በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወላጆች ምን ይላሉ?

ወላጆች ምን ይላሉ?

ወላጆች ምን ይላሉ?

የጉርምስና ዕድሜ ለብዙ ወላጆች ከዚያ ቀደም የማያውቋቸውን በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያስከትላል። እናንተንም ሆነ ልጃችሁን ግራ ሊያጋባ የሚችለውን ይህን የዕድሜ ክልል ልጃችሁ በተሳካ ሁኔታ እንዲያልፈው ልትረዱት የምትችሉት እንዴት ነው? በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አንዳንድ ወላጆች የሰጡትን አስተያየት እስቲ እንመልከት።

ለውጦች

“ልጄ ትንሽ በነበረበት ወቅት የምሰጠውን ምክር ምንም ሳያንገራግር ይቀበል ነበር። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሲደርስ ግን የእኔን ሥልጣን መቀበል ይከብደው ጀመር። የምናገረው ነገርም ሆነ የምናገርበት መንገድ ትክክል ስለመሆኑ ጥያቄ ያነሳል።”​—ፍራንክ፣ ካናዳ

“ልጄ እንደ ድሮው ብዙ አያወራም። ራሱ ይነግረኛል ብዬ ከመጠበቅ ይልቅ ምን እያሰበ እንዳለ መጠየቅ አለብኝ። ለጥያቄዬ መልስ እንዲሰጥ ማድረግ ቀላል አይደለም። ወዲያውኑ መልስ ባይሰጠኝም መልስ መስጠቱ ግን አይቀርም።”​—ፍራንሲስ፣ አውስትራሊያ

“ትዕግሥት በጣም አስፈላጊ ነው። አንዳንድ ጊዜ ልጆቻችን ላይ ለመጮኽ ብንገፋፋም ረጋ ብለን ከእነሱ ጋር መወያየቱ ምንጊዜም የተሻለ መፍትሔ ሆኖ አግኝተነዋል!”​—ፈሊሸ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

የሐሳብ ልውውጥ

“በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኘው ልጄ ላነጋግራት ስሞክር መከራከር ይቀናታል፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሆን ብዬ ስህተቷን የምለቃቅም ይመስላታል። እንደምወዳት፣ ሁለታችንም የምንፈልገው ነገር ተመሳሳይ እንደሆነና የእሷን ስኬት እንደምመኝ እንድታስታውስ ማድረግ ይኖርብኛል።”​—ሊሳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“ልጆቼ ትናንሽ ሳሉ የልባቸውን በግልጽ ይነግሩኝ ነበር። የሚሰማቸውን እንዲናገሩ ማድረግ ከባድ አልነበረም። አሁን ግን የእነሱ ሁኔታ እንደሚገባኝና እንደ ትልቅ ሰው እንደማከብራቸው ለማሳየት መሞከር ይኖርብኛል። ልባቸውን ሊከፍቱልኝ የሚችሉት በዚህ መንገድ ብቻ ነው።”​—ናንሂ፣ ኮሪያ

“በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች አንዳንድ ነገሮችን እንዳያደርጉ መከልከል ብቻውን በቂ አይሆንም። ምክንያቶቹን ማስረዳትና ልባቸውን ሊነካ የሚችል ትርጉም ያለው ውይይት ማድረግ ያስፈልገናል። ይህን ለማድረግ የሚያስችለው በር ክፍት እንዲሆን ደግሞ መስማት የማንፈልገውን ነገር ቢናገሩም እንኳ የሚሉትን ለመስማት ዝግጁ መሆን ይኖርብናል።”​—ዳሊላ፣ ብራዚል

“ለልጄ ተግሣጽ መስጠት ካስፈለገኝ እርማት የምሰጣት ሌሎች ባሉበት ሳይሆን ለብቻዋ ነው።”​—ኤድና፣ ናይጄሪያ

“አንዳንድ ጊዜ ከልጄ ጋር እየተነጋገርኩ ሳለሁ ቤት ውስጥ በማከናውናቸው ሌሎች እንቅስቃሴዎች ሐሳቤ ይሰረቅና ሙሉ ትኩረት አልሰጠውም። እሱም ይህን ሳያስተውል አልቀረም፤ ከእኔ ጋር ብዙም እንዳያወራ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ ይህ እንደሆነ ይሰማኛል። ከልጄ ጋር በማወራበት ጊዜ ስሜቱን አውጥቶ በግልጽ መናገሩን እንዲቀጥል ይበልጥ በትኩረት ለማዳመጥ መሞከር ይኖርብኛል።”​—ሚርያም፣ ሜክሲኮ

ነፃነት

“በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ለሚገኙት ልጆቼ ነፃነት መስጠት ሁልጊዜ ያስፈራኝ ነበር፤ በዚህም ምክንያት አለመግባባቶች የተነሱባቸው ጊዜያት ነበሩ። ስለ ጉዳዩ ከልጆቼ ጋር በግልጽ ተወያየሁ። ለምን እንደፈራሁ የገለጽኩላቸው ሲሆን እነሱም ተጨማሪ ነፃነት የፈለጉበትን ምክንያት አስረዱኝ። ካስቀመጥኩላቸው ምክንያታዊ የሆኑ ገደቦች ሳይወጡ ተጨማሪ ነፃነት ሊያገኙ በሚችሉባቸው መንገዶች ላይ መስማማት ቻልን።”​—ኤድዊን፣ ጋና

“ልጄ ሞተር ብስክሌት እንዲኖረው ፈለገ። ሐሳቡ ምንም ሊዋጥልኝ ስላልቻለና ስላናደደኝ ስሜቱን ለመግለጽ ዕድል ሳልሰጠው ሞተር ብስክሌት መግዛት የሚያስከትላቸውን ጉዳቶች አንድ በአንድ ዘረዘርኩለት። ይህ ደግሞ እልህ እንዲይዘው ስላደረገው ሞተር ብስክሌት ለማግኘት ቆርጦ ተነሳ! በመሆኑም ሌላ ዘዴ ለመሞከር ወሰንኩ። ከጉዳዩ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ነገሮች ማለትም የሚያስከትለውን አደጋ፣ ወጪውን፣ የመንጃ ፈቃድ ማውጣትና ማሳደስ ያለውን ውጣ ውረድ እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን ከተለያየ አቅጣጫ እንዲመለከት አበረታታሁት። በተጨማሪም በጉባኤያችን ውስጥ ያሉ ጎልማሳ ክርስቲያኖችን እንዲያማክር ነገርኩት። መፈናፈኛ ከማሳጣት ይልቅ ልጄ ስለሚፈልጋቸው ነገሮች በነፃነት እንዲናገር ማበረታታት የተሻለ እንደሆነ ተገነዘብኩ። በዚህ መንገድ ልቡን መንካት ቻልኩ።”​—ሄየንግ፣ ኮሪያ

“ለልጆቻችን ያወጣናቸው ገደቦች ቢኖሩም ቀስ በቀስ ነፃነትም እንሰጣቸው ነበር። ልጆቻችን ያላቸውን ነፃነት ኃላፊነት እንደሚሰማቸው በሚያሳይ መንገድ ሲጠቀሙበት ተጨማሪ ነፃነት እንሰጣቸዋለን። ለልጆቻችን ተጨማሪ ነፃነት ማግኘት የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች በመስጠት ነፃነት እንዲያገኙ እንደምንፈልግ እናሳያቸዋለን፤ በተሰጣቸው ነፃነት ያላግባብ ከተጠቀሙ ግን ከቅጣት አያመልጡም።”—ዶሮቴ፣ ፈረንሳይ

“ምንጊዜም ቢሆን ያወጣኋቸው መሥፈርቶች እንዲከበሩ አደርጋለሁ። ይሁንና ልጆቼ ታዛዥ በሚሆኑበት ጊዜ አስተያየት አደርግላቸዋለሁ። ለምሳሌ አንዳንድ ጊዜ ካወጣሁላቸው የሰዓት እላፊ ገደብ በላይ እንዲቆዩ እፈቅድላቸዋለሁ። የሰዓት እላፊ ገደቡን ከአንድ ጊዜ በላይ ከጣሱ ግን ይቀጣሉ።” —ኢል ሸን፣ ኮሪያ

“አንድ ሠራተኛ ታዛዥና ኃላፊነት የሚሰማው በሆነ መጠን አሠሪው የዚያኑ ያህል አስተያየት ያደርግለታል። ልጄም በተመሳሳይ ከተሰጠው መመሪያ ሳይወጣ ይበልጥ ታዛዥና ኃላፊነት የሚሰማው በሆነ መጠን በጊዜ ሂደት ተጨማሪ ነፃነት ያገኛል። አንድ ሠራተኛ ኃላፊነቱን ሳይወጣ ሲቀር ቅጣት እንደሚደርስበት ሁሉ ልጄም ኃላፊነት እንደሚሰማው በሚያሳይ መንገድ ነፃነቱን ካልተጠቀመበት ሊያጣው እንደሚችል ያውቃል።”​—ራሞን፣ ሜክሲኮ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው፤ በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።”—ምሳሌ 22:6

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

አጭር የቤተሰብ ታሪክ

“በጉርምስና ዕድሜ ያሉ ልጆችን ማሳደግ አስደሳች ነገር እንደሆነ ይሰማኛል”

ጆሴፍ፦ ሁለቱ ትልልቅ ልጆቼ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ይገኛሉ፤ እነሱን መስማትና አመለካከታቸውን መቀበል ጠቃሚ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። እንዲሁም ጉድለቶቼን በሐቀኝነት ማመኔና ከልጆቼ ጋር ስነጋገር ለእነሱ አክብሮት ማሳየቴ የሐሳብ ልውውጥ መስመሩ ክፍት እንዲሆን አስችሏል። በጥቅሉ ሲታይ፣ የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ባገኘነው መመሪያ አማካኝነት በጉርምስና ዕድሜ ያሉ ልጆችን ማሳደግ አስደሳች ነገር እንደሆነ ይሰማኛል።

ሊሳ፦ ትልቋ ልጃችን በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ስትደርስ የእኔ ትኩረት ይበልጥ እንደሚያስፈልጋት ተገነዘብኩ። እሷን በማዳመጥ፣ በማበረታታት እንዲሁም ከእሷ ጋር በመነጋገር ብዙ ጊዜ እንዳሳለፍኩ አስታውሳለሁ። እኔና ባለቤቴ፣ ልጆቻችን የሚሰማቸውን ሁሉ መግለጽ እንደሚችሉና ስሜታቸውንም እንደምናከብርላቸው እንዲያውቁ አድርገናል። “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ መሆን” እንዳለበት የሚናገረውን በ⁠ያዕቆብ 1:19 ላይ የሚገኘውን ምክር ሥራ ላይ ለማዋል እሞክር ነበር።

ቪክቶሪያ፦ እናቴ የቅርብ ጓደኛዬ ነች። የእሷን ያህል ደግና አሳቢ ሰው አላውቅም፤ ደግሞም ለሁሉም ሰው እንዲሁ ናት። እናቴ ከልቧ ጥሩ ሰው ነች ከማለት ሌላ ምንም ማለት አልችልም። ምትክ ሊገኝላት አይችልም።

ኦሊቪያ፦ አባቴ አሳቢና ለጋስ ነው። ለራሳችን የሚበቃ ነገር ባይኖረንም እንኳ ሁልጊዜ ቸር ነው። ቁም ነገረኛ ቢሆንም እንኳ ጨዋታ ያውቃል። በጣም ልዩ አባት ነው፤ የእኔ በመሆኑ እኮራለሁ!

“ፈጽሞ አይደብረንም!”

ሶኒ፦ ልጆቻችን አንድ ዓይነት ችግር ቢያጋጥማቸው በቤተሰብ ደረጃ ቁጭ ብለን እንወያይበታለን። የምናወራው በግልጽ ሲሆን ውይይታችን በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ላይ የተመሠረተ ነው። በተጨማሪም እኔና ኢኔስ ልጆቻችን ጥሩና የጎለመሱ ጓደኞች እንዲኖራቸው እናደርጋለን። የእኛ ጓደኞች የእነሱ ጓደኞች፣ የእነሱ ጓደኞች ደግሞ የእኛ ጓደኞች ናቸው።

ኢኔስ፦ በቤተሰብ ደረጃ አንድ ላይ ሆነን የተለያዩ ነገሮችን እናከናውናለን። የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናችን በአገልግሎት እንዲሁም በግልና በቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምንጠመድ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ አደጋ በደረሰባቸው አካባቢዎች እርዳታ እንደ መስጠትና በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ እንደ መካፈል ባሉ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች እንሳተፋለን። የዚያኑ ያህል ደግሞ አስደሳች በሆነ መዝናኛ እንካፈላለን። በመሆኑም ፈጽሞ አይደብረንም!

ከልሲ፦ አባቴ ጥሩ አዳማጭ ነው፤ ማንኛውንም ትልቅ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት መላውን ቤተሰብ ያማክራል። እናቴም ብትሆን እርዳታ የሚሰጠኝ ወይም የማዋራው ሰው ሲያስፈልገኝ ሁልጊዜ ከጎኔ ናት።

ሰማንታ፦ እናቴ፣ እሷ ባታስተውለውም እንኳ በጣም ልዩና ተፈላጊ እንደሆንኩ ብሎም እንደምወደድ እንዲሰማኝ ታደርጋለች። ታዳምጠኛለች እንዲሁም ታስብልኛለች። ከእሷ ጋር ያለኝን ወዳጅነት በምንም ነገር መለወጥ አልፈልግም።

[ሥዕሎች]

የካሜረ ቤተሰብ፦ ጆሴፍ፣ ሊሳ፣ ቪክቶሪያ፣ ኦሊቪያ እና ኢዛቤላ

የሳፓታ ቤተሰብ፦ ከልሲ፣ ኢኔስ፣ ሶኒ እና ሰማንታ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች መጠነኛ የሆነ ነፃነት ቢሰጡም ምክንያታዊ የሆኑ ገደቦችንም ያስቀምጣሉ