እምነት ልትጥልበት የምትችል መጽሐፍ—ክፍል 2
አሦር በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ
ይህ ርዕስ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የተገለጹትን ሰባት የዓለም ኃያላን መንግሥታት በተመለከተ “በንቁ!” ላይ ከሚወጡት ሰባት ተከታታይ ርዕሶች መካከል ሁለተኛው ነው። ዓላማውም መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበትና በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መጽሐፍ እንደሆነ እንዲሁም ተስፋ የሚፈነጥቅ መልእክት እንደያዘ ማሳየት ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ተስፋ፣ ጭካኔ የተሞላበት የሰው ልጆች አገዛዝ ያስከተለው መከራና ሥቃይ እንደሚያከትም ይገልጻል።
በጥንት ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ ይኖሩ ለነበሩት ሕዝቦች አሦር የሚለውን ስም መስማት በራሱ በፍርሃት እንዲርዱ ሳያደርጋቸው አይቀርም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የዮናስ መጽሐፍ እንደሚገልጸው ነቢዩ ዮናስ የአሦር ዋና ከተማ በነበረችው በነነዌ የአምላክን የፍርድ መልእክት እንዲሰብክ በተነገረው ጊዜ ወደ ተቃራኒው አቅጣጫ ሸሽቷል! (ዮናስ 1:1-3) ምናልባትም ዮናስ እንዲህ ያደረገው አሦራውያን የሚያስፈሩ ሕዝቦች መሆናቸውን ስለሰማ ሊሆን ይችላል።
እምነት የሚጣልበት ታሪክ
ናሆም የተባለ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ ነቢይ፣ ነነዌን “የአንበሶቹ ዋሻ” እና ‘የደም ከተማ’ በማለት ገልጿታል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ብዝበዛዋ ተግዞ አያልቅም። የጅራፍ ድምፅ፣ የመንኰራኵር ኳኳቴ፣ የፈጣን ናሆም 2:11፤ 3:1-3) ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥንቷ አሦር የሚናገረውን ነገር ዓለማዊ ታሪክ ይደግፈዋል?
ፈረስ ኮቴ፣ የሠረገሎች ድምፅ ተሰምቶአል ፈረሰኛው ይጋልባል፤ ሰይፍ ይንቦገቦጋል፤ ጦር ያብረቀርቃል፤ የሞተው ብዙ ነው፤ ሬሳ በሬሳ ሆኖአል፤ ስፍር ቍጥር የለውም፤ መተላለፊያ አልተገኘም።” (ላይት ፍሮም ዚ ኤንሸንት ፓስት የተሰኘው መጽሐፍ፣ አሦርን “ምሕረት የለሽ የጥፋት መሣሪያ” በማለት የጠራት ሲሆን አሦራውያን “በጭካኔያቸው የታወቁ መሆናቸው በጠላቶቻቸው ላይ ሽብር ለመልቀቅ የሚጠቀሙበት ዘዴ” እንደነበር ይገልጻል። ዳግማዊ አሹርናሲርፓል የሚባለው የአሦር ንጉሥ በተቃወሙት ሰዎች ላይ ስለወሰደው እርምጃ በጉራ የተናገረው ሐሳብ ከዚህ በታች ቀርቧል፦
“በከተማው መግቢያ ላይ ዓምድ አቆምሁ፤ ከዚያም ያመፁብኝን አለቆች በሙሉ ቆዳቸውን ገፍፌ በዓምዱ ላይ ለጠፍኩት፤ አንዳንዶቹን በዓምዱ ውስጥ እንደ ግድግዳ ያቆምኳቸው ሲሆን አንዳንዶቹን ደግሞ በዓምዱ ላይ ሰቀልኳቸው። . . . ያመፁብኝን ሹማምንትና መኳንንት እጆችና እግሮች ቆረጥኩ። . . . ከምርኮኞቹ መካከል ብዙዎቹን በእሳት አቃጠልኳቸው፤ በርካቶቹንም ከነሕይወታቸው ማረክኋቸው።” የአርኪኦሎጂ ተመራማሪዎች፣ የአሦርን ቤተ መንግሥቶች በቁፋሮ ባገኙበት ጊዜ አሦራውያን በምርኮኞቻቸው ላይ የፈጸሟቸውን እጅግ ዘግናኝ ድርጊቶች የሚያሳዩ ሥዕላዊ መግለጫዎችን በቤተ መንግሥቶቹ ግድግዳዎች ላይ ተመልክተዋል።
በ740 ዓ.ዓ. አሦራውያን፣ የሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ዋና ከተማ የነበረችውን ሰማርያን ድል አድርገው በመቆጣጠር ሕዝቦቿን በግዞት ወሰዱ። ከስምንት ዓመታት በኋላ ደግሞ ይሁዳን ወረሩ። * (2 ነገሥት 18:13) የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም፣ የይሁዳ ንጉሥ የሆነውን ሕዝቅያስን 30 መክሊት ወርቅና 300 መክሊት ብር እንዲገብር ጠየቀው። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ሕዝቅያስ ይህን ግብር መክፈሉን ይናገራል። ሰናክሬም ግን ይህም እንዳይበቃው የይሁዳ ዋና ከተማ የነበረችው የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ለእሱ እጃቸውን እንዲሰጡ ማስፈራራቱን ተያያዘው።—2 ነገሥት 18:9-17, 28-31
የአርኪኦሎጂ ተመራማሪዎች በነነዌ ባገኙት የሰናክሬም ዜና ታሪክ ላይ ይኸው ክንውን ተዘግቧል። ስድስት ጎን ባለው አንድ የሸክላ ቅርጽ ላይ የአሦር ንጉሥ እንደሚከተለው በማለት በጉራ የተናገረው ሐሳብ ሰፍሯል፦ “አይሁዳዊው ሕዝቅያስ ሊገዛልኝ ፈቃደኛ ስላልሆነ 46ቱን የጸኑ ከተሞቹን፣ የግንብ ምሽጎቹንና በአካባቢያቸው ያሉትን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ትንንሽ መንደሮች ከብቤ ድል አደረግኳቸው። . . . እሱንም [ሕዝቅያስን] በጎጆዋ ውስጥ እንዳለች ወፍ ንጉሣዊ መኖሪያው በሆነችው በኢየሩሳሌም እስረኛ አደረግኩት።” ከዚያም ሰናክሬም፣ ሕዝቅያስ “30 መክሊት ወርቅና 800 መክሊት ብር፣ የከበሩ ድንጋዮች፣ . . . (እንዲሁም) የተለያዩ ውድ ነገሮች” እንደላከለት ተናግሯል፤ እዚህ ላይ ሰናክሬም ሕዝቅያስ የላከለትን የብር መክሊቶች መጠን አጋንኖታል።
ይሁንና ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን ድል አድርጎ እንደተቆጣጠረ አለመናገሩን ልብ በል። ሰናክሬም፣ አምላክ በጉዳዩ ጣልቃ በመግባት ሠራዊቱን ድል ስለማድረጉ ምንም የገለጸው ነገር የለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ግን የአምላክ መልአክ በአንድ ሌሊት 185,000 አሦራውያን ወታደሮችን ገድሏል። (2 ነገሥት 19:35, 36) ጃክ ፊኔጋን የተባሉ ምሑር “የአሦራውያን ነገሥታት ዘገባዎች በጉራ የተሞሉ ከመሆናቸው አንጻር ሰናክሬም የገጠመውን ሽንፈት ይመዘግባል ብሎ መጠበቅ ያዳግታል” ብለዋል።
እምነት የሚጣልበት ትንቢት
አሦር ከመውደቋ ከአንድ መቶ ዓመታት ገደማ በፊት ይሖዋ አምላክ እነዚህን ትዕቢተኛ ወራሪዎች ለሕዝቡ ስላሳዩት ንቀት የእጃቸውን እንደሚሰጣቸው ነቢዩ ኢሳይያስ ተናግሮ ነበር። ይሖዋ “የአሦርን ንጉሥ ስለ ልቡ ትዕቢትና ስለ ንቀት አመለካከቱ እቀጣዋለሁ” ብሎ ነበር። (ኢሳይያስ 10:12) ከዚህም በላይ የአምላክ ነቢይ የነበረው ናሆም፣ ነነዌ እንደምትበዘበዝ ብሎም በሮቿ ለጠላቶቿ ክፍት እንደሚሆኑና ጠባቂዎቿ እንደሚሸሹ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ናሆም 2:8, 9፤ 3:7, 13, 17, 19) ሶፎንያስ የተባለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ ነቢይም ነነዌ “ፍጹም ባድማ” እንደምትሆን ጽፎ ነበር።—ሶፎንያስ 2:13-15
ስለ ነነዌ ጥፋት የሚገልጹት እነዚህ ትንቢቶች በ632 ዓ.ዓ. ፍጻሜያቸውን አገኙ። በዚያ ወቅት ነነዌ በተባበሩት የባቢሎንና የሜዶን ሠራዊቶች እጅ ስትወድቅ የአሦር አገዛዝ አሳፋሪ የሆነ ሽንፈት ተከናነበ። በወቅቱ የተፈጸመውን ሁኔታ የሚዘግብ አንድ የባቢሎናውያን ዜና ታሪክ፣ ወራሪዎቹ “ከተማይቱንና ቤተ መቅደሷን የበዘበዙ” ከመሆኑም ሌላ ነነዌን “የፍርስራሽ ክምር” እንዳደረጓት ይገልጻል። በአንድ ወቅት ነነዌ የነበረችበት ቦታ በዛሬው ጊዜ ኢራቅ ውስጥ ከሞሱል ከተማ ማዶ በጤግሮስ ወንዝ ምሥራቃዊ ዳርቻ ላይ የፍርስራሽ ክምር ሆኖ ይታያል።
የአሦር መጥፋት ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸምም አድርጓል። ይህ ከመሆኑ ቀደም ብሎ ማለትም በ740 ዓ.ዓ. አሦራውያን የአሥሩን ነገድ የእስራኤል መንግሥት በግዞት ወስደውት ነበር። አሦራውያን ይህን ባደረጉበት ጊዜ አካባቢ ነቢዩ ኢሳይያስ፣ ይሖዋ ‘አሦርን እንደሚያደቀው፣’ ‘እንደሚረግጠው’ እና እስራኤልን ወደ ትውልድ አገሩ መልሶ እንደሚያመጣው ትንቢት ተናግሮ ነበር። ኢሳይያስ “[አምላክ] የተረፈውን የሕዝቡን ቅሬታ ከአሦር . . . ይሰበስባል” በማለት ጽፎ ነበር። ሁለት መቶ ከሚያህሉ ዓመታት በኋላ ይህ ትንቢት በትክክል ተፈጽሟል!—ኢሳይያስ 11:11, 12፤ 14:25
እምነት ልትጥልበት የምትችል ተስፋ
ነነዌ ከመውደቋ ከረጅም ጊዜ በፊት ይኸውም ነገሥታቶቿ ጠላቶቻቸውን በፍርሃት ያርበደብዱ በነበሩበት ወቅት ኢሳይያስ ከሁሉ የተለየ ገዥ እንደሚመጣ ትንቢት ተናግሮ ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሕፃን ተወልዶልናልና፤ ወንድ ልጅ ተሰጥቶናል፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። ስሙም . . . የሰላም ልዑል ይባላል። ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም፤ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም፣ መንግሥቱን በፍትሕና በጽድቅ ይመሠርታል፤ ደግፎ በመያዝም ያጸናዋል። በዳዊት ዙፋን ይቀመጣል፤ አገሩንም ሁሉ ይገዛል፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ቅናት ይህን ያደርጋል።”—ኢሳይያስ 9:6, 7
“የሰላም ልዑል” የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ግዛት መላውን ምድር የሚያጠቃልል ይሆናል። መዝሙር 72:7, 8 እንዲህ ይላል፦ “በዘመኑ ጽድቅ ይሰፍናል፤ ጨረቃ ከስፍራዋ እስከምትታጣ ድረስም ሰላም ይበዛል። ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፣ ከታላቁም ወንዝ [ኤፍራጥስ] እስከ ምድር ዳርቻ ይገዛል።”
ይሖዋ አምላክ በዚህ ኃያል “የሰላም ልዑል” አማካኝነት በመዝሙር 46:8, 9 (የ1954 ትርጉም) ላይ የገባውን ቃል ይፈጽማል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “የእግዚአብሔርን ሥራ፣ በምድር ያደረገውንም ተአምራት እንድታዩ ኑ። እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል፤ ቀስትን ይሰብራል፣ ጦርንም ይቈርጣል፣ በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል።”
ኢየሱስ እንዳደረገው ሁሉ በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮችም ሰዎች የሰላምን መንገድ እንዲያውቁ የሚረዳ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት እየሰጡ ሲሆን ይህም ከላይ ለተጠቀሰው ትንቢት ፍጻሜ መቅድም ይሆናል። በእርግጥም በኢሳይያስ 2:4 ላይ የተመዘገበውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አምላክ እንጂ ሰው ሊፈጽመው አይችልም፤ ትንቢቱ “እነርሱም ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጋሉ። ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ጦርነትንም ከእንግዲህ አይማሩም” ይላል። ከዚህ በተቃራኒ ግን በዛሬው ጊዜ የዓለም መሪዎች ለወታደራዊ ዓላማ በየዓመቱ አንድ ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያወጣሉ!
መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት ታሪክና ትንቢት የያዘ መሆኑ ከሌሎች መጻሕፍት የተለየ እንዲሆን የሚያደርገው ከመሆኑም ሌላ በቅን ልብ እውነትን ለሚፈልጉ ሰዎች ይህ መጽሐፍ በእርግጥም እምነት ልንጥልበት የምንችል እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። በዚህ አምድ ሥር በቀጣዩ እትም ላይ የሚወጣው ርዕስ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የሦስተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት ዋና ከተማ በነበረችው በጥንቷ ባቢሎን ላይ የሚያተኩር ይሆናል።
^ አን.9 ከንጉሥ ሰለሞን የግዛት ዘመን በኋላ አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ለሁለት ተከፍሎ ነበር። የይሁዳና የብንያም ነገዶች ደቡባዊውን መንግሥት ሲመሠርቱ ሌሎቹ አሥር ነገዶች ደግሞ ሰሜናዊውን መንግሥት መሠረቱ። የደቡባዊው መንግሥት ዋና ከተማ ኢየሩሳሌም ስትሆን ሰማርያ ደግሞ የሰሜናዊው መንግሥት ዋና ከተማ ነበረች።