አስደናቂ የሆነው የሳልመን የዋና ዘዴ
ንድፍ አውጪ አለው?
አስደናቂ የሆነው የሳልመን የዋና ዘዴ
● በርካታ የሳልመን ዝርያዎች እንቁላላቸውን የሚጥሉት ወንዞች በሚመነጩባቸው አካባቢዎች ነው፤ ወደ እነዚህ አካባቢዎች ለመድረስ ቁልቁል የሚፈሰውን ውኃ እየታገሉ ሽቅብ መዋኘት ይኖርባቸዋል። ይሁንና እንዲህ ያለውን አስቸጋሪ ጉዞ ብዙም ሳይደክሙ የሚወጡት እንዴት ነው? እነዚህ የዓሣ ዝርያዎች ከሚናወጠው ውኃ ጋር ከመታገል ይልቅ ብዙም ኃይል ሳያባክኑ ለመዋኘት ነውጡን ይጠቀሙበታል። እንዴት?
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ሳልመኖች ከሚናወጠው ውኃ ጋር እየታገሉ ለመዋኘት አይሞክሩም። ከዚህ ይልቅ ወንዙ ቁልቁል በሚንደረደርበት ጊዜ ከዓለቶች፣ ከዛፍ ቅርንጫፎች ወይም ከሌሎች ነገሮች ጋር ሲጋጭ በሚፈጠረው የውኃ አዙሪት ወይም ሽክርክሪት እየተጠቀሙ ሽቅብ ስለሚዋኙ ጉልበታቸውን አያባክኑም። ወራጁ ውኃ ከሆነ ነገር ጋር ሲጋጭ በስተግራውና በስተቀኙ በኩል ሽክርክሪት ስለሚፈጠር ዓሣው እየተጠማዘዙ የሚመጡትን የእነዚህን ሽክርክሪቶች ቅርጽ ተከትሎ ሰውነቱን እያጠማዘዘና አዙሪቱ በፈጠረው ክፍተት መሃል እየተሽሎከለከ ብዙም ጉልበት መጠቀም ሳያስፈልገው ሽቅብ ይጓዛል። (ሥዕሉን ተመልከት።) እጅብ ብለው የሚጓዙ በርካታ ዓሦች ከፊታቸው የሚዋኙት ዓሦች የሚፈጥሩትን ሽክርክሪት በመጠቀም ብዙም ጉልበት ሳያባክኑ ይዋኛሉ። ሳልመን የተባሉት ዓሦች የራሳቸው ሰውነት በሚፈጥረው ነውጥ እንኳ ተጠቅመው መዋኘት ይችላሉ!
ተመራማሪዎች፣ ሳልመን ጉልበት ሳያባክን የሚዋኝበትን ዘዴ በመኮረጅ ዝግ ብሎ ከሚፈስ ውኃ ኃይል ለማመንጨት ያስባሉ። አሁን ያሉት በውኃ ኃይል የሚንቀሳቀሱ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች፣ በአብዛኛው ኃይል የሚያመነጩት በሰዓት 9.3 ኪሎ ሜትር በሚደርስ ወይም ከዚያ በሚበልጥ ፍጥነት ከሚፈስ ውኃ ነው። ተመራማሪዎች የውኃ ሽክርክሪት የሚፈጥረውን ንዝረት በመጠቀም ኃይል የሚያመነጭ መሣሪያ ለሙከራ የሠሩ ሲሆን ይህ መሣሪያ በሰዓት 3.7 ኪሎ ሜትር ብቻ ከሚፈስ ውኃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ይችላል። * ይሁን እንጂ ይህ ቴክኖሎጂ እንደ ሳልመን ያሉት የዓሣ ዝርያዎች ከሚጠቀሙበት ዘዴ ጋር ፈጽሞ ሊወዳደር አይችልም። በዩናይትድ ስቴትስ፣ የሚሺገን ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ማይክል በርኒትሳስ “በአሁኑ ወቅት የዓሦችን ያህል ችሎታ የለንም” በማለት ተናግረዋል።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? ሳልመን የውኃው ሽክርክሪት በሚፈጥረው ኃይል የመጠቀም ችሎታው እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.5 በምድር ላይ አብዛኞቹ ጅረቶች የሚጓዙበት ፍጥነት በሰዓት ከ5.6 ኪሎ ሜትር ያነሰ በመሆኑ ይህ ግኝት ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Top: © photolibrary. All rights reserved.