ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
ጣሊያን የመጀመሪያዋ የሆነውን የፍቺ ባዛር አዘጋጀች። ወደ ባዛሩ የሚሄዱ ሰዎች አዲስ የትዳር ጓደኛ ለማግኘት ከፈለጉ የጋብቻ ወኪሎችን ያማክራሉ፤ ነጠላዎች ደግሞ የሽርሽር ፕሮግራም እንዲዘጋጅላቸው የጉዞ ወኪሎችን ያማክራሉ፤ ጠበቃዎችን፣ የሒሳብ ሠራተኞችን፣ የሥነ ልቦና አማካሪዎችንና የቤተሰብ ሸምጋዮችን እንዲያፈላልጉላቸው ደግሞ ፍቺ የሚያስፈጽሙ ድርጅቶችን ያማክራሉ።—ኮሪዬሬ ዴላ ሴራ፣ ጣሊያን
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን “ቀሳውስት ሌሎችን በፆታ ማስነወራቸው ያስከተለውን ችግር ለማስተካከል ተገቢ እርምጃ ባለመውሰዷ” ምክንያት የተፈጠረው የአመኔታ መጥፋት “ባለፉት ዘመናት ሁሉ ምናልባትም በቤተ ክርስቲያኗ ታሪክ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ ድርጅታዊ ቅሌት” እንድትከናነብ አድርጓታል።—ናሽናል ካቶሊክ ሪፖርተር፣ ዩናይትድ ስቴትስ
ከሞተ 4,000 ዓመት ገደማ ከሆነው ግሪንላንዳዊ ፀጉር ላይ የተወሰደ ዲ ኤን ኤ የመረመሩ ሳይንቲስቶች ግለሰቡ “ከሳይቤርያ የመጣ እንደሚመስል” ደርሰውበታል።—ሮይተርስ ዜና አገልግሎት፣ ዩናይትድ ስቴትስ
ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ላይ የነበራቸው እምነት አሽቆልቁሏል
ዚ አይሪሽ ታይምስ በተባለው ጋዜጣ ላይ የወጣ ርዕሰ አንቀጽ “አብዛኞቹ ሰዎች [በካቶሊክ] ቤተ ክርስቲያን ላይ ያላቸው እምነት ጠፍቷል” ይላል። ይኸው ዘገባ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን፣ አብዛኞቹ የአየርላንድ ዜጎች እምነት ካጡባቸው ተቋማት ማለትም ከመንግሥትና ከባንኮች ጋር መድቧታል። ሰዎች ለቤተ ክርስቲያን ያላቸው ታማኝነት አጠያያቂ ሆኖ በማያውቅበት በዚህች አገር በቅርብ በተካሄደ አንድ ጥናት ላይ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ሰዎች መካከል ከግማሽ የሚበልጡት በቤተ ክርስቲያኗ ላይ “ጨርሶ” እምነት እንደሌላቸው (32 በመቶ) ወይም በቤተ ክርስቲያኗ ላይ “እምብዛም እምነት” እንደሌላቸው (21 በመቶ) ተናግረዋል። ሕዝቡ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ የነበራቸው እምነት ይህን ያህል ‘ያሽቆለቆለው’ በቅርቡ ቤተ ክርስቲያኗን ባናወጧት በርካታ ቅሌቶች ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።
ሥራ ያጡ የኮሌጅ ምሩቃን
የኮሌጅ ትምህርት ሥራ ለማግኘት ዋስትና ይሆናል? ማኒላ ቡለቲን እንደሚለው ብዙዎች የኮሌጅ ትምህርት መቅሰማቸው ሥራ ለማግኘት ዋስትና አልሆናቸውም። የኬሶን ሲቲ ከንቲባ የሆኑት ኸርበርት ባውቲስታ እንደሚከተለው ብለው እንደተናገሩ ጋዜጣው ዘግቧል፦ “በየዓመቱ ኮሌጆቻችንና ዩኒቨርሲቲዎቻችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ያስመርቃሉ፤ እነዚህ ምሩቃን የተማሩት ትምህርት ተፈላጊ ከሆኑት ሙያዎች ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ ሥራ አጥ ይሆናሉ።” የብዙዎቹ ዕጣ ፈንታ በጽሕፈት ሙያ መሠማራት ወይም በምግብ ቤቶች ውስጥ መሥራት ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች በቀላሉ ሥራ ሊገኝባቸው በሚችል ተፈላጊ ሙያዎች ወይም የቴክኒክ መስኮች አጫጭር ሥልጠናዎችን እንዲወስዱ መንግሥት እያበረታታ ነው።
በምራቅ የተበላ ድልድይ
በካልካታ፣ ሕንድ የ457 ሜትር ርዝመት ያለው የሃውራ ድልድይ እግረኞች በሚተፉት ምራቅ ምክንያት እየተበላ ነው። እንዴት? ብዙ ሰዎች እያኘኩ የሚተፉት ጉትከ የተባለ የቢትል ቅጠልን፣ አሪካ ነትን እና ካልሲየም ሃይድሮክሳይድን በመቀላቀል የሚሠራ ውህድ ብረትን የመብላት ከፍተኛ ኃይል አለው። ዘ ቴሌግራፍ የተባለው የካልካታ ጋዜጣ እንደገለጸው “በድልድዩ ላይ የሚተላለፉት ሰዎች በሚተፉት ምራቅ ምክንያት [የድልድዩን] ምሰሶዎች የሸፈናቸው ብረት ውፍረቱ ከ2007 ወዲህ ከስድስት ሚሊ ሜትር ወደ ሦስት ሚሊ ሜትር ቀንሷል።” በየቀኑ 500,000 የሚያህሉ እግረኞችና 100,000 ተሽከርካሪዎች ወንዙን ለማቋረጥ ይህን ድልድይ ይጠቀሙበታል።