በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሽብርተኝነት የሌለበት ዓለም ይመጣ ይሆን?

ሽብርተኝነት የሌለበት ዓለም ይመጣ ይሆን?

ሽብርተኝነት የሌለበት ዓለም ይመጣ ይሆን?

“የሰዎችን ልብና አእምሮ ለመለወጥ . . . መታገል ያስፈልገናል።” እዚህ ድምዳሜ ላይ የተደረሰው አሸባሪዎች እንደሆኑ በሚታሰቡ ሰዎች የኋላ ታሪክ ላይ ለ20 ዓመት ያህል ጥናት ከተካሄደ በኋላ ነው።

ይሁን እንጂ ዓመፅ የተሞላበትና የበቀለኝነት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ድርጊት ሲፈጽሙ የኖሩ ሰዎችን ልብና አእምሮ ምን ሊለውጠው ይችላል?

ልብን መለወጥ የሚችል መጽሐፍ

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሃፌኒ በ1990ዎቹ ዓመታት ውስጥ ሃይማኖቱን መመርመር የጀመረ ሲሆን የራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ለማግኘት ወሰነ። እንዲህ ብሏል፦ “መጀመሪያ ስለ ኢየሱስ የሕይወት ታሪክ የሚዘግቡትን ወንጌሎች [ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ የተባሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት] አነበብኩ። እነዚህን ወንጌሎች ሳነብ ቀልቤን የሳበው የኢየሱስ ባሕርይ እንዲሁም ሰዎችን በደግነትና ከአድሎ ነፃ በሆነ መንገድ የሚይዝ መሆኑ ነበር። ይህም በጣም አስደሰተኝ።”

ሃፌኒ ንባቡን ሲቀጥል ምን እንዳገኘ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኝ አንድ ጥቅስ ይኸውም የሐዋርያት ሥራ 10:34 እና 35 የአምላክን ስሜት በደንብ ለመረዳት አስቻለኝ።” ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ [አያዳላም]፤ . . . ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።”

ሃፌኒ እንዲህ ብሏል፦ “የተለያየ ጎሣ፣ ብሔርና ዘር ባላቸው ሰዎች መካከል ለሚታየው ጭፍን ጥላቻ ተጠያቂዎቹ ሰዎች ራሳቸው እንደሆኑ ተገነዘብኩ። የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት የሰዎችን አስተሳሰብ ሊለውጥ እንደሚችል እንዲሁም በሕይወት ውስጥ ከሁሉ በላይ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ነገር በአምላክ ፊት ጥሩ አቋም ይዞ መገኘት እንደሆነ ተረዳሁ። ይህም አንድ ዓይነት የቆዳ ቀለም፣ ጎሣ ወይም ዘር ላለው ሕዝብ ከመዋጋት ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነው።”

ባለፈው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ሆሴባ አንድን ፖሊስ ጣቢያ በቦምብ የማፈንዳት ዕቅድ የነበረው አንድ ትንሽ ቡድን መሪ ነበር። “ሆኖም ይህን ጥቃት ከመፈጸማችን በፊት ተያዝኩና በወህኒ ቤት ሁለት ዓመት አሳለፍኩ” በማለት ሆሴባ ተናግሯል። ከጊዜ በኋላ ባለቤቱ ሉሲ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ውሎ አድሮ ሆሴባም በውይይቱ ላይ መገኘት ጀመረ።

ሆሴባ እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ኢየሱስ ይበልጥ እያወቅሁ ስሄድ የእሱን አርዓያ መከተል ፈለግሁ። ኢየሱስ ከተናገራቸው ነገሮች መካከል ‘ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ’ የሚለው ሐሳብ ልቤን ነካው። ይህ እውነት መሆኑን አውቅ ነበር።” (ማቴዎስ 26:52) አክሎም እንደሚከተለው ብሏል፦ “አንድን ሰው መግደል የሟቹ ቤተሰቦች ጥላቻ እንዲያድርባቸውና ለመበቀል እንዲነሳሱ ከማድረግ በቀር ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም። ዓመፅ መከራ እንጂ የተሻለ ዓለም አያመጣም።” ሆሴባም አስተሳሰቡን ማስተካከል ጀመረ።

ሃፌኒም ሆነ ሆሴባ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የአንድን ሰው ሕይወት ለመለወጥ የሚያስችል ኃይል እንዳለው ከራሳቸው ሕይወት ተገንዝበዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው፤ . . . የልብንም ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል” ይላል። (ዕብራውያን 4:12) የአምላክ ቃል ያለው ኃይል ብዙ ሰዎች አስተሳሰባቸውንና አኗኗራቸውን እንዲያስተካክሉ ረድቷቸዋል። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ተግባራዊ በሚያደርጉ ሰዎች መካከል ዓለም አቀፍ አንድነት መኖሩን የሚያሳይ ማስረጃ አለ?

በፍቅር ላይ የተመሠረተ ወንድማማችነት

ሃፌኒ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ መገኘት ሲጀምር የተለያየ ዘር ባላቸው ሰዎች መካከል ሰላምና አንድነት ሰፍኖ በማየቱ ልቡ በጥልቅ ተነካ። “ከነጮች ጎን መቀመጥ ልዩ ስሜት ፈጠረብኝ” ብሏል። “በሕይወቴ ሙሉ አንድን ነጭ ሰው ወንድም ብዬ የመጥራት አጋጣሚ ይኖረኛል ብዬ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም ነበር። ይህም እውነተኛ ሃይማኖት ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ያለኝን እምነት አጠናከረው። ለረጅም ጊዜ ስጓጓለት የነበረውን አንድነት በመካከላቸው ተመለከትሁ፤ በዘር ቢለያዩም እርስ በርስ ፍቅር ነበራቸው።”

ኢየሱስ፣ እውነተኛ ተከታዮቹ ‘በመካከላቸው ባለው ፍቅር’ ተለይተው እንደሚታወቁ ተናግሯል። (ዮሐንስ 13:34, 35) በተጨማሪም ኢየሱስ በፖለቲካዊ ግጭቶች ለመካፈል ፈቃደኛ ያልነበረ ሲሆን ለደቀ መዛሙርቱም ‘የዓለም ክፍል አይደላችሁም’ ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 6:15፤ 15:19፤ ማቴዎስ 22:15-22) በዚያን ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች ተለይተው የሚታወቁት እርስ በርስ ባላቸው ፍቅርና ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ በመሆናቸው ነበር፤ ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

ኢየሱስ ያስተማረውን ተግባራዊ ማድረግ

ይሁንና አሸባሪነት እየተስፋፋና በዓለም ላይ መከፋፈልን እየፈጠረ ባለበት በዚህ ዘመን እንኳ ፍቅር ማሸነፍ የሚችለው እንዴት ነው? ፖለቲካዊ ውዝግቦች ጠላትነት የሚፈጥሩ ሲሆን ሰዎች ለዘራቸው፣ ለብሔራቸው ወይም ለጎሣቸው ያላቸው ታማኝነት ብዙውን ጊዜ አንዳቸው በሌላው ላይ እንዲነሱ አሊያም መንግሥታት እርስ በርስ እንዲጋጩ ያደርጋቸዋል።

ለምሳሌ ያህል፣ በ1914 ጋቭሪሎ ፕሪንትሲፕ የተባለው ሰው፣ የኦስትሮ ሃንጋሪ ጥምር መንግሥት አልጋ ወራሽ የነበረውን አርክዱክ ፍራንሲስ ፈርዲናንድን እንዲገድል ያነሳሳው የዘር ኩራት ነበር። ፕሪንትሲፕ “ጥቁር እጅ” ተብሎ የሚጠራው ድርጅት አባል የነበረ ሲሆን የዚህ ድርጅት የመተዳደሪያ ደንብ እንደሚለው ከሆነ ድርጅቱ ዓላማውን ለማሳካት “በማኅበረሰባዊ እንቅስቃሴዎች ከመሳተፍ ይልቅ . . . አብዮትን” ይመርጣል። የአልጋ ወራሹ መገደል፣ ክርስቲያን ነን በሚሉ አገሮች መካከል ጦርነት እንዲቀሰቀስ አድርጓል፤ ይህም ለአንደኛ የዓለም ጦርነት መነሳት እንዲሁም “የሰላም ልዑል” የሆነው የኢየሱስ ተከታዮች ነን ለሚሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ታጣቂዎች መሞት ምክንያት ሆኗል።​—ኢሳይያስ 9:6

ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ሃሪ ኢመርሰን ፎስዲክ የሚባሉ አንድ ታዋቂ ቄስ፣ ክርስቲያን ነን የሚሉ መሪዎችን አባሎቻቸው የኢየሱስን ምሳሌ እንዲከተሉ ባለማስተማራቸው አውግዘዋቸዋል። እኚህ ቄስ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ሰዎችን ለጦርነት ቀስቅሰናል። . . . ጦረኞችን እንደ ጀግና አድርገን ተቀብለናቸዋል፤ አልፎ ተርፎም በቤተ ክርስቲያኖቻችን ላይ የጦርነት ባንዲራ አውለብልበናል።” ፎስዲክ ሐሳባቸውን ሲያጠቃልሉ “በአንድ በኩል የሰላሙን ልዑል እያሞገስን በሌላው በኩል ጦርነትን አወድሰናል” ብለዋል።

ከዚህ በተቃራኒ በ1975 በታተመ አንድ የኅብረተሰብ ጥናት ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ ወጥቶ ነበር፦ “የይሖዋ ምሥክሮች በሁለቱ ታላላቅ የዓለም ጦርነቶች ወቅት እንዲሁም ከዚያ በኋላ ‘በቀዝቃዛው ጦርነት’ ዘመን በተካሄዱ ወታደራዊ ግጭቶች ላይ ከዓመፅ በመራቅ ምንጊዜም ‘ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት’ አቋማቸውን ጠብቀዋል።” የይሖዋ ምሥክሮች እንግልት ቢደርስባቸውም ሆነ ቢታሰሩ “አጸፋውን ለመመለስ በዓመፅ ድርጊት ፈጽሞ አልተካፈሉም።” የጥናቱ ማጠቃለያ እንዲህ ይላል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ትምህርት የተመሠረተው፣ መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ መሪነት የተጻፈ የአምላክ ቃል እንደሆነ ባላቸው እምነት ላይ ነው።”

የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ተግባራዊ ማድረግ ያለው ጥቅም

ለአንድ የቀድሞ የቤልጅየም ጠቅላይ ሚኒስትር፣ እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተሰኘውን ስለ ኢየሱስ ሕይወት የሚናገር መጽሐፍ አንድ ጎረቤታቸው ሰጥቷቸው ነበር። እኚህ ሰው ባነበቡት ነገር ልባቸው በጥልቅ ስለተነካ ለጎረቤታቸው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ሰዎች የወንጌልን መልእክት ለመስማት ይበልጥ ፍላጎት ቢያሳድሩና ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ቢያደርጉ ኖሮ ዛሬ ያለው ዓለም ፈጽሞ የተለየ ገጽታ እንደሚኖረው ግልጽ ነው።”

አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “የጸጥታው ምክር ቤት ባላስፈለገ እንዲሁም የአሸባሪዎች ጥቃትና ዓመፅ በዓለም ላይ ቦታ ባልኖራቸው ነበር።” ሆኖም “ይህ ሁሉ የሕልም እንጀራ ነው” በማለት ደምድመዋል። ይሁን እንጂ ይህ እውነት ነው? በዚህ በዓመፅ በተሞላ ዓለም ውስጥም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ ዘርና አስተዳደግ ያላቸው ብዙ ሰዎች ከዓመፅ እንዲርቁ አስችሏቸዋል፤ እንዲሁም ሰዎች ለበርካታ አሥርተ ዓመታት የዘለቀ ገደብ የሌለው ደም መፋሰስ በመመልከታቸው በውስጣቸው የሚፈጠረውን ምሬት እንዲያሸንፉ ረድቷቸዋል።

በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው አንድሬ የበርካታ ጓደኞቹን ሕይወት ከቀጠፈው የቦምብ ፍንዳታ የተረፈው ለጥቂት ነበር። ቦምቡን ያጠመደው አንድ የታጣቂዎች ቡድን ነበር። ከጊዜ በኋላ አንድሬ “በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር የተማረ ሲሆን ይህንንም በሕይወቱ ውስጥ ተግባራዊ አደረገው። (ቆላስይስ 3:13) የአንድሬን ጓደኞች ሕይወት የቀጠፈው የቦምብ ፍንዳታ ከተከሰተ ከዓመታት በኋላ ሃፌኒ ይህን ቦምብ ያጠመደው የታጣቂዎች ቡድን አባል ሆነ፤ ከጊዜ በኋላ ሃፌኒ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ስለተማረ ከዓመፅ ድርጊቶች ራቀ። (መዝሙር 11:5) አሁን አንድሬም ሆነ ሃፌኒ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው፤ ሁለቱም በአንድ የአፍሪካ አገር ውስጥ በሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች የትርጉም ቢሮ ውስጥ አብረው ይሠራሉ።

ወደፊት የተረጋጋ ሕይወት እንደሚኖር መተማመን

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታቸው የተረጋጋ የወደፊት ሕይወት ማግኘት እንደሚችሉ እንዲተማመኑ አድርጓቸዋል። አንድሬ ያጋጠመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ አንድ ቀን አንድሬ፣ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንደሚመጣ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ለጎረቤቱ እየነገረው ነበር። (ኢሳይያስ 2:4፤ 11:6-9፤ 65:17, 21-25፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) በድንገት፣ መሣሪያ የታጠቁ ወታደሮች ቤቱን ከበቡት፤ ከዚያም አንድሬን ለጥያቄ ስለፈለጉት ከቤት እንዲወጣ አዘዙት። አንድሬ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ እንደሆነና ጎረቤቱ እንደሚያደንቀው ሲያውቁ ግን ወታደሮቹ ትተዉት ሄዱ።

ወታደሮቹ በመጡበት ወቅት አንድሬ፣ አምላክ በኖኅ ዘመን ‘ምድር በዐመፅ በተሞላች’ ጊዜ እንዳደረገው ሁሉ ወደፊትም እርምጃ እንደሚወስድ ለጎረቤቱ እየነገረው ነበር። (ዘፍጥረት 6:11) አምላክ ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ በማምጣት በዚያን ወቅት የነበረውን ዓለም ያጠፋው ሲሆን ሰላም ወዳድ የነበረውን ኖኅን ግን ከነቤተሰቡ አትርፎታል። ኢየሱስ “በኖኅ ዘመን እንደነበረው ሁሉ የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል” ብሏል።​—ማቴዎስ 24:37-39

“የሰው ልጅ” የተባለው ኢየሱስ በሰማይ በሚገኘው የአምላክ መንግሥት ላይ እንዲገዛ አምላክ የመረጠው ንጉሥ ሲሆን በቅርቡም በሰማይ የሚገኘውን የአምላክ ሠራዊት በመምራት ዓመፅን ከምድር ላይ ያስወግዳል። (ሉቃስ 4:43) በኢየሱስ አገዛዝ ወቅት ‘ጽድቅና ሰላም ይሰፍናል’ ወይም አገዛዙ ፍትሐዊ ይሆናል። እንዲሁም ተገዢዎቹን “ከጭቈናና ከግፍ ያድናል።”​—መዝሙር 72:7, 14

በመጨረሻም፣ ጽድቅን የሚወዱና የዚህ ሰማያዊ ንጉሥ ተገዢ የሚሆኑ ሁሉ ምድር ሰላም የሰፈነባት ገነት ስትሆን ይመለከታሉ። (ሉቃስ 23:42, 43) መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሰላምና ፍትሕ በተራሮችና በኰረብቶች ላይ እንደሚገዙ’ ቃል ገብቷል።​—መዝሙር 72:1-3 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን

እንዲህ ባለ ንጉሥ በሚተዳደር ዓለም ውስጥ ለመኖር አትጓጓም? በእርግጥም በዚያ ዓለም ውስጥ ሽብርተኝነት ጨርሶ አይኖርም።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሃፌኒም ሆነ ሆሴባ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የአንድን ሰው ሕይወት ለመለወጥ የሚያስችል ኃይል እንዳለው ከራሳቸው ሕይወት ተገንዝበዋል

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘ሰዎች፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ቢያደርጉ ኖሮ ዛሬ ያለው ዓለም ፈጽሞ የተለየ ገጽታ ይኖረው ነበር። የጸጥታው ምክር ቤት ባላስፈለገ እንዲሁም የአሸባሪዎች ጥቃትና ዓመፅ በዓለም ላይ ቦታ ባልኖራቸው ነበር።’​—የቀድሞው የቤልጅየም ጠቅላይ ሚኒስትር

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሃፌኒ እና አንድሬ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረጋቸው አንዳቸው ለሌላው እውነተኛ ፍቅር እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል