የምንወደው ሰው መሞቱን አምኖ መቀበል
የምንወደው ሰው መሞቱን አምኖ መቀበል
“አባቴ እንደሞተ ሲያረዱኝ በጣም ከመደንገጤ የተነሳ ሁሉ ነገር ጨለመብኝ። ሲሞት አጠገቡ ስላልነበርኩ የጥፋተኝነት ስሜት ይደቁሰኝ ጀመር። የሚወዱትን ሰው በሞት ከመነጠቅ የበለጠ ሥቃይ የሚያስከትል ነገር የለም። አባቴ በጣም ይናፍቀኛል!”—ሣራ
ብዙ ሰዎች፣ ባሕላቸው ወይም ሃይማኖታቸው ምንም ይሁን ምን ስለ ሞት ማውራት ይከብዳቸዋል። አንዳንድ ቋንቋዎች ስለ ሞት ማውራት የሚፈጥረውን መጥፎ ስሜት ለማለዘብ የሚጠቀሙባቸው ለስለስ ያሉ አገላለጾች አሏቸው። ለምሳሌ በአማርኛ አንድ ሰው መሞቱን ለመግለጽ “አረፈ፣” “አለፈ” ወይም “ከጎናችን ተለየ” ይባላል።
ያም ሆኖ በጣም የለዘበ ነው የሚባለው አገላለጽ እንኳ የሚወዱትን ሰው በሞት የተነጠቁ ሰዎች የሚሰማቸውን ከፍተኛ ሐዘን ያን ያህል አያቀለውም። አንዳንድ ሰዎች ሐዘኑ በጣም ከባድ ስለሚሆንባቸው እውነታውን መቀበል ይከብዳቸዋል።
አንተም የምትወደውን ሰው በሞት ተነጥቀህ ከሆነ የደረሰብህን ነገር አምኖ መቀበል ከብዶህ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም በውስጥህ የሚሰማህ ሌላ ነገር ሆኖ ሳለ ደህና እንደሆንክ ለማስመሰል ትሞክር ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ሁሉም ሰው ሐዘኑን የሚገልጽበት መንገድ የተለያየ ነው፤ በመሆኑም ሐዘንህን በሚታይ መንገድ አልገለጽክም ማለት ስሜትህን አምቀኸዋል ማለት ላይሆን ይችላል። * ይሁን እንጂ ሌሎች ሰዎች ምናልባትም በሐዘን ላይ ያሉ የቤተሰብህ አባላት በሚፈልጉት መንገድ ሐዘንህን መግለጽ እንዳለብህ የሚሰማህ ከሆነ ችግር ውስጥ ልትወድቅ ትችላለህ።
“ሐዘኔን ለመግለጽ ጊዜ አልነበረኝም”
የ24 ዓመት ወጣት ሳለ እናቱ የሞተችበትን የናትንየልን ተሞክሮ ተመልከት። እንዲህ ብሏል፦ “መጀመሪያ ላይ በጣም ግራ ገባኝ። አባቴንም ሆነ በእናቴ ሞት ያዘኑ ብዙ
ጓደኞቿን ማጽናናት እንዳለብኝ ተሰምቶኝ ነበር። ሐዘኔን ለመግለጽ ጊዜ አልነበረኝም።”ናትንየል ከአንድ ዓመት በኋላም ከሐዘኑ እንዳልተጽናና ተገነዘበ። ናትንየል እንዲህ ብሏል፦ “አባቴ ሐዘኑን መግለጽ ሲፈልግ አሁንም ድረስ አልፎ አልፎ ይደውልልኛል፤ ይህ ደግሞ ጥሩ ነው። ስለተሰማው ነገር ማውራት የሚፈልግባቸው ጊዜያት አሉ፤ እኔም በእነዚህ ጊዜያት ልረዳው በመቻሌ ደስተኛ ነኝ። እኔ ግን እንዲህ ዓይነት እርዳታ በሚያስፈልገኝ ጊዜ ስሜቴን አውጥቼ የምነግረው ሰው እንደሌለ ሆኖ ይሰማኛል።”
በተጨማሪም ዘወትር ከሞት ጋር መፋጠጥ ግዴታቸው የሆነ የሕክምና ባለሙያዎችና አስታማሚዎች ስሜታቸውን አፍነው መያዝ እንዳለባቸው ይሰማቸው ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት በሕክምና ሙያ ያገለገለችውን የኤሎኢዘን ሁኔታ እንመልከት። ኤሎኢዘ የምትሠራው እርስ በርሱ በተሳሰረ ማኅበረሰብ ውስጥ ከመሆኑም በላይ ከምታክማቸው ሰዎች ጋር ቅርርብ ነበራት። “ብዙዎቹ ሲሞቱ አጠገባቸው ነበርኩ። ከአንዳንዶቹም ጋር ጓደኛ ሆነን ነበር” ብላለች።
ኤሎኢዘ ማልቀስ ከሐዘን ለመጽናናት የሚረዳ ተፈጥሯዊ መንገድ እንደሆነ ታውቅ ነበር። “ይሁን እንጂ ማልቀስ ከባድ ሆኖብኝ ነበር” በማለት ተናግራለች። “በጣም የሚያሳስበኝ በሌሎች ዘንድ ጠንካራ ሆኖ መታየት ስለነበር ስሜቴን አምቄ መያዝ እንዳለብኝ አስብ ነበር። ሌሎች ጠንካራ እንድሆን እንደሚጠብቁብኝ ይሰማኝ ነበር።”
“ቤቱ ያለ እሷ ወና ይሆንብኛል”
የሚወዱትን ሰው በሞት የተነጠቁ ሰዎች የሚያጋጥማቸው ትልቁ ተፈታታኝ ሁኔታ ብቸኝነት ሳይሆን አይቀርም። ለምሳሌ ያህል፣ አሽሊ እናቷ በካንሰር ስትሞት ዕድሜዋ 19 ዓመት ነበር። “እናቴ ከሞተች በኋላ ግራ ገብቶኝ የነበረ ሲሆን በብቸኝነት ስሜት ተውጬ ነበር” ብላለች። “እናቴ የቅርብ ጓደኛዬ ነበረች። ብዙ ጊዜ አብረን እናሳልፍ ነበር!”
አሽሊ በየቀኑ ወደ ቤት ስትገባ እናቷ እንደሌለች ማመን እንደሚከብዳት መረዳት አያዳግትም። እንዲህ ብላለች፦ “ቤቱ ያለ እሷ ወና ይሆንብኛል። ብዙ ጊዜ ወደ ክፍሌ ገብቼ ፎቶዎቿን እየተመለከትኩና አብረን እናደርጋቸው የነበሩትን ነገሮች እያስታወስኩ አለቅሳለሁ።”
የቤተሰብህን አባል ወይም የምትወደውን ጓደኛህን በሞት ተነጥቀህ ሊሆን ይችላል። አይዞህ፣ ሐዘን የደረሰብህ አንተ ብቻ አይደለህም! ብዙ ሰዎችን ሐዘናቸውን እንዲቋቋሙ የረዷቸውን ውጤታማ ዘዴዎች ቀጥሎ እንመለከታለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.5 እያንዳንዱ ግለሰብ ሐዘኑን የሚገልጽበት መንገድ የተለያየ ስለሆነ የሚወዱትን ሰው በሞት ተነጥቀው ሐዘናቸውን በሚታይ መንገድ በማይገልጹ ሰዎች ላይ መፍረድ ተገቢ አይደለም።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ግራ ገብቶኝ የነበረ ሲሆን በብቸኝነት ስሜት ተውጬ ነበር። እናቴ የቅርብ ጓደኛዬ ነበረች”—አሽሊ