በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሌሎችን ማመስገን ያለብን ለምንድን ነው?

ሌሎችን ማመስገን ያለብን ለምንድን ነው?

ብዙ ሰዎች፣ የሚያደርጉትን ጥረት ከቁብ የሚቆጥረው እንደሌለ ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ብዙውን ጊዜ ሠራተኞች፣ አሠሪዎቻቸው ልፋታቸውን ቦታ እንደማይሰጡት አድርገው ያስባሉ። በርካታ ያገቡ ሰዎችም የትዳር ጓደኞቻቸው እንደማያደንቋቸው ይሰማቸዋል። እንዲሁም አንዳንድ ልጆች፣ ‘መቼም ቢሆን ወላጆቼ እንደሚጠብቁብኝ መሆን አልችልም’ የሚል ስሜት አላቸው። ይሁንና አንዳችን ሌላውን በየጊዜው ብናመሰግን እንዲህ ዓይነቶቹ የቅሬታ ስሜቶች ሊቀረፉ እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም።

በዛሬው ጊዜ ግን ሌሎችን ከልብ ማመስገን የተለመደ ነገር አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ከተናገረው ትንቢት አንጻር ይህ ምንም አያስገርምም፤ የአምላክ ቃል እንዲህ ብሏል፦ “በመጨረሻዎቹ ቀኖች ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን [ይመጣል።] ምክንያቱም ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ . . . የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ . . . ይሆናሉ።”​—2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2

ሰዎች ከልባቸው አመስግነውህ ያውቃሉ? ከሆነ ምስጋና ምን ያህል ልብን ደስ እንደሚያሰኝና መንፈስን እንደሚያነቃቃ ታውቃለህ። መጽሐፍ ቅዱስ “[በወቅቱ] የተሰጠ ቃል ምንኛ መልካም ነው!” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 15:23) ቅዱሳን መጻሕፍት አንዳችን ሌላውን በደግነት እንድንይዝ ሊረዱን ይችላሉ።

በሌሎች መልካም ባሕርያት ላይ አተኩር

አምላክ በጥልቅ ስለሚያስብልን መልካም ባሕርያችንን እና ድርጊቶቻችንን የሚያስተውል ከመሆኑም ሌላ ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉ” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (2 ዜና መዋዕል 16:9) አምላክ፣ ሕጎቹን በመታዘዝ ለእሱ ያለንን ፍቅር ስናሳይ ይህን ሳያስተውል እንደማያልፍ ጥርጥር የለውም።

ይሖዋ አምላክ ስህተታችንን አይፈላልግም። እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ ማናችንም በፊቱ መቆም አንችልም ነበር። (መዝሙር 130:3) እንዲያውም ይሖዋ ከተከመረ ድንጋይ ውስጥ የከበሩ ማዕድናትን ለማግኘት በጥንቃቄ እንደሚፈልግ ማዕድን ቆፋሪ ነው። ማዕድን ቆፋሪው አንድ የከበረ ድንጋይ ሲያገኝ በጣም ይደሰታል። ድንጋዩ ከመጽዳቱና ተጠርቦ ከመስተካከሉ በፊት የከበረ ማዕድን ባይመስልም ማዕድን ቆፋሪው ግን ይህ ድንጋይ የሚኖረውን ከፍ ያለ ዋጋ ያውቃል። በተመሳሳይም አምላክ ልባችንን ሲመረምር ለማግኘት የሚፈልገው ውድ ባሕርያትን እንጂ ጉድለቶቻችንን አይደለም። መልካም ባሕርያችንን ፈልጎ ሲያገኝ በጣም ይደሰታል። አንድ ድንጋይ ሲጸዳና ተጠርቦ ቅርጽ ሲይዝ ውድ ማዕድን እንደሚሆን ሁሉ እኛም ያሉንን ባሕርያት ለማሻሻል ጥረት የምናደርግ ከሆነ በእሱ ፊት ውድ እንደምንሆን በሌላ አባባል ታማኝና ለአምላክ ያደርን አምላኪዎቹ እንደምንሆን ይሖዋ ያውቃል።

እኛም ከአምላክ ምሳሌ ልንማር እንችላለን። ብዙ ጊዜ በሌሎች ጉድለት ላይ ማተኮር ይቀናን ይሆናል። ሆኖም ሰዎችን ይሖዋ በሚያይበት መንገድ የምንመለከት ከሆነ መልካም ባሕርያቸውን ለማግኘት እንጥራለን። (መዝሙር 103:8-11, 17, 18) ግለሰቦቹን በደንብ አውቀናቸው መልካም ባሕርያቸውን ስናስተውል ደግሞ ልናመሰግናቸው እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን ምን ውጤት አለው? የምንናገራቸው ቃላት መንፈሳቸውን ሊያድሱላቸውና ትክክለኛ የሆነውን ነገር ለማድረግ ይበልጥ እንዲጥሩ ሊያነሳሷቸው ይችላሉ! እኛም በምላሹ መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ እናጣጥማለን።​—የሐዋርያት ሥራ 20:35

መልካም ድርጊታቸውን እንደምታደንቅ ግለጽ

ኢየሱስ ብዙውን ጊዜ ሌሎች ያከናወኗቸውን መልካም ተግባራት ትኩረት ሰጥቶ ይመለከት እንዲሁም አድናቆቱን ይገልጽ ነበር። በአንድ ወቅት፣ አንዲት የታመመች ሴት ፈውስ ለማግኘት ፈራ ተባ እያለች የኢየሱስን ልብስ በነካች ጊዜ፣ ኢየሱስ “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል” በማለት እምነቷን እንዳደነቀ ገልጾላታል።​—ማርቆስ 5:34

በሌላ ወቅት ደግሞ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ እያስተማረ ሳለ ብዙ ባለጠጋ ሰዎች መባቸውን በመዋጮ ዕቃዎቹ ውስጥ ሲከቱ ተመለከተ። ከዚያም አንዲት ድሃ መበለት “በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች” ስትከት አያት። ከእሷ የበለጠ የሰጡ ሌሎች ሰዎች ነበሩ። ሆኖም ኢየሱስ ይህች ሴት ከልቧ ስለሰጠች እንዲህ በማለት አድናቆቱን ገልጿል፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ይህች መበለት ድሃ ብትሆንም እንኳ ከሁሉ የበለጠ የከተተችው እሷ ነች። ምክንያቱም ሁሉም መባ የከተቱት ከትርፋቸው ነው፤ ይህች ሴት ግን በድሃ አቅሟ ያላትን መተዳደሪያ ሁሉ ከተተች።”​—ሉቃስ 21:1-4

ታዲያ እኛስ ኢየሱስን ልንመስለው የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ማድረግ እየቻልህ ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ አትቈጠብ” በማለት ይናገራል።​—ምሳሌ 3:27

ምስጋና ኃይል አለው

በዛሬው ጊዜ የምንኖረው ምስጋና የለሽ በሆነ ዓለም ውስጥ በመሆኑ ሁላችንም ብንሆን ሌሎች እንዲያደንቁንና እንዲወዱን እንፈልጋለን። ሌሎችን ከልብ በመነጨ ስሜት ስናመሰግናቸው እንዲበረታቱና መንፈሳቸው እንዲታደስ እናደርጋለን። ከልብ የመነጨ ምስጋና፣ ሰዎች አቅማቸው የሚፈቅደውን ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ ያነሳሳቸዋል።​—ምሳሌ 31:28, 29

መጽሐፍ ቅዱስ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ” በማለት ሁሉንም ክርስቲያኖች ይመክራል። (ዕብራውያን 10:24) ሁሉም ሰው ለሌሎች በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት የሚያሳይ፣ የሌሎችን መልካም ባሕርያት ለማየት የሚጥርና ለሚያደርጉት መልካም ነገር አድናቆቱን የሚገልጽ ቢሆን ኖሮ ዓለማችን የተሻለች ቦታ ትሆን ነበር። በእርግጥም ምስጋና ኃይል አለው!

ይህን አስተውለኸዋል?

● ሌሎች ላደረጉት መልካም ነገር አድናቆታችንን መግለጽ የሚገባን ለምንድን ነው?​—ምሳሌ 15:23

● ይሖዋ እኛን ሲመረምር ለማግኘት የሚፈልገው ምንድን ነው?​—2 ዜና መዋዕል 16:9

● ሌሎችን ማመስገን ያለብን መቼ ነው?​—ምሳሌ 3:27

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሌሎችን መልካም ሥራ በማስተዋል አድናቆትህን ትገልጻለህ?