በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እምነትና ምክንያታዊነት አብረው የሚሄዱ ነገሮች ናቸው?

እምነትና ምክንያታዊነት አብረው የሚሄዱ ነገሮች ናቸው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

እምነትና ምክንያታዊነት አብረው የሚሄዱ ነገሮች ናቸው?

አንተኒ ግሬይሊንግ የተባሉ ብሪታንያዊ ፈላስፋ፣ “እምነት የምክንያታዊነት ተቃራኒ ነው” በማለት ጽፈዋል። ይህ አባባል፣ ብዙ ጸሐፊዎችና ፈላስፎች ላለፉት በርካታ ዘመናት ሲያምኑበት የኖሩትን ‘እምነትና ምክንያታዊነት አብረው ሊሄዱ አይችሉም’ የሚለውን አስተሳሰብ ጠቅለል አድርጎ ይገልጻል።

እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ሃይማኖታዊ እምነቶች በምክንያታዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረቱ አይደሉም። ሆኖም እስቲ ይህን አስብ፦ በጥብቅ ይታመንባቸው የነበሩ በርካታ ሳይንሳዊ አመለካከቶች ከጊዜ በኋላ ስህተት መሆናቸው ተረጋግጧል። ይህ ማለት ታዲያ ሁሉም ሳይንሳዊ እምነቶች ስህተት ናቸው ወይም በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረቱ አይደሉም ማለት ነው? ታዲያ ለሃይማኖታዊ እምነቶች ሲሆን ሁኔታው በተለየ መንገድ የሚታየው ለምንድን ነው? እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸው እምነት ያለ ምንም እውቀት እንዲሁ የሚገኝ ነገር አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በእውቀትና በትክክለኛ ምክንያት ላይ የተመሠረተ ነው። ማስረጃውን ስትመረምር እውነተኛ እምነትና ምክንያታዊነት ምን ያህል አብረው የሚሄዱ ነገሮች እንደሆኑ መመልከት ትችላለህ።

በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተ እምነት

ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ አምልኮህ “በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት” እንዲኖረው ‘የማሰብ ችሎታህን ተጠቅመህ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ እንዳለብህ’ ይናገራል። በሌላ አነጋገር “እንደ ባለ አእምሮ” በማመዛዘን አምላክን ማምለክ አለብህ ማለት ነው። (ሮም 12:1አ.መ.ት) በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸው እምነት አንዳንዶች እንደሚሉት ከምክንያታዊነት የራቀ ጭፍን እምነት አይደለም። በተጨማሪም ሁሉን ነገር ዝም ብሎ አይቀበልም። ከዚህ ይልቅ እውነተኛ እምነት በጥንቃቄ አመዛዝነህ የምታገኘው ነገር ነው፤ ይህ ደግሞ በአምላክ እንድትተማመንና በምክንያታዊነት ላይ በተመሠረተው ቃሉ ላይ እምነት እንድትጥል ያስችልሃል።

እርግጥ ነው፣ በምክንያታዊነት ማሰብ ከፈለግህ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ያስፈልግሃል። በትክክለኛ የሂሳብ ስሌት ላይ የተመሠረቱ እጅግ ውስብስብ የኮምፒውተር ፕሮግራሞች እንኳ የተሳሳተ መረጃ ቢገባላቸው ግራ የሚያጋባ ውጤት ይሰጣሉ። በተመሳሳይም እምነትህ ትክክል መሆኑ የተመካው የምትሰማው ነገር ወይም ወደ አእምሮህ የምታስገባው መረጃ ምን ያህል አስተማማኝ ነው በሚለው ላይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘እምነት የሚገኘው ከመስማት ነው’ ማለቱ የተገባ ነው።—ሮም 10:17

የእምነት ዋና መሠረቱ ‘የእውነት ትክክለኛ እውቀት’ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) መጽሐፍ ቅዱስ “እውነት” አሳሳች ከሆኑ ሳይንሳዊና ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ‘ነፃ እንደሚያወጣህ’ ይናገራል። (ዮሐንስ 8:32) መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉን” ነገር አትመን በማለት ያስጠነቅቅሃል። (ምሳሌ 14:15) ከዚህ ይልቅ “ሁሉንም ነገር መርምሩ” ብሎ በመምከር የሰማነውን ነገር ከማመናችን በፊት ፈትነን እንድናረጋግጥ ያበረታታናል። (1 ተሰሎንቄ 5:21) እምነትህን መመርመርና ፈትነህ ማረጋገጥ ያለብህ ለምንድን ነው? በውሸት ላይ የተመሠረተ እምነት ከንቱ ስለሆነ ነው። በጥንቷ ቤርያ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ልበ ቀና ሰዎች ትክክለኛ እምነት ለማግኘት ጥረት በማድረግ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል። እነዚህ ሰዎች፣ ክርስቲያን ሚስዮናውያን ያስተማሯቸው ነገር ቢማርካቸውም እንኳ ዝም ብለው ከማመን ይልቅ “የሰሙት ነገር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ በየዕለቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ [ለመመርመር]” ጥረት ያደርጉ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 17:11

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት መገንባት

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ተአማኒ ስለ መሆኑ እርግጠኛ ባትሆንስ? መጽሐፍ ቅዱስ የትክክለኛ እውቀት ምንጭ እንደሆነ መተማመን የምትችለው እንዴት ነው? ለመሆኑ በሰዎች ላይ እምነት የምትጥለው እንዴት ነው? እነሱን በደንብ በማወቅ ማለትም በጊዜ ሂደት ባሕርያቸውን በማጥናትና የሚያሳዩትን ምግባር በመመልከት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ ለምን ተመሳሳይ ነገር አታደርግም? *

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው እውነተኛ እምነት “ተስፋ የተደረጉ ነገሮችን በእርግጠኝነት መጠበቅ ማለት ሲሆን እውነተኛዎቹ ነገሮች ባይታዩም እንኳ መኖራቸውን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።” (ዕብራውያን 11:1) ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደምንችለው እውነተኛ እምነት ያለው ሰው ነገሮችን ዝም ብሎ በየዋህነት ከሚቀበል ሰው በተቃራኒ እምነቱን የሚገነባው ያገኛቸውን ማስረጃዎች በሙሉ በጥንቃቄ መርምሮ በተቀበላቸው እውነታዎች ላይ ነው። እነዚህን ማስረጃዎች ምክንያታዊ ሆነህ ስትገመግም፣ እውን ቢሆኑም በዓይን ሊታዩ በማይችሉ ነገሮችም እንኳ ማመን ትጀምራለህ።

ሆኖም የተማርከው ነገር በጥልቅ ከምታምንባቸው አንዳንድ ነገሮች ጋር የሚቃረን ቢሆንስ? ችላ ልትለው ይገባል? በፍጹም። ከምታምንበት ነገር ጋር የሚቃረኑ ትምህርቶችን የሚደግፉ ጠንካራ ማስረጃዎችን መመርመርህ በጣም አስፈላጊ የሚሆንባቸው ጊዜያት ሊኖሩ ይችላሉ። አምላክ እውነትን ለሚፈልጉ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እውቀትን፣ ማስተዋልንና የመለየት ወይም የማመዛዘን ችሎታን በመስጠት ወሮታ እንደሚከፍላቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ምሳሌ 2:1-12

በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ የተገነባ እምነት ከምክንያታዊነት ጋር ይስማማል። አንተስ ያለህ እምነት ምን ዓይነት ነው? በርካታ ሰዎች የሚያምኑባቸውን ሃይማኖታዊ እምነቶች ያገኟቸው “በውርስ” ሲሆን ሥራዬ ብለው እምነታቸውን በምክንያታዊነት መርምረውት አያውቁም። አንተ ግን አስተሳሰብህ ከአምላክ ቃል ጋር የሚስማማ መሆኑን ‘መርምረህ ለማረጋገጥ’ በማሰብ እምነትህን ብትመረምር አክብሮት የጎደለው ተግባር እንደሆነ ሊሰማህ አይገባም። (ሮም 12:2) መጽሐፍ ቅዱስ “በመንፈስ የተነገሩት ቃላት ከአምላክ የመነጩ መሆን አለመሆናቸውን መርምሩ” በማለት ይመክረናል። (1 ዮሐንስ 4:1) እንዲህ የምታደርግ ከሆነ የምታምንበትን ነገር ለሚቃወሙ ሰዎች እንኳ ‘ስለ ተስፋህ ምክንያት በማቅረብ መልስ መስጠት’ ትችላለህ።—1 ጴጥሮስ 3:15

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ መረጃ ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች መጻፍ ትችላለህ

ይህን አስተውለኸዋል?

● መጽሐፍ ቅዱስ በምክንያት ማመንን ያወግዛል?—ሮም 12:1, 2

● እውነተኛ እምነት ለማዳበር ምን ዓይነት እውቀት ያስፈልጋል?—1 ጢሞቴዎስ 2:4

● መጽሐፍ ቅዱስ ለእምነት ከሚሰጠው ፍቺ ምን መማር እንችላለን?—ዕብራውያን 11:1

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አምላክ በቅን ልቦና ተነሳስተው እውነትን ለሚፈልጉ ሰዎች ወሮታ ይከፍላል