልጆቼን እንደምወዳቸውና እነሱም እንደሚወዱኝ ሙሉ ተስፋ አለኝ።
ለምን? ምክንያቱም የሚዋደድና እርስ በርስ የሚቀራረብ ቤተሰብ እንዲኖረኝ ሁልጊዜ እመኛለሁ።
እውነታውን ያገናዘበ ተስፋ፦ አንዳችን ለሌላው ያለን ፍቅር እያደር እያደገ ሊሄድ ይችላል። አሁን አስፈላጊው ነገር ቤተሰባችን ተረጋግቶና ተከባብሮ መኖር መቻሉ ነው።
2. ሁላችንም አዲሱን ሕይወት ቶሎ እንለምደዋለን።
ለምን? ምክንያቱም አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ለመጀመር ዝግጁ ነን።
እውነታውን ያገናዘበ ተስፋ፦ የእንጀራ ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች አብዛኛውን ጊዜ የተረጋጋ ሕይወት መምራት እስኪጀምሩ ድረስ ከአራት እስከ ሰባት ዓመታት ይፈጅባቸዋል። ስለዚህ እኛ ያሉብን ችግሮች የተለመዱና የሚጠበቁ ናቸው።
3. ስለ ገንዘብ አንጨቃጨቅም።
ለምን? ምክንያቱም እርስ በርስ ስለምንዋደድ በረባ ባልረባው አንነታረክም።
እውነታውን ያገናዘበ ተስፋ፦ ከገንዘብ ነክ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በቀድሞ ትዳራችን ውስጥ ውስብስብ ነገሮች አጋጥመውናል። በመሆኑም ገንዘባችንን በሙሉ በጋራ መጠቀም ሊያስፈራን ይችላል።
ተፈታታኝ ሁኔታ 2፦ የሌሎቹን ስሜት መረዳት
“ቶሎ ተግባባን፤ ሁላችንም በአዲሱ ቤተሰብ ውስጥ ያለውን ሕይወት ወዲያው ለመድነው።”—ዮሺቶ
“የቤተሰባችን ሕይወት የተሳካ እንዲሆን ከልቤ ጥረት ለማድረግ አሥር ዓመት ፈጅቶብኛል።”—ታትሱኪ፣ የዮሺቶ የእንጀራ ልጅ
እንደ ዮሺቶና ታትሱኪ ሁሉ የእንጀራ ልጆች ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ አንዱ የሌላውን ስሜት በደንብ ላይረዳ ይችላል። ይሁንና የሌላውን ስሜት መረዳት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ችግሮች ሲነሱ መጀመሪያ የሚመጣላችሁ ነገር ለችግሩ እልባት መስጠት ሊሆን ይችላል። ሆኖም ለችግሩ ውጤታማ የሆነ እልባት ለማግኘት በመጀመሪያ የቤተሰባችሁን ስሜት መረዳት ይኖርባችኋል።
ይሁንና ንግግር ሊያንጽም ሆነ ሊያፈርስ ስለሚችል ሐሳባችሁን ስለምትገልጹበት መንገድ ማሰቡ ጠቃሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “አንደበት የሞትና የሕይወት ኀይል አላት።” (ምሳሌ 18:21) ታዲያ እንዳትግባቡ እንቅፋት በሚፈጥር ሳይሆን ለመግባባት በሚያስችላችሁ መንገድ አንደበታችሁን ልትጠቀሙበት የምትችሉት እንዴት ነው?
ማድረግ የምትችሉት ነገር
• ነቃፊ ከመሆን ይልቅ የቤተሰባችሁን አባላት ስሜት ለመረዳት እንዲሁም ራሳችሁን በእነሱ ቦታ ለማስቀመጥ ሞክሩ። ለምሳሌ ያህል፦
ልጅሽ “አባዬ ይናፍቀኛል” ቢል አባቱን ማጣቱ የጎዳው መሆኑን እንደምትረጂለት አሳዪ። “የእንጀራ አባትህም እኮ ይወድሃል፤ ደግሞም ከወላጅ አባትህ ይልቅ እሱ ይሻልሃል” ብለሽ ከመመለስ ይልቅ እንዲህ ለማለት ሞክሪ፦ “በእርግጥም አባትን ማጣት ከባድ ነገር ነው። ስለ አባትህ ስታስብ በጣም የሚናፍቅህ ምን እንደሆነ እስቲ ንገረኝ?”
አዲሷ የትዳር ጓደኛህን “ጥሩ እናት ብትሆኚ ኖሮ ልጅሽ እንዲህ አይባልግም ነበር” ብለህ ከመውቀስ ይልቅ እንዲህ ማለት ትችላለህ፦ “ሉቃስ ወደ ቤት ሲገባ ሰላም ቢለኝ ደስ ይለኛል። እንዲህ እንዲያደርግ ብትነግሪው ምን ይመስልሻል?”
• አብራችሁ በመመገብ፣ በመዝናናት እና የአምልኮ እንቅስቃሴዎችን በማከናወን የምታሳልፉትን ጊዜ አንዳችሁ ስለ ሌላው ለማወቅ ተጠቀሙበት።
• በቤተሰብ አንድ ላይ ሰብሰብ ብላችሁ የመጨዋወት ልማድ ይኑራችሁ። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ሐሳቡን እንዲገልጽ ፍቀዱለት፤ ስለ አዲሱ ቤተሰብ ያሳሰበውን ጉዳይ በመግለጽ ከመጀመር ይልቅ ስለ ጥሩ ጎኑ በቅድሚያ እንዲናገር አበረታቱት። ሐሳቡን በሚናገርበት ጊዜም አታቋርጡት። ሌላው በሚናገረው ነገር ባትስማሙም እንኳ እንደምታከብሩት አሳዩ፤ እንዲሁም ሁሉም የቤተሰባችሁ አባላት የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያቀርቡ ዕድል ስጧቸው።
ተፈታታኝ ሁኔታ 3፦ የባይተዋርነት ስሜት
“ሚስቴና ልጆቿ እርስ በርስ ይመካከሩና ያብሩብኛል። ይህም ባዕድና ባይተዋር እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደርገኛል።”—ዋልት
‘በራሴ ቤተሰብ ውስጥ እንደ ባዕድ እቆጠራለሁ’ የሚለው ስጋት ከዚህ ጋር ምንም የማይገናኙ ለሚመስሉ ሌሎች ችግሮች መንስኤ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፦
• ልጆች፣ አባታቸው ወይም እናታቸው ሊያገቡት ካሰቡት ሰው ጋር ጥሩ ግንኙነት የነበራቸው ቢሆንም ከጋብቻው በኋላ ግን ሁኔታውን ለመቀበል ይቸገራሉ።
• አንድ አባት በስድስት ዓመት የእንጀራ ልጁ ይቀናል።
• ቀላል የሚመስሉ የቤተሰብ ጉዳዮች የከረረ ጭቅጭቅ ያስነሳሉ።
ይህ ሁኔታ በወላጅ አባትና በወላጅ እናት ላይም ተጽዕኖ ያሳድራል፤ አዲሱ ቤተሰባቸው እየተከፋፈለ እንደሆነ ስለሚሰማቸው ውጥረት ይፈጠርባቸዋል። ካርሜን “በባለቤቴና በሁለቱ ልጆቼ መካከል አጣብቂኝ ውስጥ መግባት በጣም ከባድ ነገር ነው” ብላለች።
ወርቃማው ሕግ ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመወጣት የሚረዳ ቁልፍ ነው። ኢየሱስ “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ አድርጉላቸው” በማለት ይህን ሕግ ገልጾታል። (ማቴዎስ 7:12) ታዲያ የእንጀራ ልጆች ያሏቸው ወላጆች የተወሰኑትን የቤተሰቡን አባላት ለማቅረብ ሲጥሩ ሌሎቹ የባይተዋርነት ስሜት እንዳይሰማቸው ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
ማድረግ የምትችሉት ነገር
• ለትዳር ጓደኛችሁ ቅድሚያ ስጡ። (ዘፍጥረት 2:24) ከአዲሱ የትዳር ጓደኛችሁ ጋር ጊዜ አሳልፉ፤ እንዲሁም የትዳር ጓደኛችሁ በቤተሰቡ ውስጥ ያለውን ቦታ ልጆቻችሁ በግልጽ እንዲያውቁ አድርጉ። ለምሳሌ ያህል፣ አባቶች ሁለተኛ ትዳር ከመመሥረታቸው በፊትም ቢሆን ለልጆቻቸው እንዲህ ሊሏቸው ይችላሉ፦ “ሐናን ስለምወዳት ልንጋባ ወስነናል። እናንተም እንደምታከብሯት እተማመናለሁ።”
• ከእያንዳንዱ ልጃችሁ ጋር ለብቻችሁ የምታሳልፉት ጊዜ መድቡ። ለእያንዳንዳቸው የተወሰነ ጊዜ መመደባችሁ ምን ያህል እንደምታስቡላቸው የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ እንደምትወዷቸው ያረጋግጥላቸዋል።
• ከእንጀራ ልጆቻችሁም ጋር በግለሰብ ደረጃ ጊዜ አሳልፉ፤ እንዲህ ማድረጋችሁ የወላጅ አባታቸው ወይም እናታቸው እርዳታ ሳያስፈልጋችሁ ከእነሱ ጋር ለመቀራረብ ያስችላችኋል።
• ልጆቹ አዲሱን ቤተሰብ “ለመቀላቀል” የቀድሞ ቤተሰባቸውን መርሳት እንዳለባቸው እንዲሰማቸው አታድርጉ። አብዛኛውን ጊዜ የእንጀራ ልጆች፣ እናታቸውን ወይም አባታቸውን በሚጠሩበት “እማዬ” ወይም “አባዬ” እንደሚሉት ባሉ ቃላት እንዲጠሯችሁ አለመጫኑ የተሻለ ነው። በተለይ ትልልቅ ልጆች መጀመሪያ አካባቢ ስለ አዲሱ ቤተሰብ ሲናገሩ “ቤተሰባችን” የሚለውን ቃል መጠቀም ሊከብዳቸው ይችላል።
• ለእያንዳንዱ ልጅ የቤት ውስጥ ሥራ ስጡት፤ እንዲሁም ማዕድ ላይ ስትቀርቡ የሚቀመጥበት ቦታ እና ቤት ውስጥ የራሱ የሆኑ ነገሮች እንዲኖሩት አድርጉ። ይህ ሁልጊዜ አብረዋችሁ የማይኖሩ ልጆችንም ይጨምራል።
• አዲስ የሆኑት የቤተሰቡ አባላት ባዕድ እንደሆኑ እንዳይሰማቸው ለማድረግ፣ መኖሪያ ቤት መቀየር ወይም ነባሩን ቤት በአዲስ መልክ ማደራጀት ትችሉ ይሆናል።
ተፈታታኝ ሁኔታ 4፦ ለልጆች ተግሣጽ መስጠት
“የካርሜንን ልጆች ለመቅጣት ስሞክር እሷ እኔን በመደገፍ ፈንታ ልጆቿን ታባብላቸዋለች።”—ፓብሎ
“ፓብሎ ልጆቼን ሲያመናጭቃቸው ልቤ ይቆስላል።”—ካርሜን
የእንጀራ ልጆች በሚገኙበት ቤተሰብ ውስጥ የልጆች አስተዳደግ አለመግባባት እንዲፈጠር ሊያደርግ የሚችለው ለምንድን ነው? አንድ ወላጅ፣ ልጆቹን ብቻውን በሚያሳድግበት ወቅት ለልጆቹ ጠንከር ያለ ተግሣጽ አይሰጣቸው ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው ሁለተኛ ትዳር ሲመሠርት ከባለቤቱ ልጆች ጋር ያን ያህል የጠበቀ ቅርርብ ላይኖረው ይችላል። ታዲያ ይህ ምን ያስከትላል? የእንጀራ ወላጅ የሆነው ግለሰብ የትዳር ጓደኛው ልጆቹን እንደሚያቀብጣቸው ሊሰማው ይችላል፤ ወላጅ እናት ወይም አባት ደግሞ የትዳር ጓደኛቸው በእነሱ ልጆች ላይ በጣም ጥብቅ የሆነባቸው ሊመስላቸው ይችላል።
መጽሐፍ ቅዱስ ልጆችን ቀጥቶ በማሳደግ ረገድ ሚዛናችንን እንድንጠብቅ ይመክረናል፤ እንዲህ ይላል፦ “ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው፤ ከዚህ ይልቅ በይሖዋ [አምላክ] ተግሣጽ እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብ በውስጣቸው በመቅረጽ አሳድጓቸው።” (ኤፌሶን 6:4) እዚህ ላይ ትኩረት የተሰጠው ነገር የልጆቻችሁን ባሕርይ መቆጣጠር ሳይሆን አስተሳሰባቸውን መቅረጽ ነው። ከዚህም ሌላ ወላጆች የሚሰጡት ቅጣት ልጆቹን የሚያስመርር እንዳይሆን ደግና አፍቃሪ እንዲሆኑ ተበረታተዋል።
ማድረግ የምትችሉት ነገር
• ቤተሰባችሁ የሚመራባቸውን ሕጎች አውጡ፤ ይህን ስታደርጉ ቀደም ሲል የነበሩትን ደንቦች ግምት ውስጥ አስገቡ። እንዲህ ዓይነት ሕጎች ያላቸውን ጥቅም ቀጥሎ ከቀረበው ውይይት መመልከት ይቻላል፦
የእንጀራ እናት፦ ያኔት፣ የቤት ሥራሽን ሳትጨርሺ በሞባይል የጽሑፍ መልእክት መለዋወጥ በእኛ ቤት ክልክል እንደሆነ ታውቂያለሽ አይደል?
ያኔት፦ እንዴ፣ እናቴ የሆንሽ መሰለሽ?
የእንጀራ እናት፦ ያኒ፣ እናትሽ እንዳልሆንኩ አውቃለሁ፤ አሁን ግን መመሪያ የምሰጠው እኔ ነኝ፤ በቤታችን ደግሞ ‘የቤት ሥራ ሳይጨርሱ በሞባይል መልእክት መለዋወጥ አይቻልም’ የሚል ደንብ እንዳለ ታውቂያለሽ።
• ብዙ ሕጎችን ከማውጣትም ሆነ ልጆቹ በቤት ውስጥ የሚያከናውኑትን ሥራ ቶሎ ቶሎ ከመቀያየር ተቆጠቡ። አንድ ወላጅ፣ የእንጀራ ልጁን የጠየቀው ነገር ቀላል ይመስለው ይሆናል፤ ሕይወቱ እንደተመሰቃቀለበት ለሚሰማው ልጅ ግን የተጠየቀው ነገር ከባድ ሸክም ሊሆንበት ይችላል። በእርግጥ በቤተሰባችሁ ውስጥ አዳዲስ ሕጎች ማውጣት ያስፈልግ ይሆናል። ለምሳሌ በዕድሜ ከፍ ያሉ ልጆች ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ አለባበስን የሚመለከት ደንብ ያስፈልጋል፤ እንዲሁም ልጆቹ ብቻቸውን መሆን በሚፈልጉበት ጊዜ አንዳቸው የሌላውን ፍላጎት እንዲያከብሩ ማድረጉ ተገቢ ነው።
• ከልጆች አስተዳደግ ጋር በተያያዘ በመካከላችሁ አለመግባባት ከተፈጠረ ጉዳዩን ብቻችሁን ስትሆኑ ተወያዩበት። ልጁ ቀደም ሲል የተሰጠው ሥልጠና ችግር እንደነበረው ከመግለጽ ይልቅ ሊታረም በሚገባው የልጁ ባሕርይ ላይ አተኩሩ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.7 በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድነት ያለው ቤተሰብ የሕልም እንጀራ ይመስል ይሆናል
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቤተሰባችሁን አባላት ስሜትና የሚያሳስቧቸውን ነገሮች ለመረዳት እንድትችሉ በጥሞና አዳምጡ
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አለመግባባት ሲፈጠር ወላጆች ጉዳዩን ብቻቸውን ሊፈቱት ይገባል