ባሪያዎች የተጓዙበትን መንገድ መጎብኘት
ባሪያዎች የተጓዙበትን መንገድ መጎብኘት
ከ17ኛው እስከ 19ኛው መቶ ዘመን ባለው ጊዜ ውስጥ የዊደ ከተማ በምዕራብ አፍሪካ ዋነኛ የባሪያ ንግድ ማዕከል ሆና አገልግላለች። በአሁኑ ጊዜ የቤኒን ሪፑብሊክ ተብሎ በሚጠራው አገር ውስጥ ከምትገኘው ከዊደ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ባሪያዎች ወደ ሌሎች አገሮች ተልከዋል። ብዙውን ጊዜ አፍሪካውያኑ ራሳቸው የአልኮል መጠጥ፣ ልብስ፣ አምባሮች፣ ቢላዎች፣ ጎራዴዎችና በተለይም በጎሣዎች መካከል ለሚደረጉ ጦርነቶች በጣም ተፈላጊ የነበሩትን ጠመንጃዎች ለማግኘት ሲሉ የአገራቸውን ሰዎች እንደ ዕቃ ይሸጧቸው ነበር።
በአዲሱ ዓለም (በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ) ውስጥ በእርሻና በማዕድን ማውጫዎች ላይ የሚሠሩ ባሪያዎች ያስፈልጉ ስለነበር በ16ኛውና በ19ኛው መቶ ዘመን መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ በግምት 12 ሚሊዮን የሚሆኑ አፍሪካውያን በመርከብ ተጭነው የአትላንቲክን ውቅያኖስ አቋርጠዋል። አሜሪካን ስሌቨሪ—1619-1877 የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚገልጸው 85 በመቶ የሚሆኑት ባሪያዎች “ወደ ብራዚልና በካሪቢያን ደሴቶች ወደሚገኙ የተለያዩ የብሪታንያ፣ የፈረንሳይ፣ የስፔንና የደች ቅኝ ግዛቶች ተልከዋል።” ስድስት በመቶ ገደማ የሚሆኑት ደግሞ ከጊዜ በኋላ የዩናይትድ ስቴትስ ክፍል ወደሆኑት ቅኝ ግዛቶች ተልከዋል። *
አብዛኞቹ ባሪያዎች በጉዟቸው መጀመሪያ ላይ በሰንሰለት ይታሰሩ፣ ይገረፉና በእሳት በመተኮስ ምልክት ይደረግባቸው ነበር፤ ከዚያም በአሁኑ ጊዜ የዊደ የታሪክ ቤተ መዘክር እንዲሆን እንደገና ከተገነባው ምሽግ ጀምሮ በባሕሩ ዳር እስከቆመው ‘የማይመለሱበት በር’ ተብሎ የሚጠራ ቦታ ድረስ ያለውን የ4 ኪሎ ሜትር መንገድ በእግራቸው ይጓዛሉ። ይህ በር ባሪያዎቹ በአፍሪካ ምድር የሚያደርጉት ጉዞ መጠናቀቁን ያመለክታል። በእርግጥ ሁሉም ባሪያዎች የሚወጡት በዚህ በኩል ስላልሆነ ይህ በር ምሳሌያዊ ትርጉም ያለው ነበር። ይሁንና የባሪያ ንግድ ይህን ያህል የተስፋፋው ለምን ነበር?
ለረጅም ጊዜ የዘለቀ አስቀያሚ ታሪክ
በጥንት ዘመናት የአፍሪካ ገዥዎች የጦር ምርኮኞችን ለአረብ ነጋዴዎች ይሸጡ ነበር። ከጊዜ በኋላ ኃያላን የሆኑ የአውሮፓ መንግሥታት በተለይ ደግሞ በአሜሪካ አህጉራት ቅኝ ግዛቶች ከመሠረቱ በኋላ በባሪያ ንግድ መካፈል ጀመሩ። በዚያን ጊዜ በሚደረጉት የጎሣ ጦርነቶች የሚማረኩት ሰዎች ባሪያ ይደረጉ ስለነበር ጦርነት ለድል አድራጊዎቹም ሆነ ለስግብግብ የባሪያ ነጋዴዎች አትራፊ ንግድ ሆኖላቸው ነበር። በተጨማሪም ሰዎችን አፍኖ በመውሰድ ባሪያ ማድረግ ወይም ባሪያዎችን ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ከሚያመጡ አፍሪካውያን ነጋዴዎች መግዛት ይቻል ነበር። ማንኛውም ሰው ሌላው ቀርቶ
የንጉሡን ሞገስ ያጣ መስፍን እንኳ ባሪያ ሆኖ ሊሸጥ ይችል ነበር።ብራዚላዊው ፍራንሲስኩ ፌሊክስ ደ ሶዘ በጣም የታወቀ የባሪያ ነጋዴ ነበር። ደ ሶዘ፣ የዊደ የባሪያ ገበያ ማዕከል የሆነውን ምሽግ በ1788 ተቆጣጠረው፤ ይህ ምሽግ የሚገኘው በቤኒን የባሕር ወሽመጥ ላይ ነበር። በዚያን ጊዜ ዊደ በደሆሜ መንግሥት ሥር ነበረች። ይሁን እንጂ በደ ሶዘ እና በደሆሜው ንጉሥ በአዳንዶዛን መካከል አለመግባባት ተፈጠረ። በመሆኑም ደ ሶዘ (በእስር ቤት እያለ ሳይሆን አይቀርም) ከንጉሡ ወንድም ጋር በማሴር በ1818 ንጉሡን ገለበጡት። በዚህ መንገድ በአዲሱ ንጉሥ በጌዞ እና በባሪያ ንግድ ላይ በኃላፊነት በተሾመው በደ ሶዘ መካከል የተመሠረተው ግንኙነት ከፍተኛ ትርፍ አስገኝቶላቸዋል። *
ጌዞ ግዛቱን የማስፋፋት ዓላማ የነበረው ሲሆን ይህን እውን ለማድረግ የአውሮፓውያን የጦር መሣሪያዎች ያስፈልጉት ነበር። በመሆኑም ከአውሮፓውያን ጋር የሚደረገውን የንግድ ልውውጥ እሱን ወክሎ እንዲቆጣጠርለት በዊደ ላይ ደ ሶዘን ሾመው። ደ ሶዘ በዚህ የአፍሪካ ክፍል የሚካሄደውን የባሪያ ንግድ ሙሉ በሙሉ ስለተቆጣጠረው ብዙም ሳይቆይ ከፍተኛ ሀብት አጋበሰ፤ እንዲሁም በቤቱ አቅራቢያ የሚገኘው የባሪያ ገበያ፣ ባሪያዎችን ለመግዛት ከሌሎች አገሮችና ከአካባቢው የሚመጡ ሸማቾች መናኸሪያ ሆነ።
በእንባ የራሰ መንገድ
በዛሬው ጊዜ የዊደን የባሪያ መንገድ የሚጎበኙ ሰዎች ጉብኝታቸውን የሚጀምሩት እንደ አዲስ ከተገነባው የፖርቹጋል ምሽግ ነው። ይህ ምሽግ መጀመሪያ የተገነባው በ1721 ሲሆን ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በአሁኑ ጊዜ በቤተ መዘክርነት ያገለግላል። ባሪያዎች በግቢው መሃል በሚገኝ ሰፊ ቦታ ላይ ታስረው ይቆዩ ነበር። አብዛኞቹ እዚህ ቦታ ላይ ከመድረሳቸው በፊት አንድ ላይ በሰንሰለት ታስረው ለበርካታ ሌሊቶች በእግራቸው ተጉዘዋል። በሌሊት የሚጓዙት ለምን ነበር? ጨለማው ባሪያዎቹ የሚጓዙበትን አቅጣጫ እንዳያውቁትና አምልጠው ወደ ቤታቸው መመለስ አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው ስለሚያደርግ ነው።
ብዛት ያላቸው ባሪያዎች እዚህ ቦታ ላይ ሲደርሱ ጨረታ ይካሄዳል፤ ከዚያም ነጋዴዎቹ የገዟቸውን ባሪያዎች በእሳት በመተኮስ ምልክት ያደርጉባቸዋል። ወደ ሌላ አገር የሚላኩት ባሪያዎች ወደ ባሕሩ ዳርቻ ከተወሰዱ በኋላ በታንኳዎች ወይም በትንንሽ ጀልባዎች ተጭነው ወደ መርከቦቹ ይወሰዱ ነበር።
ከታሪካዊው የባሪያ መንገድ ጋር በተያያዘ ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት ሌላው ስፍራ ደግሞ ‘የመርሳት ዛፍ’ ተብሎ የሚጠራው ዛፍ የነበረበት ቦታ ነው። ይህን ዛፍ ወንዶቹ ባሪያዎች ዘጠኝ ጊዜ ሴቶቹ ደግሞ ሰባት ጊዜ እንዲዞሩ ይገደዱ እንደነበር ይነገራል፤ በዛሬው ጊዜ ዛፉ በነበረበት ቦታ ላይ የመታሰቢያ ሐውልት ቆሟል። ባሪያዎቹ ዛፉን መዞራቸው የትውልድ አገራቸውን ትዝታ ከአእምሯቸው እንደሚያጠፋላቸውና ይህም ለማመፅ እንዳይነሳሱ እንደሚያደርጋቸው ይነገራቸው ነበር።
በተጨማሪም በባሪያዎቹ መንገድ ላይ ዞማኢ የሚባሉትን ጎጆዎች ለማስታወስ የቆመ ሐውልት አለ፤ እነዚህ ጎጆዎች በአሁኑ ጊዜ የሉም። ዞማኢ የሚለው ቃል ጎጆዎቹ ምንጊዜም
በጨለማ የተዋጡ መሆናቸውን የሚያመለክት ሲሆን ባሪያዎቹ በዚህ ቦታ ታጭቀው መቀመጣቸው በመርከብ ተጭነው በሚጓዙበት ጊዜ የሚደርስባቸውን እንግልት እንዲለማመዱ ያደርጋቸዋል። ባሪያዎቹ ወደ ሌላ አገር እስከሚላኩ ድረስ በእነዚህ ጎጆዎች ውስጥ ለወራት ሊቆዩ ይችላሉ። ይህን አሰቃቂ ሁኔታ መቋቋም አቅቷቸው የሚሞቱት ባሪያዎች በአንድ የጅምላ መቃብር ውስጥ ይጣሉ ነበር።ይበልጥ አሳዛኝ ትውስታ የሚፈጥረው ደግሞ የንስሐና የእርቅ ተምሳሌት የሆነው ዞማቺ ተብሎ የሚጠራው ሐውልት ነው። በዚህ ስፍራ በየዓመቱ ጥር ወር ላይ የባሪያዎቹም ሆኑ የባሪያ ነጋዴዎቹ ዘሮች፣ ያንን ግፍ ለፈጸሙት ሰዎች ምሕረት ይለምኑላቸዋል።
በዚህ ጉብኝት መጨረሻ ላይ የሚገኘው ‘የማይመለሱበት በር’ የሚባል ቅስት ሲሆን ይህም ባሪያዎቹ በአፍሪካ መሬት የሚኖራቸውን የመጨረሻ ቆይታ የሚያመለክት መታሰቢያ ነው። በዚህ ግዙፍ ቅስት ላይ በሰንሰለት የታሰሩ አፍሪካውያን በሁለት ረድፍ ሆነው ከፊት ለፊታቸው ወዳለው የአትላንቲክ ውቅያኖስ ሲጎርፉ የሚያሳይ ምስል ተቀርጾበታል። እዚህ ቦታ ላይ አንዳንድ ተስፋ የቆረጡ ባሪያዎች የትውልድ አገራቸውን ለማስታወስ በሚል አሸዋ እንደቃሙ ይነገራል። ሌሎች ደግሞ ሞትን በመምረጥ በራሳቸው ሰንሰለት ታንቀው ሞተዋል።
ነፃ መውጣት!
ከ1800ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ባርነትን ለማስቀረት የሚደረጉ ጥረቶች እየጨመሩ ሄዱ። ከዊደ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በጀልባ ተጭነው የመጡት የመጨረሻዎቹ ባሪያዎች በሞቢል፣ አላባማ ከተማ የደረሱት ሐምሌ 1860 ነበር። ይሁን እንጂ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በ1863 የነፃነት አዋጅ ስላወጣ እነዚህ ሰዎች በባርነት ያገለገሉት ለአጭር ጊዜ ነበር። በመጨረሻም ብራዚል በባርነት ማገልገል እንዲቀር ስታደርግ ይህ ዓይነቱ ልማድ በምዕራባዊው ንፍቀ ክበብ በ1888 አበቃ። *
የባሪያ ንግድ ከተወው አሻራ ሁሉ ጎልቶ የሚታየው ከአፍሪካ የፈለሰው ስፍር ቁጥር የሌለው ሕዝብ ነው፤ ይህ ሕዝብ በአሜሪካ አህጉራት በሚገኙ በርካታ አገራት የሕዝብ ብዛትና ባሕል ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ሌላው አሻራ ደግሞ ከአስማትና ከድግምት ጋር የተያያዘው ቩዱ የሚባለው ሃይማኖት መስፋፋት ሲሆን ይህ ሃይማኖት በተለይ በሄይቲ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አለው። “ቩዱ የሚለው ቃል” ይላል ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ “ቮደን ከሚለው ቃል የተወሰደ ሲሆን ቃሉ በቤኒን (የቀድሞዋ ደሆሜ) በሚገኙ ፎን በሚባሉ ሕዝቦች ቋንቋ አንድን አምላክ ወይም መንፈስ ያመለክታል።”
የሚያሳዝነው ነገር፣ ሁልጊዜ ቃል በቃል ባይሆንም እንኳ ባርነት በዛሬው ጊዜም አለ። ለምሳሌ ያህል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከባድ የኢኮኖሚ ችግርን ለመወጣት ሲሉ ከባርነት ያልተናነሰ ሕይወት ይመራሉ። አንዳንዶች ጨቋኝ በሆኑ ፖለቲካዊ አገዛዞች ሥር ይማቅቃሉ። (መክብብ 8:9) ሌሎች በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶችና የአጉል እምነቶች ባሪያ ናቸው። ታዲያ ሰብዓዊ መንግሥታት ዜጎቻቸውን ከእንደነዚህ ዓይነት ባርነቶች ነፃ ማውጣት ይችላሉ? በጭራሽ። ይህን ማድረግ የሚችለው ይሖዋ አምላክ ብቻ ሲሆን እሱም ያለ ምንም ጥርጥር ይህን ያደርጋል! በእርግጥም፣ ነፃ ከሚያወጣው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር በሚስማማ መንገድ ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች ሁሉ አንድ ቀን “የአምላክን ልጆች ክብራማ ነፃነት” እንደሚያገኙ አምላክ በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ቃል ገብቶልናል።—ሮም 8:21፤ ዮሐንስ 8:32
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 በዩናይትድ ስቴትስ የነበሩት ባሪያዎች ቁጥር በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ መጀመሪያ ላይ አነስተኛ የነበረ ቢሆንም ባሪያዎቹ እየተዋለዱ መሄዳቸው ከጊዜ በኋላ ቁጥራቸው በጣም እንዲጨምር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።
^ አን.7 “ጌዞ” የሚለው ስም በተለያየ መንገድ ይጻፋል።
^ አን.17 መጽሐፍ ቅዱስ ባርነትን በተመለከተ ምን እንደሚል ለማወቅ በጥቅምት 2001 ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት፦ አምላክ የባሪያ ንግድን አቅልሎ ይመለከተዋልን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
“ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ አለ”
የባሪያ ነጋዴዎች፣ ሰለባዎቻቸውን ያገኙ የነበሩት መንደሮችን በመውረርና የፈለጉትን ሰው አፍነው በመውሰድ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ። ይህ እውነት ሊሆን ቢችልም “የአፍሪካ መሪዎችንና ነጋዴዎችን ያካተተ በጣም የተደራጀ የግንኙነት መስመር ባይኖር ኖሮ” ባሪያ ፈንጋዮች በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በባርነት ማጋዝ እንደማይችሉ የአፍሪካ ታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሮበርት ሀርምስ በተደረገላቸው የሬዲዮ ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል። “ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ አለ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ምንኛ እውነት ነው!—መክብብ 8:9
[የሥዕሉ ምንጭ]
© Réunion des Musées Nationaux/Art Resource, NY
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
በግምት 12 ሚሊዮን የሚሆኑ አፍሪካውያን በባርነት ለማገልገል በመርከብ ተጭነው አትላንቲክን ተሻግረዋል
አፍሪካ
ቤኒን
ዊደ
የባሪያ ጠረፍ
[በገጽ 22 እና 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1721 የተገነባው ይህ የፖርቹጋል ምሽግ በአሁኑ ጊዜ የዊደ የታሪክ ቤተ መዘክር ሆኖ ያገለግላል
[የሥዕሉ ምንጭ]
© Gary Cook/Alamy
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የታሰረና አፉ የተለጎመ ባሪያን የሚያሳይ ሐውልት
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘የማይመለሱበት በር’—ባሪያዎቹ በአፍሪካ መሬት የሚኖራቸውን የመጨረሻ ቆይታ የሚያመለክት መታሰቢያ
[የሥዕሉ ምንጭ]
© Danita Delimont/Alamy