ውጥረት በእኛ ላይ የሚያስከትለው ውጤት
ውጥረት በእኛ ላይ የሚያስከትለው ውጤት
አውቶቡስ እንዳያመልጥህ ፈጠን ፈጠን እያልክ ስትሄድ በሰውነትህ ላይ ምን ለውጥ ታያለህ? የደም ግፊትህ ከፍ እንዳለና የልብህ ምት እንደጨመረ እንደምታስተውል ምንም ጥርጥር የለውም። በዚህ ጊዜ አውቶቡሱ ቢያመልጥህም እንኳ የልብህ ምትና ትንፋሽህ ቶሎ ወደነበረበት ይመለሳል።
ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ውጥረት በሚያጋጥምህ ወቅት ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ሊሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ የሚያጋጥሙት እንደ ስጋት፣ የጡንቻ መወጠር፣ የደም ግፊት መጨመርና የምግብ አለመፈጨት ያሉ ችግሮች በቀላሉ ላይሻሻሉ ይችላሉ። ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሰዎች በውጥረት የተሞላ ሕይወት እንደሚመሩ ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙዎች አሰልቺ የሆነና እርካታ የማይሰጥ ሥራ እየሠሩ ዕድሜያቸውን በከንቱ እንደሚገፉ ይሰማቸዋል። ይሁንና ውጥረት በሰውነትህና በጤንነትህ ላይ ምን ያስከትላል?
ውጥረት በሰውነትህ ላይ የሚያስከትለው ውጤት
በዚህ ዙሪያ ጥናት ያደረጉት ዶክተር ኤሪየን ፋንደርመርቨ ውጥረት በሰውነት ላይ ስለሚያስከትለው ውጤት ማብራሪያ ሰጥተዋል። ውጥረት ሰውነትህ በፍጥነት እርምጃ እንዲወስድ ያነሳሳዋል። ከባድ የሆነ “ውጥረት ደግሞ ሰውነትህ ኬሚካሎችንና ሆርሞኖችን በፍጥነት እንዲያመነጭ ያነሳሳዋል፤ እነዚህ ነገሮች በሰውነትህ ውስጥ ተሰራጭተው እያንዳንዱ የሰውነትህ ክፍልና ሥርዓት ድንገት የተፈጠረውን ሁኔታ ለመመከት በተጠንቀቅ እንዲቆም ያደርጉታል።”
አንተም ወዲያውኑ ከወትሮው የተለየ እርምጃ ለመውሰድ ትዘጋጃለህ። የማየት፣ የመስማትና የመዳሰስ ችሎታህን ጨምሮ ሁሉም የስሜት ሕዋሳትህ ዝግጁ ሆነው ይጠብቃሉ። አንጎልህ በፍጥነት ትእዛዝ ሲሰጥ አድሬናል ዕጢዎችህ ደግሞ ከመቅጽበት ኃይለኛ የሆኑ ሆርሞኖችን ያመነጫሉ፤ እነዚህ ሆርሞኖች ጡንቻዎችህ፣ ልብህ፣ ሳንባዎችህና ሌሎች የአካል ክፍሎችህ ውጥረቱ የሚፈጥረውን ሁኔታ ለመቋቋም አስፈላጊ የሆነውን ማንኛውንም እርምጃ እንዲወስዱ ያነሳሷቸዋል።
ሰውነትህ በዚህ መንገድ ለውጥረት የሚሰጠው ምላሽ ድንገት አደገኛ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ሕይወትህን ለማትረፍ ያስችልህ ይሆናል፤ ለምሳሌ መኪና እየበረረ ሲመጣብህ ዘለህ እንድታመልጥ ያደርግሃል። ውጥረቱ ፋታ የሌለው በሚሆንበት ጊዜ ግን ሁኔታው ከዚህ ፍጹም የተለየ ነው።
ውጥረት ጠላት ሲሆን
ሰውነትህ ሁልጊዜ እርምጃ ለመውሰድ እንደተዘጋጀ ቢቆይስ? ጡንቻዎችህ እንደተወጠሩ፣ የልብህ ምትና የደም ግፊትህ እንደጨመረ፣ በደምህ ውስጥ ያለው የኮሌስትሮል፣ የስብ፣ የስኳር፣ የሆርሞኖችና የሌሎች ኬሚካሎች መጠን ከፍ እንዳለ ይቆያሉ። ድንገተኛ ሁኔታ ሲያጋጥም ሰውነትህ አፋጣኝ
እርምጃ እንዲወስድ የሚያነሳሱት እንዲህ ያሉት ኬሚካሎች ለረጅም ጊዜ ከፍ ብለው መቆየታቸው ዋና ዋና የአካል ክፍሎችህ ላይ ውሎ አድሮ ጉዳት ያስከትላል። ታዲያ ይህ ምን ውጤት ይኖረዋል?በዚህ ጊዜ የወገብ ሕመምና ራስ ምታት ይጀምርህ እንዲሁም የአንገት ሕመምና የጡንቻ መኮማተር ይሰማህ ይሆናል። ሐኪሞች እንደሚናገሩት ከሆነ እነዚህ ነገሮች ብዙውን ጊዜ ሥር የሰደደ ውጥረት ምልክቶች ናቸው። አንድ ሰው የማያቋርጥ ውጥረት ሲኖርበት የፈጠራ ችሎታውና ምርታማነቱ ሊቀንስ፣ ምንም ነገር የማድረግ ፍላጎቱ ሊጠፋና ከሰዎች ጋር
ያለው ግንኙነት ሊሻክር ይችላል። በተጨማሪም የሆድ ዕቃ መታወክ፣ የምግብ መውረጃ ቧንቧ መኮማተር እንዲሁም ተቅማጥ ያጋጥመው ይሆናል። ሥር የሰደደ ውጥረት የሚያስከትለው መዘዝ ከዚህም የከፋ ሊሆን ይችላል። ጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ፣ የልብ ሕመም፣ የኩላሊት ሥራ ማቆም፣ የልብና የደም ቧንቧ ችግር፣ የስኳር ሕመም ሊያስከትል አሊያም እነዚህን ችግሮች ሊያባብስ ይችላል።ኤሪየን ፋንደርመርቨ እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል፦ “ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ውጥረት ኮርቲሶል የሚባል ሆርሞን እንዲመነጭ ስለሚያደርግ በሆድና በጀርባ አካባቢ ስብ ሊከማች ይችላል።” እንደ ችፌ ያሉ የቆዳ በሽታዎች በውጥረት ምክንያት ሊመጡ አሊያም ሊባባሱ ይችላሉ። ከባድ ውጥረት ከመንፈስ ጭንቀት፣ ጠበኛ ከመሆን፣ ከከፍተኛ የድካምና የመዛል ስሜት ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ይነገራል። የማያባራ ውጥረት የማስታወስና አንድ ነገር ላይ ትኩረት የማድረግ ችሎታንም ለዘለቄታው ሊጎዳ ይችላል። በተጨማሪም አንድን ሰው ከጉንፋን አንስቶ እስከ ካንሰር ላሉት በሽታዎች በቀላሉ እንዲጋለጥ ብሎም በሽታን የመከላከል አቅሙ እንዲዳከም ሊያደርግ ይችላል።
ውጥረት በደኅንነታችን ላይ ይኸውም በአእምሯዊ፣ በአካላዊ፣ በስሜታዊና በመንፈሳዊ ጤንነታችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር ውጥረትን መቆጣጠር የምንችልበትን መንገድ ማወቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ሲባል ግን ሰውነታችን ውጥረት ሲያጋጥመው የሚሰጠውን ምላሽ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ይኖርብናል ማለት አይደለም። ለምን?
ውጥረት፣ ለመጋለብ ከሚቅበጠበጥ ፈረስ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። እንዲህ ያለውን ፈረስ በሚያስደስት ሁኔታ ልንጋልብበት እንችላለን። ፈረሱ ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ ግን ሕይወታችንን አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል። በተመሳሳይም መጠነኛ ውጥረት የፈጠራ ችሎታችን እንዲዳብር ብሎም ምርታማ፣ ንቁዎችና ጤናሞች እንድንሆን በማድረግ ለሕይወታችን ጣዕም ይሰጠዋል።
ይሁንና ሕይወታችን ይበልጥ አስደሳች እንዲሆንና የሚሰማን ውጥረት ከቁጥጥራችን ውጭ እንዳይሆን ምን ማድረግ እንችላለን? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ውጥረትን መቆጣጠርና ውጥረት በእኛ ላይ የሚያስከትለውን ውጤት መቀነስ የምንችልባቸውን መንገዶች እንመለከታለን።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ጥበበኛና አፍቃሪ የሆነ ፈጣሪ “ግሩምና ድንቅ” አድርጎ ፈጥሮናል
ሰውነታችን ለውጥረት የሚሰጠው ምላሽ፣ ጥንታዊው ሰው ማሞዝና ረጃጅም ጥርስ ያላቸው ነብሮች ሲመጡበት በውስጡ ከተሰማው የስጋት ስሜት የወረስነው ነው ከሚለው በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ካለው ጽንሰ ሐሳብ ተቃራኒ ነው። ከዚህ ይልቅ ውስብስብ የሆነው የሰውነታችን ሥርዓት በረቀቀ ሁኔታ የተነደፈው ድንቅ ችሎታ ባለው ፈጣሪ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ደም የሚረጋበት ውስብስብ ሥርዓት፣ ደም በሽታ አምጪ ተሕዋሲያንን በመዋጋትና ቁስልን በማዳን የሚጫወተው አስደናቂ ሚና እንዲሁም ሰውነታችን ውጥረት ሲያጋጥመው የሚሰጠው ምላሽ በእርግጥ ጥበበኛና አፍቃሪ ንድፍ አውጪ ለመኖሩ ምሥክር ነው።
በሰውነታችን ውስጥ ያሉት እንዲህ ያሉ ሥርዓቶች “ግሩምና ድንቅ” ሆነን እንደተፈጠርን ያረጋግጣሉ። (መዝሙር 139:13-16) አምላክ መንፈሳዊም ሆነ አካላዊ ፍላጎታችንን እንድናረካ በፍቅር ተነሳስቶ ያደረገልን ዝግጅትና ሰዎች በሕይወት እንዲደሰቱ አድርጎ የፈጠረበት አስደናቂ መንገድ በመጪው ምድራዊ ገነት ውስጥ ሥቃይ፣ ለቅሶ ወይም ሞት የሚያስከትል አንዳች ነገር እንደማይኖር ያረጋግጡልናል።—ራእይ 21:3-5
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ውጥረት በሰውነት ላይ የሚያስከትላቸው መጥፎ ውጤቶች
ራስ ምታት
የአንገት ሕመም
ጥርስን ማፋጨት
የወገብ ሕመም
የልብ ሕመም
የጨጓራ ቁስለት
የጡንቻ መኮማተር