በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሙዚቃ በጥንቷ እስራኤል

ሙዚቃ በጥንቷ እስራኤል

ሙዚቃ በጥንቷ እስራኤል

ሙዚቃ በጥንቷ እስራኤል ባሕል ውስጥ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ነገሮች አንዱ ነበር። ሕዝቡን ለአምልኮ እንዲሰበሰብ ለመጥራትና ወሳኝ የሆኑ ክንውኖችን ለማሳወቅ መለከቶችና ቀንደ መለከቶች ይነፉ ነበር። የንጉሣውያንን ቤተሰብ መንፈስ ዘና ለማድረግ በገና ይደረደር እንዲሁም ክራር ይመታ ነበር። (1 ሳሙኤል 16:14-23) ለየት ባሉ ወቅቶች ደግሞ ሰዎች በከበሮ፣ በሲምባልና በጸናጽል ታጅበው አስደሳች ጊዜያትን ያሳልፉ ነበር።​—2 ሳሙኤል 6:5፤ 1 ዜና መዋዕል 13:8

የቃየን ዘር የሆነው ዩባል “የበገና ደርዳሪዎችና የዋሽንት ነፊዎች አባት” እንደነበረ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሷል። (ዘፍጥረት 4:21) የትንፋሽና ባለአውታር የሙዚቃ መሣሪያዎችን የፈለሰፈው እሱ ሊሆን ይችላል።

በተለያዩ ዝግጅቶች ወቅት ሰዎች ሙዚቃ ይጫወቱ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ይሁን እንጂ ስለ ሙዚቃ መሣሪያዎቹ እምብዛም አይናገርም። እንደዚያም ሆኖ ምሑራን በአርኪኦሎጂ ግኝቶችና በጥንታዊ ጽሑፎች ታግዘው የጥንቶቹ የሙዚቃ መሣሪያዎች ምን ሊመስሉና እንዴት ያለ ድምፅ ሊያወጡ እንደሚችሉ ለመገመት ሞክረዋል። ከደረሱባቸው ድምዳሜዎች ውስጥ አንዳንዶቹ መላ ምት ቢሆኑም በበቂ መረጃ ላይ የተመሠረቱም አልጠፉም። እስቲ ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹን እንደ ምሳሌ እንመልከት።

አታሞ፣ ጸናጽልና ሲምባል

አምላክ ሙሴንና እስራኤላውያንን በተአምር ቀይ ባሕርን ባሻገራቸው ጊዜ የሙሴ እህት ማርያም ‘ከተቀሩት ሴቶች’ ጋር በመሆን አታሞ ወይም ‘ከበሮ በማንሳት’ ጨፍራ ነበር። (ዘፀአት 15:20) በጥንት እስራኤላውያን ዘመን ሰዎች ዛሬ የምናውቀውን ዓይነት አታሞ ይጠቀሙ እንደነበር የሚያሳዩ ማስረጃዎች ባይገኙም በእስራኤል ውስጥ ለምሳሌ አክዚብ፣ መጊዶና ቤትሳን በሚባሉ ቦታዎች በእጅ የሚያዙ ትናንሽ ከበሮ የያዙ ሴቶችን የሚያሳዩ የሸክላ ምስሎች ተገኝተዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ ብዙ ጊዜ አታሞ ወይም ከበሮ እየተባለ የተተረጎመው ይህ መሣሪያ በእንጨት ገበቴ ላይ የእንስሳት ቆዳ በመወጠር የሚዘጋጅ ሳይሆን አይቀርም።

የእስራኤል ብሔር ከመቋቋሙ በፊት ባለው ዘመን በክብረ በዓላት ላይ ከበሮ የሚመቱት ሴቶች ሲሆኑ በዘፈንና በጭፈራም ይታጀቡ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው የእስራኤላውያን መሪ የነበረው ዮፍታሔ በአንድ ጦርነት ላይ ወሳኝ ድል አግኝቶ በተመለሰ ጊዜ ሴት ልጁ “አታሞ እየደለቀች በመዝፈን” ልትቀበለው ወጥታ ነበር። በሌላ ወቅት ደግሞ ዳዊት ድል ተቀዳጅቶ ሲመለስ ሴቶች “ከበሮ” ይዘው ‘በመዝፈንና በመጨፈር’ ደስታቸውን ገልጸው ነበር።​—መሳፍንት 11:34፤ 1 ሳሙኤል 18:6, 7

ንጉሥ ዳዊት የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ባመጣበት ጊዜ ሕዝቡ “በዝማሬ፣ በበገና፣ በመሰንቆ፣ በከበሮ፣ በጽናጽልና በቃጭል [“በሲምባል፣” NW] ባለ ኀይላቸው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ያሸበሽቡ ነበር።” (2 ሳሙኤል 6:5) ከጊዜ በኋላ ደግሞ በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ ሲምባል፣ መለከት፣ በገናና ሌሎች የአውታር መሣሪያዎችን በመጫወት የተካኑ ሙዚቀኞችን ያቀፈ የራሱ የሆነ የሙዚቃ ቡድን ነበረው።

አታሞዎች ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ መጠነኛ ግንዛቤ አግኝተናል፤ ይሁንና ጸናጽልስ ምንድን ነው? የባላ ቅርጽ ባለው ብረት ላይ የሚንሸዋሸዉ ነገሮችን በማድረግ የሚሠራ የሙዚቃ መሣሪያ ሳይሆን አይቀርም። አንድ ሰው ጸናጽል በማወዛወዝ ቀጠንና ጎላ ያለ ድምፅ ማውጣት ይችላል። ጸናጽል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። የተጠቀሰውም የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም እንደተወሰደ በሚገልጸው ዘገባ ላይ ነው። ይሁን እንጂ የአይሁድ አፈ ታሪክ እንደሚገልጸው ጸናጽል በሐዘን ወቅትም ጥቅም ላይ ይውል ነበር።

በጥንት ዘመን ስለነበሩት ሲምባሎችስ ምን ማለት ይቻላል? እርስ በርሳቸው ሲጋጩ ድምፅ የሚፈጥሩ የድስት ክዳን የመሰለ ቅርጽ ያላቸው ሁለት ሰፋፊ ዝርግ ብረቶች እንደሆኑ ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ በጥንቷ እስራኤል የነበሩት አንዳንድ ሲምባሎች ስፋታቸው ከ10 ሴንቲ ሜትር የማይበልጥ ሲሆን ‘ኪሽ’ የሚል ድምፅ የሚያወጡ ናቸው።

በገናና ሌሎች የአውታር መሣሪያዎች

በዕብራይስጥ “ኪኖር” ተብሎ የሚጠራውና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ቦታዎች ላይ “በገና” ወይም “ክራር” ተብሎ የተተረጎመው የሙዚቃ መሣሪያ በጥንቷ እስራኤል በሰፊው ጥቅም ላይ ይውል ነበር። ዳዊት በዚህ የሙዚቃ መሣሪያ በመጫወት የንጉሥ ሳኦልን መንፈስ ያረጋጋ ነበር። (1 ሳሙኤል 16:16, 23) ምሑራን ጥንት በተቀረጹ ዐለቶች ላይ እንዲሁም በድሮ ዘመን በተሠሩ ሳንቲሞች፣ ሥዕሎች፣ ሐውልቶችና ማኅተሞች ላይ ቢያንስ 30 የሚያህሉ የክራር ምስሎችን አግኝተዋል። ዘመናት ባለፉ ቁጥር የዚህ መሣሪያ ቅርጽ እየተቀያየረ መጥቷል። ተጫዋቹ መሣሪያውን በክንዱ ደግፎ ከያዘው በኋላ በጣቶቹ ወይም በመግረፊያው ተጠቅሞ ይጫወታል።

ኔበል የተባለው የአውታር መሣሪያ ከኪኖር ጋር ይመሳሰላል። ኔበል ባለ ስንት አውታር እንደሆነ፣ መጠኑ ምን ያህል እንደሆነ እንዲሁም ሰዎቹ ይጫወቱት የነበረው ጅማቶቹን በመግረፍ ይሁን አሊያም ለየብቻ በማንዘር በውል የሚታወቅ ነገር የለም። ይሁን እንጂ ኔበልም ሆነ ኪኖር አንድ ሙዚቀኛ እንደ ልብ ከቦታ ወደ ቦታ ይዟቸው ሊንቀሳቀስ የሚችሉ መሣሪያዎች እንደሆኑ አብዛኞቹ ምሑራን ይስማማሉ።

መለከትና ቀንደ መለከት

ሙሴ ሁለት መለከቶችን እንዲሠራ አምላክ አዝዞት ነበር። እነዚህ መለከቶች ከተቀጠቀጠ ብር የተሠሩ መሆን ነበረባቸው። (ዘኍልቍ 10:2) ካህናቱ ከቤተ መቅደሱና ከተለያዩ በዓላት ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ በርካታ ክንውኖችን ለማስታወቅ ይጠቀሙባቸው ነበር። ሊያስተላልፉ እንደፈለጉት መልእክት፣ መለከቱ የተለያየ ድምፅ ለምሳሌ ከፍና ዘለግ ያለ ወይም ለአጭር ጊዜ የሚቆይ የሚያንባርቅ ድምፅ እንዲያወጣ ያደርጉ ነበር። በጥንት ዘመን ሰዎች ይጠቀሙበት የነበረ አንድም መለከት ባለመገኘቱ በወቅቱ የነበሩት መለከቶች ትክክለኛ ገጽታ ምን ሊመስል እንደሚችል እስካሁን በእርግጠኝነት አይታወቅም። የተገኘ ማስረጃ ቢኖር ሰዎች በሠሯቸው የሥነ ጥበብ ውጤቶች ላይ የሚታዩት ምስሎች ብቻ ናቸው፤ በሮም በሚገኘው የቲቶ ቅስት ላይ የተቀረጸው የመለከት ምስል ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው።

የዕብራይስጥ ቃል የሆነው ሾፋር (ቀንደ መለከት ማለት ነው) በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከ70 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል። ይህ መሣሪያ የሚዘጋጀው ከፍየል ወይም ከአውራ በግ ቀንድ ነበር። የአይሁድ የመረጃ ምንጮች እንደሚያመለክቱት ቀንደ መለከት ሁለት ዓይነት ቅርጽ አለው። አንደኛው ቀጥ ያለ ሆኖ የወርቅ መንፊያ ሲኖረው ሌላኛው ደግሞ ጠመዝማዛ ሆኖ በብር ያጌጠ ነው። ቀንደ መለከት ከርቀት የሚሰማ ሁለት ወይም ሦስት ዓይነት ድምፅ ሊያወጣ ስለሚችል አብዛኛውን ጊዜ የሚያገለግለው መልእክት ለማስተላለፍ ነበር።

በጥንቷ እስራኤል ቀንደ መለከት ከአምልኮ ጋር በተያያዘ ለሕዝቡ መልእክት ለማስተላለፍ ለምሳሌ ሰንበት መግባቱንና ማብቃቱን ለማስታወቅ ያገለግል ነበር። ይሁን እንጂ አገልግሎቱ በዚህ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። ለአብነት ያህል፣ እስራኤላውያን በጦርነት ጊዜያት ይጠቀሙበት ነበር። የጌዴዎን ሠራዊት በሌሊት በምድያማውያን ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከመሰንዘሩ ቀደም ብሎ 300ዎቹ ሰዎች ቀንደ መለከት ሲነፉ የተሰማው ኃይለኛ ድምፅ ምን ያህል አስፈሪ እንደሚሆን መገመት እንችላለን።​—መሳፍንት 7:15-22

ሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎች

በጥንት ዘመን ሰዎች እንደ ቃጭልና ዋሽንት ያሉ እንዲሁም ከማንዶሊን ጋር የሚመሳሰሉ ሉት የሚባሉ መሣሪያዎችን ይጠቀሙ ነበር። በጥንቷ ባቢሎን በግዞት ይኖር የነበረው የይሖዋ ነቢይ ዳንኤል፣ የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለነበረው የሙዚቃ ቡድን ጽፏል። ይህ የሙዚቃ ቡድን ከሚጫወታቸው መሣሪያዎች መካከል እምቢልታና ዋሽንት ይገኙበታል።​—ዳንኤል 3:5, 7

በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከተጠቀሱት የሙዚቃ መሣሪያዎች በጥቂቶቹ ላይ ያደረግነው ቅኝት በጥንቶቹ እስራኤላውያን ምናልባትም በሌሎቹ ጥንታዊ ማኅበረሰቦች የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ሙዚቃ መስማት የተለመደ እንደነበር ያረጋግጣል። በቤተ መንግሥትና በአምልኮ ስፍራዎች እንዲሁም በመንደሮችና በመኖሪያ ቤቶች ውስጥም ጭምር ሙዚቃ ይሰማ ነበር።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጥንት ዘመን ሰዎች ጸናጽልን በማወዛወዝ ድምፅ ያወጡ ነበር

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳዊት በገና በመጫወት የተካነ ነበር

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የእስራኤል ብሔር ከመቋቋሙ በፊትም ሰዎች አታሞ ይጠቀሙ ነበር

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መለከት የተለያዩ ክንውኖችን ለማሳወቅ ያገለግል ነበር

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምት መሣሪያ የያዘች ሴት ምስል፣ በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ.

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአውታር መሣሪያ ምስል የተቀረጸበት ሳንቲም፣ በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም.

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገኘ “የመለከት መንፊያ ቦታ” የሚል ጽሑፍ የተቀረጸበት ድንጋይ፣ በአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ.

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]

Pottery figurine: Z. Radovan/BPL/Lebrecht; coin: © 2007 by David Hendin. All rights reserved; temple stone: Photograph © Israel Museum, Jerusalem; courtesy of Israel Antiquities Authority