በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራሴን ችዬ ለመኖር ደርሻለሁ?

ራሴን ችዬ ለመኖር ደርሻለሁ?

የወጣቶች ጥያቄ

ራሴን ችዬ ለመኖር ደርሻለሁ?

“አሥራ ዘጠኝ ዓመት ቢሆነኝም አሁንም ከወላጆቼ ጋር እየኖርኩ በመሆኑ ሰዎች ዝቅ አድርገው እንደሚመለከቱኝ የሚሰማኝ ጊዜ አለ፤ ራሴን ችዬ መኖር ካልጀመርኩ በቀር ትልቅ ሰው መሆን እንደማልችል የሚያስቡ ይመስላል።”—ኬቲ *

“ሃያ ዓመት ሊሞላኝ ቢሆንም ሕይወቴን እንደፈለግሁት መምራት አለመቻሌ ያስጠላኛል። ወላጆቼ የእኔን ፍላጎት ችላ ብለው ከእኔ የተሻለ እንደሚያውቁ መናገራቸው ስለሰለቸኝ ከቤት ወጥቼ ለመኖር አስቤያለሁ።”—ፊዮነ

ቤት ለመውጣት መመኘት የጀመርከው ራስህን ችለህ ለመኖር የሚያስችል ዕድሜ ላይ ከመድረስህ ከረጅም ጊዜ በፊት ሊሆን ይችላል። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያለው ስሜት ተፈጥሯዊ ነው። ደግሞም የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ወጣቶች አድገው አባታቸውንና እናታቸውን በመተው የራሳቸውን ቤተሰብ እንዲመሠርቱ ነው። (ዘፍጥረት 2:23, 24፤ ማርቆስ 10:7, 8) ይሁን እንጂ የበለጠ ነፃነት ለማግኘት ጓግተሃል ማለት ራስህን ችለህ ለመኖር ዝግጁ ነህ ማለት ነው? ሊሆን ይችላል። ይሁንና በእርግጥ ከቤት ወጥተህ ራስህን ችለህ ለመኖር ዝግጁ መሆንህን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? መልስ ልትሰጥባቸው የሚያስፈልጉ ሦስት ዓበይት ጥያቄዎችን ተመልከት። የመጀመሪያው ጥያቄ የሚከተለው ነው።

ዓላማዬ ምንድን ነው?

ከቤት ለመውጣት የፈለግክበትን ትክክለኛ ዓላማ ለመረዳት የሚከተለውን ዝርዝር ተመልከት። ከእነዚህ መካከል ከቤት ለመውጣት ምክንያት ይሆኑኛል የምትላቸውን ነገሮች ዋነኛ ከምትለው ጀምረህ በቅደም ተከተል ቁጥር ስጣቸው።

․․․ በቤት ውስጥ ካሉት ችግሮች ለመሸሽ

․․․ የበለጠ ነፃነት ለማግኘት

․․․ ጓደኞቼ ለእኔ ያላቸው ግምት ከፍ እንዲል

․․․ ብቻውን ከሚኖር ጓደኛህ ጋር በመኖር እሱን ለመርዳት

․․․ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆኖ ወደ ሌላ አካባቢ ለመሄድ

․․․ ራሴን ችዬ ለመኖር የሚያስችል ልምድ ለመቅሰም

․․․ ወላጆቼ ላይ ተጨማሪ ሸክም ላለመሆን

․․․ ሌላ

ከላይ የተዘረዘሩት ምክንያቶች ሁሉ መጥፎ ላይሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ከቤት ለመውጣት የተነሳሳህበት ምክንያት ከወላጆችህ ተለይተህ መኖር ከጀመርክ በኋላ ደስተኛ እንድትሆን ወይም እንዳትሆን ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በቤት ውስጥ ካሉት ችግሮች ለመሸሽ ወይም የበለጠ ነፃነት ለማግኘት ብለህ ከቤት ብትወጣ ያልጠበቅከው ሌላ ችግር ሊያጋጥምህ ይችላል።

በ20 ዓመቷ ለተወሰነ ጊዜ ከቤት ወጥታ የነበረችው ዳንየል ካገኘችው ተሞክሮ ብዙ ተምራለች። እንዲህ ትላለች፦ “ሁላችንም ብንሆን ነፃነታችንን በሆነ መንገድ የሚገድብ ነገር ያጋጥመናል። ለብቻህ ስትኖር የሥራህ ባሕርይ ወይም የገንዘብ እጥረት ማድረግ የምትችለውን ነገር እንዳታደርግ እንቅፋት ሊሆንብህ ይችላል።” ለስድስት ወራት ወደ ሌላ አገር ሄዳ የነበረችው ካርመን እንዲህ ብላለች፦ “እንዲህ ያለውን አጋጣሚ ማግኘቴ አስደስቶኛል፤ ትርፍ ጊዜ እንደሌለኝ ብዙ ጊዜ ይሰማኝ ነበር። ቤት ማጽዳት፣ መጠገን፣ የግቢውን አትክልት መንከባከብ፣ ልብስ ማጠብ፣ ወለሉን ማጽዳትና የመሳሰሉትን የተለመዱ የቤት ውስጥ ሥራዎች ማከናወን ነበረብኝ።”

ከቤት መውጣትህ ተጨማሪ ነፃነት ሊያስገኝልህ እንዲሁም ጓደኞችህ ለአንተ ያላቸው ግምት ከፍ እንዲል ሊያደርግ እንደሚችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ወጪዎችህን የምትሸፍነው፣ ምግብህን የምታዘጋጀውና ቤትህን የምታጸዳው አንተው ራስህ ከመሆኑም በላይ ቤተሰብህና ጓደኞችህ አጠገብህ ስለማይኖሩ የተወሰነውን ጊዜ ብቻህን ማሳለፍ ይኖርብሃል። በመሆኑም ሌሎች ሰዎች የችኮላ ውሳኔ ላይ እንድትደርስ እንዲያደርጉህ አትፍቀድ። (ምሳሌ 29:20) ከቤት ለመውጣት የሚያስችል በቂ ምክንያት ቢኖርህም እንኳ ስኬታማ ለመሆን ሌላ የሚያስፈልግህ ነገር ይኖራል። ራስህን ችለህ ለመኖር አንዳንድ አስፈላጊ ችሎታዎችን ማዳበር ይኖርብሃል፤ ይህ ደግሞ ወደ ሁለተኛው ጥያቄ ይመራናል።

ዝግጁ ነኝ?

ራስህን ችለህ ለብቻህ መኖር ለሽርሽር ከከተማ ወጣ ከማለት ጋር ይመሳሰላል። ድንኳን መትከል፣ እሳት ማቀጣጠል፣ ምግብ ማብሰል ወይም ካርታ ማንበብ ሳታውቅ ወደ ገጠራማ አካባቢ ጉዞ ለማድረግ ትነሳለህ? በጭራሽ አታደርገውም! ሆኖም ብዙ ወጣቶች ስለ ቤት አያያዝ በቂ ችሎታ ሳይኖራቸው ከቤት ይወጣሉ።

ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 14:15) ራስህን ችለህ ለመኖር ዝግጁ መሆን አለመሆንህን ማወቅ እንድትችል የሚከተሉትን ንዑስ ርዕሶች ተመልከት። አሉኝ በምትላቸው ችሎታዎች ላይ ምልክት አድርግ፤ እንዲሁም ላዳብራቸው ይገባኛል በምትላቸው ችሎታዎች ላይ ደግሞ ምልክት አድርግ።

◯ ገንዘብ አያያዝ። የ19 ዓመቷ ሰሪነ “ከራሴ ገንዘብ ላይ ለምንም ነገር ሒሳብ ከፍዬ አላውቅም። ከቤት ወጥቼ የራሴን ገንዘብ ባጀት ስለማድረግ ሳስብ ያስፈራኛል” ብላለች። ታዲያ ስለ ገንዘብ አያያዝ መማር የምትችለው እንዴት ነው?

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ጥበበኞች ያድምጡ፤ ትምህርታቸውንም ያዳብሩ” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 1:5) ታዲያ ወላጆችህን አንድ ሰው በየወሩ ለቤት ኪራይ ወይም የባንክ ዕዳ ለመክፈል፣ ለምግብ፣ ለመኪና ወጪ ወይም ለመጓጓዣ ምን ያህል እንደሚያስፈልገው ለምን አትጠይቃቸውም? ከዚያም ወላጆችህ ለገንዘብህ እንዴት ባጀት ማውጣት እንደምትችልና የተለያዩ ወጪዎችህን እንዴት መሸፈን እንደምትችል እንዲያስተምሩህ አድርግ። በባጀት የመመራት ልማድ ማዳበር ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? የ20 ዓመቱ ኬቨን እንዲህ ይላል፦ “ለብቻችሁ መኖር ስትጀምሩ ብዙ ያልተጠበቁ ወጪዎች ያጋጥሟችኋል። ካልተጠነቀቃችሁ ዕዳ ውስጥ ልትዘፈቁና ዕድሜ ልክ ስትገፈግፉ ልትኖሩ ትችላላችሁ።”

ታዲያ ከቤት ከመውጣትህ በፊት ሁኔታው ምን እንደሚመስል መሞከር ትፈልጋለህ? ሥራ ካለህ ለተወሰነ ጊዜ በየወሩ ለምግብ፣ ለቤት ኪራይና ለሌሎች ወጪዎች የሚያስፈልገውን አጠቃላይ ገንዘብ ለወላጆችህ ስጣቸው። ከወላጆችህ ጋር ሳለህ ለመተዳደሪያ የሚሆንህን ወጪ ለመክፈል ካልቻልክ ወይም ፈቃደኛ ካልሆንክ ራስህን ችለህ ለመኖር ዝግጁ አይደለህም ማለት ነው።—2 ተሰሎንቄ 3:10, 12

◯ የቤት ውስጥ ሥራ። የ17 ዓመቱ ብራየን ከቤት ወጥቶ ስለመኖር ሲያስብ በጣም የሚያስፈራው ነገር የራሱን ልብስ ማጠብ እንደሆነ ተናግሯል። ታዲያ ራስህን ለመቻል ዝግጁ መሆንህን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? የ20 ዓመት ወጣት የሆነው አሮን የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥቷል፦ “ለአንድ ሳምንት ያህል ራሳችሁን ችላችሁ እንደወጣችሁ አድርጋችሁ ለመኖር ሞክሩ። ራሳችሁ የሠራችሁትን፣ ራሳችሁ የገዛችሁትንና ከራሳችሁ ገንዘብ አውጥታችሁ የከፈላችሁበትን ምግብ ብሉ። ራሳችሁ ያጠባችሁትንና የተኮሳችሁትን ልብስ ልበሱ። ቤታችሁን ራሳችሁ አጽዱ። እንዲሁም የሚወስዳችሁና የሚመልሳችሁ ሰው ሳይኖር ወደሚያስፈልጋችሁ ቦታ ራሳችሁ ለመሄድ ሞክሩ።” ይህን ሐሳብ መከተልህ ሁለት ጥቅሞችን ያስገኝልሃል፦ (1) ጠቃሚ የሆኑ ችሎታዎችን እንድታዳብር ይረዳሃል፤ (2) ወላጆችህ ለሚያደርጉልህ ነገር ያለህን አድናቆት ይጨምርልሃል።

◯ ማኅበራዊ ኑሮ። ከወላጆችህ እንዲሁም ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር ተስማምተህ ትኖራለህ? ካልሆነ ከቤት ብትወጣና ከጓደኛህ ጋር ብትኖር ሕይወት ቀላል እንደሚሆንልህ ይሰማህ ይሆናል። ምናልባት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የ18 ዓመቷ ኢቭ የተናገረችውን ልብ በል፦ “ሁለት ጓደኞቼ ከቤት ወጥተው አብረው መኖር ጀመሩ። ከዚያ በፊት በጣም ጓደኛሞች ነበሩ፤ ይሁን እንጂ ተስማምተው መኖር አልቻሉም። አንደኛዋ ቤቱን በንጽሕናና በሥርዓት የምትይዝ ስትሆን ሌላዋ ግን ዝርክርክ ነበረች። አንዷ መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያላት ስትሆን ሌላዋ ግን እምብዛም ነበረች። ሁለቱም በጭራሽ ሊስማሙ አልቻሉም!”

የ18 ዓመቷ ኤሪን ከቤት ወጥታ መኖር ትፈልጋለች። ሆኖም እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ከወላጆቻችሁ ጋር እያላችሁ ከሰዎች ጋር እንዴት ተስማምታችሁ መኖር እንደምትችሉ ብዙ መማር ትችላላችሁ። ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደምትችሉና ችሎ ማለፍን ትማራላችሁ። ከወላጆቻቸው ጋር የሚፈጠረውን አለመግባባት ለመሸሽ ብለው ከቤት የሚወጡ ወጣቶች የሚማሩት ችግሮችን እንዴት እንደሚፈቱ ሳይሆን ከተፈጠረው ችግር እንዴት እንደሚሸሹ ብቻ መሆኑን አስተውያለሁ።”

◯ የግል መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች። አንዳንዶች ከቤት የሚወጡት ወላጆቻቸው ከሚጠብቁባቸው ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች ለመሸሽ ሲሉ ነው። ሌሎች ደግሞ ከቤት ከወጡ በኋላ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸውንና የአምልኮ ፕሮግራሞቻቸውን ይዘው ለመቀጠል ቢያስቡም ብዙም ሳይቆይ መጥፎ ልማድ ውስጥ ይዘፈቃሉ። ታዲያ ‘አደጋ ደርሶበት እንደተሰባበረ መርከብ እምነትህ እንዳይጠፋ’ ምን ማድረግ ትችላለህ?—1 ጢሞቴዎስ 1:19

የወላጆችህን ሃይማኖታዊ ትምህርት በጭፍን አትቀበል። ይሖዋ አምላክ ሁላችንም የምናምንበትን ነገር ራሳችን መርምረን እንድናረጋግጥ ይፈልጋል። (ሮም 12:1, 2) ስለዚህ ጥሩ የአምልኮና የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም ይኑርህ፤ እንዲሁም ይህን ፕሮግራም በጥብቅ ተከተል። መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችህን በቀን መቁጠሪያ ላይ በመጻፍ ያለ ወላጆችህ ጉትጎታ ለአንድ ወር ያህል ይህን ፕሮግራም መከተል ትችል እንደሆነ ለምን ራስህን አትፈትንም?

ልታስብበት የሚገባው ሦስተኛው ጥያቄ ደግሞ የሚከተለው ነው።

ግቤ ምንድን ነው?

አንዳንዶች ከቤት የሚወጡት ከችግሮች ለመሸሽ ወይም ከወላጆቻቸው ቁጥጥር ነፃ ለመውጣት ነው። እነዚህ ወጣቶች ትኩረታቸው ያረፈው በሚሸሹት ሁኔታ ላይ እንጂ ወደፊት በሚያጋጥማቸው ነገር ላይ አይደለም። ይህ ሁኔታ በመኪና የኋላ መመልከቻ መስታወት ላይ ብቻ ዓይንን ተክሎ ለመንዳት ከመሞከር ጋር ይመሳሰላል። ሾፌሩ ትቶት ያለፈው ነገር ላይ ትኩረት ካደረገ ከፊት ለፊቱ የሚያጋጥመውን ነገር ማየት አይችልም። ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ስኬታማ ለመሆን ከቤት ወጥቶ በመሄድ ላይ ብቻ ሳይሆን በአንድ ዓይነት ጠቃሚ ግብ ላይ ትኩረት አድርግ።

የይሖዋ ምሥክር የሆኑ አንዳንድ ወጣቶች በአገራቸው ውስጥ ባሉ ገለልተኛ ስፍራዎች ወይም በውጭ አገር ለመስበክ ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ሄደዋል። ሌሎች ደግሞ የአምልኮ ቤቶች በሚገነቡባቸው ቦታዎች ለመርዳት ወይም በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ለመሥራት ሲሉ ከቤት ይወጣሉ። ሌሎች ደግሞ ትዳር ከመመሥረታቸው በፊት ለብቻቸው መኖር እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። *

ከቤት ወጥተህ ልትደርስበት የምትፈልገውን ግብ እዚህ ላይ ጻፍ።

ከወላጆችህ ጋር ለረጅም ዓመታት ብትኖርም እንኳ ራስህን ችለህ ለመኖር የሚያስፈልግህን ብስለትና ችሎታ ሳታዳብር ልትቀር የምትችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። ያም ቢሆን ውሳኔ ለማድረግ አትቸኩል። ጉዳዩን በሚገባ አስብበት። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “የትጕህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል፤ ችኰላም ወደ ድኽነት ያደርሳል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 21:5) ወላጆችህ የሚሰጡህን ምክር አዳምጥ። (ምሳሌ 23:22) ስለ ጉዳዩ ጸልይ። ውሳኔ ስታደርግ ከላይ የተወያየንባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከግምት አስገባ።

ግምት ውስጥ ሊገባ የሚገባው ጥያቄ ‘ራሴን ችዬ ለመኖር ደርሻለሁ?’ የሚለው ሳይሆን ‘የራሴን ቤት ለማስተዳደር ዝግጁ ነኝ ወይ?’ የሚለው ነው። ለሁለተኛው ጥያቄ መልስህ አዎን የሚል ከሆነ ራስህን ችለህ ለመኖር ደርሰሃል ማለት ነው።

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.33 በአንዳንድ ባሕሎች አንድ ልጅ በተለይም ሴት ልጅ አግብታ እስክትወጣ ድረስ ከወላጆቿ ጋር መኖሯ የተለመደ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጉዳይ በተመለከተ በቀጥታ የሚናገረው ሐሳብ የለም።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

የቤተሰብ ሕይወትህ አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳ ለተወሰነ ጊዜ ከወላጆችህ ጋር መኖርህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

ከወላጆችህ ጋር ስትኖር ቤተሰብህን የሚጠቅም እንዲሁም ራስህን ችለህ ለምትኖርበት ጊዜ ሊያዘጋጅህ የሚችል ምን ነገር ማድረግ ትችላለህ?

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

እኩዮችህ ምን ይላሉ?

“ወላጆቻችሁ ከቤት ስትወጡ የምትሸከሙትን ዓይነት ኃላፊነት የሚሰጧችሁ ከሆነ ከወላጆቻችሁ ጋር የምታሳልፉት ሕይወት ራሳችሁን ችላችሁ ለምትኖሩበት ጊዜ ጥሩ ሥልጠና ይሰጣችኋል።”

“ራስን ችሎ ለመኖር መፈለግ ተፈጥሯዊ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ከቤት ለመውጣት የፈለጋችሁት ከወላጆቻችሁ ቁጥጥር ነፃ ለመውጣት ከሆነ ይህ ሁኔታ ራሳችሁን ችላችሁ ለመኖር ዝግጁ እንዳልሆናችሁ ያሳያል።”

[ሥዕሎች]

ሣራ

አሮን

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለወላጆች የቀረበ ሐሳብ

በዚህ ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ሰሪነ ራሷን ችላ ከቤት መውጣት ትፈራለች። ለዚህ አንደኛው ምክንያት ምንድን ነው? እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “በራሴ ገንዘብም እንኳ ቢሆን አንድ ነገር ለመግዛት ስፈልግ አባቴ አይፈቅድልኝም። ይህ የእሱ ኃላፊነት እንደሆነ ይነግረኛል። ከራሴ ገንዘብ ላይ ሒሳብ ስለ መክፈል ሳስብ ያስፈራኛል።” የሰሪነ አባት እንደዚህ የሚያደርገው በክፋት ተነሳስቶ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ልጁ የራሷን ቤተሰብ ለምታስተዳድርበት ጊዜ እያዘጋጃት ያለ ይመስላችኋል?—ምሳሌ 31:10, 18, 27

እናንተስ ለልጆቻችሁ ከመጠን በላይ ከመሳሳታችሁ የተነሳ ምንም ነገር እንዳይሠሩ ማድረጋችሁ ራሳቸውን ችለው ለሚኖሩበት ጊዜ እንዳይዘጋጁ እያደረጋቸው ይሆን? ይህን እንዴት ማወቅ ትችላላችሁ? እስቲ ደግሞ አሁን በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱትን አራት ነጥቦች ከወላጆች አንጻር እንመልከት።

ገንዘብ አያያዝ። በዕድሜ ትልልቅ የሆኑት ልጆቻችሁ ከግብር ጋር የተያያዙ ሕጎችን ለመታዘዝ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያውቃሉ? (ሮም 13:7) ከዱቤ አወሳሰድ ጋር በተያያዘ ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ ሥልጠና አግኝተዋል? (ምሳሌ 22:7) ለገቢያቸው ባጀት በማውጣት እንደ አቅማቸው መኖር ይችላሉ? (ሉቃስ 14:28-30) ሠርተው ባገኙት ገንዘብ አንድ ነገር መግዛት የሚያስገኘውን ደስታ ቀምሰው ያውቃሉ? ጊዜያቸውንና ጥሪታቸውን ተጠቅመው ሌሎችን መርዳት የሚያስገኘውን የላቀ ደስታ አጣጥመው ያውቃሉ?—የሐዋርያት ሥራ 20:35

የቤት ውስጥ ሥራ። ሴቶች እና ወንዶች ልጆቻችሁ ምግብ መሥራት ይችላሉ? ልብስ ማጠብና መተኮስ አስተምራችኋቸዋል? ልጆቻችሁ መኪና የሚነዱ ከሆነ ፊዩዝ፣ ዘይት ወይም ጎማ እንደመቀየር ያሉ ቀላል ሥራዎችን ማከናወን ይችላሉ?

ማኅበራዊ ኑሮ። በዕድሜ ትልቅ የሆኑ ልጆቻችሁ ሲጨቃጨቁ ሁልጊዜ ለችግሩ መፍትሔ የምትሉትን ሐሳብ እንዲቀበሉ በመጫን እንደ ዳኛ ትሆናላችሁ? ወይስ ልጆቻችሁ ተነጋግረው ችግሩን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱትና የደረሱበትን ውጤት እንዲነግሯችሁ አሠልጥናችኋቸዋል?—ማቴዎስ 5:23-25

የግል መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች። ለልጆቻችሁ ምን ማመን እንዳለባቸው ትነግሯቸዋላችሁ? ወይስ አስረድታችሁ ታሳምኗቸዋላችሁ? (2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15) ልጆቹ ለሚያነሷቸው ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ጥያቄዎች ሁልጊዜ መልስ ከመስጠት ይልቅ የማመዛዘን ችሎታቸውን እንዲያዳብሩና “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት” እንዲያሠለጥኑ እያስተማራችኋቸው ነው? (ምሳሌ 1:4፤ ዕብራውያን 5:14) በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ረገድ ለልጆቻችሁ ጥሩ ምሳሌ ትሆናላችሁ? ወይስ እናንተ የማታደርጉትን እንዲያደርጉ ትፈልጋላችሁ?

ከላይ የተዘረዘሩትን ነጥቦች በሚመለከት ልጆቻችሁን ለማሠልጠን ጊዜና ከፍተኛ ጥረት እንደሚጠይቅ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ደስታና ሐዘን በተቀላቀለበት ስሜት ልጆቻችሁን የምትሰናበቱበትና ራሳቸውን ችለው ለመኖር ከእናንተ የሚለዩበት ቀን ሲመጣ ልፋታችሁ ይካሳል።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ራስህን ችለህ ለብቻህ መኖር ለሽርሽር ከከተማ ወጣ ከማለት ጋር ይመሳሰላል። ጉዞ ከመጀመርህ በፊት አስፈላጊ የሆኑ ችሎታዎችን መማር ይኖርብሃል