አስገራሚ የሆነው የቢራቢሮ ክንፍ
ንድፍ አውጪ አለው?
አስገራሚ የሆነው የቢራቢሮ ክንፍ
● አንዳንድ ቢራቢሮዎች በክንፋቸው ላይ የሚታየው ማራኪ የሆነ አንጸባራቂ ቀለም እንደሚታይበት አቅጣጫ ይለዋወጣል። አንድ የቢራቢሮ ዝርያ የክንፉ ቀለም በጣም ደማቅና ጥርት ያለ ከመሆኑ የተነሳ ይህን ቢራቢሮ ከ800 ሜትር ከሚበልጥ ርቀት ላይ እንኳ ማየት ይቻላል። የቢራቢሮን ክንፍ ይህን ያህል የተለየ ያደረገው ምንድን ነው?
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ አረንጓዴ ቀለም ያለው ስዋሎቴይል የሚባለው የቢራቢሮ ዝርያ ክንፎች ላይ ስርጉድ ስርጉድ ያለ ቅርጽ ያላቸውና በመደዳ የተደረደሩ በዓይን የማይታዩ ጥቃቅን ቅርፊቶች የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ቅርፊቶች ብርሃንን በተለያየ መንገድ ያንጸባርቃሉ። ለምሳሌ፣ እያንዳንዱ ስርጉድ ያለ የቅርፊቱ ክፍል መሃሉ ላይ ብርሃን ሲያርፍበት ሎሚ የሚመስል ቀለም የሚያንጸባርቅ ሲሆን የቅርፊቱ ጠርዞች ደግሞ ሰማያዊ ቀለም ያንጸባርቃሉ። በተጨማሪም በቅርፊቱ መሃል ላይ የሚያርፈው ብርሃን በቀጥታ ተንጸባርቆ ይመለሳል፤ ዳርና ዳሩ ላይ የሚያርፈው የብርሃን ጨረር ግን ከቅርፊቱ የተለያዩ ጠርዞች ጋር እየተጋጨ ስለሚሄድ የብርሃኑ ሞገድ ይበልጥ ይደምቃል እንዲሁም በተወሰነ መጠን ይጣመማል። በዚህ መንገድ የሚገኘው ቀለም ስትራክቸራል ከለር ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ይህም ቢራቢሮዎቹ በተፈጥሮ ያላቸውን ቀለም ሳይሆን በቅርፊታቸው ቅርጽ ምክንያት የሚፈጠረውን ቀለም ያመለክታል።
ተመራማሪዎች የቢራቢሮን ክንፍ አሠራር ኮርጀው እሱን የሚመስል ቀላል ሞዴል ለመሥራት አሥር ዓመት ፈጅቶባቸዋል። ይህ ዓይነቱ ቴክኖሎጂ፣ የሐሰት ገንዘብንና ክሬዲት ካርድን መሥራት ከባድ እንዲሆን ለማድረግ እንዲሁም በፀሐይ ብርሃን የሚጠቀም ይበልጥ ውጤታማ የሆነ መሣሪያ ለመሥራት እንደሚያስችል ተመራማሪዎች ተስፋ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ የቢራቢሮን ክንፍ አስመስሎ መሥራት ቀላል ነገር አይደለም። በካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ የናኖሳይንስ ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ኡልሪክ ሽታይነ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ስለ ብርሃን ጥልቅ የሆነ ሳይንሳዊ ግንዛቤ ቢኖረንም በተፈጥሮ ላይ የምናያቸው በጣም አስገራሚ የሆኑ የተለያዩ ቀለማት አብዛኛውን ጊዜ በቴክኖሎጂ አማካኝነት ልንፈጥራቸው ከምንችላቸው የቀለም ዓይነቶች እጅግ የላቁ ናቸው።”
ታዲያ ምን ይመስልሃል? የቢራቢሮ ክንፍ እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አረንጓዴ ስዋሎቴይል ቢራቢሮ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቢራቢሮ ክንፍ በአጉሊ መነጽር ሲታይ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Butterfly: Faunia, Madrid; microscopic view: © Eye of Science/Photo Researchers, Inc.