ልጆችህን ለብቻህ የምታሳድግ ቢሆንም ሊሳካልህ ይችላል
ልጆችህን ለብቻህ የምታሳድግ ቢሆንም ሊሳካልህ ይችላል
አንዳንድ ሰዎች ‘ሁለቱም ወላጆች ያሉበት ቤተሰብ እንስሳ ቢሆን ኖሮ ለመጥፋት ከተቃረቡ ዝርያዎች ዝርዝር ውስጥ ይካተት ነበር’ ይላሉ። እስቲ አስበው፦ በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ፣ ያለ ትዳር ጓደኛ እርዳታ ልጅ የሚያሳድጉ ወላጆች ቁጥር ከ13 ሚሊዮን የሚበልጥ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ብቻቸውን ልጆች የሚያሳድጉ እናቶች ናቸው። በዚያች አገር ውስጥ ካሉት ልጆች መካከል ግማሽ የሚሆኑት ከወጣትነት ዕድሜያቸው ውስጥ ቢያንስ የተወሰነውን የሚያሳልፉት በአንድ ወላጅ ብቻ በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ።
ልጆችህን ለብቻህ የምታሳድግ ወላጅ ከሆንክ ወይም ከሆንሽ የተሳካ የቤተሰብ ሕይወት ሊኖራችሁ እንደሚችል እርግጠኛ ሁኑ። የሚከተሉትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ጣሩ።
▪ አሉታዊ ሐሳቦችን አስወግዱ። መጽሐፍ ቅዱስ “ልቡ የሚያዝን ሰው ዘመኑ ሁሉ የከፋች ናት፤ የልብ ደስታ ግን ሁልጊዜ እንደ ግብዣ ነው” ይላል። (ምሳሌ 15:15 የ1954 ትርጉም) እውነት ነው፣ ሕይወታችሁ እንደ ግብዣ አስደሳች እንዳልሆነ ይሰማችሁ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ጥቅስ እንደሚያመለክተው ደስታ በአብዛኛው የተመካው አንድ ሰው በሚገኝበት ሁኔታ ላይ ሳይሆን በልቡ ላይ ነው። (ምሳሌ 17:22) ቤታችሁ እንዳበቃለት ወይም ደግሞ ልጆቻችሁ ዕድለ ቢሶች እንደሆኑ አድርጋችሁ ማሰብ የሚፈይደው ነገር የለም። እንዲህ ብላችሁ ማሰባችሁ ይበልጥ ተስፋ የሚያስቆርጣችሁ ሲሆን የወላጅነት ኃላፊነታችሁን መፈጸም ይበልጥ አስቸጋሪ እንዲሆንባችሁ ያደርጋል።—ምሳሌ 24:10
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ሁኔታችሁን ለመግለጽ ብዙ ጊዜ የምትናገሯቸው አሉታዊ አነጋገሮች ካሉ በወረቀት ላይ ጻፏቸውና ከእያንዳንዱ አነጋገር ጎን እሱን የሚተካ አዎንታዊ ሐሳብ ጻፉ። ለምሳሌ ያህል፣ “አሁንስ አልቻልኩም” የሚለውን “የወላጅነት ኃላፊነቴን መወጣት እችላለሁ፤ የሚያስፈልገኝን እርዳታም ማግኘት እችላለሁ” በሚለው ተኩ።—ፊልጵስዩስ 4:13
▪ በጀት አውጡ። ልጆቻቸውን ለብቻቸው የሚያሳድጉ በርካታ ወላጆችን፣ በተለይም እናቶችን ይበልጥ የሚያስጨንቃቸው የገንዘብ ችግር ነው። ሆኖም በአንዳንድ ሁኔታዎች የገንዘብ ችግር ጥሩ በጀት የማውጣት ችሎታን በማዳበር ሊቃለል ይችላል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል” ይላል። (ምሳሌ 22:3) ከገንዘብ ጋር በተያያዘ “አደጋ” እንዳይደርስ ለመከላከል ጥሩ እቅድ ማውጣትና አርቆ ማሰብ አስፈላጊ ነው።
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ በጀታችሁን በጽሑፍ አስፍሩ። ለአንድ ወር ያህል ወጪዎቻችሁን መዝግቡና ገንዘባችሁን ምን ላይ እንዳዋላችሁ እወቁ። የገንዘብ አወጣጥ ልማዳችሁን በጥንቃቄ ገምግሙ። ዱቤ ታበዛላችሁ? ልጆቻችሁ አንደኛው ወላጅ አብሯቸው ባለመኖሩ የተነሳ እንዳይከፋቸው ስትሉ አንዳንድ ነገሮችን ትገዙላቸዋላችሁ? ልጆቻችሁ ነፍስ ያወቁ ከሆኑ አብራችሁ ቁጭ በሉና ገንዘብ መቆጠብ ስለሚቻልባቸው መንገዶች ተነጋገሩ። እንዲህ ማድረጉ ለእነሱ ጥሩ ሥልጠና ይሆንላቸዋል። ደግሞም ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ሐሳብ ያፈልቁ ይሆናል!
▪ ከቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ይኑራችሁ። ልጃችሁን የማሳደግ ኃላፊነት የተጣለው በሁለታችሁም ላይ ከሆነ ስለ ቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ መጥፎ ነገር ለልጃችሁ መናገራችሁ ወይም ስለ ሕይወታቸው ለማወቅ ልጃችሁን እንደ ሰላይ አድርጋችሁ መጠቀማችሁ ተገቢ አይደለም። * ከዚህ ይልቅ ተግሣጽን ወይም የልጃችሁን ደኅንነት የሚነኩ ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ከቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ ጋር እንደምንም ብላችሁ ተባብራችሁ መሥራታችሁ የተሻለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ” ይላል፤ “ከሰው ሁሉ ጋር” የሚለው የቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁንም ይጨምራል።—ሮም 12:18
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ከዚህ በኋላ አለመግባባት ሲነሳ የቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁን እንደ አንድ የሥራ ባልደረባችሁ አድርጋችሁ ለመያዝ ጥረት አድርጉ። በሥራ ቦታ ከሁሉም ጋር፣ የማትወዱት ጠባይ ካላቸው የሥራ ባልደረቦቻችሁ ጋር ሳይቀር ተግባብታችሁ ለመሥራት ትጥራላችሁ። ከቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ ጋር ባላችሁ ግንኙነትም ተመሳሳይ ነገር አድርጉ። ሁልጊዜ አትስማሙ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ በሆነ ባልሆነው መጨቃጨቅ የለባችሁም።—ሉቃስ 12:58
▪ ጥሩ ምሳሌ ሁኑ። ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘ልጆቼ እንዲኖራቸው የምፈልገው ምን ዓይነት ሥነ ምግባርና አመለካከት ነው? ልጆቼ እንዲከተሉ የምፈልጋቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶችና አመለካከቶች እኔ ራሴ አንጸባርቃቸዋለሁ?’ ለምሳሌ ያህል፣ ምንም እንኳ ልጆቻችሁን ብቻችሁን የምታሳድጉ ብትሆኑም በአጠቃላይ ሲታይ ደስተኞች ናችሁ? ወይስ ያላችሁበት ሁኔታ ለሕይወት ያላችሁን አመለካከት እንዲያጨልመው ትፈቅዳላችሁ? የቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ ባደረሰባችሁ በደል አሁንም ትበሳጫላችሁ? ወይስ የደረሰባችሁን ግፍ ለማስቀረት ልታደርጉት የምትችሉት ነገር እንደሌለ በማሰብ ችላችሁ አልፋችሁታል? (ምሳሌ 15:18) እርግጥ ነው፣ እነዚህ ጉዳዮች ቀላል ባለመሆናቸው እናንተም ፍጹም በሆነ መንገድ አትወጧቸውም። ያም ሆኖ ልጆቻችሁ ስለ ሕይወት በሚኖራቸው አመለካከት ረገድ በእናንተ ላይ የሚያዩትን ማንጸባረቃቸው አይቀርም።
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ልጆቻችሁ አድገው ትልልቅ ሰዎች ሲሆኑ እያንዳንዳቸው እንዲያሳዩ የምትፈልጓቸውን ሦስት ባሕርያት በወረቀት ላይ ጻፉ። * ከእያንዳንዱ ባሕርይ ጎን ልጃችሁ ያንን ባሕርይ እንዲያዳብር ለመርዳት በአሁኑ ጊዜ ምን በማድረግ ምሳሌ ልትሆኑት እንደምትችሉ ጻፉ።
▪ ራሳችሁን ጠብቁ። ሕይወታችሁ በሩጫ የተሞላ በመሆኑ አካላዊና ስሜታዊ ጤንነታችሁን በቀላሉ ችላ ልትሉ ትችላላችሁ። እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዳይደርስባችሁ ጥንቃቄ አድርጉ! በተለይ ደግሞ ለመንፈሳዊ ፍላጎታችሁ ትኩረት መስጠታችሁ በጣም አስፈላጊ ነው! (ማቴዎስ 5:3) ነዳጅ የሌለው መኪና ብዙ መጓዝ እንደማይችል አትዘንጉ። እናንተም ብትሆኑ ጊዜ ወስዳችሁ “ነዳጅ ካልሞላችሁ” ርቃችሁ መሄድ አትችሉም።
በተጨማሪም ‘ለመሳቅም’ ሆነ ዘና ለማለት ጊዜ እንዳለው አስታውሱ። (መክብብ 3:4) መዝናናት ጊዜ ማባከን አይደለም። መዝናናት ኃይላችሁን የሚያድስላችሁ ከመሆኑም በላይ የወላጅነት ኃላፊነታችሁን ለመወጣት የሚያስችል ብርታት ይጨምርላችኋል።
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ልጆቻቸውን ብቻቸውን የሚያሳድጉ ሌሎች ወላጆች ራሳቸውን ለመጠበቅ ምን እንደሚያደርጉ ጠይቋቸው። “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ ማወቅ” እንዳለባችሁ የታወቀ ነው። ሆኖም በእያንዳንዱ ሳምንት ደስ የሚያሰኟችሁን ነገሮች በማድረግ የተወሰነ ጊዜ ማሳለፍ ትችሉ ይሆን? (ፊልጵስዩስ 1:10) ምን ብታደርጉ ደስ እንደሚላችሁ እንዲሁም ያንን ነገር መቼ ልታደርጉት እንደምትችሉ በወረቀት ላይ ጻፉ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.8 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በዚህ መጽሔት ከገጽ 18-21 ላይ የሚገኘውን “ለሁለት የተከፈለ ቤት—መፋታት በወጣቶች ላይ የሚያስከትለው ችግር” የሚለውን ርዕስ ተመልከቱ።