ከትንሽ ፍሬ ግዙፍ ወደሆነ የኦክ ዛፍ
ከትንሽ ፍሬ ግዙፍ ወደሆነ የኦክ ዛፍ
● አንድ ትንሽ ፍሬ ከዛፉ ላይ ተቀንጥሶ መሬት ላይ ይወድቃል። ከዚያም ጥድፍ ጥድፍ እያለች የምትሄድ አንዲት ሸለውለዊት (squirrel) ፍሬውን አፈር ውስጥ ትቀብረውና እንደተረሳ ይቀራል፤ በኋላም ፍሬው ማቆጥቆጥ ይጀምራል። ከጊዜ በኋላ ትልቅ የኦክ ዛፍ ይሆናል፤ ይህ ዛፍ በብሪታንያ ከሚገኙት አገር በቀል ዛፎች ሁሉ እጅግ ግዙፉ ነው።
ታዋቂ የሆኑ የታሪክ ዘገባዎችና አፈ ታሪኮች እንደሚሉት ከሆነ የኦክ ዛፍ ከሺህ ለሚበልጡ ዓመታት ይኖራል። ከዚህም በላይ የአንዳንዶቹ ቁመት እስከ 40 ሜትር ሊደርስ ይችላል! ዕድሜ ጠገብ የሆኑት የኦክ ዛፎች በሰፋፊ ግንዶቻቸውና ወደጎን በተንሰራፉት ቅርንጫፎቻቸው ይታወቃሉ። ብሪታንያ ሁለት ዓይነት የኦክ ዛፍ ዝርያዎች ሲኖሯት በመላው ዓለም ግን 450 የሚያክሉ ዝርያዎች ይገኛሉ። ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው አነስተኛ መጠን ያለው ፍሬያቸው ነው።
በብሪታንያ ከሚገኙት ዛፎች ሁሉ ለበርካታ ዓይነት ሕያዋን ፍጥረታት መጠለያ በመሆን ረገድ የኦክ ዛፍን የሚወዳደረው የለም። ከእነዚህም መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የነፍሳት ዝርያዎች ይገኛሉ። ብዙ አባጨጓሬዎች በበጋ ወቅት የሚወጡትን የዛፉን ለስለስ ያሉ ቅጠሎች መመገብ ይወዳሉ። ይሁን እንጂ ዛፉ ራሱን መከላከል ይችላል። ለጋዎቹ ቅጠሎች ነፍሳቶች እንዳይበሏቸው ለማድረግ ሲሉ መጥፎ ጣዕምና ጠረን ያለው ንጥረ ነገር ያመነጫሉ።
ሁሉም የዛፉ ክፍሎች ለነፍሳት መጠለያነት ያገለግላሉ። በላዩ ላይ የሚኖሩት በርካታ ነፍሳት በጣም ብዙ የሆኑ ወፎችንና ሸረሪቶችን ይስባሉ። ጥንዚዛዎች የግንዱን ወፍራም ቅርፊት ይቦረቡራሉ። ጉጉቶችና ብዙ ቁጥር ያላቸው የሌሊት ወፎች ግንዱ ላይ የሚገኙትን ክፍተቶች ለመኖሪያነት ይጠቀሙባቸዋል። እንደ አይጥ፣ አይጠ መጎጥ፣ ጥንቸል፣ ሸለምጥማጥና ቀበሮ ያሉ ትናንሽ የዱር እንስሳት በዛፉ ሥሮች መካከል ባለው ቦታ ተጠልለው ይኖራሉ።
የኦክ ዛፍ የወዳደቁትን ቅጠሎቹንና ፍሬዎቹን የሚያስወግድበት መንገድ አለው። እድገቱን ከጨረሰ አንድ የኦክ ዛፍ ላይ በየዓመቱ ሩብ ሚሊዮን የሚያክሉ ቅጠሎች ይረግፋሉ። ፈንገሶችና ባክቴሪያዎች መሬት ላይ የወደቁትን ቅጠሎች በማበስበስ ጠቃሚ የሆኑት ንጥረ ነገሮች ወደ አፈር ውስጥ እንዲመለሱ ያደርጋሉ። አንድ ዛፍ በአንዳንድ ዓመታት እስከ 50,000 የሚደርሱ ፍሬዎችን ያፈራል። አእዋፍና እንስሳት አብዛኞቹን ፍሬዎች ይበሏቸዋል ወይም ይሰበስቧቸዋል። ምስጦችና ጥንዚዛዎች የሞቱ ቅርንጫፎችን ሲያስወግዱ ፈንገሶች ደግሞ የዛፉን ቅርፊቶች ይመገባሉ።
ከኦክ የሚዘጋጅ ጣውላ በጣም ጠንካራና ረዥም ዕድሜ መቆየት የሚችል ነው። ከብዙ ዘመናት ጀምሮ ቤቶችን ለመገንባትና ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የቤት ቁሳቁሶችን ለመሥራት ተመራጭ ሆኖ ቆይቷል። ቢራና ወይን ጠጅ ለማቆየት የሚያገለግሉ በርሜሎችን ለመሥራትም በጣም ይፈለጋል። የብሪታንያ ባሕር ኃይል ለብዙ ዓመታት በባሕር ላይ የበላይነቱን ይዞ ሊቆይ የቻለው ከኦክ ዛፍ የተሠሩ ጠንካራ መርከቦች ስለነበሩት ነው።
ዛሬም ቢሆን ከኦክ የሚዘጋጅ ጣውላ በጣም ይወደዳል። የብሪታንያ መልክዓ ምድር ወሳኝ ገጽታ ሆኖ የቆየው ይህ ዛፍ በጠንካራነቱ፣ በአስተማማኝነቱና ረጅም ዕድሜ በመኖሩ መወደሱ የተገባ ነው። የኦክ ዛፍ ከአንድ ትንሽ ፍሬ ተነስቶ እጅግ ግዙፍ መሆን መቻሉ በእርግጥም ድንቅ የተፈጥሮ ሥራ ነው።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኦክ ዛፍ ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ ሊኖር ይችላል፤ ቁመቱ እስከ 40 ሜትር ውፍረቱ ደግሞ እስከ 12 ሜትር ሊደርስ ይችላል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Tree: © John Martin/Alamy; acorn: © David Chapman/Alamy