በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

ከሀብት ይልቅ ብልጫ ያላቸው በረከቶች (መጋቢት 2009) በዚህ ርዕስ ላይ፣ ኮስታስ “አምላክ የቅንጦት ሕይወት እንድንኖር አይፈልግም” በማለት የተናገረው ሐሳብ ተጠቅሶ ይገኛል። ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ እሱን እስካስቀደሙ ድረስ የሚያከማቹት ቁሳዊ ነገር ብዙም ሆነ ጥቂት ገደብ የሚያበጅላቸው አይመስለኝም ነበር። ይሖዋን በታማኝነት እስካገለገልን ድረስ የቅንጦት ሕይወት ብንመራ ስህተት ነው?

ጄ. ዲ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“የንቁ!” መጽሔት አዘጋጆች መልስ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ሀብትን አያወግዝም። እንዲያውም በጥንት ጊዜ የነበሩ በርካታ የአምላክ አገልጋዮች ሀብታሞች ነበሩ። (ዘፍጥረት 25:5፤ 26:12-16፤ ኢዮብ 1:1-3) ይሁንና ሀብታም የሆኑ የአምላክ አገልጋዮች “ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመነጭ” እንዳልሆነ መዘንጋት የለባቸውም። (1 ዮሐንስ 2:16) ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያው ጳውሎስ “የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር ነው” ብሏል። አክሎም አንዳንዶች፣ ሀብታም ለመሆን ካላቸው ምኞት የተነሳ መንፈሳዊ ጉዳዮቻቸውን መሥዋዕት በማድረጋቸው “ከእምነት ጎዳና ስተው ወጥተዋል፤ እንዲሁም ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል” ሲል ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 6:10) እርግጥ ነው፣ የአምላክ ቃል ሀብታሞች ከሌሎች የበለጠ ነገር ስላላቸው የጥፋተኝነት ስሜት ሊያድርባቸው እንደሚገባ አይናገርም። ክርስቲያኖች በቁሳዊ ሀብት ረገድ ምንም ያህል ትንሽ ወይም ብዙ ቢኖራቸው “ለጋሶችና ለማካፈል ፈቃደኞች እንዲሆኑ” ተበረታተዋል።—1 ጢሞቴዎስ 6:18

ሊሰማ የሚችል ድምፅ አልባ ንግግር (ጥቅምት 2008) ሬት ሲንድሮም በተባለ በሽታ ስለተያዘች ሂላሪ የተባለች ልጅ የሚናገረው ይህ ርዕስ በጣም አበረታቶኛል። የአምስት ዓመቱ የልጅ ልጄ ማየት፣ መስማት፣ መናገር፣ መራመድና መቀመጥ አይችልም። ስዘምርለት፣ ሳነብለት፣ ሳዋራውና ስደባብሰው ወይም ሰውነቱን ሳሸው አእምሮው ውስጥ የሆነ ነገር ይሰማው ይሆናል ብዬ ተስፋ ማድረግ ጀምሬያለሁ። የሂላሪ እናት ‘ምንም እንኳ እኔ የምትናገረውን ልሰማት ባልችልም ይሖዋ ግን ይሰማታል’ በማለት የተናገረችውን ሐሳብ ሳነብ አለቀስኩ። የእሷ ተሞክሮ የልጅ ልጄ ቃላት አውጥቶ መናገር ባይችልም ልቡ ውስጥ ያለውን ይሖዋ እንደሚያውቅ እንድገነዘብ ረድቶኛል።

ኤም. ኣ.፣ ጃፓን

ልጄ 43 ዓመቷ ቢሆንም ያለባትን ችግርና መንስኤውን ለመጀመሪያ ጊዜ እንድረዳ ያስቻለኝ ይህ ርዕስ ነው። ለሂላሪ፣ ለእናቷና ለእህቷ በጣም ነው ያዘንኩት። የምንኖረው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ቢሆንም ያለንበት ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፤ የእነሱን እምነት፣ ፍቅርና ጽናት አደንቃለሁ።

ቲ. ዋይ.፣ ጋና

ፅንስ ማስወረድ ምንም ችግር የማያስከትል መፍትሔ ነው? (ሰኔ 2009) ፅንስ ማስወረድን በተመለከተ ስላወጣችሁት ተከታታይ ርዕስ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ። በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለሁ አስወርጃለሁ፤ ይህን ማድረጌ ደግሞ በጣም ይጸጽተኛል። በአሁኑ ጊዜ እውነትን ባላውቅ ኖሮ ተስፋ እቆርጥ ነበር። ተስፋ ስላለኝና ይሖዋ ይቅር ባይ መሆኑን ስላወቅሁ በጣም አመስጋኝ ነኝ።

ስም አልተጠቀሰም፣ ዩናይትድ ስቴትስ

የወጣቶች ጥያቄ . . . የወላጅ ሞት ያስከተለብኝን ሐዘን እንዴት መቋቋም እችላለሁ? (ነሐሴ 2009) ዕድሜዬ 22 ነው፤ አባቴ ሳይታሰብ በድንገት መሞቱ በከፍተኛ ሐዘን እንድዋጥ አድርጎኛል። ይህ ርዕስ እንደገለጸው በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ በምሰጣቸው ወቅቶች ከአባቴ ጋር መሆን አለመቻሌ በጣም ያሳዝነኛል። ከሦስት ዓመት በኋላም ወደ ቀድሞ ሕይወቴ መመለስ ከብዶኛል። ያም ሆኖ ይህ ርዕስ በጣም አጽናንቶኛል። በዚህ ርዕስ ላይ የወጡት ሐዘንን ለመቋቋም የሚረዱ ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ከባድ ቢሆኑም ውጤታማ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ለምታከናውኑት ግሩም ሥራ በጣም አመሰግናችኋለሁ።

ኤን. ፒ.፣ ፈረንሳይ