ልጆች ካንሰር ሲይዛቸው
ልጆች ካንሰር ሲይዛቸው
“በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተውጬ ነበር። የምረግጠው መሬት የከዳኝ መሰለኝ። ትንሿ ልጄ ሞተች የተባልኩ ያህል በሐዘን ተቆራመድኩ።”—ዣኢልቶን፣ ልጁ ካንሰር እንዳለባት ባወቀ ጊዜ
ልጃችሁ ካንሰር እንዳለበት ማወቅ በጣም የሚያስደነግጥ ብሎም ቅስም የሚሰብር ነገር ነው። እንዲህ ያለው ሁኔታ ምን ያህል ያጋጥማል? ካንሰርን ለመዋጋት የተቋቋመው ዓለም አቀፍ ኅብረት እንደገለጸው “በካንሰር የሚያዙ ልጆች ቁጥር ከአጠቃላዩ የካንሰር ሕመምተኞች ቁጥር ጋር ሲወዳደር አነስተኛ ቢሆንም በየዓመቱ [በመላው ዓለም] ከ160,000 የሚበልጡ ልጆች የካንሰር ሕመምተኞች መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ባደጉ አገሮች ለልጆች ሞት ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከል ከአደጋ ቀጥሎ ካንሰር ሁለተኛውን ደረጃ ይይዛል።” ብራዚልን እንደ ምሳሌ ብንወስድ፣ ብሔራዊ የካንሰር ተቋም እንደገለጸው “በየዓመቱ 9,000 ገደማ የሚሆኑ ልጆች የካንሰር ሕመምተኞች መሆናቸው ይታወቃል።”
ልጆች በካንሰር መያዛቸው “እገሌ ከገሌ ሳይባል ሁሉንም የቤተሰብ አባላት የሚያስጨንቅ መቅሰፍት” እንደሆነ ኣ ማርዠንግ ዱ ሌቶ ኣ ማይ ኢ ኦ ካንሰር ኢንፋንቲል (እናት በካንሰር የተያዘ ልጇን ስታስታምም) የተሰኘው መጽሐፍ ይናገራል። ብዙውን ጊዜ ልጁ ካንሰር እንዳለበት ሲታወቅ ቀዶ ሕክምና ያስፈልገዋል፤ ከዚህም በተጨማሪ የኬሞቴራፒ ወይም የጨረር ሕክምና አሊያም ሁለቱም ሕክምናዎች የሚሰጡት ሲሆን እነዚህም የጎንዮሽ ጉዳት ያስከትላሉ። ይህ በወላጆች ላይ ከፍተኛ የስሜት ሥቃይ ያስከትላል፤ በፍርሃት፣ በሐዘንና በጥፋተኝነት ስሜት ይዋጡ፣ በቁጣ ይሞሉ እንዲሁም ሁኔታውን ለማመን ይቸገሩ ይሆናል። ታዲያ ወላጆች ይህን አስጨናቂ ሁኔታ መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው?
ቤተሰቡን በዋነኝነት ሊያጽናኑት የሚችሉት አሳቢ የሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች ናቸው። በርካታ የካንሰር ሕመምተኞችን የረዱ በኒው ዮርክ የሚገኙ አንድ ሐኪም እንዲህ ብለዋል፦ “የሕክምና ባለሙያዎች፣ [ወላጆችን] ሊያጽናኗቸው የሚችሉ መረጃዎችን ሊያካፍሏቸው እንዲሁም ወደፊት ሊያጋጥሙ የሚችሉ አንዳንድ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ሊገልጹላቸውና ምን ሊጠብቁ እንደሚችሉ ሊነግሯቸው ይችላሉ። ሐኪሞቹ እንዲህ ያሉ መረጃዎችን መስጠታቸው የወላጆችን ሥቃይ ሊቀንስላቸው ይችላል።” ልጆቻቸው ካንሰር ይዟቸው የነበሩ ወላጆችም ሌሎችን በጣም ሊያጽናኑ ይችላሉ። የንቁ! መጽሔት አዘጋጆች ይህን በማሰብ በብራዚል ከሚኖሩ አምስት ወላጆች ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።
● ዣኢልቶን እና ኔኧ “ሴት ልጃችን ገና በሁለት ዓመት ከስድስት ወሯ ሊምፎብላስቲክ ሉኪሚያ የተባለ ከባድ የደም ካንሰር እንደያዛት አወቅን።
ሕክምናው ምን ያህል ጊዜ ወሰደ?
“ወደ ሁለት ዓመት ተኩል ለሚጠጋ ጊዜ የኬሞቴራፒ ሕክምና ተደረገላት።”
ሕክምናው ምን የጎንዮሽ ጉዳት አስከተለባት?
“በተደጋጋሚ ጊዜ ያስመልሳት የነበረ ሲሆን ፀጉሯ ረገፈ። ጥርሷም በለዘ። እንዲሁም ሦስት ጊዜ የሳንባ ምች በሽታ ይዟት ነበር።”
በዚህ ጊዜ ምን ተሰማችሁ?
“መጀመሪያ ላይ የምትሞት መስሎን በጣም ተደናግጠን ነበር። ጤንነቷ እየተሻሻለ መሄዱን ስናይ ግን እንደምትድን እርግጠኞች ሆንን። አሁን ዘጠኝ ዓመት ሊሞላት ነው።
ይህን በጣም አስጨናቂ ሁኔታ ለመቋቋም የረዳችሁ ምንድን ነው?
“መጽሐፍ ቅዱስ በ2 ቆሮንቶስ 1:3, 4 ላይ ይሖዋ አምላክ ‘በመከራችን ሁሉ እንደሚያጽናናን’ ይናገራል፤ እኛም በእሱ መታመናችን ይህንን ሁኔታ ለመቋቋም እንደረዳን ምንም ጥርጥር የለውም። ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም ከፍተኛ ድጋፍ አድርገውልናል። የሚያበረታቱ ደብዳቤዎች ይጽፉልን፣ ስልክ ይደውሉልን፣ አብረውን ይጸልዩ እንዲሁም ስለ እኛ ይጸልዩ አልፎ ተርፎም በገንዘብ ይረዱን ነበር። ከዚያም ልጃችን በሌላ የአገሪቱ ክፍል ወደሚገኝ ሆስፒታል መዛወር ባስፈለጋት ጊዜ በዚያ ያሉት ክርስቲያን ወንድሞቻችን ማረፊያ ያዘጋጁልን ሲሆን ተራ ገብተው ወደ ሆስፒታል ያመላልሱን ነበር። ላገኘነው ድጋፍ ሁሉ ምስጋናችንን ለመግለጽ ቃላት ያጥሩናል።”
● ሉዊዝ እና ፋቢያና “ልጃችን እምብዛም የማያጋጥም ዓይነት በጣም አደገኛ ካንሰር እንዳለባት በ1992 አወቅን፤ ልጃችን የያዛት ካንሰር እንቁላል የሚያመነጨውን የማህፀን ክፍል የሚያጠቃ ነው። በዚያን ጊዜ ዕድሜዋ 11 ዓመት ነበር።”
ይህን ስታውቁ መጀመሪያ ላይ ምን ተሰማችሁ?
“ፈጽሞ ማመን አልቻልንም። ልጃችን ካንሰር እንዳለባት መቀበል አቃተን።”
ምን ዓይነት ሕክምና ተሰጣት?
“ቀዶ ሕክምና የተደረገላት ሲሆን የኬሞቴራፒ ሕክምናም ተሰጣት፤ ሕክምናው ያስከተለው ውጤት በሁላችንም ላይ አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ሥቃይ አስከትሎብናል። ልጃችን ሁለት ጊዜ የሳንባ ምች ይዟት ነበር። በሁለተኛው ጊዜ ከሞት ለጥቂት ነው የተረፈችው። በተጨማሪም በሰውነቷ ውስጥ ያለው ፕሌትሌት የሚባለው ደም አርጊ ሕዋስ መጠን ስላነሰ በድንገት ይነስራት እንዲሁም ቆዳዋ ይደማ ነበር። የተሰጣት መድኃኒት ይህ ችግር እንዲቀንስ አድርጓል።”
ሕክምናው ምን ያህል ጊዜ ወሰደ?
“የመጀመሪያው ምርመራ ከተደረገላት ጊዜ አንስቶ የመጨረሻውን የኬሞቴራፒ ሕክምና እስከወሰደችበት ጊዜ ድረስ ስድስት ወራት ፈጅቷል።”
ልጃችሁ ካንሰር እንዳለባት ሲነገራትና ሕክምናውን ስትወስድ ምን ተሰማት?
“መጀመሪያ ላይ ምን እየተከናወነ እንዳለ አላወቀችም ነበር። ሐኪሙ ‘በሆዷ ውስጥ አንድ ትንሽ ኳስ እንዳለና መውጣት እንደሚኖርበት’ ነገራት። በኋላ ላይ ግን ነገሩ ከባድ እንደሆነ ገባት። ‘አባዬ፣ ካንሰር ይዞኛል እንዴ?’ ብላ ጠየቀችኝ። እኔም ምን ብዬ እንደምመልስላት ግራ ገባኝ።”
ልጃችሁ ስትሠቃይ ምን ተሰማችሁ?
“ያሳለፍነውን የስሜት ሥቃይ በቃላት መግለጽ ይከብዳል። ለምሳሌ ያህል፣ ትንሿ ልጃችሁ የኬሞቴራፒ ሕክምና ሲሰጣት መርፌው የሚገባበትን የደም ሥር ለማግኘት ነርሷን ስትተባበራት ስታዩ ምን እንደሚሰማችሁ እስቲ አስቡት። ሁኔታው በጣም በሚከብድበት ጊዜ መታጠቢያ ቤት ገብቼ አለቅስ እንዲሁም እጸልይ ነበር። አንድ ቀን ማታ ላይ በጭንቀት ልፈነዳ ስለደረስኩ በልጄ ፈንታ እኔ እንድሞት ይሖዋን ጠየቅሁት።”
ይህን ሁኔታ ለመቋቋም የረዳችሁ ምንድን ነው?
“በዋነኝነት የረዳን ነገር ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ያገኘነው ድጋፍ ሲሆን አንዳንዶቹ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ስልክ ይደውሉልን ነበር። አንድ ተወዳጅ ወንድም መጽሐፍ ቅዱሴን እንዳወጣ ጠየቀኝ። ከዚያም ከመዝሙር መጽሐፍ ላይ አንዳንድ ጥቅሶችን በሚያበረታታ መንገድ አነበበልኝ። ይህ ጊዜ እኔና ባለቤቴ ከልጃችን ሕክምና ጋር በተያያዘ ካሳለፍናቸው በጣም ከባድ ወቅቶች አንዱ በመሆኑ በጊዜው የሚያስፈልገን እንዲህ ያለ ማበረታቻ ነበር።”
● ሮዚመሪ “ሴት ልጄ የደም ካንሰር እንዳለባት በምርመራ ሲታወቅ የአራት ዓመት ልጅ ነበረች።”
ይህን ስታውቂ መጀመሪያ ላይ ምን ተሰማሽ?
“ጆሮዬን ማመን አቃተኝ። ሌት ተቀን አለቅስ እንዲሁም አምላክ እንዲረዳኝ እለምነው ነበር። ትልቋ ልጄም እህቷ በጠና መታመሟን ስታይ በጣም ስለተረበሸች እሷን ወደ እናቴ ቤት መላክ ነበረብኝ።”
ሕክምናው በልጅሽ ላይ ምን የጎንዮሽ ጉዳት አስከተለባት?
“በየዕለቱ የምትወስደው የኬሞቴራፒ ሕክምና የደም ማነስ ስላስከተለባት ሐኪሞቹ የቀይ የደም ሴሏን መጠን ለመጨመር የብረት ማዕድንና ኢሪትሮፖይትን የተባለውን ሆርሞን ሰጧት። የደሟ መጠን ስለሚወርድ ሁልጊዜ ያሳስበኝ ነበር። በተጨማሪም ያንዘፈዝፋት ነበር።
ሕክምናው ለምን ያህል ጊዜ ቀጠለ?
“ለሁለት ዓመት ከአራት ወር ከበድ ያለ የኬሞቴራፒ ሕክምና ተሰጥቷታል። በዚያን ጊዜ ፀጉሯ የረገፈ ከመሆኑም ሌላ ክብደቷ በጣም ጨመረ። ደግነቱ ተጨዋች መሆኗ ሁኔታውን ለመቋቋም ረድቷታል። ከስድስት ዓመታት ገደማ በኋላ ልጄ የበሽታው ምልክት እንደማይታይባት ሐኪሞቹ ነገሩኝ።”
ይህን በጣም አስጨናቂ ሁኔታ ለመቋቋም የረዳሽ ምንድን ነው?
“እኔና ልጄ አዘውትረን እንጸልይ እንዲሁም የተለያዩ ፈተናዎችን በጽናት የተወጡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በተዉት ምሳሌ ላይ እናሰላስል ነበር። በተጨማሪም በማቴዎስ 6:34 ላይ የሚገኘውን በዛሬው ጭንቀታችን ላይ የነገውን ጭንቀት መጨመር እንደሌለብን ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ በቁም ነገር እንመለከተው ነበር። በአካባቢያችን ያለውን የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ ጨምሮ ክርስቲያን ባልንጀሮቻችን እንዲሁም ብዙ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች የሚያጋጥሟቸው አሳቢ የሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች ከፍተኛ እርዳታ አድርገውልናል።”
የምታውቁት ምናልባትም የቤተሰባችሁ አባል የሆነ ልጅ ካንሰር ይዞታል? ከሆነ ከላይ የቀረቡት ቃለ ምልልሶች በሁኔታው ማዘናችሁ እንግዳ ነገር አለመሆኑን እንድትገነዘቡ እንደሚረዷችሁ ተስፋ እናደርጋለን። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “ለማልቀስ ጊዜ አለው።” (መክብብ 3:4) ከሁሉ በላይ ደግሞ “ጸሎትን የምትሰማ” ተብሎ የተጠራው እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ከልባቸው ወደ እሱ የሚጸልዩትን ሁሉ እንደሚያጽናና እርግጠኛ ሁኑ።—መዝሙር 65:2
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የሚያጽናኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች
“ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት።”—ማቴዎስ 6:34
“ከርኅራኄ የመነጨ ምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት የተባረከ ይሁን፤ . . . እሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።”—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4
“ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
“የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ [በአምላክ] ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።”—1 ጴጥሮስ 5:7
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ፍቅራዊ ዝግጅት
በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚገኙት የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ዓላማ፣ በሆስፒታሎችና በሕመምተኞች መካከል የትብብር መንፈስ እንዲኖር ማድረግ ነው። እነዚህ ኮሚቴዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከደም ራቁ’ በማለት የሚሰጠውን መመሪያ ለመታዘዝ የሚፈልጉ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሕመምተኞችን ፍላጎት የሚያከብሩ ብቃት ያላቸው ሐኪሞች በማግኘት ረገድ እገዛ ያበረክታሉ።—የሐዋርያት ሥራ 15:20
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኔኧ፣ ስቴፋኒና ዣኢልቶን
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሉዊዝ፣ አሊንና ፋቢያና
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አሊንና ሮዚመሪ