በታይላንድ የሚገኙ ማራኪ የሆኑ የደጋ ጎሣዎች
በታይላንድ የሚገኙ ማራኪ የሆኑ የደጋ ጎሣዎች
በቺያንግ ሜይ ከተማ በሚገኙት የገበያ ቦታዎች ሕዝቡ እንደ ጉንዳን ይርመሰመሳል። በመንገዶቹ ዳርና ዳር የሚያማምሩ ዕቃዎች ለሽያጭ ቀርበዋል። ሸማቾች በገበያው መሃል እየተጋፉ የሚፈልጉትን ለመግዛት ድምፃቸው ከመኪኖቹ ጩኸት በላይ እንዲሰማ ጮክ ብለው ከነጋዴዎቹ ጋር ይከራከራሉ። በሰሜናዊ ታይላንድ ወደሚገኘው ወደዚህ ሕዝብ የሚበዛበት አካባቢ የሚመጡ ጎብኚዎች ማራኪ የሆኑትን የታይላንድ የደጋ ጎሣዎች ማግኘት ይችላሉ።
በታይላንድ ከሚኖረው 65 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል የደጋ ጎሣዎች ተብለው የሚጠሩ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ 23 ጎሣዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ ጎሣዎች ውስጥ አብዛኞቹ የሚኖሩት በሰሜናዊ ታይላንድ ነው፤ አካባቢው ተራሮች፣ ወንዞችና ለም የሆኑ ሸለቆዎች የሞሉበት ሲሆን ይህ ውብ መልክዓ ምድር እስከ ምያንማርና ላኦስ ድረስ ይዘልቃል።
አብዛኞቹ የታይላንድ የደጋ ጎሣዎች ወደዚህ አካባቢ የመጡት ባለፉት 200 ዓመታት ውስጥ ነው። ከስድስቱ ዋና ዋና ጎሣዎች ትልቁ የሆነው ከሪን የሚባለው ጎሣ የመጣው ከምያንማር ነው። ላሁ፣ ሊሱ እና አካ የሚባሉት ጎሣዎች የመጡት በቻይና ደቡባዊ ምዕራብ ተራራማ አካባቢዎች ከሚገኘው ዩናን የሚባል ክልል ነው። እንዲሁም ህሞንግ እና ሚን የሚባሉት ጎሣዎች የመጡት ከማዕከላዊ ቻይና ነው። *
ጎሣዎቹ ወደዚህ አካባቢ የፈለሱበት ዋነኛው ምክንያት ከጦርነት፣ ማኅበረሰቡ ከሚያሳድርባቸው ተጽዕኖ እንዲሁም ለም መሬት ለማግኘት ከሚደረገው ሽኩቻ ለመሸሽ ነበር። * ርቆ የሚገኘውና ተራራማ የሆነው እንዲሁም እምብዛም ሰው የማይኖርበት የሰሜናዊ ታይላንድ አካባቢ ለእነዚህ ጎሣዎች ተስማሚ መጠጊያ ሆነላቸው። በተጨማሪም የታይላንድ መንግሥት ስደተኞቹ እንዲኖሩ ፈቀደላቸው። ብዙም ሳይቆይ ልዩ ልዩ ባሕሎችና ቋንቋዎች ያሏቸው የተለያዩ ጎሣዎች አለፍ አለፍ እያሉ መንደሮች በመመሥረት በአካባቢው አብረው መኖር ጀመሩ።
ለየት ያለ አለባበስና ማራኪ ባሕል
እያንዳንዱ የደጋ ጎሣ ከሌሎቹ ልዩ የሚያደርገው አለባበስ አለው። ለምሳሌ ያህል፣ አካ የሚባለው ጎሣ አባላት የሆኑ ሴቶች ከብር የተሠራና በመነሳነስ፣ በጥልፍ እንዲሁም በሳንቲም ያሸበረቀ እንደ ጎፈር ያለ ጌጥ ጭንቅላታቸው ላይ ያደርጋሉ። አንዳንዶቹ የራስ መሸፈኛዎቻቸው ደግሞ
በሚያብረቀርቁ አዝራሮች፣ ዶቃዎችና ኳሶች ያጌጡ ከብረት ቁርጥራጮች የተሠሩ የራስ ቁሮች ይመስላሉ። የሚን ጎሣ ሴቶች ባማረ ጥልፍ የተንቆጠቆጡ ሱሪዎች (ለመሥራት እስከ አምስት ዓመት ሊፈጁ ይችላሉ) ይለብሳሉ። በዚህ ላይ ደግሞ ቄንጠኛ ጥምጣሞች አድርገው እንዲሁም በቀይ ላባ የተሠራ አንገትጌ ያላቸው እስከ ቁርጭምጭሚት የሚደርሱ ቀሚሶች ለብሰውና ወገባቸውን በወይን ጠጅ መቀነቶች ሸብ አድርገው አምረውና ደምቀው ይታያሉ።የደጋ ጎሣዎቹ ሴቶች ሙሉ የባሕል ልብሳቸውን ሲለብሱ ለሚመለከቷቸው ሰዎችም ሆነ ሊያጯቸው ለሚመጡ ሰዎች የኑሮ ደረጃቸውንና ሀብታቸውን የሚገልጹባቸው የሚያቃጭሉና የሚያብለጨልጩ ብዙ የብር ጌጣጌጦች ያደርጋሉ። መስታወትን፣ እንጨትንና ክርንም እንደ ጌጥ ይጠቀሙባቸዋል።
አብዛኞቹ የደጋ ጎሣዎች በባሕላቸው ይኮራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የከሪን ጎሣ ኮረዳዎች ከሌላ ከማንኛውም ሥነ ሥርዓት ይልቅ በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ይበልጥ አምረው ይታያሉ። ለምን? በርካታ ወጣቶች ወደፊት የትዳር ጓደኛ የሚሆናቸውን ሰው ለማግኘት ተስፋ በማድረግ በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ስለሚገኙ ነው። ጀምበር ከጠለቀች በኋላ ወጣት ወንዶችና ሴቶች እጅ ለእጅ ተያይዘው በአስከሬኑ ዙሪያ እየዞሩ ሌሊቱን በሙሉ ባሕላዊ የፍቅር ዘፈኖችን ሲዘፍኑ ያድራሉ።
የህሞንግ ጎሣ ወጣቶች የዘመን መለወጫ በዓል በሚከበርበት ዕለት በሚካሄደው ልዩ ጨዋታ ላይ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ይጫወታሉ። በፍቅር የተሳሰቡ ጎረምሶችና ኮረዶች ከሌሎች ነጠል ብለው ከሄዱ በኋላ በመሃላቸው የተወሰነ ርቀት እንዲኖር በማድረግ ፊት ለፊት እየተያዩ በመደዳ ይቆማሉ። ከዚያም ጎረምሳውና ኮረዳዋ አንዳቸው ለሌላው ከጨርቅ የተሠራ ኳስ ይወራወራሉ። ከሁለት አንዳቸው ሆን ብለውም ይሁን በአጋጣሚ ኳሱ ከወደቀባቸው አንዳቸው ለሌላው ትንሽ ጌጥ ይሰጣሉ። ምሽቱ እየገፋ ሲሄድ ጌጡን የሰጠው ወገን ዘፈን በመዝፈን ዕቃውን ማስመለስ ይችላል። ወጣቱ ወይም ወጣቷ ጥሩ አድርገው ከዘፈኑ ብዙ ተመልካቾች የሚሰበሰቡ ከመሆኑም ሌላ የፍቅር ጓደኛ የሚሆናቸውን ሰው ቀልብ ሊስቡ ይችላሉ።
ከለውጥ ጋር መላመድ
ቀደም ባሉት ጊዜያት አብዛኞቹ የደጋ ጎሣዎች እህል ለመዝራትና ከብቶችን ለማርባት ሲሉ ማንም ነክቶት የማያውቀውን ደን እየመነጠሩ ያቃጥሉ ነበር። ይህ ልማድ ደግሞ አሳሳቢ የሆኑ አካባቢያዊ ችግሮችን አስከተለ። አሁን አሁን ግን ሕዝቡ ይበልጥ ኃላፊነት እንደሚሰማው በሚያሳይ መንገድ መሬቱን የሚንከባከብ ሲሆን ይህም ጠቃሚ ውጤት አስገኝቷል።
ብዙዎቹ የደጋ ጎሣዎች ታይላንድ፣ ላኦስና ምያንማር በሚዋሰኑበትና ጎልደን ትራያንግል በሚባለው አካባቢ ስለሚኖሩ ኦፒየም የሚባለውን ዕፅ ያመርቱ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን የታይላንድ ንጉሣዊ ቤተሰብና ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ሕዝቡ በኦፒየም ፋንታ እህል እንዲያለማ ለማበረታታት ላደረጉት ጥረት ምስጋና ይድረሳቸውና ቡና፣ አትክልት፣ ፍራፍሬና አበቦችን ያመርታሉ። በተጨማሪም ብዙዎቹ የደጋ ጎሣዎች ሸቀጣ ሸቀጦችን በመሸጥ፣ አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ለመጡት ቱሪስቶች ባሕላዊ የእጅ ሥራ ውጤቶችን በመሸጥ ይተዳደራሉ።
ይሁን እንጂ ድህነት፣ የንጽሕና ጉድለትና መሃይምነት ብዙዎች ሕይወት ከባድ እንዲሆንባቸው አድርገዋል። የተፈጥሮ ሀብት መመናመን፣ የባሕል ለውጥ፣ የዘር ጥላቻ እንዲሁም አደንዛዥ ዕፆችንና የአልኮል መጠጥን አላግባብ መውሰድ የደጋ ጎሣዎቹን ኑሮ አስቸጋሪ ካደረጉባቸው ሌሎች ነገሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ቅድመ አያቶቻቸው ወደ ታይላንድ የመጡት እነዚህን ችግሮች ሸሽተው ነበር። በዛሬው ጊዜስ መጠጊያ ከየት ማግኘት ይችላሉ?
አስተማማኝ መጠጊያ
የደጋ ጎሣዎች አባላት ለሆኑ በርካታ ሰዎች፣ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ከሁሉ የተሻለ መጠጊያ ሆኖላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 34:8 ላይ “እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ፤ እርሱን መጠጊያ የሚያደርግ ምንኛ ቡሩክ ነው!” በማለት ይናገራል። የላሁ ጎሣ አባል የሆነው ጆሌ እንዲህ ይላል፦ “በ19 ዓመቴ ትዳር ስመሠርት ሰካራምና የዕፅ ሱሰኛ ነበርኩ። ዕፅ ካልወሰድኩ መሥራት አልችልም፤ ካልሠራሁ ደግሞ ገንዘብ አይኖረኝም። ባለቤቴ አኖታይ እንደማልወዳትና ችላ እንደተባለች ይሰማት ነበር። ነጋ ጠባ እንጨቃጨቅ ነበር።
“ሴት ልጃችን ሱፐዋዲ ከተወለደች በኋላ አኖታይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። እኔ ግን የይሖዋ ምሥክሮቹ ወደ ቤታችን ሲመጡ ሮጬ ወደ ጫካ እገባ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ የባለቤቴ ባሕርይ መሻሻል ጀመረ። በአክብሮት የምታነጋግረኝ ከመሆኑም ሌላ ለቤት ውስጥ ሥራዎቿ ይበልጥ ትኩረት መስጠት ጀመረች። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና ስታበረታታኝ ተስማማሁ።
“የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ልቤን ሲነኩት ቀስ በቀስ ለውጥ አደረግሁ። በመጨረሻም በአምላክ እርዳታ ከነበሩብኝ ሱሶች ተላቀቅሁ። ከሁሉ የተሻለውን የሕይወት መንገድ ስላገኘን አሁን ቤተሰቤ በጣም ደስተኛ ነው! በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስን ጠቃሚ ትምህርቶች ለሌሎቹ የደጋ ጎሣዎች አባላት ማካፈል ያስደስተናል።”
ጆሌ የተናገራቸው ቃላት በዚህ ክፉ ዓለም የመጨረሻ ቀኖች “ለብሔር፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለሕዝብ ሁሉ . . . የዘላለም ምሥራች” እንደሚታወጅ በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን ትንቢት ያስታውሰናል። (ራእይ 14:6) አምላክ ማራኪ የሆኑትን የታይላንድ የደጋ ጎሣዎች ጨምሮ ሁሉንም ሕዝቦች እንደሚወድ በሚያረጋግጠው በዚህ የስብከት ሥራ መካፈልን የይሖዋ ምሥክሮች እንደ ታላቅ መብት ይቆጥሩታል።—ዮሐንስ 3:16
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.4 ጎሣዎቹ የተለያዩ ስሞች አሏቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ሚን የሚባለው ጎሣ በተለያዩ አገሮች ሉ ሚን፣ ሚአን፣ ያው፣ ዳው፣ ዛው ወይም ማን ተብሎ ይጠራል።
^ አን.5 በቻይና እንዲሁም በቬትናም፣ በላኦስና በምያንማር አሁንም ቢሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የደጋ ጎሣዎች ይኖራሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአውስትራሊያ፣ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በፈረንሳይና በሌሎች አገሮችም በርካታ የደጋ ጎሣ ማኅበረሰቦች ተፈጥረዋል።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የአንገት ቀለበቶች አንገትን ያስረዝማሉ?
በርካታ የካያን ሴቶች እስከ 38 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያላቸው የሚያብረቀርቁ የነሐስ ቀለበቶችን በአንገታቸው ዙሪያ ያጠልቃሉ። * ሴቶች ልጆች እነዚህን ቀለበቶች በአንገታቸው ዙሪያ ማድረግ የሚጀምሩት አምስት ዓመት ገደማ ሲሆናቸው ነው። ከዚያም በየተወሰኑ ዓመታት አንገታቸው ላይ ያሉት ቀለበቶች ይበልጥ ረጅምና ከባድ በሆኑ ቀለበቶች እየተተኩ ይሄዳሉ፤ ሴቶቹ ትልቅ ሰው ሲሆኑ እስከ 13 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ 25 ቀለበቶችን ያደርጋሉ! አንገታቸው ሲታይ የረዘመ ቢመስልም እንደ እውነቱ ከሆነ ቀለበቶቹን ማድረጋቸው አንገታቸውን አያስረዝመውም። ከዚህ ይልቅ ቀለበቶቹ የትከሻቸውን አጥንት ወደታች በመግፋት የጎድን አጥንታቸውን ይጫኑታል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.25 የካያን ጎሣዎች ወደ ታይላንድ የመጡት ከምያንማር ሲሆን 50,000 የሚያህሉ የዚህ ጎሣ አባላት አሁንም በምያንማር ይኖራሉ። ይህ ጎሣ በምያንማር ፐዳውንግ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ትርጉሙም “አንገተ ረጃጅሞች” ማለት ነው።
[ምንጭ]
Hilltribe Museum, Chiang Mai
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ስለ ታላቅ የውኃ መጥለቅለቅ የሚገልጹ አፈ ታሪኮች
የሊሱና የህሞንግ ጎሣዎች ስለ ታላቅ የውኃ መጥለቅለቅ የሚገልጹ አፈ ታሪኮች አሏቸው። በአንድ የህሞንግ አፈ ታሪክ መሠረት “የሰማይ ጌታ” ምድር በጎርፍ እንደምትጥለቀለቅ ሁለት ወንድማማቾችን አስጠነቀቃቸው። የሰማዩ ጌታ፣ ዓመፀኛ የሆነውን ታላቅየውን የብረት ጀልባ እንዲሠራ ሲያዘው ገራም የሆነውን ታናሽየውን ግን የእንጨት ጀልባ እንዲሠራ ነገረው። ከዚያም ከወንድማማቾቹ ለትንሹ እህቱን እንዲሁም ከእያንዳንዱ የእንስሳት ዝርያ ተባዕትና እንስት፣ ከእያንዳንዱ የዕፅዋት ዓይነት ደግሞ ሁለት ሁለት ዘሮችን ይዞ ከእንጨት ወደተሠራው ጀልባ እንዲገባ ነገረው።
ጎርፉ ሲመጣ የብረት ጀልባው ሲሰጥም ከእንጨት የተሠራው ጀልባ ግን ተንሳፈፈ። ከዚያም የቀስተ ደመና ቅርጽ ያለው ዘንዶ ውኃውን ከምድር ላይ አደረቀው። በመጨረሻም ታናሽየው እህቱን አገባና ዘሮቻቸው ተባዝተው ምድርን ሞሏት። በዚህ አፈ ታሪክና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዘፍጥረት ምዕራፍ 6 እስከ 10 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው ትክክለኛ ዘገባ መካከል ያለውን ተመሳሳይነት ልብ በል።
[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የደጋ ጎሣ አባላት የሆኑ ሴቶች ሙሉ የባሕል ልብሳቸውን ለብሰው
[ምንጭ]
Hilltribe Museum, Chiang Mai
[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ጆሌ ከቤተሰቡ ጋር
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ሁለቱም ሥዕሎች፦ Hilltribe Museum, Chiang Mai