ከጋብቻ በፊት አብሮ መኖር ምን ችግር አለው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ከጋብቻ በፊት አብሮ መኖር ምን ችግር አለው?
ሙሉ ልብስ ለመግዛት አስበሃል እንበል፤ ልብሱ እንደሚሆንህ ለማየት ሳትለካው ትገዛዋለህ? እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው። በኋላ ላይ ስትለብሰው ልክህ ሳይሆን ቢቀር ጊዜህንና ገንዘብህን ያባከንከው በከንቱ ይሆናል።
በትዳር ረገድም ብዙ ሰዎች ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር ያደርጋሉ። አንድ ወንድና አንዲት ሴት፣ ባልና ሚስት ለመሆን ቃል ኪዳን ከመግባታቸው በፊት አብረው መኖራቸው የተሻለ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች ‘አንድ ወንድና አንዲት ሴት እንደማይጣጣሙ ከተሰማቸው ፍቺ የሚያስከትለው ውስብስብ የሆነና ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ጣጣ ውስጥ ሳይገቡ በቀላሉ መለያየት ይችላሉ’ ብለው ያስባሉ።
ምናልባትም አንዳንዶች እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ሊኖራቸው የቻለው፣ የሚፈጸምባቸውን በደል ችለው የሚኖሩ ያገቡ ጓደኞቻቸውን ስላዩ ይሆናል። ወይም ደግሞ ፍቅር የሌለበት ትዳር የሚያስከትለውን የስሜት ሥቃይ ተመልክተው ይሆናል። በዚህም ምክንያት ከዚህ ሁሉ ለመዳን የተሻለው አማራጭ በሕግ ሳይጋቡ አብሮ መኖር እንደሆነ አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ።
በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ይህን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት የአምላክ ቃል ስለ ጋብቻ ምን እንደሚል እንመልከት።
“አንድ ሥጋ”
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰዎች ጋብቻን ክቡር ዝግጅት እንደሆነ አድርገው እንዲመለከቱት ያበረታታል። ይህ መሆኑ አያስደንቅም፤ ምክንያቱም የጋብቻ ዝግጅት እንዲኖር ያደረገው መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው ይሖዋ አምላክ ነው። (ዘፍጥረት 2:21-24) ገና ከጅምሩ የይሖዋ ዓላማ አንድ ወንድና አንዲት ሴት በጋብቻ አማካኝነት “አንድ ሥጋ” እንዲሆኑ ነው። (ዘፍጥረት 2:24) ኢየሱስ ይህ ሐሳብ የሚገኝበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ከጠቀሰ በኋላ “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” በማለት ተናግሯል።—ማቴዎስ 19:6
እርግጥ ነው፣ ጋብቻ የሚመሠርቱ አንዳንድ ሰዎች የኋላ ኋላ ይፋታሉ። * ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ሁኔታ የሚያጋጥመው የጋብቻ ዝግጅት በራሱ የሚጎድለው ነገር ስላለ ሳይሆን አንደኛው ወይም ሁለቱም ተጓዳኞች የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን አክብረው ባለመኖራቸው ነው።
ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፣ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ሁለቱም የሚጠቀሙበት አንድ መኪና አላቸው እንበል። ይሁን እንጂ በፋብሪካው መመሪያ መሠረት ለመኪናው እንክብካቤና ጥገና አላደረጉለትም። በዚህ ምክንያት መኪናው ቢበላሽ ተጠያቂው ማን ነው? መኪናውን የሠራው ፋብሪካ ነው? ወይስ አስፈላጊውን ጥገና ሳያደርጉ የቀሩት የመኪናው ባለቤቶች?
ይህ ምሳሌ ለጋብቻም ይሠራል። አንድ ባልና ሚስት በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ከተንከባከቡትና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ቁርጥ ውሳኔ ካደረጉ የመፋታታቸው አጋጣሚ በጣም ጠባብ ነው። በተጋቡበት ጊዜ ሁለቱም ቃል ኪዳን ገብተዋል፤
ይህ ደግሞ በትዳሩ ውስጥ የመተማመን መንፈስ እንዲኖር ያደርጋል። በዚህ መንገድ ጋብቻ በፍቅር ለመተሳሰር የሚያስችል መሠረት ሆኖ ያገለግላል።‘ከዝሙት ራቁ’
ያም ሆኖ አንዳንዶች ‘አንድ ወንድና ሴት ከጋብቻ በፊት አብረው ቢኖሩስ? የጋብቻ ቃል ኪዳን ከመፈጸማቸው በፊት አብረው በመኖር ጥምረቱ ይሰምር እንደሆነ መሞከራቸው ቅዱስ ለሆነው ጋብቻ አክብሮት እንዳላቸው የሚያሳይ አይሆንም?’ ብለው ያስቡ ይሆናል።
መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መልስ የማያሻማ ነው። ጳውሎስ ‘ከዝሙት ራቁ’ በማለት ጽፏል። (1 ተሰሎንቄ 4:3) “ዝሙት” የሚለው ቃል ከትዳር ውጭ የሚፈጸምን ማንኛውንም ዓይነት የጾታ ግንኙነት ያመለክታል። ይህ ደግሞ ለመጋባት ያሰቡ ቢሆኑም እንኳ ሳይጋቡ አብረው የሚኖሩ ወንድና ሴት የሚፈጽሙትን የጾታ ግንኙነት ይጨምራል። በመሆኑም አንድ ወንድና አንዲት ሴት፣ ወደፊት የመጋባት ዓላማ ቢኖራቸውም እንኳ አብረው መኖራቸው ስህተት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።
ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት ጊዜ ያለፈበት ነው? አንዳንዶች እንደዚያ ይሰማቸው ይሆናል። ደግሞም በብዙ አገሮች ውስጥ አንድ ወንድና ሴት ወደፊት የመጋባት እቅድ ኖሯቸውም ይሁን ሳይኖራቸው አብረው መኖራቸው የተለመደ ነገር ሆኗል። ይሁን እንጂ ይህ ምን ሊያስከትል እንደሚችል አስቡ። ሳይጋቡ አብረው መኖራቸው የተሳካ የቤተሰብ ሕይወት አስገኝቶላቸዋል? ከተጋቡ ባልና ሚስት የበለጠ ደስታ አላቸው? ጋብቻ ከመሠረቱ በኋላስ ከጋብቻ በፊት አብረው ካልኖሩ ባልና ሚስት ይበልጥ ለትዳራቸው ታማኝ ይሆናሉ? ጥናቶች የሚያሳዩት ተቃራኒውን ነው። በእርግጥም ከመጋባታቸው በፊት አብረው የኖሩ ባልና ሚስት፣ ከጋብቻ በፊት አብረው ካልኖሩ ባልና ሚስት ይበልጥ በትዳራቸው ውስጥ ችግር እንደሚያጋጥማቸው፣ የኋላ ኋላ የመፋታታቸው አጋጣሚም ከእነዚያ አንጻር ሲታይ የበለጠ እንደሆነ ለማስተዋል ተችሏል።
አንዳንድ ባለሙያዎች እንዲህ ዓይነቶቹ ጥናቶች ስህተት እንዳለባቸው ይናገሩ ይሆናል። አንዲት የሥነ ልቦና ተመራማሪ “አብረው ከመኖራቸው በፊት ለመጋባት የሚመርጡ ሰዎች፣ ከመጋባታቸው በፊት አብረው ለመኖር ከሚወስኑ ሰዎች ቀድሞውንም የተለየ አመለካከት ያላቸው ናቸው” በማለት ጽፈዋል። እኚህ ሴት ክርክራቸውን በመቀጠል ዋናው ጉዳይ አብሮ መኖር ወይም አለመኖር ሳይሆን ‘ለጋብቻ ዝግጅት ምን ያህል አክብሮት አላቸው’ የሚለው እንደሆነ ተናግረዋል።
የእሳቸው አባባል እውነት ቢሆን እንኳ፣ አምላክ ለጋብቻ ዝግጅት ያለው ዓይነት አመለካከት ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን የሚያጠናክር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር . . . ይሁን” ይላል። (ዕብራውያን 13:4) አንድ ወንድና አንዲት ሴት አንድ ሥጋ ሆነው ለመኖር ቃል ኪዳን ሲገቡና ለጋብቻ ዝግጅት አክብሮት ሲያሳዩ በመካከላቸው ያለው ግንኙነት በቀላሉ አይበጠስም።—መክብብ 4:12
አሁን በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ ወደጠቀስነው ምሳሌ እንመለስ። አንድ ሰው ሙሉ ልብስ ከመግዛቱ በፊት ልብሱን መለካቱ አስተዋይነት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ከጋብቻ በፊት በደንብ ለመተዋወቅ እንጂ አብሮ ለመኖር ምሳሌ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም አንድ ሰው የሚገዛውን ልብስ እንደሚለካው ሁሉ ልታገቡት ያሰባችሁትን ሰው በቂ ጊዜ ወስዳችሁ አስቀድማችሁ በደንብ ለማወቅ መጣራችሁ ተገቢ ነው። ይህ አስፈላጊ የሆነ፣ ሆኖም ብዙ ጊዜ ችላ የሚባል እርምጃ ለተሳካ የቤተሰብ ሕይወት ቁልፍ ከሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
ይህን አስተውለኸዋል?
▪ መጽሐፍ ቅዱስ የጾታ ግንኙነት በተጋቡ ሰዎች መካከል ብቻ መደረግ እንዳለበት የሚደነግገው ለምንድን ነው? —መዝሙር 84:11፤ 1 ቆሮንቶስ 6:18
▪ ለትዳር ጓደኝነት የምትመርጡት ሰው ሊኖሩት ይገባል የምትሏቸው ባሕርያት ምንድን ናቸው?—ሩት 1:16, 17፤ ምሳሌ 31:10-31
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
‘በራስ አካል ላይ የሚፈጸም ኃጢአት’
መጽሐፍ ቅዱስ “ዝሙት የመፈጸም ልማድ ያለው . . . በራሱ አካል ላይ ኃጢአት እየሠራ ነው” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 6:18) ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት በኤድስና በጾታ ግንኙነት በሚተላለፉ ሌሎች በሽታዎች ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸው የዚህን ጥቅስ እውነተኝነት ያረጋግጣል። ነገር ግን ይህ ብቻ አይደለም። ሳያገቡ የጾታ ግንኙነት ከሚፈጽሙ ወጣቶች መካከል ብዙዎች የመንፈስ ጭንቀት እንደሚያጠቃቸውና ራስን የማጥፋት ሙከራ እንደሚያደርጉ ጥናቶች ይጠቁማሉ። በተጨማሪም ልቅ የሆነ የጾታ ግንኙነት መፈጸም ላልተፈለገ እርግዝና ሊዳርግ ይችላል፤ ይህ ደግሞ አንዳንዶች ፅንሱን ለማስወረድ እንዲፈተኑ ያደርጋቸዋል። ከዚህ አንጻር ስንመለከተው የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ሕግ ጊዜ ያለፈበት አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ እንችላለን።