ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እንዳውቅ ያነሳሳኝ ነገር
ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እንዳውቅ ያነሳሳኝ ነገር
ቶማስ ኦሮስኮ እንደተናገረው
የይሖዋ ምሥክሮች በመንግሥት አዳራሻቸው ውስጥ በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኘሁበት ዕለት አንድ ትንሽ ልጅ ንግግር ሰጥቶ ነበር። ቁመቱ አትራኖሱ ላይ መድረስ ባይችልም እርጋታውና ችሎታው አስደናቂ ነበር። በልጁ ሁኔታ በጣም ተገርሜ ነበር።
ተሰብሳቢዎቹ ልጁን በጥሞና ያዳምጡት እንደነበረ አስተዋልኩ። በዩናይትድ ስቴትስ የቦሊቪያ ወታደራዊ ዲፕሎማት፣ የባሕር ኃይል ምክትል አዛዥ እንዲሁም የፕሬዚዳንቱ አማካሪ ሆኜ ስላገለገልኩ የሌሎችን አክብሮት ማትረፍ ለእኔ እንግዳ አልነበረም። ይሁን እንጂ ተሰብሳቢው ለዚህ ልጅ ያሳየው አክብሮት በሕይወቴ ውስጥ ያሉኝን ግቦች እንደገና እንድመረምር አነሳሳኝ።
አባቴ የሞተው በ1930ዎቹ አጋማሽ ላይ በፓራጓይና በቦሊቪያ መካከል በተደረገው የቻኮ ጦርነት ላይ ነበር። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በካቶሊኮች አዳሪ ትምህርት ቤት ገባሁ። ለብዙ ዓመታት በየዕለቱ በሚካሄድ የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ እገኝ ነበር፤ በእነዚህ ሥነ ሥርዓቶች ላይ መዝሙሮችን እንዘምር፣ የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን እናዳምጥ እንዲሁም ጸሎቶችን በቃላችን እንደግም ነበር። እንዲያውም በቅዳሴ ሥነ ሥርዓቶች ወቅት አንዳንድ ሥራዎችን በመሥራት አገለግል የነበረ ሲሆን በመዘምራን ቡድን ውስጥ ዘማሪ ነበርኩ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን ፈጽሞ አንብቤ እንዲያውም ለዓይኔ እንኳ አይቼው አላውቅም ነበር።
ሃይማኖታዊ በዓላት በሚከበሩበት ዕለት ድግስ ስለማይጠፋና ከወትሮው የተለየ ቀን ስለሚሆን ደስ ይለኝ ነበር። ይሁን እንጂ ቀሳውስቱና ሌሎች የሃይማኖት አስተማሪዎች ክፉዎች ነበሩ። ወደ እነሱ እንድቀርብ ሳይሆን እንድርቃቸው የሚያደርግ ባሕርይ ነበራቸው። በዚህ ምክንያት የሃይማኖት ነገር አንገሽግሾኝ ነበር።
ወታደራዊ ሥነ ሥርዓት ማረከኝ
በአንድ ደስ የሚል ፀሐያማ ቀን የሚያምር አለባበስ ያላቸው ሁለት ወጣት የጦር መኮንኖች ወደ ትውልድ ከተማዬ ወደ ታሪሃ መጥተው ነበር። እነዚህ መኮንኖች ከቦሊቪያ ዋና ከተማ ከላ ፓዝ ለእረፍት የመጡ ነበሩ። በዋናው አውራ ጎዳና ላይ ዘና ብለው ሲራመዱ ግርማ ሞገሳቸው ይማርካል። ጨዋነት የሚታይበት ንጹሕና ክብር የተላበሰው ቁመናቸው ማረከኝ። አረንጓዴ የደንብ ልብስ የለበሱ ሲሆን ከዚያ ጋር የሚሄድ የሚያብረቀርቅ ጠርዝ ያለው ባርኔጣም አድርገዋል። እኔም በዚያው ሰዓት የጦር መኮንን ለመሆን ወሰንኩ። ሕይወታቸው በተሞክሮ የበለጸገና በሚያስከብር ተግባር የተሞላ መሆን አለበት ብዬ አሰብኩ።
በ1949 ይኸውም 16 ዓመት ሲሞላኝ ቦሊቪያ ወታደራዊ ኮሌጅ ውስጥ ገባሁ። ለምዝገባ በሄድኩበት ዕለት ወጣቶች ከሕንፃው አንስቶ እስከ ዋናው በር ድረስ ረጅም ሰልፍ ተሰልፈው
ነበር፤ ሰልፍ ይዤ ወደ ውስጥ እስክገባ ድረስ ወንድሜም ከእኔ ጋር ነበር። ወንድሜ ከመቶ አለቃው ጋር አስተዋወቀኝና መቶ አለቃውን ‘የወንድሜን ነገር አደራ’ አለው። ከዚያም እኔን የሚያሞግስ ቃል ተናገረ። ወንድሜ ከሄደ በኋላ ለአዲስ ምልምል ወታደሮች የተለመደው ሰላምታ ተሰጠኝ። መቶ አለቃው መትቶ መሬት ላይ ጣለኝና “እዚህ ማን መሞገስ እንዳለበት የምንወስነው እኛ ነን!” አለኝ። ከወታደራዊ ዲሲፕሊንና ማስፈራሪያ ጋር የተዋወቅሁት በዚህ መንገድ ነበር። ይሁን እንጂ ኩራቴን ዋጥ አድርጌ የደረሰብኝን ነገር ችዬ አለፍኩ።ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የውጊያ ሥልጠና ያገኘሁ ሲሆን የተከበርኩ የጦር መኮንን ሆንኩ። ይሁን እንጂ ከውጪ የሚታየው ንጹሕና ክብር የተላበሰው የወታደሮች አለባበስ አታላይ ሊሆን እንደሚችል ከራሴ ተሞክሮ መገንዘብ ችያለሁ።
ልዩ ማዕረግ አገኘሁ
ሥራ ከጀመርኩ በኋላ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎችን መያዝ በምትችለው ኬኔራል ቤልግራኖ በምትባል የአርጀንቲና የጦር መርከብ ላይ ሥልጠና ሰጥቼ ነበር። ይህች መርከብ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት ዩ ኤስ ኤስ ፊኒክስ በሚል ስም ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሥራ ጀምራ የነበረ ሲሆን በኋላም በ1941 በሃዋይ በምትገኘው ፐርል ሃርበር ላይ ከጃፓን ከተሰነዘረባት ጥቃት ተርፋለች።
ከጊዜ በኋላ በቦሊቪያ ክልል ውስጥ በሚገኙ መርከብ የሚጓዝባቸው የውኃ አካላት ላይ የቅኝት ተግባር በሚያከናውነው የባሕር ኃይል እዝ ውስጥ ምክትል አዛዥ ሆንኩ። እነዚህ የውኃ አካላት፣ በአማዞን ሸለቆ ውስጥ የሚገኙ ወንዞችን እንዲሁም በዓለም ላይ ለመርከብ ጉዞ እጅግ ምቹ የሆነውን ቲቲካካ ሐይቅን ይጨምራሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግንቦት 1980 የወታደራዊ ዲፕሎማቶችን ያቀፈው ኮሚሽን አባል ሆኜ ስለተመረጥኩ የዩናይትድ ስቴትስ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ሄድኩ። ይህ ቡድን ከተለያዩ ወታደራዊ ዘርፎች ማለትም ከምድር ጦር፣ ከአየር ኃይልና ከባሕር ኃይል ከፍተኛ ማዕረግ ያለውን መኮንን በመምረጥ የተዋቀረ ሲሆን እኔም ከሁሉም የበለጠ የአገልግሎት ዘመን ስለነበረኝ የቡድኑ አስተባባሪ ሆኜ ተሾምኩ። በዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሁለት ዓመት ገደማ ከኖርኩ በኋላ ወደ አገሬ ተመልሼ የቦሊቪያ ፕሬዚዳንት አማካሪ ሆንኩ።
የጦር አዛዥ እንደመሆኔ መጠን በየሳምንቱ እሁድ ዕለት
ቤተ ክርስቲያን የመገኘት ግዴታ ነበረብኝ። በሠራዊቱ ውስጥ የሚያገለግሉት ቀሳውስት በአብዮታዊ እንቅስቃሴዎችና በጦርነቶች ውስጥ ጣልቃ የሚገቡ መሆናቸው የሃይማኖት ነገር ግራ እንዲገባኝ አደረገ። አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ባሉት ደም መፋሰሶች ውስጥ እጃቸውን ማስገባታቸው ስህተት እንደሆነ አውቅ ነበር። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ ግብዝነት ሃይማኖትን እንድጠላ ሳይሆን እውነት እንድፈልግ አነሳሳኝ። መጽሐፍ ቅዱስ ፈጽሞ አንብቤ ስለማላውቅ አልፎ አልፎ የተወሰኑ ጥቅሶችን ማንበብ ጀመርኩ።በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ያየሁት ሥርዓታማነት
ባለቤቴ ማኑዌላ፣ ጃኔት ከምትባል ሚስዮናዊት የሆነች የይሖዋ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እንደ ጀመረች ሳውቅ ገረመኝ። በኋላም ማኑዌላ የመንግሥት አዳራሽ ተብሎ በሚጠራው የአምልኮ ቦታቸው በሚካሄድ ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመረች። እኔም ማኑዌላን ወደ ስብሰባ ቦታው አደርሳት የነበረ ቢሆንም በዚያ መገኘት አልፈልግም ነበር። ስብሰባዎቹ ጫጫታ የሚበዛባቸውና ስሜታዊነት የሚንጸባረቅባቸው እንደሚሆኑ ተሰምቶኝ ነበር።
አንድ ቀን ማኑዌላ የጃኔት ባል መጥቶ ቢያነጋግረኝ ደስ ይለኝ እንደሆነ ጠየቀችኝ። መጀመሪያ ላይ ሐሳቡን አልተቀበልኩም ነበር። በኋላ ግን ባገኘሁት ሃይማኖታዊ ሥልጠና ተጠቅሜ እሱ የሚያምንበት ነገር ስህተት መሆኑን ማሳመን እንደምችል ተሰማኝ። ከኢየን ጋር መጀመሪያ በተገናኘንበት ዕለት በጣም የማረከኝ የተናገረው ነገር ሳይሆን ባሕርይው ነበር። ያገኘውን ሥልጠናና የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ተጠቅሞ ሊያሸማቅቀኝ አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ ደግና ሰው አክባሪ ነበር።
በቀጣዩ ሳምንት በመንግሥት አዳራሹ በሚደረግ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወሰንኩ፤ በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት ትንሽ ልጅ ንግግር ሲያቀርብ የተመለከትኩት በዚህ ወቅት ነበር። ልጁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው ከኢሳይያስ መጽሐፍ ላይ ጥቅሶችን አንብቦ ሲያብራራ ልዩ የሆነ ድርጅት እንዳገኘሁ ገባኝ። ወጣት ሳለሁ የተከበርኩ የጦር መኮንን የመሆን ምኞት ነበረኝ፤ አሁን ግን እንደዚያ ልጅ ሆኜ መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ፍላጎት ሲያድርብኝ በጣም ገረመኝ። ልቤ በድንገት ለስልሶ የሚነገረውን የሚቀበል ያህል ሆኖ ተሰማኝ።
ከዚህም በላይ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ በይሖዋ ምሥክሮች ሰዓት አክባሪነት፣ ሁልጊዜ ሲያገኙኝ በሚሰጡኝ ከልብ የመነጨ ሰላምታ እንዲሁም እንግድነት እንዳይሰማኝ በሚያደርጉት ጥረት ልቤ ተማረከ። ንጹሕና ሥርዓታማ አለባበሳቸውም አስደነቀኝ። ከሁሉ በላይ ያስደሰተኝ ደግሞ የስብሰባዎቹ ሥርዓታማነት ነው፤ በስብሰባዎቹ ላይ አንድ ንግግር እንደሚቀርብ ፕሮግራም ከወጣ በዚያ ዕለት የሚሰጠው ያ ንግግር ነው። እንዲህ ያለው ሥርዓታማነት ሊገኝ የቻለው በማስፈራራት ሳይሆን በፍቅር መሆኑን መገንዘብ ቻልኩ።
ለመጀመሪያ ጊዜ በስብሰባ ላይ ከተገኘሁ በኋላ ከኢየን ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማሁ። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የምንጠቀምበት መጽሐፍ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የሚል ነበር። * በዚህ መጽሐፍ ሦስተኛ ምዕራፍ ላይ ያለውን አንድ ጳጳስ ወደ ጦርነት ሊሄድ የተዘጋጀን ሠራዊት ሲባርክ የሚያሳይ ሥዕል እስካሁን ድረስ አስታውሰዋለሁ። ይህ ሁኔታ ሲፈጸም በገዛ ዓይኔ ስላየሁ ትክክለኝነቱን ቅንጣት ታክል አልተጠራጠርኩም። ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር የተሰኘውን መጽሐፍ ከመንግሥት አዳራሽ አገኘሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገለልተኝነት የሚናገረውን ሐሳብ ሳነብ አንዳንድ ለውጦች ማድረግ እንዳለብኝ ተረዳሁ። ወደ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፈጽሞ ላለመመለስ የወሰንኩ ሲሆን በመንግሥት አዳራሹ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ አዘውትሬ መገኘት ጀመርኩ። እንዲሁም ከወታደራዊ አገልግሎት በጡረታ ለመገለል እቅድ አወጣሁ።
እድገት አድርጌ ለመጠመቅ በቃሁ
ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ጉባኤው መጪው ትልቅ ስብሰባ የሚደረግበትን ስታዲየም እንደሚያጸዳ ሰማሁ። እኔም በስብሰባው ላይ ለመገኘት ጓጉቼ የነበረ ሲሆን በጽዳት ሥራው ለመካፈል ወደ ስታዲየሙ ሄድኩ። እዚያ ከደረስኩ በኋላ ከሌሎች ጋር አብሬ ስሠራ ቆየሁ፤ ሥራውም ሆነ ከሌሎች ጋር ያሳለፍኩት ጊዜ በጣም አስደሳች ነበር። ወለሉን እየጠረግሁ እያለ አንድ ወጣት ወደ እኔ ቀረብ ብሎ የባሕር ኃይል ዋና አዛዡ መሆን አለመሆኔን ጠየቀኝ።
“ነኝ” ብዬ መለስኩለት።
በመገረም “እኔ አላምንም! የባሕር ኃይል ዋና አዛዡ
ወለል እየጠረገ ነው!” በማለት ጮኸ። ከፍተኛ ማዕረግ ያለው አንድ የጦር መኮንን ወለል መጥረግ ይቅርና አንዲት ብጣሽ ወረቀት እንኳ ከመሬት አያነሳም። ይህ ሰው እኔን ለማመላለስ የተመደበ የግል ሾፌሬ የነበረ ሲሆን አሁን ግን የይሖዋ ምሥክር ሆኗል!በፍቅር ላይ የተመሠረተ ኅብረት
ወታደራዊ ሥነ ሥርዓት፣ ወታደሮች ለማዕረግ ባላቸው አክብሮት ላይ የተመሠረተ ነው፤ እንዲህ ያለው ሥርዓት ደግሞ በውስጤ ሰርጾ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ባላቸው የኃላፊነት ቦታ ወይም በሚያከናውኑት ተግባር የተነሳ ከሌሎቹ ይበልጡ እንደሆነ ጠይቄ እንደነበር አስታውሳለሁ። ስለ ማዕረግና ስለ ሥልጣን የነበረኝ አመለካከት በውስጤ ሰርጾ የነበረ ቢሆንም አስገራሚ ለውጥ የማደርግበት ጊዜ በጣም ተቃርቦ ነበር።
በዚያ ወቅት ይኸውም በ1989 አንድ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል ከኒው ዮርክ ወደ ቦሊቪያ እንደሚመጣና በስታዲየሙ ንግግር እንደሚሰጥ ሰማሁ። የድርጅቱ “ቁንጮ” የሆነ ሰው እንዴት ያለ አቀባበል እንደሚደረግለት ለማየት ጓጉቼ ነበር። እንዲህ ባለ የኃላፊነት ቦታ ላይ ያለ ሰው ደማቅ አቀባበል ይደረግለታል ብዬ አስቤ ነበር።
ስብሰባው ሲጀመር የተለየ ሰው እንደመጣ የሚያመለክት ምንም ነገር አለመኖሩን ሳይ ገረመኝ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከእኔና ከማኑዌላ ጎን አረጋዊ የሆኑ ባልና ሚስት ተቀምጠው ነበር። ማኑዌላ ሚስትየው እንግሊዝኛ የመዝሙር መጽሐፍ መያዟን አስተዋለች፤ በእረፍት ሰዓት ላይ ማኑዌላ ከሴትየዋ ጋር መጨዋወት ጀመረች። ከዚያ በኋላ ግን ባልና ሚስቱ አጠገባችን አልነበሩም።
ትንሽ ቆይቶ የዚያች እህት ባል ዋናውን ንግግር ለማቅረብ ወደ መድረኩ ሲወጣ ሁለታችንም በጣም ተገረምን! በዚያች ቅጽበት በወታደር ቤት ስለ ማዕረግ፣ አክብሮት፣ ሥልጣንና ደረጃ የተማርኩት ነገር ሁሉ ከጭንቅላቴ ወጣ። ከዚያም “እስቲ አስቡት፣ ከእኛ ጋር በስታዲየሙ ውስጥ ምቾት በሌላቸው ወንበሮች ላይ ተቀምጦ የነበረው ወንድም የበላይ አካል አባል ነበር!” ብዬ ተናገርኩ።
ኢየን በማቴዎስ 23:8 ላይ የሚገኙት “እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት እንዳስተውል ምን ያህል እንደጣረ ሳስታውስ ሳቄ ይመጣል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በስብከቱ ሥራ ተካፈልኩ
ወታደራዊ ግዳጄን ካጠናቀቅኩ በኋላ ኢየን ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው የስብከት ሥራ አብሬው እንድካፈል ጋበዘኝ። (የሐዋርያት ሥራ 20:20) የሄድንበት ሰፈር ፈጽሞ ልሄድበት የማልፈልገው ወታደሮች በብዛት የሚገኙበት ሰፈር ነበር። አንድ ቤት ስናንኳኳ ላገኘው የማልፈልገው አንድ ጄኔራል በሩን ከፈተ። እሱን ሳየው በተለይም ቦርሳዬንና መጽሐፍ ቅዱሴን አይቶ በንቀት “ምን ነካህ?” ብሎ ሲጠይቀኝ እንደመደናገጥና እንደመፍራት ብዬ ነበር።
ወዲያውኑ አጭር ጸሎት ካቀረብኩ በኋላ ልበ ሙሉነትና የመረጋጋት ስሜት ተሰማኝ። ጄኔራሉ የምናገረውን መልእክት ያዳመጠኝ ከመሆኑም ሌላ አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ተቀበለ። ይህ ሁኔታ ሕይወቴን ለይሖዋ እንድወስን አበረታታኝ። በመሆኑም ጥር 3, 1990 ራሴን መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ።
ከጊዜ በኋላ ባለቤቴ፣ ወንድ ልጄና ሴት ልጄ የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። በአሁኑ ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ሽማግሌና የአምላክ መንግሥት ምሥራች የሙሉ ጊዜ ሰባኪ ሆኜ በማገልገል ላይ እገኛለሁ። ከሁሉም በላይ ያገኘሁት እጅግ ውድ መብት ይሖዋን ማወቅና በእሱም ዘንድ መታወቅ ነው። ይህ ደግሞ ማንኛውም ሰው ከሚመኘው ወይም ሊደርስበት ከሚችለው ከየትኛውም ማዕረግ ወይም ሥልጣን ይበልጣል። በእርግጥም ሥርዓታማነት ሲባል ፍቅርና አሳቢነት እንጂ ኃይለኝነትና ግትርነት የሚንጸባረቅበት መሆን የለበትም። ይሖዋ የሥርዓት አምላክ ነው፤ ከሁሉም በላይ ግን የፍቅር አምላክ ነው።—1 ቆሮንቶስ 14:33, 40፤ 1 ዮሐንስ 4:8
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.21 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን መታተም አቁሟል።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1950 ከወንድሜ ከሬናቶ ጋር
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከቻይና እና ከሌሎች አገሮች ከመጡ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ጋር በአንድ ማኅበራዊ ዝግጅት ላይ